“አቤት?” አልኩት ለሰላምታ የዘረጋውን እጁን ችላ ብዬ ወንበሬ ላይ እየተቀመጥኩ። ፀጉሩ አልፎ አልፎ ከመሸበቱ ውጪ ብዙም አልተለወጠም።
“ደህና ነሽ ሚሚሾ?”
“ምን ፈልገህ ነው የመጣኸው? ደህና መሆኔ አሳስቦህ አይሆንም መቼም!! የልጅህ ሰርግ ጥሪ ወረቀት እንደደረሰኝ ለማረጋገጥ ከሆነ ደርሶኛል። እማም ደርሷታል። ጨርቄን ጥዬ እንደሆን እንድታይ ሚስትህ ከሆነ የላከችህ። ሂድና ንገራት! ረስተናችኋል። እባካችሁ ከህይወታችን ውጡ። እና ከቢሮዬም ውጣ……” መናደድ አልፈልግም። ግን አስቤያቸው አለመናደድ ያቅተኛል። ሁሌም እንዲህ ናቸው። ስተዋቸው አይተውኝም። ዝቅጥ ብለው ያዘቅጡኛል። ስለእውነቱ የሁሉም ክፉ ነገር ሀሳብ ባለቤት ሚስቱ ናት። እሱ መልሱ ዝምታ ነው። ጋግርት። ግን ከእርሷ ቅጥ የለሽ ክፋት በላይ የሱ ዝምታ ይሰብረኝ ነበር።
“ለግሌ ጉዳይ ነው የመጣሁት።” አለኛ አፉን ሞልቶ።
“ሰውየው ከእኔ ጋር የሚያገናኝ የግል ጉዳይ የለህም። እባክህ መጥፎ ነገር አታናግረኝ። ውጣልኝ……”
“የውብዳርን ልፈታት ነው። በመሀከላችን ብዙ ጣጣዎች ስላሉ ጠበቃ ያስፈልገኛል። …” ወደ በሩ እየተራመደ “… ትረጂኛለሽ ብዬ ተስፋ ነበረኝ። ጭራሽ ልትሰሚኝ እንኳን ፈቃድሽ ካልሆነ ምን አደርጋለሁ? ባልደረቦችሽን ላማክራቸዋ?” በሩን ከፍቶት ወጣ። ምን? እኮ የቤተሰቤን ጉድ ባልደረቦቼ ሊሰሙ? በተለይ ደግሞ ፍትህ? ኡኡኡ ልል ትንሽ ነበር የቀረኝ። በሩጫ ተከተልኩት። አጠገቡ ስደርስ እልህም ንዴትም አነቀኝ። ጮኬ ማውራት ግን አልችልም። እኔን የሚያነድበት አንዲት የነገር ሽራፊ ለሚፈልገው ፍትህ ራሴን አላጋልጥም።
“ምንድነው ግን ከኔ የምትፈልገው? ምን አድርጌ ነው እየተከታተላችሁ ልታጠፋኝ የምትተጉት? በምትወዳት ልጅህ ይሁንብህ ተወኝ?” አልኩት ጥርሴን ነክሼ ከእንባዬ እየታገልኩ። ሁሌም እንደዚህ ነው። ቤተሰቤን አስመልክቶ መጨረሻዬ እንባ ነው። ተሸናፊ ነኝ። አሸናፊዎች ናቸው። በፈለጉበት ቀን መጥተው ከዓይኔ እንባዬን ለመቅዳት የመብታቸው ያህል ቀላል ነው። የፈለጉትን ይቀሙኛል። …… እኔ ይህቺ ነኝ! የአደባባይ አንበሳ! የቤቴ አይጥ ነኝ።
“አንድ ጊዜ ብቻ ቁጭ ብለሽ እንድትሰሚኝ እፈልጋለሁ። እውነቱን ላስረዳሽ እፈልጋለሁ። የምፈልገው እሱን ነው።”
“እባክህ ሂድልኝ። እባክህ ተወኝ። አንድ ያልነጠቃችሁኝ ነገር ስራዬ ነው። አንድ የእናንተ የክፋት እጅ ያልደረሰበት ቦታ የስራ ቦታዬ ነው። እባክህ ልለምንህ እሱን ተውልኝ።………” ከየት መጣ ሳልለው ፍትህ አጠገባችን ደርሶ
“እንዴ አባባ ሻይ ቡና ምን ይምጣሎት?…” እየለፈለፈ እያለ አየኝና ደነገጠ። “…… እንዴ ቦስ ችግር አለ እንዴ?ምነው የተፈጠረ ነገር አለ?” አብረን ስራ የጀመርን ሰሞን ሊያናድደኝ ሲፈልግ ‘ቦስ’ እያለ መጥራት ጀመረ። ዛሬም ድረስ እንደዛ ነው የሚጠራኝ። ዝም ካልኩት መጠየቁን እስከማታ አያቆምም።
“ፍትህ ዘወር በልልኝ!” ብዬ ጮህኩበት።
ለምኜም ተቆጥቼም አባቴን ሸኘሁት። ሌላ ቀን እንደሚመለስ ነግሮኝ ሲወጣ ያዘነልኝ ይመስል ነበር። የውላችሁ…… እዚህ ተረክ ውስጥ ማንም ጥሩ ማንም መጥፎ የለም። ሁሉም ጥሩ አይደሉም። ሁሉምም መጥፎ አይደሉም። እናቴን ጨምሮ!! ስለቤተሰቦቼ ሁሉንም ባላውቅም አንዳቸውም ንፁህ አይደሉም። የተዘራሩትን ነው የሚተጫጨዱት። ለነገሩስ የሰው መቶ ፐርሰንት ጥሩ ወይ መጥፎ የታለው? ጥሩ የምንለው ሰው ክፋቱን በጥሩነቱ የሸፈነ። ክፉ የምንለውስ ጥሩነቱን በክፋት የሸፈነ አይደለምን? እንጂማ ሁሉም የክፋትና የመልካምነት ስብጥር አይደል? ጎልቶ ባሳየው ይጠራበታል።
እኔስ? ባልበላሁት ጉሮሮዬን እየቧጠጠ ያስመልሰኛል። ያልዘራሁት እሾህና አሜኬላ እየበቀለ እድሜዬን ሙሉ ሲያንቀኝ አለ። ራሴ ከዘራሁት መልካም ዘር ቀድሞ እነሱ የዘሩት እንክርዳድ ደርሶ እበላዋለሁ። እንደአረቄ አዙሮ ይደፋኛል።
“ቦስ ቡና ላምጣልሽ?” ቢሮዬ መጥቶ ነው።
“እባክህ ፍትህ… … እየደጋገምክ የቢሮዬን በር መክፈት አቁም።”
“Am just worried… … የሆንሽውን እያየሁ ዝም ብዬ ልቀመጥ?”
“አዎን እንደሱ አድርግ። ዝም በለኝ።”
“እሺ እቤት ሄደሽ እረፊ። እዚ ሆነሽ ምንም ነገር በትክክል አትሰሪም።” አለኝ። እማ ትዝ አለችኝ። ኮቴን አንስቼ አልፌው ሄድኩ። እቤት ስደርስ የቀረበላት ምግብ ላይ ትተክዛለች። የማይሰማ ነገር ታጉተመትማለች። ሰራተኛዋ ቆማ እየጠበቀቻት ነበር።
“እማ እባክሽ ዛሬ አይሆንም። ዛሬ ደህና ሁኚልኝ። ዛሬ አልችልም። አልችልም!!”
ቀና ብላ አየችኝ። “አንቺ ደግሞ ማነሽ? የውብዳር ናት የላከችሽ? ” አምላኬ ሆይ አይሆንም! አይሆንም!!
“አይደለም እማ አንዱዓለም ነው የላከኝ።” ከቃላቶቹ ጋር እንባዬ ይወርዳል። እሷ የእሱ ስም ከተነሳ እያለቀስኩ ይሁን እየሳቅኩ ግድ የላትም። ሲጀምራት ሰሞን የእርሱ ስም ያረጋጋታል። እሱ ይሄን ማወቁን እንጃ! እብደቷም መድሃኒቷም እሱ ነው።
“እና ምን አለሽ?”
“የኔ ጨረቃ ናፈቅሽኝ እኮ! ባክሽ ይሄ ስራ ይቅርብሽና ሁሌ ማታ ማታ ልይሽ?………”ባሏ እሷ ስራ ስትሄድ የፃፈላት ደብዳቤዎች ናቸው። እሷም በቃሏ ሁሉንም ታውቃቸዋለች። እኔም እንደዛው። ለዓመታት በቃሌ አነብንቤላታለሁ። አብራኝ ቃሎቹን እያጣጣመች እንቅልፍ ይወስዳታል። ……… ዛሬም ለአንድ ሰዓት ያህል የባሏን መልእክት ነግሪያት እሷ ሶፋው ላይ ፈገግ እንዳለች እንቅልፍ ጣላት።