ምክንያት በጠና ታማለች:: ምን እንደነካት ማንም አያውቅም:: አሉባልታ ግን አለ:: እነ ባህል; ዕድር; ሃይማኖት…መርዘዋት ነው የሚሉ አሉ:: ፍልስፍናም ይህን አሉባልታ ሰምቷል:: ሳይንስ ናት የነገረችው:: ባሉባልታ አያምንም:: ባያምንም ሰምቷታል::
ሁሉም በምክንያት ዙሪያ ቁጭ ብለዋል:: ፍልስፍና ያዘነ ይመስላል- ፊቱ ስለማይነበብ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም::
ሳይንስ ምክንያትን ሊያድን የሚችል መድሃኒት ለመፍጠር በተመስጦ እየሰራች ነው:: ሃይማኖትና ወንድሞቹ ደስ ያላቸው ይመስላል:: ምክንያት በጠና ታማለች:: እድር ጥሩንባውን እያዘጋጀ ነው:: ውስጡ ደስ ቢለውም ባህል ምን ይለኛል በሚል ደስታውን ለመሸሸግ ሞክሯል::
ባህል ባህሉ በሚፈቅደው መሰረት ምክንያት ስትሞት መደረግ ያለበትን ያስባል::
ሳይንስ መድሃኒቱን ለማግኘት እየጣረች ነው::
ፍልስፍና በሀሳብ ጭልጥ ብሏል::
ምክንያት ሕመሟ እየጠናባት ነው::
እግዜር ይማራት!