አብረን ያየን ሰው ሁሉ ‹‹አፈስሽ አፈስሽ›› እያለ ያወራል።
ቆንጆ፣ ሎጋ፣ ረጋ ያለ እና ዝምተኛ ነው። የወንድ ልጅ አማላይነት የተሰራው ከእነዚህ ተንኮለኛ ንጥረ ነገሮች አይደል?
በፍቅር መውደቅ ከገደል እንደመውደቅ ያማል?
በፍቅር መያዝ እንደ ተስቦ ያማቅቃል?
አዎ። ቢሆንም እያመመኝ እወደዋለሁ። እየማቀቅኩ አፈቅረዋለሁ።
እኔ እወደዋለሁ።
እሱ ግን እንደሁሉም ሰው በግብረስጋ ሳይሆን ከመላእክት ተዳቅሎ እንደተፈጠረ ይለጠጥብኛል። ይንበላጠጥብኛል።
ቢሆንም ስሜቴ ለእርሱ ባሪያ ነው። ሲያወድሰኝ ብቻ የማብብ- ሲኮንነኝ የምጠወልግ ፣ ሲመለከተኝ የማምር- ፊቱን ሲያዞርብኝ የማስቀይም እስከሚመስለኝ ድረስ እወደዋለሁ።
ይሄን አውቃለሁ። ፍቅሬ አቅብጦታል። መውደዴ አቀማጥሎታል።
ብዙ ጊዜ ደህና ስንጫወት እንውልና በድንገት ያኮርፈኛል። ይኮፈሳል። አይኔን ማየት ይጠላል። ያን ጊዜ ሁሉ ነገር ይዞርብኛል። ሳቄ ይከስማል። የልቤ ቡረቃ በሃዘን አታሞ ይተካል።
ይገርመኛል። በስሜቴ ላይ እንዲህ እንዲሰለጥን ከመፍቀዴ በፊት…እሱን ከማግኘቴ በፊት በምን ነበር የምስቀው? በምንስ ነበር የምደሰተው?
‹‹ምን ሆንክብኝ›› እለዋለሁ ልክ እንደዚያ ሲሰራው።
‹‹ምንም አልሆንኩም…ተይኝ ላንብብበት›› ለዚህች ለዚህች ጊዜ ተዘጋጅታ የምትቀመጥ፣ መዥረጥ አድርጎ የሚያወጣት መደበኛ እና የዘወትር መልሱ ናት።
– ኤሊ..
– እ… (ከልቡ ሳይሆን)
– ሻይ በጦስኝ ላፍላልህ?
(ሻይ በጦስኝ ስለሚወድ)
– አልፈልግም
– ፍሬንድስን ልክፈትልህ?
(ፍሬንድስን አይቶ ስለማይጠግብ)
– አላሰኘኝም
– ቶሎ ሃያ ሁለት ሄጄ የፀሃይን ሽሮ ይዤልህ ልምጣ?
(ከትግሬ ሽሮ ሌላ በአለም ላይ ደህና ምግብ ያለ ስለማይመስለው)
– አልራበኝም…
– እሺ ምንድነው ምትፈልገው?
– ተይኝ ላንብብበት…
ይሄኔ ነው የአዳም ረታን አንዱን መፅሃፍ አውጥቶ ጥሎኝ የሚሄደው። ይሄኔ ነው የራሱን ክብ አለም ፈጥሮ አፈናጥሮ የሚያስወጣኝ። ያን ጊዜ ማውራት መቀጠሌ ለሬሳ መድሃኒት ከመስጠት እንደማይለይ ስለማውቅ ጥዬው ለመሄድ እሰናዳለሁ።
መፅሃፉ ላይ ተተክሎ አንዴ የለዘዘ ፈገግታ ሲያሳይ፣ አንዴ ጮህ ብሎ ሲስቅ፣ ከዚያ እንደማልቀስ ሲሰራው በእሱ ስሜት ላይ በሰለጠነው ብቸኛው ሰው አዳም ረታ እቀናለሁ። አንዳንዴም የምወደውን ልጅ ስለነጠቀኝ እያልጎመጎምኩ በልቤ እረግመዋለሁ። ‹‹ብእርህ ይንጠፍ..እጅህን ቁርጥማት ይዘዝበት›› አይነት ነገር።
‹‹ልሄድ ነው ቻው›› እለዋለሁ ጫማዬን አጥልቄ ስጨርስ።
– እሺ..ቻው… ይለኛል ቦግ ቦግ ያሉ አይኖቹን ከመፅሀፉ ሳይለይ። ስሜቱን ከአዳም ረታ ገፀ ባህሪያት ሳያላቅቅ።
ያን ጊዜ ከእንባዬ እየታገልኩ ወደ ቤቴ!
ስምንት ወር አብረን ስንወጣ- ስንገባ – ስንተኛ ስንነሳ- ብረት አሎሎ ልቡን አልፈታልኝም። ስለአለፈ ሕይወቱ አይነግረኝም። ስለወደፊቱ አያወራኝም። ከቤተሰብ- ጓደኛ አያስተዋውቀኝም።
እየቆየ የትርፍ ሰአት ስራው መሆኔ ሲገለፅልኝ ጨምቷ ልጅ ላብድ ደረስኩ። ተዉኩት ስል እያገረሸ በሚያስቸግረኝ አስቀያሚ ፍቅሩ ብሸነፍም ቁርጤን ማወቅ እንዳብኝ አመንኩ።
አንዱን ቅዳሜ ስገሰግስ ቤቱ ደረስኩ። ከሰአት 9 ሰአት ቢሆንም አብዝቶ የሚለብሰውን እህቱ ከካናዳ የላከችለትን ፒጃማ አድርጎ ሶፋው ላይ ተጋድሞ ያነባል። ማንን? ያንን በየአመቱ መፅሃፍ የሚያመርተውን አዳም ረታ።
– ስማ ኤልያስ …እኔ እንደዚህ መቀጠል አልችልም…ማውራት አለብን… አልኩ ቦርሳዬን አንዱ ሶፋ ላይ ወርውሬ አጠገቡ እየተቀመጥኩ።
– እ…. ? አለኝ መፅሀፉን ሳይዘጋ ቀና ብሎ እያየኝ..
– አመልህ ሊገባኝ አልቻለም…እኔ እወድሃለሁ…ግን ማትወደኝ ከሆነ…ማለቴ ልብህን ማትሰጠኝ ከሆነ…
ሳልጨርስ አቋረጠኝ።
– ምንድነው ምትፈልጊው? ተናዶም በማይለወጠው እርጋታና ግዴለሽነቱ ጠየቀኝ
(መፅሃፉን ዘጋ። ጉዳዩ ሲሪየስ ነው!)
– እኔ?
– አዎ አንቺ…ምንድነው ምትፈለጊው?
ምንድነው የምፈልገው? እንዴትስ ብዬ ነው የምጠይቀው…?
ከአንጀቱ- እንዲህ በትኩረት እያየኝ ይጠይቀኛል ብዬ አስቤ ስለማላውቅ እያሰብኩ ያንን ውብ ፊቱን አየሁት።
ጢሙ እንደምወደው አድጓል። ጠጉሩ ጨብረር ብሏል። መከረኛ ፒጃማው እጅጌ እና አንገቱ ጋር መንችኳል።
ዝም ብሎ ያየኛል። ብዙ ጊዜ ይሄን ያህል ጊዜ ሰጥቶ አያየኝም። አንሶላ መሃል ገብተን ወንድና ሴት- ድርና ማግ ስንሆን እንኳን ሳያስበው አይኖቹን በአይኖቼ ስይዘው አይኖቹ ላይ ትኩረትና ፍቅር አላይም። አንዳንዴ እንደውም ውስጤ መቆየት የሰለቸው…እሙሙዬ ውስጥ ዘልአለም የከረመ ያህል የታከተው የሚመስል ነገር አይኖቹ ላይ አነባለሁ።
እንዲህ አይቶኝ አያውቅም።
በማውራት ይሄን ያልተለመደ ክስተት ላቋርጥና ላበላሽ ስላልፈለግኩ ካለሁበት ሶፋ እየተሳብኩ ተጠጋሁት። ማየቱን ቀጥሏል። ደርሼ አንገቴን አንገቱ ውስጥ ቀብሬ በጥልቀት አሸተትኩት። ጦስኝ ጦስኝ ይላል።
ልቤ እንደሰም ሲቀልጥ፣ መንፈሴ በስሜት ማእበል ሲታመስ እንኳን የማወራው የማስበው ነገር ከአንጎሌ ሲተን…
– እህስ….ምንድነው የምትፈልጊው? አለኝ ከአንገቱ ውስጥ በእጁ ጎትቶ እያወጣኝ…
– ምንም…
– ምንም አትፈልጊም?
– ኤሊ…እንድትወደኝ…እንድትወደኝ ነው የምፈልገው…ያ ይከብዳል? ወደ አንገቱ ስር ተመልሼ ልወሸቅ ስል አሁንም መልሶ አወጣኝና በእነዚያ አሸባሪ አይኖቹ እያየየኝ
– መች ጠላሁሽ… ?አለኝ።
– እንደማትጠላኝ አውቃለሁ..ግን አንድ ቀን እወድሻለሁ ብለኸኝ አታውቅም…እ…ከመሬት ተነስተህ ታኮርፈኛለህ…ታበሻቅጠኛለህ…
– ምንድነው የምትፈልጊው? በስርአት ቁጭ ብለን ይሄን ነገር እንቋጨው…አለኝ ለስብሰባ እንደተቀመጠ ሰው መፅሃፉን እንደተከፈተ ሶፋው ላይ አስቀምጦ፣ እጆቹን አጣምሮ።
ቀና ብዬ ተቀመጥኩ።
– ልብህን…ልብህን ነው የምፈልገው…
እጆቹን አመሳቀለና ሳቀ።
ተበሳጨሁ።
– ያስቃል?
– ሃሃ…አዎ..እዚህ መፅሃፍ ላይ ያለው…አንዱ የአዳም ካራክተር ምን አለ መሰለሽ… ልቤን ለሴት ከምሰጥ ለጎረቤት ድመት ብሰጥ ይሻለኛል…
ዝም ብዬ አየሁት።
– ምን ታይኛለሽ..ካንጀቴ እኮ ነው…እውነቱን ነው…
አሁንም ዝም ብዬ አየሁት
– ጨረስን? ወደ መፅሃፌ ልመለስ?
– እየቀለድክ አይመስለኝም…አልኩ በተቀመጥኩበት እየተቁነጠነጥኩ
– አይደለም አልኩሽ እኮ…
– የአንድ ደራሲ ተረት ተረት እያነበብክ የእኛን ሕይወት ማበላሸት አለብህ?
– አዳም ስለማይገባሽ አልፈርድብሽም….
– እሱን ተወው..ዝባዝንኬ አይገባኝም…ድመት ምናምን…ሰውየው የሚያወራውን አያውቀውም…ግን አንተ ምነው ለልብህ እንደዚህ ሳሳህ? ልብህን ሰጥተኸው የጎዳህ ሰው ነበር እንዴ…እየተቁለጨለጭኩ ተጠየቅኩት
ዝም ብሎ ሲያየኝ ቆየና…
– ለምን ጦስኝ ሻይ አታፈይልኝም? ጠዋት የጠጣሁ ነኝ አለኝ መፅሃፉን እያነሳ…
– ለምን አትመልስልኝም…ለምንድነው እንደዚህ ፍቅርን የምትፈራው?
– በናትሽ ሻዩን…እያዛጋኝ ነው….
የምናብ ደጁ ሊዘጋብኝ ነው። ለዛሬ ከዚህ በላይ ሊያናግረኝ አልፈቀደም።
ለሻዩ ወደ ኩሽና መንገድ ጀመርኩና መለስ ብዬ አየሁት
-ኤሊ…
– እ….? (ከልቡ ሳይሆን)
– ልቤን ለሴት ከምሰጥ ለድመት ብሰጥ ይሻለኛል ነው ያልከኝ አይደል..?
– እ…አዎ…
የኩሽና መንገዴን ቀጠልኩ።
ሻይ ጀበናውን በውሃ ሞልቼ ምድጃው ላይ ጣድኩ።
ጦስኙን አዘጋጀሁ።
የእሱን ልብ እንዳገኝ ሰውነቱ ቀርቶብኝ ምነው ለአንዲት ቀን ድመት ባደረገኝ።
የማፈቅረው ልጅ መልሶ እንዲያፈቅረኝ ምነው ለአንድ ሌት ሚያው ባስባለኝ።
ሚያው….
2 Comments
ጥሩ ፀሀፊወች በዚህ አሉ:: ደስ ይላል እና ደሞ “ለጎረቤት ድመት” ተመችቶኛል
እሷ ምርጥ ልብ ለዛውም አፍቃሪ ልብ ነው ያላት ። እሱ ግን የአንባቢ ገልቱ ባይገልፀውም ልብ የለውም ሳምባ ነው ያለው ለድመት የሚሰጠው