Tidarfelagi.com

ራእይ

ከካፌ በረንዳ ለይ ተቀምጬ ያላፊ አግዳሚውን ፊት በማየት መደነቅ ማደነቅ እወዳለሁ። ፊት የውስጥ ስሜት መገለጫ ሰሌዳና የሰፊው ሕይወታችን መታያ ሜዳ ነው።ለእንቦቀቅላ ሕጻናትም የሰው ፊት ከሁሉ የሚያዝናናቸውና የሚያስደምማቸው አሻንጉሊት ነው ይባላል። ፊት ባለ ብዙ ቀለም (ነጭ፣ ቀይ፣ ቡኒ፣ ጥቁር …)፣ ተንቀሳቃሽ ምስልና ድምፅ አፍላቂ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በብዙ ስሜት የተሞላ መሆኑም ነው።

ታዲያ አንድ ቀን እንዲሁ ቁጭ ብዬ አላፊ አግዳሚውን ስቃኝ አንዲት ትንሽ ልጅ ቀረብ ብላ በሚቁለጨለጩ አይኖቿና ሀዘን በተሸከመ ድምጿ ገንዘብ እንድሰጣት ታግባባኝ ጀመር። የአፍታ ትውውቃችን ሲጨምር ታሪኳን በወፍ በረር አወጋችኝ … ምን ያህሉ እውነት ይሆን? እኔ እንጃ። ግና … ልጅ ናትና ያነገረችኝን ሁሉ ማመን መረጥኩ።ከወሬያችን ቅንጫቢው እንዲህ ነበረ።

“ሚሚዬ ስታድጊ ምን መሆን ነው የምትፈልጊው?” አልኩ እጅ እጄን የሚያዩ አይኖቿንና ቀልቧን ለመግዛት እየሞከርኩ።
ብዙም ሳታቅማማ “የቤት ሰራተኛ” አለች አንገቷን ሰበር አድርጋ። ምላሿ ከነበርኩበት ዝምብሎሽዮሽ ጨዋታ አወጣኝ። ከልቧ መሆኑን ስረዳ አቀማመጤን አስተካክዬ ነገረ-ነገሬን ወደርሷ ሙሉ ለሙሉ አዞርኩኝ። “ለምን?” አልኳት … ‘የቤት ሰራተኛ መሆን እንዴት ላንድ ህጻን ልጅ የህልም ጥግ ሊሆን ይችላል’ አልኩ በልቤ። ምክንያቱም … ‘ጥያቄው የምኞትና ስለምኞት ነው … ታዲያ ለምን መሃንዲስ፣ ጠበቃ፣ አስተማሪ ወይም ፓይለት …አላለችም? ብዬ አሰብኩ’። አሳዘነችኝ።

“የፈለኩትን ምግብ እስክጠግብ እንድበላ” ብላ፣ የሚንከራተቱ አይኖቿን በልጅነት የዋህነቷ በጎሬያቸው ውስጥ ስታንከባልላቸው ልቤ በደረቴ ውስጥ ተላወሰ። ባዶ እግሯን ናት። ፊቷና ልብሷ አቧራ ጠግቧል። ባንድ እጇ የተንጨበረረ ጸጉሯን እያከከች ዙሪያ ገባዋን ቃኘት ቃኘት አደረገች። ከኔ የተሻለ ሳያስለፈልፍ የሚሰጥ ሰው የፈለገች መሰለኝ። ትንሽ አወራሁዋት። የሰጠሁዋትን ተቀብላ ብን ብላ ካጠገቤ ስትጠፋ ምስሏና ምኞቷ ግን ከእኔ ህሊና ተጣብቆ ቀረ። ድህነት ምኞትን የሚኮስስ ህልምን የሚገድል መርዝ መሆኑን ተረዳሁ።

ልጅቱን ከዛ ወዲህ አላየሁዋትም። የዛሬ አምስት አመት ኤድና ሞል አካባቢ ነበር። ያኔ እድሜዋ ስምንት አመት ቢሆናት ነበር። ዛሬስ ህልሟ የት አድርሷት ይሆን? እርሷስ ህልሟን የት አድርሳው ይሆን?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *