ሥራ ካለው ቦርጭ አለው

ላግባ እንዴ ለምትል ላጤ ሴት ካገባችና ( እስካሁን) ደስተኛ በሆነ ትዳር ውስጥ ከምትገኝ ባለትዳር ሴት የቀረበ ምክረ ሃሳብ

እንግዲህ ካገባሁ ሁለት አስርት ዓመታት ልደፍን ትንሽ ቀረኝ።

ወቅቱ የሰርግ ነው፣ እኔም ቢከርምም ሙሽርነቴ በጥር ነበርና፣

እነሆ ስለትዳር ሃቅ ሃቁን መስማትን ለምትፈልጉ እንስቶች

እቅጭ እቅጩን ፣ ነጭ ነጩን

ሳላሞካሽ፣ ሳልቀባባ፣

እንደሚከተለው እመክራለሁ።

ቅድመ-ጋብቻ

——

ምርጫ ተትረፍርፎልሽ “ማንን ላግባ” በሚል የግርታ ጉም ተጋርደሽ ከሆነ

ከዚህ በታች ያለው ሊጠቅምሽ ይችላልና አንብቢው፡፡

እቱ ገላ!

ከሁሉ በፊት ይህንን እወቂ!

አንድ)

ለትዳር ብቁ የሆነ ወንድ…

ስራ ካለው ቦርጭ አለው።

ብር ካለው መላጣ ነው።

ታታሪና ቤቴ ቤቴ ባይ አባወራ ሰላላ እግሮችና ነጋሪት ሆድ እንጂ ጡንቻና ሲክስ ፓክ ይለውም።

አብላጫው ወንድ ገንዘብ በበሩ ሲገባ ፀጉሩ በመስኮት ይወጣል።

ፀጉሩ ያላፈገፈገ፣ ባለሞዴል አቋም እና ሃላፊነት የሚሰማው ወንድ በአንድነት ባል ሆነው ሲመጡ ካየን ቆይተናል።

ስለዚህ ምርጫሽ ላይ ተጠንቀቂ።

‹‹ሲክስ አብ›› አይተሽ፣ በባትና ደረቱ ተማርከሽ ስታለከልኪ፣ አጇኳሚው ላይ እንዳትወድቂ።

ሁለት )

አበባ እየገዛ እሾህ ከሚሆንብሽ፣ ቫኬሽን እያዞረሽ ዓይኑ ሌላ ከሚቀላውጥ ወንድ ይልቅ ሮማንቲክ ባይሆንም፣ ገና እምቦቃቅላ ሳለሽ የትራስ ጨርቅሽን የቬሎ የራስ ልብስ አስመስለሽ ያገባሽው የእቃቃ ባልሽ አይነት ባይሆንም ፣

( እንደ አቅሙ) የሚያስፈልግሽን ነገር ሳትጠይቂው የሚያደርግልሽን ሰው ባል ካደረግሽ መለስተኛ ገነት ገባሽ። ይሄን ስልሽ አበባ ሰጥቶ ማር፣ ቫኬሽን አዙሮ ታማኝ የሆነ ወንድ የለም ማለቴ አይደለም፡፡ ግን ብዙ አይደሉም፡፡ ካሉም አግብተዋል፡፡

ስለዚህ….አብዛኛው አይነት ገጥሞሽ በብልጥልጥና ጊዜያዊ ብልጭልጭ ነገር ተታለሽ ይህን ከሳትሽ ዘላቂ ሲኦል ወረድሽ።

እሺ…መምረጡንስ መረጥኩ…ግን ለመሆኑ ትዳር ግን እንዴት ነው? ካልሽ ደግሞ የሚከተለውን ተመልከች።

አንድ)

ትዳር ነጋ ጠባ የምትሳሳሚበትና ፍትፍት እየተጎራረስሽ” ፍቅርዬ ወዬ ወዬ” የምትባባይበት ሮማንቲክ ኮሜዲ አይደለም።

ዘጠና በመቶው ሎጅስቲክ ፣ አሰልቺ የቀን ተቀን ኑሮን መግፊያ መስተጋብር፣ ደሞዝ አልባ ስራ ነው።

እውነቱን ፍርጥርጥርጥ አድርጌ ልንገርሽ?

የት ነህ)የት ደረስክ) ልጆቹ ምግብ በሉ?) አምፖሉን መግዛት እንዳትረሳ) ዳይፐር ይዘህ ና) እናትህ ዛሬም ይመጣሉ) ቀዩን ሸሚዜንን የት ከተትሽው) እራት ዛሬም ምስር ነው) ሁሌ እርጥብ እየበላሽ እንዴት ልትከሺ ነው)

ዓይነት ነገር ይበዛዋል።

ከዚያ ግን አልፎ አልፎ በፊት፣ ገና አፍላ ፍቅር ላይ ሳላችሁ እንደሚያደርገው አየት፣እቅፍ፣ ሳም፣ ውድድ ሲያደርግሽ ነፍስ ትዘሪያለሽ።

የሆነ ሰውዬ ሚስትና የሆኑ ልጆች እናት ከመሆንሽ በፊት ማን እንደነበርሽ ትዝ ይልሻል።

ሴክሲ ሴክሲ ያጫውትሻል።

እንኳን አገባሁ ትያለሽ።

ወዲያው ግን በፍቅር ድግስ ልባችሁ ጠፍቶ ደክማችሁ በተንጋለላችሁበት፣

“አከራያችን ደጋግሞ ሲደውል ነበር። አላነሳሁለትም። ይሄ አሳማ! ጨምሩ ሊላለን ነው መሰለኝ። ?”ሲልሽ ወደ ፈዛዛው ፣ ደብዛዛው፣ ለዛዛው መደበኛ ትዳርሽ ተስፈንጥረሽ ትመለሻለሽ።

ሁለት)

ካልተጣላችሁ ትፋታላችሁ!

ይሄን ስልሽ ደግሞ ዘወትር በነገር ተቋሰሉ፣ ነጋ ጠባ ጠበኛ ሁኑ እያልኩሽ አይደለም፡፡ ግን የሚዋደድ ባልና ሚስት አልፎ አልፎ ካልተጋጨ፣ ቀን እየዘለለ ካልተደባበረ፣ ተደባብሮ ካልታረቀ፣ ታርቆ እንደገና ካልተደባበረ….ነገር አለ!

ተጣላችሁ ማለት ትፋታላችሁ ማለት አይደለም፡፡

ይልቁንም ነገርን እያድበሰበሱ በሆድ ይፍጀውና በችዬው ልኑር በከመሩት ቁጥር ክብደቱ ከመጠን ያልፍና ወገብም ቅስምን ሰብሮ ባልጠበቁት ሰአት ትዳሩን ይበትነዋል፡፡

እንደ ተቀበረ ቦንብ የት ጋር ነበር ሳይባል ፈንድቶ ሁለታችሁንም ይበታትናችኋል፡፡

ስለዚህ መሰረታዊ ባልሆነ ነገር ጊዜያዊ ጠብ ብትጣሉ አትሸበሪ፡፡

ይልቅ ካልተጣላችሁ..ለመጣላት እንኳን ግድ ካልሰጣችሁ … ያኔ….እሱን ፍሪ!

ሶስት)

ባልሽን ሳታቋርጪ ስትነተርኪው ምንም ካልመለሰልሽ የምትይውን ማዳመጥ ካቆመ ቆይቷል።

አለ አይደል….አንቺ ሳይከፍል ስለረሳው የልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ ስትለፈልፊ እሱ አርሴናል እኔ ሳልሞት ዋንጫ ይበላ ይሆን ብሎ እያሰበ፣ አውራ ዶሮ ግን ከረቫት ቢያደርግ ምን ትመስል ይሆን በሚል የቂል ሃሳብ ራሱን እያዝናና ነው።

ይሄ ደግሞ ክፋት አይደለም፡፡ ወንድነት ነው፡፡ አንቺ ፊትሽ እንዳይጨማደድ ሞይስቸራይዘር እንደምትለቀለቂው እሱም ይሄን ሲያደርግ ራሱን እየጠበቀ ነው- በወንድኛ!

፪) ባልሽ ምን አንጀትሽን ቢበጥሰው….(እመኚኝ ደህና የሚባለው ባል እንኳን ደጋግሞ ይበጥሰዋል) አፀፋውን ልመልስ ብለሽ ካንቋሸሽው፣ በሰው መሃል ካዋረድሽና ካሳንሽው፣ ወይ ደግሞ ሲደክም በማበርታት ፈንታ ልግመኛ ካልሽው፣ ሲከፋው እንደማፅናናት ሆድ ብሶት ሳለ ማጭድ ካቀበልሽው፣ ሲጎድልበት ከተሳለቅሽበት፣ ሲወድቅ ከረገጥሽው፣ ለሸረኛና አሽሟጣጭ ሰው አሳልፈሽ ከሰጠሽው፣

እንደው ባጠቃላይ ባሌ ነው ብለሽ የመረጥሽውን ሰው እንደልቤ አልሆነልኝም ብለሽ የወንድነት ክብሩን ከነካሽው፣ የአባወራ ማእረጉን ግፍፍ አድርገሽ ካኮሰስሽው

እቱ ገላ! ሁሉ ነገር ማክተሙ ነው።

በቃ ምን ልበልሽ?

ባልሽን እንዲህ ያለ ነገር (በተለይ ደጋግመሽ ) ከሰራሽው

የጎጆሽን ስርና መሰረት ነቀነቅሽው።

አራት)

ባልሽ ( ልክሽ ባይሆንም፣ አንቺ ለራስሽ የማትመርጪው ነገር ቢሆንም፣ ባትወጂውም) አስቦ ስጦታ ቢጤ ሲያመጣልሽ፣ ያላሰብሽውን ሸክም ሲያቀልልሽ አቅፎ በማመስገን ፋንታ ቆሌውን ከገፈፍሽው ….ቢፋቅ ቢፋቅ የማይደበዝዝ ደማቅ ስህተት ሰራሽ።

አለ አይደል…

ስጦታውን እያየሽ…

ሲያስጠላ!

ምን ሆነህ ነው ይሄን የገዛኸው?

ርካሽ ነው አይደል?

አንድ ነገር ሲፈጽምልሽ ፣

ድሮስ ማን ሊሰራልህ ነበር?

ምናምን እያልሽ ቅስሙን አትስበሪው፡፡

ለምን አትይም?

ወንድ ልጅ ከውጪ ሲታይ የአዞ ቆዳ ይኑረው እንጂ ውስጡ እምቡጥ ነው፡፡

ጥሩ የሰራ ሲመስለው፤ ከምንም በላይ ጎሽ መባልን፣ በሚስቱ መመስገንን፣ ከባለቤቱ አበጀህ የኔ አንበሳን የሚሉ ቃላትን ይናፍቃል።

ይሄንን በፌኒዝምኛ ስታወራርጅው ባይጥምሽም ዋጭው።

ስለዚህ የባልሽን ስጦታና ድርጊት እንዳልወደድሽው ወይ እና እንዳልተስማማሽ መንገር ቢኖርብሽ እንኳን የተሻለ ጊዜና ሁኔታ ምረጪ።

እንዴት ልበልሽ…በክፉ ቃላት ሰብረሽው ትዳርሽን ከማመስ ይልቅ ያምራል ብሎ የገዛልሽን የስልሳ ዓመት ባልቴት የሚያስመስልሽን ዥንጉርጉሩን ገርዳሜ ቀሚስ ለአንዲት ቀን ለብሰሽ ከአይኑ ብትሰውሪውና ቆይተሽ በመላ…እኔ የምወደው ቀሚስ እኮ እንዲህ ያለ ነው ብትይው አይሻልም?

ከፋሽ እንዴ?

አይክፋሽ።

እመኚኝ ይህንን ሁሉ ቀድመሽ በማወቅሽ በኃላ ከሚመጣ የከፋ የልብ ስብራት ትድኛለሽ።

ልደምድምልሽ።

ምን መሰለሽ?

ትዳር እንከን አልባ ሰውን ፍልጎ በማግባት የሚቆም ለደስታና ለጨዋታ ብቻ የተሰራ ተቋም አይደለም።

እንዳይጎረና የሚማሰል ወጥ፣ እንዳይደርቅ የሚኮተኮት የአትክልት ስፍራ፣ እንዳይታመም የሚከተብ ሕይወት ያለው ነገር ነው፡፡

ስለዚህ እንከን አልባ ሰው በመፈለግና ያገባሽውን ሰው እንከን ለማጥፋት በከንቱ ከመዳከር ይልቅ ከእንከኑ በላይ እወደዋለሁ ከምትይው ሰው ጋር ተጣምሮ ለመኖር የሚወሰንበት ጉዳይ መሆኑን አምነሽ ግቢበት።

አለ አይደል…

ይህችን እስስት ዓለም ብቻዬን ከምፋለማት አብሮኝ ቢሆን ሸክሜን ያቀለዋል የምትይውን፣ ሲከፋኝ ጀርባዬን በመዳፉ ቸብ ቸብ ያደርግልኛል፣ ሳለቅስ እምባዬን ይጠርግልኛል የምትይውን ሰው ባል አድርጊ።

ይሄው ነው። ከዚህ የረቀቀ፣ የተወሳሰበ ጉዳይ የለውም።

ውይ…ረስቼው…

እቱ ገላ!

አደራሽን ይህችን እንዳትዘነጊ! ከትዳር በፊት ያለውን ነገር ስታደርጊ…በገርልፍሬንድ ማእረግ ሚስት ሆነሽ እንዳትገኚ! በእጮኝነት ዘመንሽ የሚስትነት ሃላፊነትን አትረከቢ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *