ሰላምታ ለሀሳብ ወዳጆቼ፣ ቤተሰብና ጎረቤቶቼ …
እንደገና በመጽሀፈ-ፊት (fb) ገጻችን ምስል ለምስል ለመተያየት ያበቃን አምላክ ምስጋና ይድረሰው። ትዝ ካላችሁ የትንሿ ልጅ አሳዛኝ ታሪክ በምናቧ የቀረጸውን ስንኩል ህልም አንስተን ነበር ባለፈው። የመንደርደሪያ ሀሳቦችን ወርወር አድርጌ ነበር … ነገሩ እንደ ተጀመረ በእን…ጥል…ጥል የተሰናበትነው። ከጽሁፉ ግርጌና ከመልእክት ሳጥኔ ራስጌ የሰጣችሁኝን አስተያይቶችና ጥያቄዎች በማየት አመስግኛችኋለሁ። ከታሪኩ እውነታ ባሻገር የሁላችንም የየቅል ምልከታ ሳይዘነጋ … እስኪ ትንሽ ከትንሿ ልጅ ህልምና አሳዛኝ እጣ ፈንታ እንውጣ። ደግሞም የሷ አይነቶቹን የብዙ ሕጻናትን መራር እጣ ፈንታ ለአሁን … ለጊዜው ተወት እናድርገው (ለጊዜው ነው ያልኩት) ። የየራሳችንን የልጅነት ህልምና የ‘አዋቂነት’ ራእይ … የመኖራችንን አላማ … በምልሰት እንዳስስ … እናስታውስ እስኪ …
በየመስሪያ ቤቱ ደጃፍ ተለጥፈው ከምናያቸው ግዙፍ የራእይና የእሴት ሰሌዳዎችን አንዱን ባይነ ልቦናችን ከፊቱ ቆም ብለን ከታች እስከ ላይ እንቃኝ። ከዚያ ደግሞ … ወደ ልባችን ጓዳ ገብተን የራሳችንን ራእይና የእሴቶቻችንን ሰሌዳ እንፈትሽ … ካለን ማለት ነው። ምን አገኛችሁ? እዚያው መስሪያ ቤት ደጃፍ እንደቆማችሁ ሰሌዳው ላይ ያለውን ጽሁፍ አጥፉት። አሁን የራሳችሁን ህልምና ራእይ … እሴትና የህይወት መርህ ከእውነቱ ሳትዛነፉ … እዛው እነጩ ሰሌዳ ላይ … በሰማያዊ ቀለም ራእያችሁን … በቀይ ቀለም ደግሞ እሴታችሁን ደርድሩ። ምን ጻፋችሁ? … ራእይና እሴትን ባጭሩ መጻፍ እንዲህ ይከብዳል እንዴ?
የእሴቶቹን ጉዳይ ለጊዜው እንተወውና እስኪ ራእዩ ላይ እናተኩር ለዛሬ። … እሴት የሌለው ህልም የማይፈጸም የቀን ቅዠት መሆኑን እንደምታውቁም አውቃለሁ።
በመጀመሪያ ግን … አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ። አንድ ጤነኛ የሆነ አካለ ሙሉ ሰው ስንት አይን አለው? … ቀላሉና ቀናው መልስ ሁለት ነው … ያውም የግራና የቀኝ። ሁለቱን አይኖቻችሁን ከታች ወደ ላይ … ከግራ ወደ ቀኝ አሽከርክራችሁ ትከሻችሁን ስትንጡት ታየኝ። ለእኔ ግን መልሱ ሶስት ነው። በሹፈት ነገር … ፈገግ አላችሁ እንበል … ጨዋ ስለሆናችሁ። የምር ግን መልሱ ስንት ነው? … አዎን … ሶስት ነው። በምስራቅ ፍልስፍና አይነት የመሀል ግንባሩን ሦስተኛ አይን ተብዬ ጨምሬ ግን አይደለም።
እንዲህ ነው ነገሩ … ቁጠሩ።
1. አይነ ሥጋ – ግራና ቀኝ አይኖቻችን – sight
2. አይነ ልቦና – ምናብ – imagination
3. አይነ ሕሊና – ራእይ/ህልም – vision
እፍርታም … እንደሱ አትልም ታዲያ አላችሁ? … ታዲያ ድሮስ እንደ ምን ብዬ ኖሯል? … እነዚህ አይኖች ተግባራቸው ለየቅል ቢሆንም እጅጉን የተሳሰሩ ናቸው። አንዱ ያለሌላው ስንኩል ነው፣ የቱም በየትኛው ሊተካ አይችልም። ነገረ ስራቸውን ለመረዳት የሚከተለውን አረፍተ ነገር በማንበብ እንጀምር። አረፍተ ነገሩን አንብቡና መልሱን ለራሳችሁ ስጡ።
“ከአስር አመት በኋላ ምን ስትሰራ/ሪ ራስህ/ሽን ታያለሽ/ህ?”
1. ጽሁፉን ባይነ ስጋችን አይተን አነበብነው (ቁሳዊውን ነገር የምናየው በዚህ አይናችን ነውና) – we see things with our physical eyes
2. ካነበብነው በኋላ ደግሞ ዛሬ ካለንበት ተነስተን በአስር አመት ውስጥ ልንሆን የምንችለውን ባይነ ልቦናችን ለማየት ሞከርን (መሆን የሚችለውን በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ያለውን ነገር የምናየው ደግሞ በዚህ አይናችን ነው) – we see ideas/possibilities with our imagination
3. አፈጣጠራችንና ጥልቅ የውስጥ ረሃባችንን ከረቂቅ ማንነታችን ውስጥ በርብረን ልናይ ስንሞክር ደግሞ ህልማችንን/ራእያችንን (መሆን ያለበትንና የተፈጠርንለትን ያንን ነገር በአይነ-ህሊናችን እናያለን) – we discover our vision (purpose + potential) with our spiritual eyes.
ለዚህ ነው ሰው በአይነ ስጋው ብቻ ካየ ቁሳዊ ፍላጎቱንና ሜዳዊ ህይወቱን በመምራት ከእንሰሳ ያልተለየ፣ ለሰውነቱ ፍላጎት ያደረ፣ የስጋውና ያካባቢው እውነታ ባሪያ የሚሆነው። ከዚህ ነፃ የሚያወጣው ነገር አይነ ልቦናውን መጠቀም ሲችል ነው። በአካላዊ አለሙ ያለውን ችግርና እድል አመዛዝኖ፣ ከፍ ባለው የአእምሮው ምናባዊ አይን (imagination) ተጠቅሞ … ስውር መርሆችን በመጠቀም ቁስን ለሀሳብ ሲያስገዛ … ከችግሩ በላይ በመኖር ለራሱም ለሌሎችም የተረፈ ኑሮ የሚኖረው። ከጤፍ እንጀራን … ከወርቅ ጌጥን … ከብረት መኪናን … ከቃላት ቅኔን … ስልክና ቴሌቪዥንን … መድሃኒትና ኤሌክትሪክን … ስንቱን እንዘርዝረው … የሚፈጥረው።
አይነ ልቦና (imagination) በልጦ አይነ ስጋን (sight) ሲመራው … ከችግር ውስጥ እድልን ማየት ይቻላል … ትግልም የድል ምንጭ ይሆናል። ሀሳብ ከቁስ ይልቃልና … ቁሳዊ ውሱንነታችን ለሀሳብ የበላይነት እጁን ይሰጣል። በሮቢን ደሴት ካለችው አስከፊና ጠባቧ እስር ቤት ይልቅ … አፓርታይድን ገርስሶ ያሸነፈውን እርቅ ሰላምና እኩልነት የሰፈነባት አዲስ ደቡብ አፍሪካን በእይነ ልቡናቸው ማየት ለማንዴላ … ሀያ ሰባት አመት በፈጀው መራራ ትግልና ፈተናን የማለፍ ጉልበትና የድል ብቃትን ሰጥቷቸው ነበር። ግን ደግሞ ይህ ሀሳብ እውን ለመሆን … በአይነ ልቦናቸው ላዩዋት አዲስቲቱ ደቡብ አፍሪካ መፈጠር … ሀይልና እርግጠኝነቱ ከየት ተገኘ? ብሎ መጠየቅን ያጭራል።
አይነ ልቦና ሀሳባዊ እውነቱን አይቶ ቁሳዊ እውነታውን እንዲያስገዛ ደግሞ የግድ ሌላው ሶስተኛ እይታ አስፈላጊ ነው።ይህ ነው ራእይ ወይም ህልም የምንለው። ልክ ቁስ ለሀሳብ እንደሚገዛ፣ ሀሳብም ለህልም/ራእይ ይንበረከካል። ለዚህም ነው … “ህልም አለኝ … አንድ ቀን ልጆቼ በቆዳቸው ቀለም ሳይሆን በባህሪያቸው ይዘት ማንነታቸው ይለካል” … በማለት እስከዛሬ በሚያስተጋባው ንግግሩ የሚታወቀው የባለራእዩ ማርቲን ሉተር ኪንግ ህልም አነሰም በዛ ዛሬ ተፈጽሞ ያየነው። እንኳን መመረጥ … መምረጥም በማይችሉበት ሀገር ውስጥ ያ ድንቅንግግርበአደባባይ በተደረገ በሀምሳ አመት ውስጥ … ዛሬ ጥቁር አሜሪካዊ ፕሬዝዳንትን ለማየት መብቃታችን … የራእይ ተአምር ሊባል ይችላል። ህልም/ራእይ ሀሳብን ይገዛልና።
ራእይ ከውስጥ በአይነ ህሊናችን የምናየው የመሆን ብቃትንና መቻልን የማየት የእይታ ደረጃ ነው። ለዚያ አይነቱ እይታ ደግሞ የሀሳቡ አለም ይገዛል። የቁሱ አለም ደግሞ የሀሳቡን አለም መሰስ ብሎ ይከተላል። ሰው ሲፈጠር ቁሳዊ አካል ያለው ሰውነት/አይን ብቻ ሆኖ ሳይሆን ሀሳብን በሚገዛና በሚረዳ አእምሮ/ምናብም ታጥቆ ነው። ለዚህ ምናባዊ እይታ ደግሞ ረቂቅ አእምሮ (Mind) እና አስገራሚ አንጎል (Brain) ተሰጥቶታል። ሊገባን ከሚችለው በረቀቀ ደረጃ … ሰው የመፈጠሩን አላማ (Purpose) እና በውስጡ የተሰወረውን ያንን የማስፈጸም እምቅ ብቃቱን (Potential) ይዞ የተፈጠረ ስለሆነ … ባለራእይና ባለህልም የመሆን ብቃት አለው።
በአየነ ስጋ ለማየት አይንና ብርሃን ያስፈልጋል። በአይነ ልቦና ለማየት ደግሞ ሀሳብና ማሰቢያ አእምሮ ያስፈልጋል። በአይነ-ህሊና/ራእይ ለማየት ደግሞ የተፈጠርንበትን አላማ (purpose) እና ለዚያ ማስፈጸሚያ በውስጣችን ተቀብሮ ያለውን እምቅ አቅም (potential) መረዳትና መጠቀም ያስፈልጋል። ይህም እንደሚከተለው ሊከለስ ይችላል።
አይነ ሥጋ (eyes) + ብርሃን (light) = እይታ (sight)
አይነ ልቦና (insight) + ሀሳብ (idea) = ምናብ (imagination)
አላማ (purpose) + እምቅ አቅም (potential) = ራእይ (vision)
ራእይ የሌለውና ምናቡ የቆረቆዘበት ሰው ቁሳዊ እይታውና ችግሩ ይገዛውና የችግሩ ባሪያ የካባቢው አሽከር ይሆናል።
ስለራእይ በጀመርነው ሀሳብ … እንቀጥላለን … መልካም ጊዜ … ከምስጋና ጋር … ሀሳባችሁንና ጥያቄያችሁን እንጋራው … አመሰግናለሁ።
አይነ ሁለንተናችን… ሦስቱም ፏ ብለው ይብሩልን።
2 Comments
ድንቅ ገለፃ ነው,,,,,,
በአይነ ስጋዬ አንብቤ
በአይነ ልቦናዬ ራሴን ፈትሼ
በአይነ ህሊናዬ ነገዬን ብሩህ ለማድረግ እሩጫዬን ጀምሬያለው!
ማራክ ነው !