Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስራ ዘጠኝ)

«ማዕረጌን ከጎኔ አድርጌ የተጋበዝነውን እራት ልንታደም ስንሄድ ዘውድ እንደተደፋለት ልዑል አንገቴን ቀና አድርጌ በኩራት ነበር። ምንም የጎደለኝ ነገር አልነበረም። ማዕረጌ ከጎኔ ነበረቻ!! ከሶስት ሳምንት በኋላ እሷ እንደተመኘችው በሷው አባባል <እልልልልልልል በተባለለት ሰርግ> ወዳጅም ጠላትም ምስክር ሆኖ ባደባባይ የእኔ ልትሆን ነዋ!! ዓለም የእኔ ብቻ ነበረች። የሆነኛው ዓለም በጦርነት ንፁሃን እንደማይሞቱ፣ የሆነኛው ሀገር ህፃናት በርሃብ እንደማይሞቱ፣ የሆነኛው የዓለም ክፍል በተፈጥሮ አደጋ እንደማይተራመስ ……… በቃ ከእኔና ከእሷ ውጪ ሌላ ምንም ዓለም እንደሌለ …… ዓለም በእኔና በእሷ ዙሪያ ብቻ እንደምትዞር …… ዓለሜ እሷ ብቻ እንደሆነች ….. እንደዛ እያደረገኝ ነበር። ፈጣሪን ለሰጠኝ ዓለም እየደጋገምኩ አመሰግነው ነበር።

የሚመጣውን ሰርጋችንን እና እርቁን አስመልክቶ የተወሰነ የማውቃቸው ጎረቤቶች እና ዘመዶችን ያካተተ እራት እንጀራ እናቴ ነበረች ያዘጋጀችው። ወንድሜም ያለወትሮው ብሉልኝ ጠጡልኝ ሲል አመሸ። ለደስታችን ውድ የተባሉ መጠጦች ተከፈቱ። እያስመሰልኩ አልነበረም ውስጤ ልቤን ስልብ የሚያደርግ ፍርሃት ሃሳቤን በየመሃሉ ከመስረቁ ውጪ ደስተኛ ነበርኩ። ማዕረግ ወይን እየጠጣች ነበር እና በመሃል ውሃ መጠጣት ፈልጋ ጠረጴዛው ላይ ያለው ውሃ በማለቁ ላመጣላት ራሴው ተነሳሁ። ወደጓዳ እየሄድኩ ድሮ የእኔ ክፍል ከነበረው መኝታ ቤት ድምፅ ያለው ለቅሶ ሰማሁ እና አንኳኩቼ ገባሁ። የጎረቤታችን ልጅ ናት። ከረሜላ የምገዛላት ሚጢጥዬ ልጅ ነበረች።
<ምነው ሉሲ ምን ሆነሽ ነው እዚህ ተደብቀሽ የምታለቅሺው?> ብዬ ላባብላት አጠገቧ ተቀመጥኩ። ከእናቷ ጋር በወንድ ምክንያት ተጣልታ እንደሆነ ስትነግረኝ በጣም ገርሞኝ።
<ስንት ዓመትሽ ነው?> አልኳት።
<14> አለችኝ። የእውነቷን እያለቀሰች ስለነበር የምላት ግራ ገብቶኝ አቅፌ እያባበልኳት እናቷ ለእርሷ ብላ እንደሆነ እና በዚህ እድሜዋ ወንድ እንዳያታልላት ስመክራት የሆነ ደቂቃ ቆየሁ።
ከዚህ በኋላ የተፈጠረው ዛሬም ድረስ የሆነ መጥፎ ቅዠት ነው የሚመስለኝ። ኮሪደሩ ላይ የእንጀራ እናቴ የሰራተኛዋን ስም እየጠራች ስሰማ እና ሉሲ እሪሪሪሪ ብላ ስትጮህ እኩል ነበር። እየሆነ ያለውን የምረዳበት ምንም ሰከንድ አልነበረም። የእንጀራ እናቴ በሩን በርግዳ ስትገባ ሉሲ እኔ የሆነ ነገር ያደረግኳት ዓይነት እየተንዘፈዘፈች ሄዳ ጉያዋ ተወሸቀች። እሪሪሪሪ እያለች ትጮሃለች። ከሳሎን ሁሉም ሰው እየተሰባበረ ለወሬ ሲመጣ እንጀራ እናቴ ትደነፋለች
<ምን አይነቱ አውሬ ብትሆን ነው ትናንት አይንህ እያየ ያሳደግካትን ህፃን ለማባለግ ሰውነትህ እሺ ያለህ! ቱ!> የቀረው አሟሟቂ ያማትባል፣ በስመአብ ይላል።
<ሉሲ? እንዴ ንገሪያቸው እንጂ ምን እንደተፈጠረ? በስመአብ እንዴት እንደዛ ያደርጋል ብላችሁ ታስባላችሁ?> ብዬ ወደፊት ከመራመዴ ሉሴ ድራማዋን ከወነችው። ሸሽታ እንጀራ እናቴን እየተጣበቀች እና እንባ እና ሳጓን እየደባለቀች
< እንዳልጮህ አፌን አፍኖኝ! ህህ ህህ ወይኔ እናቴ! > የሰዎቹ ፊት ዱላ ሆኖ የሚጋረፍ ቢሆን የሚታይ የሰውነት አካል እስከማይኖረኝ ሰንበር በሰንበር እሆን ነበር። የማዕረግ እይታ ግን ከሁሉም የከፋ ነበር። <ከአውሬ ጋር ነበር የምኖረው?> አይነት እይታ!
<ኸረ ባካችሁ ሰዎች እኔ ምንም አላደረግኩም! ውሸቷን ነው!> ብል ማን ይስማኝ። ወንድሜ
<መጠጡንኮ በላይ በላዩ ስትለው ይህቺን ዓመልህን ስለማውቅ ቀስ በል ብዬህ ነበር።> ብሎ በልግጫ እሳቱ ላይ ጋዝ አርከፈከፈ። በአካባቢው ያልነበረችው የልጅቷ እናት ግርግሩን ከመቀላቀሏ ፖሊስ ካልተጠራልኝ ማንም ከዚህ ንቅንቅ አይልም ብላ ቀወጠችው። ሁሉም ነገር የሆነ በድካም ካለፈ ቀን በኋላ ያለ ቅዠት ነበር የሚመስለኝ።

ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ ሳድርም የማስብ የነበረው ማዕረግ ልታየኝ ስትመጣ የሆነውን ሁሉ እንዴት እንደማስረዳት እንጂ የተከሰስኩበትን ምክንያት እንኳን በውል አላሰላሰልኩትም <በስካር መንፈስ የ14 ዓመት ህፃን በመድፈር!> ከአፋቸው ስሰማው ራሱ አንዳች መዘግነን ዘገነነኝ። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ስንት ዓመት ለምታውቀኝ ማዕረግ ማስረዳት ህመምም መዘግነንም ነበረው።

<አታውቂኝም ማለት ነው? ምን ላገኝ ብዬ ነው ህፃን የምደፍረው? እንኳን አስገድጄ ልደፍር ደስታሽ ከስሜቴ ጋር ካልተመጣጠነ ሰውነቴ እንደማይታዘዝልኝ አታውቂም?> አልኳት ልቤ እንክትክት ሲል እየታወቀኝ
<አላውቅም! ማንን ማመን እንዳለብኝ አላውቅም! እሷስ ምን ልታገኝ ትዋሻለች? እንደዛ ሰውነቷ እየተርገፈገፈ ውሸቷን ነው ብዬ ማመን ከበደኝ። አንተን ስለማውቅህ ደግሞ እውነቷን ነው ብዬ ማመን ጨነቀኝ። ጠጥተህ ነበርኮ! አላውቅም ምን ማሰብ እንዳለብኝ!> አለችኝ
<ልብሽን ስሚው! ልብሽ አዲስ ይሄን ያደርጋል ብሎ ያምናል?> አልኳት ድክም ብሎኝ። ያላደረግኩትን ነገር አለማድረጌን ለማሳመን የምሄደው እርቀት ጭራሽ ለጥፋቴ ማስተባበያ እየሰጠሁ ዓይነት ስሜት እንዲሰማኝ እያደረገኝ።
<እሺ ምንድነው የምሆነው? ከተፈረደብህ ምንድነው የሚውጠኝ?> ስትለኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የፍርድ ሂደት ላይ መሆኔን አስታወሰኝ።
<እንዴ በፍፁም አይሆንም! ባላደረግኩት ነገር ሊፈረድብኝ አይችልም!>
<አለማድረግህን በምንድነው የምታረጋግጠው? የህክምና ማስረጃዋ መደፈሯን መስክሯል። በቦታው የነበሩ ሰዎች የእንጀራ እናትህን ጨምሮ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ይሄን የሚሽር ምን ማስረጃ ታቀርባለህ?>
<እንዴ? ኸረ በእግዚአብሄር?> ከማለት ውጪ ማለት የቻልኩት የለም።
<ጎበዝ የተባለ ጠበቃ ቀጥሪያለሁ። አላውቅም ሌላ ምን ማድረግ እንደምችል። ከሰዓት መጥቶ ያገኝሃል> ብላ አባብላኝ ስትሄድ ልቤ ወደቀ። እሷ በሙሉ ልቧ ካላመነችኝ ማንንም ማሳመን እንደማልችል ገባኝ። ወደ ፈጣሪ ደጋግሜ አጉተመተምኩ። ምን ብዬም እንደምፀልይ ግራ ገባኝ። <ሌላ ሰው ባያውቅ አንተ ንፅህናዬን ታውቃለህ አይደል እንዴ? በውሸት ሲመሳጠሩብኝ ዝም ብለህ አታይምኣ? አንተ ሁሌም የእውነት ፈራጅ ነህ! በሰው ሳይሆን ባንተ እተማመናለሁ!> አልኩት። ከዚህ በኋላ የነበረው እልም ያለ አስፈሪ ቅዠት ነበር። ከእርሷ ውጪ የማምነውም የምቀርበውም ሰው ስላልነበረ የፍርድ ሂደቱ የሚወስደውን ጊዜ ስላላወቅን ስራዎቹን ውክልና ለእርሷ ሰጠኋት።
<ጥሪ የደረሳቸውን ሰዎች ሰርጉ መሰረዙን ለማሳወቅ በተቻለኝ መጠን ለማዳረስ ሞክሪያለሁ።> ያለችኝ ቀን የእርሷን ህይወት ስላበላሸሁ ራሴን ጠላሁት። ፊቷ ላይ የነበረው መሰበር እኔን አደቀቀኝ። የሆነውን ሳስበው ራስምታት ይለቅብኛል።> » ብሎኝ ራሱን እንዳመመው ነገር የግንባሩን ጠርዞች ይነካካ ጀመር።

«ታርፋለህ? ወይ በቃ ነገ እንቀጥል?» አልኩት ስለእውነቱ ግራ ገብቶኝ እንጂ ልለው የፈለግኩትስ <ምን ጉድ ነው ያሳለፍከው? አንድ ሰው ይሄን ሁሉ መከራ አልፎ እንዴት ይቆማል? ኸረ ይሄ ሁሉስ የአንድ ሰው ህይወት ነው?> ነበር።

«ኖ! እዚህ ምዕራፍ ላይ መመለስ አልፈልግም! ጨርሼው መገላገል ነው የምፈልገው! ይልቅ ልቀመጥ! አስቀምጪኝ !» አለኝ። ሶፋው ላይ እንዲቀመጥ እያገዝኩት የእውነቴን አሳዘነኝ። በእያንዳንዱ ትናንቱ ውስጥ የበደለኝን በደል እየሸረፈው እየሸረፈው ከራሴ ህመም በላይ ለእርሱ መታመም ጀምሬያለሁ።
«በናትህ አትከልክለኝ ልቀፍህ?» አልኩት። አይዞህ መባል ሞቱ ነውኮ አውቃለሁ! ሲታዘንለት የተሸነፈ ነው የሚመስለው ያንንም አውቃለሁ። ግን በቃ አቅፌው ዝም ማለት ፈለግኩ። ራሱ አቀፈኝ! በሱ ህመም እኔ ተባበልኩ። ደረቱ ላይ እንዳቀፈኝ ብዙ የማፅናኛ ቃል ብለው ብዬ አስባለሁ። እንደማይወደው ስለማውቅ ዝም ብዬ ለደቂቃዎች ከታቀፍኩ በኋላ ወደ ፅሁፋችን ተመለስን።

«የትኛው ይበልጥ እንደሰበረኝ አላውቅም። ባላደረግኩት ነገር መከሰሴ ወይስ ምስክሮቹ የራሴው ቤተሰቦች መሆናቸው? ምንስ በደል ብበድላቸው ነው በዚህ መጠን ሊከፉብኝ የቻሉት? እኔ የማውቀው ወንድሜንም ሆነ እንጀራ እናቴን የበደልኩት ትዝ አይለኝም። እነሱ ግን ፍርድ ቤት ቆመው ምለው በውሸት ሲመሰክሩብኝ ዓይናቸው ውስጥ የነበረው የበቀል እርካታ በምንም ልኬት የማልገልፀው ነበር። 7 ዓመት! 7 ዓመት ተፈረደብኝ! ከእውነት ጎን የሚቆመው አምላክ ከእነሱ ጎን ቆመ!»
«እመቤቴ ድረሽ!» አልኩኝ መጻፉን ትቼ
«አዎ! 7 ዓመት የሚለውን ዳኛው ሲናገር ዞሬ ማዕረግን አየኋት። አንጀቷን በአንድ እጇ ደግፋ ድምፁ የማይሰማ ለቅሶ ስታለቅስ አየኋት። እጅ የሰጠ ለቅሶ ፣ ተስፋ የቆረጠ ለቅሶ ፣ ዛሬም ድረስ ጭንቅላቴ ውስጥ ያለ ምስሏ ነው። ለመጨረሻ ጊዜ የተወችልኝ ምስሏ ነው። የፍርድቤቱ የእንጨት ወንበር ላይ ወደኋላ ተደግፋ በቀኝ እጇ የተጣበቀ አንጀቷን ደግፉ ስቅስቅ ብላ የማይሰማ ለቅሷ የምታለቅሰዋ ማዕረግ!! ለመጨረሻ ጊዜ ያየኋት ያኔ ነው። የእስር ቤት የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ከዛሬ ነገ ማዕረግን መጥታ አያታለሁ በሚሉ ናፍቆቶች የተሞላ ስለነበር የእስር ቤቱን ድብርት ፣ አለመመቸት ፣ ምግብ አለመጣፈጥ አላስተዋልኩትም። ብደውል ባስደውል ስልኳ ዝግ ነው። ወር አለፈ። ስራ ቦታ መታሰሬን ማንም እንዳያውቅ ፈልጌ ስለነበር ለማንም እኔ በበኩሌ ምንም አላልኩም! የሷን ደህና መሆን አለማወቅ ሊያሳብደኝ ሲሆን ለእንድርያስ ደወልኩለት። ሊያየኝ እስር ቤት መጥቶ ማዕረግ ስራ ቦታ ብቅ እንደምትል ግን ድባቴ ውስጥ እንደሆነች ነገረኝ። መኖሯ አፅናናኝ። ልታየኝ አለመፈለጓ ደግሞ አመመኝ። ሁለት ወር ሶስት ወር …… ሲለቃት ትመጣልኛለች እንጂ የእኔ ማዕረግ አትተወኝም ብዬ ጠበቅኳት። ቀኑ በጨመረ ቁጥር መጠበቄ እየቀነሰ ፣ ተስፋዬ እየሞተ ፣ በምትኩ ውስጤ ጨለማ እየነገሰ መጣ። ወራት ነጎዱ…….. ውስጤ ፀጥ እያለ፣ ውስን ድምጾች ብቻ ውስጤ እየቀሩ፣ የማዕረግን የመጨረሻ ምስል ጨምሮ በጣም ውስን ምስሎች ብቻ ጭንቅላቴ ውስጥ እየቀረ ከቀን ወደ ቀን እየሞትኩ እንደሆነ ይሰማኝ ጀመር።

ሁለት ድፍን አመት! ልታየኝ አልመጣችም። ስራ ቦታ በጣም አክቲቭ ሆና እየሰራች እንደሆነ ሰማሁ። ደጋግሜ ደወልኩ። ደጋግሜ ደብዳቤ ላኩላት። ልታየኝ አልፈለገችም። በሁለተኛው ዓመት ጎብኚ መጥቶልሃል ተብዬ ስጠራ ልቤ ዘላ ምላሴን ነክታው ነበር የተመለሰችው። በመጨረሻም ልታየኝ መጣች ብዬ!! በምትኩ በቁሜ ልትጨርሰኝ የተከሰተችው የእንጀራ እናቴ ነበረች። እንደወዳጅ ሰላም ካለችኝ በኋላ
<ከሌላ ሰው ከምትሰማው ብዬ ነው ራሴው ልነግርህ የመጣሁት> ብላ የሰርግ ቴንኪው ካርድ አቀበለችኝ። ያየሁትን ከማምን የራሴን ጤንነት አለማመን ተሻለኝ እናም ሰሞኑን ጭንቅላቴ ልክ አይደለም አይደል? የእኔ ማሰቢያ ተናግቶ ነው እንጂ የእኔ ማዕረግ ሰርጋችን በተሰረዘ በሁለት ዓመቱ አትሞሸርም! ያውም ደግሞ መቀመቅ ሊከተኝ ካሴረብኝ ወንድሜ ጋር! በፍፁም!!

<እናትህ ህይወቴን ቀምታኝ እሷ ስትስቅ እኔ ባዶ ቤቴን እና ልጄን ታቅፌ እንባዬን ቁርስ እራት ስበላ ለዓመታት ኖሬያለሁ። እጅ ሳልሰጥ ነው አባትህን የመለስኩት። አንተ ደግሞ በተራህ የልጄን ህይወት ስትቀማው ዝም ብዬ የማይህ ነበር የመሰለህ? ሙትቻ ! እያየሁህ ከሞት ተነስተህ ልትነግስ?> ያለችኝን ሰምቻታለሁ። ምን ያህል እንደምትጠላኝ ድምፅዋም ፊቷም ላይ ይሰማል ይታያል። እግሬን እየጎተትኩ ማዕረግ ከወንድሜ ጉያ በነጭ ቬሎ አጊጣ ያለችበትን ካርድ በእጄ ይዤ ከኋላዬ ትቻት ሄድኩ። የሚቀጥለው ሲዖል ነው። ራሴን የምስት ይመስለኛል ግን አውቃለሁ። ጭንቅላቴን ድቅድቅ ጨለማ ተቆጣጥሮታል። የእናቴ ሬሳ ሽታ እንደገና አፍንጫዬ ላይ ነገሰ። ሁለት ድምፆች ብቻ ጭንቅላቴ ውስጥ ይሰሙኛል።
<አዲስ አንተ ካልሞከርክ እኔ ላግዝህ አልችልም! መናገር ከፈለግክ ታገል። አንተ ብቻ ነህ ራስህን ልታድነው የምትችለው> የሚለው ያኔ ከእናቴ ሞት በኋላ መናገር ሲያቅተኝ ያከመኝ ዶክተር ንግግር እና
<አንተ ደግሞ በተራህ የልጄን ህይወት ስትቀማው ዝም ብዬ የማይህ ነበር የመሰለህ?> የሚለው የእንጀራ እናቴ ድምፅ።
ከጨለማው ሌላ ጭንቅላቴ ውስጥ ያለው ያ ከእጄ የማይጠፋው የወንድሜ እና የማዕረግ ምስል ነው። አዕምሮዬ የእኔ ሳይሆን ቆይቶ ስነቃ ይታወቀኛል። እታገላለሁ። ግን አቅም ያንሰኛል። እንዳለፈው ጊዜ ዲዳ እንዳልሆንኩ አውቃለሁ ግን ምንም ቃል ታዝዞ ከአፌ አይወጣልኝም። የሆነ የማላውቀው ሃይል አስፈሪ ጨለማ ውስጥ የጣለኝ ይመስለኛል። ፍርሃቴ ሰውነቴን ያርደዋል። ቀኑ ቅዳሜ ይሁን ሰኞ፣ ወሩ ሀምሌ ይሁን ጥር ቀኑ ጠዋት ይሁን ውድቅት ለሊት አላውቅም። የሆነ ቀን ጭንቅላቴ ምልስ ሲልልኝ ልብሴ ላይ ሽንቴን ሸንቻለሁ። የዛን ቀን የአዕምሮ ህክምና ሆስፒታል ተወሰድኩ። እጅ ላለመስጠት እታገላለሁኮ ግን ከራሴ ጨለማጋ እንዴት እንደምዋጋ አላውቅበትም። ጨለማው ይዞኝ ሲሄድ ይታወቀኛል። ከምስሎቼ እና ከድምፆቼ ጋር በሚያርድ ፍርሃት ውስጥ ሲነክረኝ ይታወቀኛል። እንዴት ልውጣ? መንገዱ በየት ነው? መሞት እፈልግ እና አስበዋለሁኮ! ከዚህ ስቃይ ሞት ይሻላል እላለሁ። ግን አይሆንልኝም! »

እጆቼ ይፅፋሉ እንጂ እንባ እና ንፍጤ እየተቀላቀለብኝ እየተነፋረቅኩ ነው። እሱም ተመልሶ ይሄን ክፍል ላለማሰብ በሚመስል ቶሎ ለመገላገል ዓይነት እያወራኝ ፊቱ ግን አሁን ከሚያወራልኝ ጨለማ ጋር ግብ ግብ የገጠመ ይመስል በስቃይ ተሸፍኗል።
«ሁሉን ያያል ይሰማል የተባለው ፈጣሪ ሊያድነኝ አልመጣም! ማዕረግ ከሞት ልትቀሰቅሰኝ አልመጣችም! አባቴ ሊታደገኝ የለም! እኔ እና እኔ ብቻ! ቀስ በቀስ የሰላሜ ሰዓት እየረዘመ፣ የትግሉ ሰዓት እየቀነሰ መጣ። እዚህጋ ሌላ ድምፅ ጭንቅላቴ ውስጥ ተጨመረ ድምፁ የአባቴ ነው ቃላቶቹ ግን እኔ የማስባቸው ናቸው። <ይሄን ሁሉ አልፈህማ እዚህጋ እጅ አትሰጥም!> የሚለኝ! በመሃል ረጭ ሲልልኝ <ብቻ አንዴ ከዚህ ስቃይ ልውጣ እንጂ መቼም እዚህ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ አልመለስም> እላለሁ። ወደ ራሴ ስመለስ 11 ወር እንዳለፈኝ አወቅኩ። ሌላ ሰው ሆንኩ። ፍጹም ሌላ ሰው ……. ከዚህ በኋላ ያለውን አዲስ እወደዋለሁ። ማንም ይወደዋል። ምክንያቱም ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል።» ብሎኝ በረዥሙ የመገላገል ትንፋሽ ተነፈሰ። እየተነፋረቅኩ እንደሆነ አሁን ነው ያየኝ። እንደመደንገጥ ብሎ እቅፉ ውስጥ እንድገባ ዘረጋልኝ። ጭራሽ ብሶብኝ አረፍኩት።
«ለምን አልነገርከኝም? ምንአለ ነግረኸኝ ቢሆን?»
«ከዛስ? ነግሬሽ ቢሆን ልታስተካክዪኝ ትሞክሪ ነበር። ዳሜጅ ሆኗል ብለሽ ያሰብሽውን ፓርቴን ልታበጃጂ ትደክሚ ነበር። ከዛ ለማጠፋው ጥፋት ሁሉ እንደሰው በጥፋቴ ሳይሆን ባለፈው ቁስሌ እየዳነሽ ይቅር ትዪኝ ነበር። አይደለም?»
«እሺ ከዚህ በኋላ አስቸጋሪ ወቅት የለኝም በለኝ?»
«አልነበረኝም! አንቺ እስከመጣሽበት የህይወቴ ምዕራፍ!»
«እኔኮ ግን ለትናንት ስቃይህ ያበረከትኩት አንዳችም ነገር አልነበረም። በሙሉ ልቤ ከማፍቀር ውጪ የበደልኩህ አልነበረም። የእናትህን፣ የማዕረግን ፣ የወንድምህን፣ የእንጀራ እናትህን …… ሁሉንም እኔን አስከፈልከኝ። ነግረኸኝ ቢሆን ፍቅሬ አይጎልም እንደውም ይበልጥ አፈቅርህ ነበር።»
«አልገባሽም! እዛ ጨለማ ውስጥ ራሴን ከምመልስ ምንም አደርግ ነበር።» ላለፉት ዓመታት ያላለቀስኩት እንባዬ ሁሉ ይግተለተል ጀመር። ስቃዩ የሱ ሳይሆን የእኔ ይመስል ያባብለኝ ያዘ።
«እሺ ከዛስ?»
«ከዛማ አዲስን ከተበታተነበት እፍ እፍ ብዬ አራግፌ ገጣጥሜ አቆምኩት። እስር ቤት ሶስት ዓመት ከሁለት ወር እንደታሰርኩ በምህረት ተፈታሁ እና ከተበዳይ ቤተሰብጋ እርቅ መፈፀም ግዴታ ስለነበረብኝ ያን አደረግኩ። ወንድሜ እና ማዕረግ ድርጅቶቹን እንዳልሆነ እንዳልሆነ አድርገው በእዳ እና በቋፍ ሁለቱ ጭራሽ ተሽጠው። የቀረኝ እዳ እና ማሽኖች ብቻ ነበሩ።እነርሱ ከሀገር መውጣታቸውን ሰማሁ። ቤቴ ብቻ በእኔ ስም ስለነበር ተከራይቶ ኪራዩ ለእንጀራ እናቴ ገቢ እየሆነ ጠበቀኝ። ቤቴን ሸጬ እዳዎቹን ከፋፍዬ ሀ ብዬ ቢዝነሱን ጀመርኩ። አዲስ አዲስን ሰራሁ። ትናንት እና ትናንት ላይ የነበሩኝን ሰዎች ሁሉ ከማህደሬ ሰረዝኩ። ትንሽ ቢያታግለኝም እንደገና ወደመስመር ገባሁ። እሺ አሁን የምታለቅሺው ለምንድነው?»
«እኔእንጃ! አልወጣልኝማ!»

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል ሀያ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *