ሰወርዋራ

ያገባሁት ሰው እንዴት እንዴት ብሎ ሕይወቴን ብልሽትሽት እንዳደረገው፣ በእድሜዬ ጢቢ ጢቢ እንደተጫወተ ልንገራችሁ።

እንዴት የሰው ልጣጭ፣ የሰው ቁሩ እንዳደረገኝ፣ በረቀቀ ዘዴ ቀስ በቀስ ከሰው ሁሉ እንደነጠለኝ፣ እንዴት ዋጋ ቢስ ነኝ ብዬ እንዳስብ፣ብቸኛ፣ ፈሪ፣ ጠርጣራና በእሱ ላይ ብቻ ጥገኛ እንድሆን እንዳደረገኝ ልንገራችሁማ፡፡

በእኔ ላይ የደረሰውን ቢያዩ እንደ ትግስት ዋልተንጉስ አይነቶቹ ባለሙያዎች፣

‹‹ይሄ ሰው እዚህች ሴት ላይ የተጠቀመው የማታለል ዘዴ የመረጣትን ሴት ከምትወዳቸውና ከሚወዷት ሰዎች ለመነጠል፣ በራስ መተማመኗን ለመሸርሸር፣ በአጭር ገመድ ለማሰርና በመጨረሻም ተስማምታ በገነባቸው የስሜት እስር ቤት ውስጥ አንደ ባሪያ ለመግዛት ብዙ ጊዜ ስራ ላይ የሚውለውን ዘዴ ነው›› ሊሏችሁ ይችላሉ፡፡

እኔ ግን ነገር ሳላራቅቅ፣ የደረሰብኝን አንድ ሁለት እያልኩ፣ ፍትፍት -ብትንትን አድርጌ አስረዳችኋለሁ፡፡

አንዲት ቀን እጁን ለጥፊ ሳያነሳብኝ እንዴት እራሴን ችዬ የምንቀሳቀስ ሰው ሳልሆን የእሱ ተቀጥያ፣ የእሱ ጅራት የሆንኩ እስኪመስለኝ ድረስ እንዳሽመደመደኝ እነግራችኋለሁ፡፡

ያደረገኝን ነገር በድንገት፣ በአንድ ጊዜ አላደረገውም፡፡

እያሳሳቀ፣ ቀስ በቀስ ነው ዙሪያዬን መሰላል በማይደርስበት ግድግዳ የከበበው፡፡

ገና የሸር ድሩን ማድራት ሲጀምር እንዲህ አለኝ፤

“ለምንድነው ሁልጊዜ ስለ ሁሉም ነገር ከእሷ ጋር የምታወሪው? የእራሴ የምትይው በእኔና አንቺ የሚቀር አንድ ምስጢር እንኳን የለሽም”

“እሷ” የሚለው የእድሜ ዘመን የልብ ጓደኛዬን ነው፡፡

የእቃቃ ጓደኛዬን፡፡ የልጅነቴን፡፡

የእቃቃ ሙሽራ ስሆን ሁሌም አንደኛ ሚዜዬ ነበረች፤ እኔ ደግሞ የእሷ፡፡

ሸክላ ፈጭተን ሽሮ ነው ብለናል፤ ቅጠል ቆራርጠን ጎመን ወጥ ሰራን ተባብለናል፡፡

የሰፈር ወንዝ ወርደን በጠፍጣፋ ደረታችን ላይ ብቅ ያሉትን አጎጠጎጤዎች በፍጥነት ወደ ጡትነት ለመቀየር የውሃ እናቶችን አስጠብተናል፡፡

በአስራ አምስት አመቴ በአይን ስላፈቀርኩት ልጅ ካለእሷ የነገርኩት አልነበረም፡፡

እስከ ዛሬ ድረስ ከእሷ የቀረበ የእኔ የምለው ሰውም የለኝም፡፡

በእሱ አፍ ግን “ወሬኛ” እና ‹‹ቀናተኛ›› ተብላ ተወነጀለች።

“ነገር ማባባስ፣ ድራማ ማብዛት ትወዳለች።›› ተብላ ተወቀሰች፡፡

‹‹አታግኚያት›› አላለኝም፡፡

‹‹ከጓደኝነት ሰርዢያት›› ብሎ አልጠየቀኝም፡፡

ግን በወሬ መሃል ስሟ በተነሳ ቁጥር ፊቱ ይለዋወጣል፡፡

ስልኬ ጮሆ እሷ መሆኗን ሲያውቅ አይኖቹን ወደ ላይ ሰቅሎ በረጅሙ ይተነፍሳል፡፡

የጓደኝነት ጨዋታችንን “የህጻን ወሬ ” ብሎ ያንቋሽሻል፡፡

እና አንድ ጊዜ ፣ በሆነ ጉዳይ ስንጨቃጨቅ (እኔ እና እሱ)

ልክ ከባድ ወንጀል ስፈፅም እጅ ከፍንጅ እንደያዘኝ ተደስቶ፣

“አይሽ! አገኘሁሽ! አሁን ያልሽኝ ነገር በፍጹም ካንቺ አእምሮ የወጣ አይደለም፡፡እሷ ናት እንዲህ ካለሽ እንዲህ በይው ያለችሽ አይደል…እርግጠኛ ነኝ…ሁለታችሁም በእሷ አንጎል አይደለ የምስቡት›› ብሎ ከሰሰሰኝ፡፡ አሸማቀቀኝ፡፡

ስለዚህ ከጓደኛዬ ምስጢር መደበቅ ጀመርኩ፡፡

መጀመሪያ መደወል፣ ከዚያ ደግሞ ስትደውል ማንሳት አቆምኩ።

“ደህና አይደለሽም እንዴ?” ብላ ቴክስት ስትልክብኝ፣ “ስራ በዝቶብኝ ነው” እያልኩ በሰበብ አስባቡ ለወትሮው ሳላወራት የማልውለውን ጓደኛዬን ጭራሹን ሸሸኋት፡፡

ለእሱ ደግሞ በገዛ ፈቃዴ የምታሰርበትን ሰንሰለት አቀበልኩት፡፡

ቀጥሎ ያቆራረጠኝ ከአክስቴ ልጅ ነው።

አንድ ግቢ ውስጥ አብሬው ያደግኩት የአክስቴ ልጅ።

ስሙ የአክስት ልጅ ሆነ እንጂ ለእኔ ከወንድም በላይ ነው፡፡ በዚያ ላይ ወንድም የለኝም፡፡

የአክስቴን ልጅ ደግሞ “በማያገባው መግባት ይወዳል” አለኝ።

ለማለት የፈለገው ግን ላንቺ አብዝቶ ይቆረቆራል ነው፡፡

“አንቺ ልጅ ካገባሽ ወዲህ መፍዘዝ አበዛሽ ”

“የሌለብሽን ትካዜ ጀመርሽ” አይነት ነገር ማለቱ ነው የባሌ ጥርስ ውስጥ ያስገባው፡፡

አንዱን ቀን የአክስቴ ልጅ በተናገረው ቀልድ ከጣሪያ በላይ ሳቅኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ከባሌ ጋር ወደቤት ስንሄድ ልረዳው ባልቻልኩት መንገድ አኮረፈኝ፡፡ ምነው ስለው

‹‹ምነው በእኔ ቀልድ እንዲህ አትስቂ?›› ብሎ መለሰልኝ፡፡

ከዚያ ወዲህ ባሌ አጠገባችን ካለ በአክስቴ ልጅ ቀልዶች መሳቅ ቀነስኩ፡፡

እንዲያውም የአክስቴን ልጅ ማግኘቱንም ቀነስኩ፡፡

እሱን ባገኘሁት ቁጥር ተመጣጣኝ ያልሆነ አገር የሚያስለቅቅ ንጭንጭ ስለሚነጫነጭ ከዚህ ሁሉ ቢቀርብኝስ ብዬ፡፡

ሳይኮሎጂስቶች እስካሁን በእኔ ላይ የደረሰውን ነገር “ሶሻል አይሶሌሽን ነው “ይሉታል፡፡ በኋላ ሲገባኝ ከሰው ሁሉ ነጥሎኝ ቢከፋኝ መሄጃ እንዳጣና በብቸኝነት እንድቆራመድ ለማድረግ ሆን ብሎ የሸረበው ነው፡፡

እናቴን እንኳን አልተወልኝም፡፡

‹‹ሁሉ ነገር ላይ እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ እያሉ ኑሯችንን እየበጠበጡ ነው›› ብሎ የገዛ እናቴን እንድጠራጠራት አደባብኝ፡፡

ከጊዜ በኋላ ከእሱ ጋር ሆኜ ከደወለችልኝ አለማንሳት፤ ቆይቼ ደግሞ ብቻዬን ሆኜም ስትደውል መልስ አለመስጠቱን መረጥኩ፡፡

” ለምን ጠፋሽ”

” እንዴት ጠፋሽ”

” ማን አጠፋሽ” ከሚሉት መልሳቸው ከሚያስፈራኝ ጥያቄዎች ለመሸሽ እናቴን ቆርጨ ጣልኳት፡፡

እኔ አዲስ አበባ እሷ አርሲ ኔጌሌ መሆኗ ደግሞ ክፍተቱን የባሰ አሰፋው፡፡

ከሚወዱኝ ሰዎች አቆራርጦኝ ሲያበቃ ሌላ ሌላ ነገሩን በስልት ጀመረ፡፡

ሲወጣና ሲገባ፣

‹‹እኔ የምለው…ምንድነው ግን ሁልጊዜ ስልክሽ ላይ የምትጣጂው…? እንቶ ፈንቶ ላይ ስታፈጪ ከምትውዩ መጽሐፍ ብታነቢ አይሻልም?›› ሲለኝ ከቀሩኝ ጓደኞቼም ጋር ተለያየሁ፡፡

ሶሻል ሚዲያ ሙሉ በሙሉ አቆምኩ፡፡

‹‹የእኔ ደሞዝ ለሁለታችን ቀርቶ ሰባት ብንወልድ አንቀባሮ ያኖረናል…በዚያ ላይ አንቺ የምታገኚው ከቅባትሽ አያልፍም…ሰዉ እየቸገረው ነው እንጂ ላደለው እኮ የሴት ልጅ ቦታዋ ቤት ነው…ስራውን ተይውና እናት ለመሆን ተዘጋጂ…እንደ እመቤት አንቀባርሬ ላኑርሽ ›› ብሎ ሲያባብለኝ የምወደውን ስራ ለቀቅኩ፡፡

ቤት ስውል ከእዚህ በፊት ማን እንደነበርኩ እስኪጠፋብኝ ድረስ ተቀየርኩ፡፡

ቀስ በቀስ እየደበዘዝኩ፣ በባሌ ላጲስ እየጠፋሁ ነበር፡፡

እርግጥ ነው አንድም ቀን አፍ አውጥቶ፣

‹‹ከቤት እንዳትወጪ›› ብሎኝ አያውቅም፡፡

የእሱ አካሄድ ሰወርዋራ ነው፡፡

ለመውጣት ስለባብስና ስቀባባ ቅር ተሰኝቶ ፣

‹‹አምሮብሻል…ግን ትንሽ በዛ…ይሄ ሁሉ መሽቀርቀር ለማን ነው…?”

‹‹ከእንግዲህ እኮ ባለትዳር ነሽ…ለምን ገና ባል እንደምትፈልግ ሴት ትለብሻለሽ?››

‹‹አባባ ምን ይል ነበር መሰለሽ…ቅንድቧን የምትላጭና ደም የመሰለ ሊፒስቲክ የምትቀባ ሴት ሸርሙጣ ናት›› አይነት ነገር ይለኛል፡፡

ስለዚህ የበፊት ማንነቴን እንደ ልብስ አውልቄ ጣልኩና ፍጹም ተቀየርኩ፡፡

ታኮ ያላቸው ጫማዎቼን ሰጥቼ ጨረስኩ፡፡

ቀይ ሊፕስቲኮቼን በ‹‹ገላ›› ቀለም ሊፒስቲኮች ተካሁ፡፡

ከዚያ በቻፒስቲክ፡፡

ከዚያ ደግሞ ቫዝሊን እንኳን በጠማው ደረቅና የተሰነጣጠቀ ከንፈር፡፡

እሱ የሚፈልጋትን አይነት ሴት ለመሆን፣ እሱ የሚፈቅዳትን ሚስት ለመሆን የበፊቷን እኔን አፍኜ ገደልኳት፡፡

በር ቆልፎብኝ አያውቅም፡፡ አትውጪ ብሎኝ አያውቅም፡፡

ከበራችን ባሻገር ያለው ዓለም በእሾህና በአሜኬላ የተሞላ አድርጎ ሳለልኝና እንዳልወጣ በፍርሃት ሸበበኝ፡፡

መንገድ እንዳሳያቸው የሚጠይቁ አረጋዊያን ሳይቀሩ ከእኔ ከአንድ ነገር በስተቀር ሌላ እንደማይፈልጉ ደጋግሞ እየነገረ በወንዶች ላይ ያለኝን እምነት ፈረካከሰው፡፡

‹‹እኔ እኮ ሁሉ ነገሬ ፊት ለፊት ስለሆነ ነው እንጂ በሆዴ ክፋት የለም››

‹‹እንደልብሽ አኖርሻለሁ፡፡ በዚያ ላይ እንደ ስንቶቹ አረመኔ ወንዶች እጄን አላነሳብሽ…ጥሩ ባል ነኝ እኮ እ…እግዜሩን አመስግኚ››

እያለ እኔን መርጦ ማግባቱ ለእኔ ታላቅ ውለታ እንደሆነ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እየሞላ ቀስ በቀስ ልክ እንደሆነ አሳመነኝ፡፡

‹‹እስቲ አስቢው…ይሄን ሁሉ እንከንሽን ችላ ብሎ እንደ እኔ የሚያፈቀርሽ ሰው ታገኛለሽ?›› እያለ ከእሱ መገናኘቴ የሕይወቴ ትልቁ እድል እንደሆነ ደጋግሞ አስረዳኝ፡፡

እኔም የሚለውን ሁሉ አመንኩት፡፡

ማነጻሪያ የለኝምና፣ ከሰው አልገናኝምና፣ የሁሉ ነገሬ ምንጭ እሱ ብቻ ነውና በፍጹም ልቤ አመንኩት፡፡

ይሄን ሁሉ ቀስ በቀስ፣ በዝግታ ካደረገኝ በኋላ እሱን ጥዬ መሄዱ ከእሱ ጋር ከመቆየት በላይ ያስፈራኝ ጀመር፡፡

እናም በፈቃዴ ባስጠለቅኩት ሰንሰለቱ ታስሬ መኖርን ኑሮ ነው ብዬ መኖርን ለመድኩ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *