Tidarfelagi.com

‹‹ቀጮ!››

(ማሳሰቢያ፤ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ የህክምናም ሆነ የስነ ምግብ ባለሙያ አይደለችም፡፡ በዚህ ፅሁፍ ላይ የተካተተው መረጃ በግል ልምድ ላይ የተመሰረተ እና ለሌሎች ይጠቅም ይሆናል ከሚል ቀና አስተሳሰብ የመነጨ ምክር እንጂ በጥልቅ መረጃና ሳይንሳዊ መሰረት ላይ የቆመ ነው ለማለት አይቻልም)

ከተወለድኩ አንስቶ አብዛኛውን እድሜዬን ቀጭን ነበርኩ፡፡
ያውም የማሳቅቅ …‹‹ምግብ አትበላም እንዴ?›› የምባል ቀጭን፡፡ ከአስቴር አወቀ ድምፅ ሁሉ እቀጥን ነበር (ሃሃ)

በሽታ ጢባጢቢ ይጫወትብኝ ነበር፡፡ ሰበበኛ ነበርኩ፡፡
ለምሳሌ አስራ ሁለተኛ ክፍል ደርሼ ማትሪክ ለመፈተን ሁለት ወራት ሲቀሩኝ ታይፎይድና ታይፈስ በተባበረ ክንዳቸው ደቆሱኝና አልጋ ላይ ዋልኩ፡፡ ይታያችሁ፤ ያኔ ቀሪ የሕይወት ዘመን እጣ ፈንታን የሚወስን የነበረ ማትሪክን የሚያህል ፈተና ፊት ለፊቴ አስቀምጬ ታምሜ ተኛሁ፡፡ ቤተሰቤ፣ መምህሮቼ፣ ጓደኞቼ በሙሉ ‹‹ምን አይነት እድል ነው…አጥንታ አጥንታ ባለቀ ሰአት መታመሟ!›› ብለው ከንፈር መጠጡልኝ፣ ተጨነቁልኝ፡፡ በሽታዬ ሳይታወቅ ከዛሬ ነገ ይለቃታል ተብሎ ሃኪም ቤት ሳልሄድ አንድ ሁለት ቀናት ስቆይ፤ በፊትም ከሲታ የነበረው ሰውነቴ በየቦታው መሰርጎድ፣ እየታየሁ ማነስ ጀመርኩ፡፡ ያኔ ታላቅ ወንድሜ እንደ ሻንጣ አንጠልጥሎ የሰፈር ክሊኒክ ወሰደኝ፡፡ በጣም መታመሜን ሲሰማ አባቴ መጣ፡፡

በጊዜው የቤተሰብ ሃኪም ለመሆን ጥቂት ይቀራቸው የነበሩት ጋሽ ጠና (ዶክተርዬ የሚል ወግ ከዚህ በፊት አቅርቤባቸዋለሁ) አባቴን በመገረምና በመቀየም አይተው ያሉት አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ‹‹ ይህችኛዋ ልጅህ አይደለችም እንዴ?›› ዶክተርዬ ይህንን ያሉት ያገጠጠ አጥንቴን፣ የሰረጎደ ቆዳዬን አይተው ወይ በማደጎ ወስዶ ያመጣት ግን ስጋው ያልሆነች ልጅ ስለሆነች በምግብ ይበድላታል ብለው አስበው ነበር፡፡ ይህን ያህል ነበር ቅጥነቴ፡፡

ያ ሁሉ አልፎ፣ ማትሪክንም አልፌ ራሴን ከቻልኩና ትዳር ከያዝኩ በኋላ ግን በፍጥነት በስጋ መሞላት፣ በአስገራሚ ሁኔታ መፋፋት ጀመርኩ፡፡ ሃምሳ ኪሎ የሰማይ ያህል ይርቀኝ የነበርኩ ልጅ ሁለት አመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ሃምሳ ስምንት ኪሎ ገብቼ አረፍኩ፡፡
ያን ጊዜ ጨነቀኝ፡፡ ያልለመድኩት ገላ፣ የኔ ያልሆነ ስጋ አስጨነቀኝ፡፡ የተገዛ ስጋ በፌስታታ ይዤ የምሄድ ያህል ይከብደኝ ነበር፡፡ ሰው አይቶ ‹‹ያቺ ወፍራሟ ልጅ›› የሚለኝ ሰው አልነበረኩም ፣ መወፈሬ ሊያስጨንቀኝ የሚገባ ደረጃም አልደረሰም ግን ከነበርኩበት የመጣሁት ርቀት ረጅም ነበርና ጨነቀኝ፡፡

በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ በውፍረት የሚጨነቁ ወዳጆቼን ሁኔታ አይኔን ከፍቼ አየሁ፡፡ ሁሉም በራሳቸው መንገድ ስባቸውን ለማቅለጥ፣ ስጋቸውን ለመቀነስ ይሯሯጣሉ፡፡

ለምሳሌ መስኪ በሳምንት ሶስት ቀን ሌላ ምግብ ሳትነካ ብርቱካን ብቻ እየበላች፣ የሞቀ ውሃ በዝንጅብል እየጠጣች ነው፡፡ ከወራት በኋላም የቀነሰው ግን አምርራ የምትጠላው ቦርጭዋ ሳይሆን የመኖር ፍላጎቷ ነበር፡፡ በቀላሉ የምትናደድ፣ በዚህም በዚያም የምትበሳጭ፣ ሁሉ ነገር እጅ እጅ የሚላት ልጅ አደረጋት፡፡

በመሃል ይባስ ብዬ ስልሳ አምስት ኪሎ ገባሁ፡፡

የሚያየኝ ሰው ሁሉ ‹‹ምነው ምን ሆነሽ ነው…በጣም ወፈርሽ እኮ….›› እያለ ያልጠየቅኩትን አስተያየት ሲሰጥ፣ ጭንቀቴ ከክብደቴ ጋር ቢጨምርም የመስኪን ስቃይ ግን አልሞከርኩትም፡፡
የመስኪን ብቻ ሳይሆን የፅዮንን በሳምነት አምስት ቀን በቀን ሶስት ሰአት ጂም መስራት እና ሰላጣ እና ዘይት የሌለው ጥቅል ጎመን ብቻን መብላትን አልሞከርኩትም፡፡
የሰላምን ሙዝ እና ገብስ ዳቦ ብቻ በልቶ ‹‹ዲቶክስ›. የማድረግን ‹‹ዳይት›› ለመሞከርም አልዳዳኝም፡፡
ከአሜሪካ የመጣ የሚያከሳ ኪኒን የሚውጡ፣ ቅባት እና ስጋ ያለበት ሳይሆን የነካውን ነገር እንደ ጦር የሚፈሩ፣ ሙቅ ውሃ በሎሚ ሲጠጡ የሚውሉ፣ ካሎሪ ኢን እና ካሎሪ አውት በሚል የሚበሉትን እያንዳንዱን ነገር ሁሉ በካሎሪ የሚቆጥሩ፣ ማር በውሃ የሚጠጡ፣ ሰላጣ ብቻ የሚበሉ….ሌላም ሌላም ብዙ ሰዎችን አይቻለሁ፡፡ አንዱም ጤናማ፣ አንዱም ዘላቂ፣ አንዱም አስተማማኝ የክብደት መቀነሻ መንገድ መስሎ ስላልታየኝ አልሞከርኩትም፡፡

2011 መባቻ ላይ ከስልሳ አምሰት ኪሎ በኋላ የተወሰኑ ኪሎዎችን እንደጨመርኩ ቢሰማኝም ሚዛን ፈራሁ፣ መስታወትን መሸሽ ጀመርኩ፡፡ ድሮ የፈለጉትን ልብስ ገዝቼ የምለብሰው (ፋሽን ነፍሴ ነውና) ልጅ እየሰፋ የመጣውን ሰውነቴን ለመሸፈን እድሜ ላይ አስር አመት የሚጨምሩ ሰፋፊና ረጃጅም ‹‹ሸፋኝ››እና ‹‹ለውፍረት ይቅርታ የሚያደርጉ›› ልብሶችን አሳድጄ መግዛት ጀመርኩ፡፡

ግን ነገሩ ያማረኝን መልበስ፣ ዘንጬ የመታየት ብቻ አልነበረም፡፡ ወደ ላይ እንጂ ወደ ታች የማይሄደው የክብደቴ መጨመር ያሳስበኝ የጀመረው የእግር ጉዞ ሳደርግ ቶሎ መድከም፣ ለመሮጥ ስሞክር ማለክለክ፣ አንዳንዴም ከባድ የራስ ምታት እና አንገቴ ላይ የመጨምደድ ስሜት ይሰማኝ ሲጀምር ነው፡፡ ይሄኔ ነው ይሄ ጉዳይ የታይታ፣ የውበት ጉዳይ ሳይሆን ጊዜ ልሰጠው የማይገባ ነገር እንደነ ይሰማኝ የጀመረው፡
ግን የት ልጀምር?
ክብደትን ለመቀነስ ምን ላድርግ ብዬ ጉግል ባደርግ በመቶዎች የሚቆጠሩ እርስ በርስ የሚጣረሱ መረጃዎች ይዘረጋፋሉ፡፡ ሰው ብጠይቅ ሁሉም ለእኔ ይሄ ነው የሰራው የሚል የሚጋጭ መንገድ ይናገራሉ፡፡ አንዱ በደም አይነትሽ ብዩ ሲል ሌላው ደግሞ እሱ ዝምብሎ ወሬ ነው ይላል፣ አንዱ ድንች ሲል ሌላው ቡኒ ሩዝ ቀቅይና ሞክሪ ይላል፡፡

በዚህ አይነት ግራ መጋባት ውስጥ ሆኜ ነው ሁለት ልጆችን ከወለደች በኃላ እንደ ድሮው የመንግስት እርሻ የሰፋቸው የቀድሞዋ ‹‹ ሱፐር ሞዴል›› መሳይ ወዳጄ ቅድስት ሁሉን ነገር የቀየረቸው፡፡ ቅድሰትን- ሶስት ወር ሳላያት ቆይቼ ሳገኛት …የልጅነት መልኳን መልሳ፣ ሳትጎሳቆል ከስታ፣ ሳትጎዳ ተሸናቅጣ ውብ ሆና አገኘኋት፡፡ ውበት ደፍቶባት፣ ማማር ዘንቦባት ነበር፡፡

መገረሜ ሳያባራ፤ ሰላም እንኳን ሳልላት ምን አልኳት?

‹‹ምን አድረገሽ ነው?››

ይሄ ከሆነ ዛሬ ልክ አንድ አመቱ ሆነው፡፡ የቅድስት መልስ ሕይወቴን ከቀየረ፣ የልጅነት ቁመናዬን ከመለሰ፣ ለፋሽን ያለኝን ፍቅር እንደ አዲስ ካደሰ፣ ከሁሉ በላይ ግን ጤንነቴን ፍፁም ካስተካከለ ዛሬ አንድ አመቱ ነው፡፡

ለመሆኑ ቅድስት እንዴት አድርጋ ጊዜን ወደኋላ ሾፈረችው? ለእኔስ ምን ነግራኝ በአራት ወራት ውስጥ ከላዬ ላይ አስራ አራት ኪሎ አንዳራግፍ አደረገችኝ?

ቀጮ! (ክፍል ሁለት)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *