Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል ሀያ አንድ)

ፅፎ እስኪጨርስ እረፍት አጣሁ። አስሬ ላይብረሪ እመላለሳለሁ። ጣቶቹ አሁንም 100% ስላልሆኑ ቀስ ብሎ ነው የሚፅፈው።
«እሺ የፃፍከውን ላንብበውና ትቀጥላለህ?» እለዋለሁ።
«አይሆንም ህፃን አትሁኚ!» ይለኛል።
«ጮክ ብለሽ አታንብቢልኝ! የምትጠይቂኝ ነገር ከሌለ በቀር! ለራስሽ አንብቢው» ብሎኝ ሶፋው ላይ አጠገቡ እንድቀመጥ በእጁ እየመታ አሳየኝ። መስገብገቤ የሆነ እርቦት ውሎ ምግብ እንደሰጡት ርሃብተኛ ነው።

«ከድምፅ ጋር የተለየ ፍቅር አለኝ። ሰውን ሳላየው በድምፁ ብቻ መልክ እስላለሁ። ከድምፁ ቃና ፐርሰናሊቲውን መገመት ደግሞ የበለጠ ደስ ይለኛል። ሬስቶራንት ውስጥ ከጀርባዬ ድምፅዋን ስሰማው ጠይም ጎራዳ ፣ ጥርት ያለቆዳ ያላት ፣ ጥርሷ የሚያምር ፣ ከንፈሯ ስስ ……… ገመትኩ። ድምፅዋ ውስጥ የዋህነት ደግሞ ለዛ ሙሉነት ነበር በመጀመሪያ የሰማሁት። ዞሬ ሳላያት ከውጪ ከመጡ ተለቅ ያሉ ሴት ጋር ስታወራ ድንገት ድምፅዋ ወደ ቁጣ ሲቀየር ግን ቃላቶቿን ደምሬ ስሰማት የሆነች መብረር ፈልጋ ክንፎችዋን የፊጥኝ የተያዘች ነፍስ ያላት ሴት …… እድሉን ብታገኝ እልም ብላ የምትበር ዓይነት። ሲትየዋ ጥለዋት ሲሄዱ ዞሬ አየኋት እና ወንበር ቀይሬ አጠገቧ መጣሁ። መልኳን ከከንፈሯ እና ከቀለሟ ውጪ ብዙ አልሳትኩም። ቀይ ናት የጎራዳ ውብ፣ ቆዳዋ ከመጥራቱ የተነሳ ውሃ ስትጠጣ በረዥሙ አንገቷ ወደሆዷ ሲንቆረቆር ውሃው ኩልል ብሎ የሚታይ የሚመስል። ከንፈሯ ብዙ ስጋ የፈጀ አበባ የመሰለ ፣ ጥርሷ በድዷ ጥቁረት ደምቆ የሚያጥበረብር ፣ ሴት ልጅ ከኋላ የፀጉሯ ማብቂያጋ የተደፉ ሉጫ ፀጉሮች ሲኖሯት ባላውቃት እንኳን እጄን ሰድጄ መንካት ይቃጣኛል። እሷ ደግሞ ወደላይ ባስያዘችው ጥቁር ፁጉሯ ጆሮዋ ስር ድረስ ለጥ ብለው ንካኝ ንካኝ የሚሉ ሉጫ ፀጉሮች ነው ያላት። የዓይኖቿን ውበት ውስጡ በጉልህ የሚነበበው ሀዘን አደብዝዞታል።

ስለስብዕናዋ ግን ሁሉንም ልክ ነበርኩ። ለመነበብ የማትከብድ ያልተወሳሰበች፣ የዋህ፣ ለዛ ሙሉ፣ ልዝብ ያለች ፣ ስርዓት ያላት ግን ደግሞ ግልፅ ነገር፣ ባህልን ባታምንበትም ለቤተሰብ እና ለማህበረሰብ ግምት ብላ የምትኖርበት፣ ሀይማኖትን ግን አምናበት የምትከተል (ብዙ የማውቃቸው ሰዎች ሀይማኖት ያላቸው ሲኦል እና ገነት አለ ስለተባሉ ነው። ከክፋት የሚቆጠቡት ሲኦልን ፍራቻ እንጂ መልካም መሆን ምንም ሽልማት የለውም ክፉ መሆንም ምንም ቅጣት የለውም ቢባሉ ለክፋት የሚግደረደሩ ናቸው። በሰውነት ሰው ስለመሆን ሳይሆን እግዚአብሔር ወይም አላህ ወይም ሌላኛው አምላክ በክፋታቸው ይቀጣናል ፤ በመልካም ስራቸው ይሸልመናል ብለው ስለሚያምኑ ነው ሚዛን የሚሰሩት። እስኪ እውነት እናውራ ከተባለ የብዙ ሀይማኖቶች መደምደሚያ ከሞት በኋላ ያለ ሽልማት ወይ ቅጣት ባይሆን ምን ያህል ሰው ሀይማኖት ይኖረው ነበር? ምን ያህል ሰው ቅዱስ የሚለውን ስራ ለመስራት ይጋጋጣል? ምን ያህሉስ ሰው ወደሀይማኖት ተቋማቱ እየሄደ አቴንዳንስ ያስመዘግብ ነበር?) የሷን ሀይማኖተኝነት የምወድላት ቅጣትን ከመፍራት እና ሽልማትን ከመሻት ባለፈ አምላኳን በየቀን ህይወቷ ታምንበታለች።

እያወራን ሳለ የምትኖርበት ትርጉም ያጣች ጣዕም አልባ ነፍሷን ሰማኋት። ማምለጥ እየፈለገ የታነቀ ስብዕናዋን አየሁት። ሙሉ አደርጋታለሁ ብዬ አስቤ አይደለም። በህይወቴ ውስጥ ከዚህ በፊት የነበሩት ሴቶች ከሰጡኝ የተለየ የምትጨምርልኝም ነገር አለ ብዬ አስቤ አይደለም። እሷ ቤተሰቦቿን የምታስደስትበት ባል ትፈልጋለች። እኔ ደግሞ አጉል ባልከረረ ትስስር ቀኔን የምታጅብልኝ ሴት እፈልግ ነበር። የዛኑ ቀን እንጋባ አልኳት። በዛ ላይ በየቀኑ የምነካው የኋላ ቤቢ ሄር አላት። እያወቅኳት ስመጣ ባወቅኳት በደቂቃዎች ውስጥ እንድታገባኝ መጠየቄ ልክ መሆኑን አወቅኩ። ምንም ነገር ላይ የተሰማትን እና ያመነችበትን አስተያየት ከመስጠት ወደኋላ አትልም። የማታውቀውን ነገር አላውቅም ለማለት አታፍርም! እንደአዋቂ ለመታየት እና እኔን ለማስደመም ቅንጣት አትሄድም። ጠያቂነቷን እወድላታለሁ። ትጠይቃለች። መልሴ ካላሳመናት ለምን አዳር አይሆንም ትጨቃጨቀኛለች። ጭንቅላቴን ስለምትፈትነኝ ከሷ ጋር የማሳልፈውን ጊዜ እወደው ነበር። ገና ሳንጋባ አንድ የኑሮ ህጌን አስፈረሰችኝ። ሰውን እርዳታ መጠየቅ! ልታገባኝ ስትስማማ ሰርግ እፈልጋለሁ አለችኝ። ምክንያቷ ለራሷ ከእገሊት የተሻለ ሰርግ ነበረኝ ለማለት ወይም ሰርግ በራሱ ትርጉም የሚሰጣት ነገር ስለነበረ አልነበረም። በቤተሰቦቿ አይን ለመሙላት ፣ አጎደልኩባቸው ብላ ያሰበችውን ለመካስ ፤ ውርደታቸው ሆንኩ ብላ ያሰበችውን ክብር ልትደርብላቸው፣ በሷ ሰርግ እነርሱን ለማድመቅ ነበር እና እውነት ለማውራት አሳዘነችኝ። ሰው በ34 ዓመቱ የራሳቸውን ህይወት ኖረው ላገባደዱ ቤተሰቦቹ ይኖራል? ማስደሰት አንድ ነገር ነው። እሷኮ የህይወት ግቧም ፣ ስኬቷም ፣ ደስታ ሀዘኗም፣ ህልሟም፣ ትርጉሟም እነርሱ ናቸው። ዘመኗን ሙሉ በፈጠሩባት የትንሽነት እና የከንቱነት ስሜት ለእነርሱ ኖራ ራሷን ፕሩቭ ካላደረገች (የማለፊያ አረንጓዴ መብራት ካላሳይዋት) የራሷን ኖሮ መኖር እንደማይገባት ለራሷ አሳምናለች። እንኳን የራሴን ሰርግ ልደግስ የሰው ሰርግ የማልታደም ሰው ሰርግ ልደግስላት ተስማማሁ። ችግሩ ከእኔ ወገን የሆነ ሰርጌን የሚያጅበኝ ዘመድም ሆነ ጓደኛ አልነበረኝም። ወይም ማንንም በዛ ልክ ማቅረብ አልፈልግም።

የእኔ ሚዜ አልባ መሆን ወይም ዘመድና ጓደኛ አለመኖር ለሰርጉ የነበራትን ደስታ ወደጭንቀት ቀየረባት። ይሄም ለራሷ አልነበረም!! ዘመድ አልባ ባል አገባች ብለው ቤተሰቦቿ እንዳያዝኑባት እንጂ! 34 ዓመት አልጨበጥ ብሏት ስታሳድደው የኖረችውን ህልሟን በሳምንታት ላስቀይራት አልችልም ነበር። በህይወቴ ውስጥ ከምጠላቸው ዋና ዋና ነገሮች ውስጥ አንዱን አደረግኩ። ስራ ቦታ አብረውኝ ብዙ የሰሩ የስራ አጋሮቼን ሚዜ እንዲሆኑኝ ጠየቅኩ። በእርግጥ ከስራ ውጪ ማርስ ላይ ልደር ወይ ጎዳና፣ ሚስት ይኑረኝ ቅምጥ ምንም መረጃ ለሌላቸው ለብልጫዎቹ የስራ ባልደረቦቼ የቅርበት ምልክት አድርገው ስለወሰዱት በደስታ ነበር የተቀበሉኝ። የስራ ህይወቴን እና የግል ህይወቴን ማዳቀል የፈጠረብኝን መወላገድ ድጋሚ ልደግመው ስለማልፈልግ የግል ህይወቴን በአድራሻም በወሬም አርቄ ነው ያኖርኩት የነበረው። ተጋባን!!

መጀመሪያ ላይ ድንበሩን የጠበቀ፤ ያልከረረም ያልላላም፣ ያልሳቀም ያልተኮሳተረም፣ የማያቃጥልም የማይበርድም ዓይነት ትርጉም የነበራቸው ዓመታት ነበረን። እንደአብዛኛዋ ሴት ስም ያለው ቦርሳ መሸመት ፤ አዲስ የወጣ ፋሽን ልብስ እና ጫማ አሳዶ ማጌጥ ፣ አዲስ በተከፈቱ ሬስቶራንቶች መታየት ፣ ፊቷን ሜክአፕ ለመሰራት ጊዜ መፍጀት ……. አታውቅበትም። የመኪና መንጃ ፈቃድ እንኳን ያወጣችው እኔ ጨቅጭቄያት ነው እንጂ ራሴው ነበርኩ የማመላልሳት። ከመሰረታዊ ነገሮች ውጪ ገንዘብ ካወጣች ባትነግረኝም አውቃለሁ። ለቤተሰቦቿ ነው!! ገንዘብ አንዱ የነፃነት በር መሆኑን ባውቅም ከሚያስፈልገኝ ውጪ ባለ ትርፍ ገንዘብ የሚያሳምነኝ ምክንያት ይሁን እንጂ አልሳሳም። ለፍቼ ያመጣሁት ገንዘብ ነውና ሚዛን በማይደፋ ምክንያትም እንዲበተን አልፈቅድም። (ገንዘብ የነፃነት በር ነው ያልኩት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለነፍሳችን አስተዋዕፆ ስላለው ነው። እንደአለመታደል ሆኖ ሀይማኖቶቻችንም ሆኑ ባህሎቻችንን ድህነትን የሚያሞካሹ እና ገንዘብን ልክ ከአምላካቸው ወይ ከስርዓታቸው ወይም ከደስታቸው የሚያርቅ መዓት አድርገው ይጠምዱታል። ድህነት ውስጥ ደስታ ያለ ሀብት ደግሞ እንቅልፍ አልባ ለሊቶችን ያቀፈ አድርገው ስለነገሩን ሁሌም ገንዘብ ያለው ሰው ለገንዘቡ ሲል በደልን የፈፀመ እንቅልፍ አልባ ምስኪን ይመስለናል። ያለኝን ህይወት እወደዋለሁ። ማድረግ የምፈልገውን ነገር ማድረግ በፈለግኩ ሰዓት ማድረግ መቻሌን እወደዋለሁ። ከማንም ምንም ፈልጌ አላጎበድድም። ከማንም ምንም ስለማልፈልግ ድንበሬ ይከበርልኛል። ሰውኮ እንዲህ ነው …….. በተለይ በኢኮኖሚ እንደተደገፍከው እና የእሱ መኖር እንደሚያስፈልግህ ሲያውቅ ከሱ በምታገኘው ጥቅም ክብርህን ሊገዛህ ይዳዳዋል። በማጣትህ ሽንፈት ይጠቀምበታል። ገንዘብ ይሄን ነፃት ይሰጥሃል። በማንም በምንም ተሸናፊ ያለመሆንን። ከዚያ በተጨማሪ ገንዘብ ስላለኝ ነው ከእስርት ዓመታት በላይ የጭንቅላቴን ውጥረት ማርገብ በፈለግኩ ሰዓት የምሄድበት ዶክተር ያለኝ። ብዙ በተለያዩ ትራውማ እና የአዕምሮ ህመም እየተሰቃዩ አቅሙ ስለሌላቸው መታከም ያልቻሉ ሰዎች አሉና)
ግንኙነታችን ያሰመርኩትን መስመር መች እንዳለፈ አላውቅም። ከአራት ዓመታት በኋላ የሆነ ቀን እንደተለመዱት ምሽቶቻችን ልንተኛ ስንል የከንፈር ብቻ ያልሆነ መሳም ሳመችኝ። ስትስመኝ ወፍራም ከንፈሯን እወደዋለሁ። የዛን ቀን ከተለመደው ስሜት ውጪ ለእኔ መልዕክት ያደረሰ መሳም ሳመችኝ። አስቁሚያት መሳሟ ለውጥ እንዳለው ስነግራት ለውጡ እንዳልተሰማት ነገረችኝ። የዛን ቀን ለመግለፅ የሚከብድ ቅር የሚል ስሜት ተሰማኝ። የሆነ ያልተለመደ ወይም የረሳሁት ቅሬታ!! ከዚህ ስሜት በኋላ ብዙም ባልራቀ ቀን አልጋችን ላይ ጨዋታና ፍቅር ደርበን እየፈተልን
«እኔ ከዚህ በላይ ማስመሰል አልችልም! ከአቅሜ በላይ ነው የምወድህ!» አለችኝ እንደገረፉት የሁለት ዓመት ህፃን ልጅ ህቅ ህቅ እያለች። የሆነ መኪናዬን እየነዳው ተጋጭቶ ኤርባጉ ተነፍቶ ፊቴን ሲጠልዘው ያለው ዓይነት ስሜት ነው የተሰማኝ። ያ ስሜት እንደነበራት ባትነግረኝም አውቀው ነበርኮ የማላውቀው ከአፏ ሲወጣ እኔጋ ሊፈጥር የሚችለውን ስሜት ነበር። እንጂማ ብዙ የማውቃቸው ሴቶች ብለውኛል። የማናቸውም እኔጋ የፈጠረው ስሜት አልነበረም። የተሰማኝ ፍቅር አይደለም። ፍርሃት ነበር።»
(ይሄን ሳነበው ልቤ ዝቅ ሲልብኝ ተሰማኝ!!)
«ማብራራት የሚከብደኝ የማጣት ዓይነት ፍርሃት ፤ ላላስታውሰው ረስቼዋለሁ ያልኩት ድሮዬ ላይ የማውቀው የመለየት ፍርሃት ፤ የዛሬውን አዲስ ከአንድ ጠጠር እና አሻዋ ጀምሬ ከመገንባቴ በፊት ሰውነቴን የወረረኝ መሸነፍ!! የምትፈልገውን እንድታደርግ እና በፈለገችው ቁልምጫ እንድትጠራኝ ፈቅጄላት የመጨረሻዬ እንደሆነ የወሰንኩትን ፍቅር ሰራን። ደረቴ ላይ ሆና የፈገገ ፊቷን ሳትመልሰው እንቅልፍ ወስዷት ምን እንደማደርግ ሳስብ አደርኩ። ከራሴ በላይ እንዳላጣው የምሳቀቅለት ነገር እንዲኖረኝ አልፈልግም!! ከማዕረግ በኋላ ያለው አዲስ ስሜቱንም ውሳኔውንም ለማንም ለመናገር አይደለም ሊፈራ ሁለቴ አያስብም ነበር። አዲስ ፍርሃትን ከላዩ ከገፈፈ ዓመታት ተቆጥረዋል። የተሰማኝን ልነግራት መጨነቄ ይበልጥ ያለሁበትን ሁኔታ እንድጠላው አደረገኝ።

የኑሮ ዋና መርሄን ተፈታተነችው! በስሜቴ ከእኔ ውጪ ማንም አያዝበትም የሚለውን!! አዲሱ አዲስ ስሜቱ ራሱ የሚያዘው ፤ ማንም የማይሰለጥንበት ነው። አልነገርኳትም! በነገታው የእርሷን በቅርቤ መኖር ጠላሁት! ራሴን እንዳላዘው እየሆንኩ እንደሆነ ገባኝ። ትቻት ሌላ ክፍል ተኛሁ። እንቅልፍ ግን አልወሰደኝም። በመሃል በሩን ከፍታ መኖሬን አረጋግጣ ስትመለስ እሰማታለሁ። ሲነጋላት መጥታ
«……… ላፍቅርህ ብዬ ነው ወይ ያፈቀርኩህ? ለምን ትቀጣኛለህ?» ስትለኝ ውስጤ ሲረበሽላት ሰማሁት። ከማዕረግ ውጪ ለማንም ያልሆንኩት መሆን ስሆነው ታወቀኝ። ያ ስሜት ደግሞ ከደስታው በላይ ስቃይ እና ሰቀቀኑ ነው ትዝ የሚለኝ። «እንፋታ» ስላት ራሴን ሰማሁት። ከዛ በኋላ ለሳምንታት ከልቧ ልታወጣኝ እየታገለች መሰለች። አብራኝ መዓድ ብትቀመጥም ብዙ አታወራም!! ያሰብኩት ወይም የተመኘሁት ልክ እንዳልሆነ ፀዲ ስትደውልልኝ ገባኝ! ፀዲ የደወለችልኝ ቀን እራት ላይ ፀዲጋ እንደሄደች ስትነግረኝ የማውቀው ነገር በመሆኑ አልተገረምኩም። የተገረምኩት አድርጋ የማታውቀውን ሜካፕ እና ሊፒስቲክ ፊቷ ላይ ማየቴ ነበር። እቤት ውስጥ በቱታ ወይ በቁምጣ አልያም በኔ ቲሸርቶች እንጂ የማውቃት ቀሚስ ለብሳ አላስታውስም! የእኔን ትኩረት ለመሳብ መሆኑን ሳስብ አሳዘነችኝ። ያንን ግን እሷ እንድታውቀው ማድረግ አልፈለግኩም። በነጋታው ሀኪሜጋ ሄጄ የተፈጠረውን ነገርኩት።

«ወደሃታል! በፍቅር መሸነፍን እንደድክመት የምታይበት የራስህ በቂ ምክንያት አለህ ያን እረዳልሃለሁ! ግን ይህችኛዋ የተለየች ብትሆንስ? ከመስበር ይልቅ የምታጎብዝህ ብትሆንስ? ከእውነቷ የምታፈቅርህ ብትሆንስ? » አለኝ
«ዶክተር ባትሆንስ? ብትሆንስ በሚል ግማሽ እምነት ባትሆን የማጣውን መቋቋም አልችልም።»
«በባትሆን ፍርሃትህ በፍቅር ውስጥ ያለውን ደስ የሚል ህይወት ራስህን እያሳጣኸው ነውኮ! ራስህን እየቀጣኸው ነው!»
«am fine ፍቅር በሚሉት ግማሽ ደስታ ግማሽ ሰቀቀን ያለበት እሳት መጫወት ለጊዜው ምርጫዬ አይደለም። ደስታው ይቅርብኝ እና ሰቀቀኑንም ይዞልኝ ይሂድ!» አልኩት ተነስቼ ቢሮው ውስጥ እየተንጎራደድኩ።

«አዲስ! እንዳንተ በጥንካሬ የማይታለፈውን ያለፈ ሰው አላውቅም። የምትኖራቸው ህጎች እና መርሆች ስለፈወሱህ I appreciate that! ከነዚህ ዓመታት በኋላ እንኳን ይሄን ሁሉ በራስ መተማመንህን እና የገነባኸውን እውቀት የሚከድን ፍርሃት ካነቀህ አሁንም ከትናንት ህመምህ አልዳንክም! ስለሸሸኸው ደግሞ አታመልጠውም! እባክህ አስብበት! ደጋግሜ ከዚህ በፊት እንዳልኩህ እሱን ፋይል ገልጠህ ለማውራት ራስህን አዘጋጅ!» አለኝ
ያን ህመም ቀስቅሼ ላወራ መቼም አልዘጋጅም!! የሬሳ ሽታ፣ የጨለማ ጣር ፣ የሚያደነዝዝ ድምፅ……… ያለበትን ፋይል ከፍቼ መተንፈስ አቅቶኝ መንፈራገጥ የቅርብ ዓመታት እቅዴ ውስጥ አልነበረም!! ወደቤቴ ተመልሼ ላለፉት ሳምንታት እንደተለመደው ዓይነት መግባት መውጣቴን ቀጠልኩ። የሆነ ቀን እራት ላይ ሳትመጣ ቀረች። ፀሃይን እንድትጠራት ስጠይቃት።
«አሟታልኮ ተኝታ ነው የዋለችው! አላስተዋልካትም እንጂ ምንም ደህና አይደለችምኮ! እንደው በማያገባኝ መግባት አይሁንብኝና እንደው በመሃከላችሁ ምን ክፉ ዘልቆ ነው?»
«ገባሽ ፀሃይ! በማያገባሽ ገባሽ!» ብያት ወደመኝታ ቤት ላያት ሄድኩ። ስታለቅስ እንደዋለች ታስታውቃለች። እንፋታ ካልኳት ቀን በኋላ በትኩረት ያየኋት የዚህን ቀን ነው። ከሰውነቷ መክሳት የፊቷ መገርጣት አስደነገጠኝ። አጠገቧ ሄጄ ስነካት ታተኩስ ነበር። እጠይቃታለሁ። አትመልስልኝም! ክፍሏ በታመቀ አየር ተሞልቷል። መስኮቱን እየከፋፈትኩ ሀኪም ቤት እንድወስዳት ደጋግሜ ጠየቅኳት። ቃል አልመለሰችልኝም። ፊቷን አዙራ በትራሷ ተሸፈነች። እራሴን ከመውደዴና ከፍርሃቴ ያየለ ስሜቴ አቅፌ ምን ሆንሽብኝ? ሁላ ልላት እያመነታብኝ ተንጎራደድኩ። ኮቴዬን እየሰማች እስክወጣላት እንደምትጠብቅ ነገር በትራሷ እንደተከለለች ዝም አለች። ይሄኛው አዲስ ስሜቱን መለየት ተቸግሮ አያውቅም ነበር። ዝብርቅርቅ ያለ ስሜት ተሰማኝ። ጠልታኛለች ልታየኝም ልታናግረኝም የማትፈልግበት ደረጃ ደርሳለች። ግን ደግሞ ብትጠላኝ እንዲህ ትጎሳቆል ነበር?»
«ፊቴን አዙሬብህ አልነበረም! (የዛኔው ህመሜ ከማንበቤ ጋር መጣ) ባለቅስም እንደማታዝንልኝ አስቤ ሳታየኝ በትራሱ ተሸፍኜ እያለቀስኩ ነበርኮ!» አልኩት በቀዘቀዘ ድምፅ። እጁን ሰዶ የኋላ ቤቢ ሄሮቼን መነካካት ጀመረ።

«የትኛው ምን አይነት ስሜት እንደሰጠኝ አላውቅም። ብትጠላኝ እና አልፈልግህም በቃ ብላ ጥላኝ ብትሄድ ደስ ይለኛል። ግን ሙሉ በሙሉ ደስ ይለኛል? በእኔ ምክንያት እንዲህ መሆኗ ደግሞ የሚያስጠላ ስሜት ሰጠኝ። ለተከታታይ ቀናት እኔ ያለሁበት ላለመሆን ወሰነች። ፀሃይን ደህና እንደሆነች ስጠይቃት
«ዛሬ ምንም አትል! ቅድም አየር ልትቀበል ብቅ ብላ ነበር» አለችኝ። ልታየኝ አለመፈለጓን አከበርኩላት!!! ከቀናት በኋላ ግን አባቷ ሞተው በለሊት ደውለው መርዶውን ሊነግሯት ሽማግሌዎች እንደሚመጡ ነገሩኝ! ሳሎን ቁጭ ብዬ ስጠብቃቸው ሊነጋጋ ገደማ መጡ! ገና እሷ መርዶውን ሳትሰማ በፊት እጄ እና እግሬ ሲንቀጠቀጥ ይታወቀኛል። ሳሎን ብቅ ከማለቷ ሰዎቹን ስታያቸው የተፈጠረውን አውቃለች መሰለኝ በቁሟ ተገነደሰች። የሚርበተበት ሰውነቴ እንዴት እንደታዘዘልኝ አላውቅም። መሬቱ ላይ ከመውደቋ በፊት እጄ ደረሰ።

እስከዛሬ የሆንኩትን ሁሉንም በአንዴ ሆንኩት። እናቴ ሬሳ ላይ ስደርስ ከአፌ ቃል አልወጣ ብሎኝ ያማጥኩትን ከነሬሳ ሽታው፣ ማዕረግ ወንድሜ ክፍል ስትሳለቅብኝ ያደረግኩትን ፓኒክ ፣ ማዕረግ ወንድሜን እንዳገባች የእንጀራ እናቴ ከነገረችኝ በኃላ የከደነኝ ጨለማ ……. የለም ብዬ ያመንንኩትን እግዜር ለመንኩላት። <እሷ የምታምንህ አምላክ ካለህ ምንም አታድርጋት! ለእኔ ብለህ ሳይሆን ለእርሷ ብለህ ስማኝ ምንም አትሁን!> አልኩት። ሆስፒታል ተሰናብቻት እንደወጣሁ ታክሲ ጠርቼ ዶክተርጋ ሄድኩ።

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል ሃያ ሁለት)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *