Tidarfelagi.com

ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኩ ነው (ክፍል ስድስት)

ሳፈቅር ገገማ ነኝ!! ግግም ያልኩ ሰገጥ!! የተመታሁት እኔ …… ቢላ አንገቴ ላይ የተደረገው እኔው …… እሱ ለሰራው ጥፋት ማስተባበያ የምሰጠውም እኔው ……. ሁለቱንም ጊዜ እኔ ስቆጣ ነው ሌላ ሰው የሆነው ስለዚህ እኔ እሱ ሲቆጣ ባልፈው ያኛው እሱ አይመጣም ብዬ አሰብኩ!(ሰገጥ ነኝ አላልኳችሁም?)
እንዴት እንደማስተካክለው …. እንዴት ሁለቱን ማንነቱን እንደማስማማ እንጂ የማስበው ከሱ መለየት በፍፁም ለምርጫ የሚቀርብ አይደለም። ከሚሆነው ሁሉ እሱን የማፈቅርበት ጥግ ያልፋል። እናም ሁለቱን ባሎቼን በአንድ ሱፍ አገባኋቸው!! አባቴ እግሩን ስሜ እንኳን ስወጣ በሙሉ ዓይኑ አላየኝም። እሱኛው ቅፅበት ባሌ ካላሰኝ ጥፊ በላይ ያም ነበር።
በሆነ ጊዜ አንዴ የሚመጣውን ያኛውን እሱን በየቀኑ እንደሚሰበር ነገር ለሚጠነቀቅልኝ እሱ ስል ልችለው ወሰንኩ!! ምን እንደሚያስከፍለኝ የማውቅበት የእድሜም የብስለት ደረጃም ላይ አልነበርኩም። የማውቀው ያለእድሜዬ ያነበብኳቸው የፍቅር መፅሃፍት ውስጥ እና ያየኋቸው ፊልም ላይ ያለውን አድቬንቸር የሆነ ፍቅር ነው። ያ ደግሞ እንኳን ጥፊ ሞት ይጨለጥበታል።
ማሚ “የመጀመሪያ ልጅ እናት ቤት ነው የሚወለደው” ብላ አላፈናፍን ስትለን እሱ ደስ ሳይለው ሄድኩ። ወለድኩ!! ፀግዬን ወለድኩ!! ልክ ተገላግዬ ክፍሉ ውስጥ ሲገባ አልጋዬ አጠገብ በጉልበቱ ተነበርክኮ የሆነው መሆን ……. አምጥተው ህፃኗን ሲያስታቅፉት የተሰፈሰፈው መንሰፍሰፍ በጥይት መቶኝ ቢሆን ሁላ እረሳለት ነበር። (ሰግጣለሁ አልኳችሁኮ)
ልጄን አቅፎ በሚያምር ድምፁ እየዘመረ ሲያስተኛት እያየሁት ለሁለቱ ስል ምንም መሰናክል እንደማልፍ ወሰንኩ። ማሚ ህፃን ማጠብ ለእኔ ሳይሆን ለሱ ነበር ያስተማረችው። ለሊት ተነስታ ስታለቅስ ልናስተኛት አሳራችንን ስናይ የምታሰቃየን ልጅ ልክ እሱ አቅፏት መዘመር ሲጀምር ትተኛለች። እና በዚህ ፍቅር ቂም መያዝ ይቻለኝ ነበር?
የእናቴ ቤት ድሎት ኮሰኮሰኝ ምክንያቱም እሱ ስራ መግባት ስለነበረበት ተመልሶ ሄደኣ። በየቀኑ ስልክ እየደወለልኝ ለሰዓትት እናወራለን። አባቴ አሁንም ከ’ደህና አደርሽ?’ እና ‘ህፃኗ እንዴት አደረች?’ ያለፈ አያወራኝም። ጭራሽ ሆድ ባሰኝ እሪሪሪሪ ብዬ በ45 ቀኔ ወደ ባሌ እቅፍ ተመለስኩ። (መሰስ ብዬ ቦክስ ሪንግ ውስጥ መግባቴ የታወቀኝ ሰንብቶ ነው።)
የሚናደድበት ምክንያትና ሰዓት እስኪዋቀጥብኝ የሚናደድባቸው ነገሮች እየበዙ መጡ። ሲናደድ ምን እንዳደረገ የሚያውቀው ካደረገ በኋላ ነው። ጭራሽ አያውቀውም። ካደረገው በኋላ ለቀናት በሙሉ ዓይኑ አያየኝም። የተለመደ ይቅርታ…. የተለመደ ማሪኝ…. የተለመደ ለቅሶ…. ለሰርጋችን ያልመጡት ቤተሰቦቹ መውለዴን ሲሰሙ ደወሉ። እናቱ ልክ የሆነ አንዳንዴ መክሰስ መብላት ይዘላል አይነት ነገር ቀለል አድርገው
“አንዳንዴ ሲናደድ አብሾ አለችበት ቦግ ይላል !! አይዞሽ ታገሺው ….. እንጂ ልቡ ወርቅ ነው!!” ብለውኝ አረፉት።
“ለምን ነርሲንግ አትማሪም?” አለኝ የሆነ ቀን አለ አይደል? ‘ገና አስራሁለተኛ ክፍል ተምረሽ ዩንቨርስቲ መግባት ከልጅ ጋር ይከብድሻል’ የሚል አንድምታ የያዘ። ማሚ ናት ለኳሿ እሷን አልሰማ ስላልኩ ነው በሱ በኩል የመጣችው!!
“አባ 12 እማራለሁ አሪፍ ውጤት አመጣለሁ። ህግ እማራለሁ። ምንም የሚቀየር እቅድ የለም።”
“እሺ ካልሽ ከጎንሽ ነኝ አለሁልሽ” አለኝ። ማሚም ንቅንቅ እንደማልል ስታውቅ ይጠቅማታል ያለችውን ሀሳብ ሰነዘረች። እሷጋ ከነልጄ ሄጄ እንድማር እና ስጨርስ ወደባሌ እንድመለስ ወይም ልጄን እሷጋ ትቼ ከባሌጋ ሆኜ እንድማር። ሁለቱንም እንቢ አልኩ። ልጄን እያሳደግኩ ከባሌጋ ሆኜ እማራለሁ። ያለችኝን ነገርኩት። በሆነ መልኩ እናቴ እኔን እየነጠቀችው እንደሆነ ተሰማው ተጠማመዱ።
ማሚ በደወለች ቁጥር ቤታችን በአንድ እግሩ ይቆማል። ሁሌ እምላለሁ “እሱ ሲናገር አልመልስለትም ዝም እላለሁ” ብዬ ሁሌ ያን ማድረግ ያቅተኝና የተዋበች ቡጢ ስቀምስ ፀጥ እላለሁ። እየተደጋገመ ሲሄድ የሚቀጥለው ህይወቴ ቀላል እንዳልሆነ ገባኝ። ይሄ ሁሉ ሆኖ ለእሱ ያለኝ ፍቅር ንቅንቅ አለማለቱ ይገርመኛል። ሁሌም እሱን ብቻ ጥፋተኛ ማድረግ አይሆንልኝም። እንዲህ አድርጌ ቢሆን እንዲያ አድርጌ ቢሆን እላለሁ ግን አይሆንምኮ ሲቆጣ እንደማዕበል ከየት መጣ ሳልለው ነው ዱብ የሚልብኝ። በተጣላን ቁጥር ወይም ሊያስቆጣው ይችላል ብዬ የማስበው ነገር ሲፈጠር ስለት ያላቸውን ነገሮች ሰብስቤ እቆልፋለሁ። ….
የሆነ ቀን እሱ እየተቆጣ ሲያወራ ፀጊ አልቅሳ አላባራ አለች። “ዝም አስብያት” ብሎ ጮኸ። ምንም ባደርጋት ጭራሽ ዝም አልል አለች። ይሄኔ ልብ አይሞትምኮ የሱ ብስጭት ቅውስ አድርጎኝ እኔ ብሼ ተገኘሁ።
“ለጸብ ሰበብ ነው እንዴ የምትፈልገው? ምን ልሁን ነው የምትለው? ጭራሽ ልጅህ አለቀሰች ብለህ ፀብ ታጋግላለህ?” ብዬ ፊጥ ፊጥ ማለት።
ፀጊን ከእጄ ተቀብሎ ሊያባብላት ሲሞክር እኔን ማን ያቁመኝ ብሶቴ ሁሉ ተሰብስቦ መጣብኝ። እያለቀስኩ እደነፋ ጀመር። ፀጊም እሪታዋን አላቆም አለች።
ሰይጣኑ ቆንጆ ተቀባብሎ ሰፈረበታ!! ልጅቷን እንደሆነ ነገር አልጋው ላይ ጥሏት። ብቻ በጠረባ ከታች ወደላይ ሲያነሳኝ አየር ላይ ትንሽ ተንሳፍፌ …. ጣራውጋ ያለችውን እስከዛሬ እርቃኝ ያልደረስኩባትን የሸረሪት ድር እግረመንገዴን አፅድቼ ተመልሼ ፈረጥኩ። የዛን ቀን በዛው ወጥቶ አምሽቶ ገባ። ቁጭ ብዬ አሰብኩ። የትኛው ህመም እንደሚብስ ልጄን ለእናቴ ሰጥቼ ቡጢዬን ለምሳ እየሸከፍኩ ትምህርቴን ከእርሱ ጋር ሆኜ መቀጠል። “አልፈልጋችሁም እሱ ይበልጥብኛል” ያልኳቸው ቤተሰቦቼጋ “እንደወደዳችሁ አድርጉኝ” ብዬ ሽንፈቴን መዋጥ(ይሄ እሱን ማጣት አለው) ወይም ልጄንም ይዤ ቡጢዬንም ችዬ ትምህርቴን መቀጠል። የመጨረሻው የማይታሰብ እንደሆነ የገባኝ ልጄን አልጋው ላይ ወርውሮ እንደጨርቅ ሲያነጥፈኝ ነው። እሱን ማጣትም አልችልም!! ከዛ በሚያነክስ ልብ ትምህርቴን ተምሬ ውጤት ማምጣት እንደማይሆንልኝ ገባኝ። ልጄን ለማሚ ልሰጣት እንደሆነ ስነግረው “በፍፁም!” ብሎ በጣም ተጣላን።
“ልጄ ናት በልጄ ላይ የመወሰን መብት አለኝ!” አለኝ
“ያ ማለት ሰይጣንህ ሲመጣ እየወረወርካት ማለት ነው? ይቅር አልማር? ከዛ ቁጭ ብዬ ልጄን ላሳድግ? ያውም ባሻህ ጊዜ እየጠፈጠፍከኝ?” ይሄ ድክመቱ ነው!! ብቻ ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ተስማማ ግን ለሚቀጥሉት ብዙ ቀናት የፀብ እርሾ ሆነ። ‘ልጄን ቀማሽኝ’ የሁል ጊዜ ፀብ ሁለት ነጥብ ሆነ::
መስከረም መጥቶ ትምህርት ሊጀመር ሲል ፀግዬ 6 ወሯ ነበር። ለማንም ስለእሱ አንዲት ነገር ተናግሬ አላውቅም። ልጄን እያጠባሁ ወስጄ ለእናቴ ሰጥቻት ተመለስኩ። ከመሳሳቴ የተነሳ ብዙ ጊዜ ሀሳቤን ልቀይር ዳዳኝ።
‘ለምን ትምህርቱ ራሱ ጥንቅር ብሎ አይቀርም ልጄን ለምን አርፌ አላሳድግም እኔ ከሌሎች ሴቶች በምን ተለይቼ ነው ዓላማ ቅብርጥሶ እያልኩ የምጋጋጠው? ወይም ለምን ልጄ ከፍ ብላ ትምህርት ቤት ስትገባ ከዛ አልማርም?’ ብዙውን አሰብኩ
የጡቴ ወተት ሞልቶ ማጅራቴን ህመሙ እያሰቃየኝ ከሀዋሳ አርባምንጭ እንባዬን እየዘራሁ ልጄን ትቼ ተመለስኩ። እንደዛ እንደምሆን ገብቶት ስለነበር ፈቃድ ወስዶ ምግብ ሰርቶ ቤቱን አስተካክሎ ጠበቀኝ። እሱን ሳገኘው ጭራሽ ማን ይቻለኝ ? በነገታው ተመልሼ አልፈልግም በቃ ልጄን ስጡኝ የምል ነበር የመሰለኝ። ለቀናት አለቀስኩ:: እየደወልኩ መንሰቅሰቅ ስራዬ ሆነ ….

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *