በዛ ….ከምር በዛ …!! እንዴ እግዜር በሚያውቀው እኔ ክፉ ነገር አስቤ ወይ የሱን ትዳር ለመበተን አስቤ ያደረኩት ነገር አይደለም ….በቃ በበጎነት በፍፁም ቅንነት ያደረኩት ነገር ነው ! እውነቴን ነው …የሱ ትዳር ስለተበተነ እኔ ምን አገኛለሁ ?…ትዳሩስ ስለሞቀና ስለደመቀ ምን አጣለሁ ?… እንደው አንዳንዱ ሰው የሱ ተራ ጉዳይ ሳይቀር ማምሻውን በቢቢሲ የተዘገበ በአልጀዚራ ተሰራጭቶ አየሩን ሁሉ የሸፈነው ይመስል ‹‹አሁን አንተ ይሄን ነገር ሳትሰማ ቀርተህ ነው ????›› ብሎ መቆነን ያምረዋል !ቁንን !! የሱን የጓዳ እንቶ ፈንቶ የምሰማው ምን ስለሆነ ነው …አይ እዚህ ሰፈር አጉል ተናንቀናል …
እስቲ አሁን ማን ይሙት…ጥፋቴ ምንድነው ምን አጠፋሁ? ….ባለፈው እሁድ ጧት እንቁላልና ዳቦ ገዝቸ (ለቁርስ) ከሱቅ ስመለስ ልክ ኮንዶሚኒየሙ ደረጃ ላይ አንዲት ቆንጆ ልጅ የወገቧ ቅጥነት የማይታይ መዳፍ ግራና ቀኝ ጨምቆ የያዛት የሚመስል…. በዛ ላይ ደግሞ ባየር ላይ የቆሙ የሚመሳስሉ ትላልቅ ጡቶች ያላት …. እንደነገሩ በሻሽ ሸብ ያደረገችው ፀጉሯ ግማሹ ከሻሹ አምልጦ ትከሻዋ ላይ ጥቁር ሰርዶ መስሎ የሚዘናፈል…ትልቅ ሻንጣ እያንዘፋዘፈች ከብዷት ደረጃውን ስትወርድ ተገጣጠምን …ደግሞ የአይኖቿ መተላለቅና ጥራት …‹‹ይችን የመሰለች ቆንጆ ከበላየ አድራ›› ሲያቃዠኝ አለማደሩ ብል ማጋነን ይመስላል !
እውነቱን ለመናገር ከዚህ በፊት አይቻት እንኳን አላውቅም ! ሴት ልጅ ስትቸገር መርዳት ደንብ ነው ብየ …..እንቁላልና ዳቦየን የደረጃው ከፈፍ ግንብ ላይ አስቀመጥኩና (እንደውም አንዱ እንቁላል ተሰብሯል) ሻንጣዋን ይዠ ደረጃውን አወረድኩላት …ፊት ለፊት ወደቆመው ታክሲም ሸኘኋት….. በዛ የንጋትት ኮከብ በሚመሳስሉ ውብ አይኖቿ አንዴ አይታኝ ‹‹እግዚአብሔር ይስጥልኝ›› ብላኝ ቁሞ በሚጠብቃት ላዳ ታክሲ ተሳፍራ ሄደች …በቃ ይሄው ነው ! እኔ በህልሜም በውኔም እንዲህ ያለ ጉድ ይመጣብኛል ብየ በምን አባቴ አስቤ …ይች በጎነት መዘዟን መዘዘቻ !
ለካስ የሸኘኋት ቆንጆ አራተኛ ፎቅ ላይ የምትኖር ባለትዳር ነበረች! ወንድየ የሚባል ባል ያላት ! ማታ ባሏ ጋር ትጣላና ሻንጣዋን ይዛ ትወጣለች …ባል የሆነ ቡጥጥ ኩራተኛ ቢጤ ነው እሱን እንኳን በአይኔ አውቀዋለሁ የአገር ቁልፍ የተሰካበት የቁልፍ መያዣ እንደፅናፅል እያንቯቯ የሚወጣና የሚወርድ ጎልማሳ ነው …እንደውም እኔ በፊት በፊት የብሎኩን ቤቶች ሁሉ ቁልፍ የሚይዝ ነበር የሚመስለኝ ! እና ይች ቆንጆ ሚስቱ በብስጭት ሻንጣዋን ይዛ እሄዳለሁ ስትል …‹‹ጥርግ በይ›› ብሏት ጭራሽ ከነሻንጣዋ ወደውጭ ገፈታትሯት በሩን ከኋላዋ ጠረቀመባት ….እኔማ ማታ አራት ሰዓት አካባቢ በር በሃይል ሲጋጭና ብሎኩ ሲንቀጠቀጥ ሰምቸ ነበር … እስቲ አሁን ማን ይሙት እንኳን በር አይን እንኳን ተጨክኖ የማይከደንባት የምታሳሳ ቆንጆ ልጅ ላይ እንዲህ ይደረጋል ?ወይስ የፈለገ ቆንጆ ብትሆን ሴት ልጅ ሚስት ስትሆን የሆነ የሚሰለች ነገር አላት ??የራሳቸው ጉዳይ ሚስቱ ናት እንደፈለገ !
በዛ በጨለማ ሻንጣዋን ይዛ መሄጃ ስታጣ እዛው ጎረቤት ያለች ገና ከወለደች አንድ ሳምንት የሆናት ጓደኛዋ ቤት ትገባና …እስከሚነጋ ጓደኛዋ እዚሁ እደሪ ብላት ታድራለች ….ጧት ታዲያ ከጓደኛዋ ቤት ስትወጣና ደረጃውን ስትወርድ ነበር እኔ ጋር የተገጣጠምነው …(መቸም የሳትራት ነኝ እድሌ የሚጥለኝ እሳት ላይ ነው) እንግዲህ ባል ሚስቱ የት ትደር የት አያውቅም ጧት በመስኮቱ ብቅ ሲል ሻንጣዋን እያንዘፋዘፍኩ ታክሲ ውስጥ ሳስገባት አየኛ ! በሱ ቤት ሚስቱ እኔ ቤት አድራ እጅ ከፍንጅ ይዞን ልቡ ውልቅ ብሏል !
‹‹ሲያጋልጥ የየዋህ አምላክ ልበ ንፁህነቴን አይቶ …..›› ብሎ ፉከራውን ጀመረዋ ! ‹፣እዚሁ አፍንጫየ ስር ምናለ ራቅ ብትል …ምናለ ብሎክ አስራዘጠኝ …ሃያ… ሃያ አንድ …ሃያ ሁለት ብትሄድ….ብሎክ ሃያ ሶስትም ቢሆን በዚህ በግሮሰሪው በኩል ቅርብ ነው …. እዚሁ በአልጋየ ትክክል ከስሬ …አለ ወደታች ወደኔ ቤት እየጠቆመና በእግሩ የእኔን ቤት ከሱ ቤት የሚለየውን ወለል በእልህ እየረገጠ …›› በዚህ ሊያበቃ መሰላችሁ …ቀጠለ ‹‹ ይሄ ማለት ሌላ ቤት መሄድ አይደለም እኮ ወገኖቸ ….. ሌላ ወንድ ይዛ አልጋየ ስር እንደተኛች ነው የምቆጥረው …ያውም እኔ አልጋው ላይ ተኝቸ …ታዲያ ይሄ ሞት አይደለም ወገኖቸ …?ሰው ወዶ ነው ሚስቱን በገጀራ የሚገድለው …? ሰው ወዶ ነው አንድ ጠርሙዝ አረቄ ብቻውን አንጠፍጥፎ የሚጠጣው …? እ… ፍረዱኝ እንጅ>> ….ይላል …ያች ነገረኛ ጎረቤታችን ደግሞ እንደትልቅ ሰው እንደማረጋጋትና እንደመምከር ነገሩን ያባብሳሉ …
‹‹ ይሄማ ንቄት ነው ምን ጥያቄ አለው …… ምን አንተን ብቻ እኛንም ጎረቤቱን አገሩን የ<ኢቶቢያን> ህዝብ ሁሉ መናቅ ነው …ዘነዘና አለ መፍለጫ አለ ቢጠፋ ቢጠፋ ድንጋይ አለ …ሞቅ ብሎህ የሞት ታናሽ የሆነ እንቅልፍ ወስዶህ እግዜር ጋረደላቸው እንጅ … ድንገት በለጭ ብሎብህ በተኙበት ጨፍጭፈህ እጅህን ለመንግስት ብትሰጥ የማን ያለህ ይባላል ….አንተ እንደሆንክ እንኳን ሰይጣንህ ተነስቶ ብቻህንም አንድ ጦር አይመልስህ …ጎረቤቱም ቢሆን ደግ አረገ ነው የሚልህ ›› ይሉታል ! ይታያችሁ አሁን ይች ሴትዮ ባልቴት ናቸው?! እኔንማ እዚህ ቤት ከተከራየሁ ጀምሮ ጥምድ አድርገው ይዘውኛል ….ምክንያታቸው ደግሞ ‹‹ሲገባ ሲወጣ ሰላም አይለኝም›› የሚል ነው !
‹‹እኔማ አሁን ሂጀ ነው ተሸክሜ አራተኛ ፎቅ ካመጣሁት በኋላ ቁልቁል የምፈጠፍጠው አለቀውም እዛ ብሎኬቱ ጋ ነው የምፈጠፍጠው …›› አለ ጎረቤቱ አንገቱን ቁልቁል አስግጎ የምፈጠፈጥበትን ቦታ እያየ ያማትባል …ፎካሪው ‹እኔን ከቤቴ ተሸክሞ ለመውሰድ መንገድ ሲጀመር ‹‹ተው ተው ጦስ ይሆንብሃል ›. ብለው ከፊት ከኋላ ከግራ ከቀኝ ይዘው ያቆሙታል …‹‹ወይኔ ወንድየ አንበሳው›› ብሎ በመዳፉ ክንባሩን ይገጭና በብስጭት ይብከነከናል ጎረቤቶቹ ከንፈራቸውን ይመጡለታል ! ‹‹ ማን እንደሆንኩ አሳየዋለሁ›› ይላል
‹‹አንተ ማን እንደሆንክ ድፍን ጎተራ እስከሳሪስ …ድፍን ቄራ እስከሳር ቤት እና ሜክሲኮ ያውቃል ….ሳያውቅህ ቀርቶ መሰለህ መታወቅ ቢያስከብር ከሚስትህ በላይ ማን ያውቅህ ነበር ›› ይላሉ ነገረኛዋ ባልቴት ….‹‹ወንድየ አንበሳው›› ሚስቱ እንዳስደፈረችው ትዝ ይለዋል ‹‹ ልቀቁኝ የገባችበት ገብቸ አነጠለልጥየ አምጥቸ ው ከዚህ ፎቅ ላይ ወርውሬ የምፈጠፍጣት ›› ብሎ ጎረቤት ለምኖ ያስቆመዋል …እንግዲህ እንደሰማሁት የሚስቱ ሰፈር ኮተቤ ነው አሉ ….ከኮተቤ እዚህ ድረስ ተሸክሞ አምጥቶ ያችን ቆንጆ ስንቱ በፍቅሯ ከንፎ ልፈጥፈጥልሽ የሚላትን ልጅ ሲፈጠፍጣት ታየኝ … ከኮተቤ እዚህ እንኳን የሱን ሚስት መፈጥፈጫ ባዣንጥላ የሚያዘልሉ ስንት ፎቆች አሉለት አይደል …ወሬኛ !!
ይሄን ሁሉ ፉከራ የምሰማው በኋላ ነው …እኔ እንቁላል ፍርፍር እየሰራሁ ትልቅ የሳይንስ ጥናት እንደሚሰራ ኬሚስት በቅመማ ተመስጫለሁ ! ለካስ ወንዴ አንበሳው እንደእንቁላል ፈጥርቆ የወኔ አስኳሌን ሊያፈሰው ከበላየ በሰላሳ ገላጋይ ተይዞ እየተጋበዘ ነው !ባልቴቷ ወንዴ አንበሳው ቀዝቀዝ ያለ ሲመስላቸው እንዲህ ሲሉ ለአንዷ ገላጋይ የሚያወሩ መስለው በሾርኔ እኔን መጨፍጨፊያ መሳሪያ ያለበትን ቦታ ይጠቁሙታል…
‹‹ አልጋነሽ ሙች ! እውነቴን እኮ ነው …አሁን ይሄ ልጅ ድንገት ማታ እጅ ከፍንጅ ቢይዛቸው (((እኔ በር ሃያ አራት ሰዓት የሚቀመጥ))) ገብስ መፈተጊያው የእንጨቱ ሙቀጫ ዘነዘና አለ ….. ድንገት ፊቱ ሲያገኘው ላጥ አድርጎ እንካ ቅመስ ቢለው ….››
አልጋነሽ ታዲያ እንዲህ አለቻቸው ‹‹ በቀደም ለማሪያም ዝክር መውቀጫ አውሱኝ ብልዎት የለም ጠፋ አላሉም እንዴ ?›› …ማን ያውቃል ጠቡን ሲሰሙ ለወንዴ አንበሳው ሊያስታጥቁ አውጥተው አስቀምጠውት ይሆናል !መቸም ሴትዮይቱ ወደኔ የሚዘምት አጥተው እንጅ ስንቅና ትጥቅ ከማቀበል አይመለሱም !!
ወንዴ አንበሳው አሁንም ይጋበዛል ‹‹ልቀቁኝ…… በእማማ ቁንጥሬ ገብስ መፈተጊያ ዘነዘና ነው አናቱን የማፈራርስለት›› እያለ ! …እውነትም እማማ ቁንጥሬ !!
ከዚህ ቀን በኋላ ወንዴ አንበሳው ብስጭቱ ቢበርድለትም በአይነቁራኛ እያየኝና እየገለመጠኝ ያልፋል ! በነገራችን ላይ ወንዴ አንበሳው ፈሪ ነው! ይሄን ነገር ከሰማሁ በኋላ እውነቱን ላስረዳው ፈለኩ !ድነገት ደረጃው ላይ ስንገናኝና ደረቱን ነፍቶ ገልምጦኝ ሊያልፍ ሲል ‹‹ወንድየ›› አልኩት እኔ ደግሞ ‹‹ምናባህ ፈለክ ›› ይለኛል ይሄ ባይሆን እንኳን ‹፣ስምህን ቄስ ይጥራው ›› ይለኛል ብየ ነበር እሱ እቴ …ልክ ድምጼን ሲሰማ እንደተተኮሰባት ሚዳቋ በድንጋጤ ዘሎ አማተበ፡) አማትቦ እስከሚጨርስ ጠበኩና የሆነውን ሁሉ ረጋ ብየ አስረዳሁት …
‹‹አውቃለሁ አብርሃም …አውቃለሁ እሷ አለሌ ነገር ናት… እንዳታሳስትህ ብየ እንጅ አንተማ በምን እዳህ ›› ብሎኝ እርፍ ! ስሜን ማን ነገረው …ኧረ ጉድ !! ቆይ ይሄ ሰውየ ምንድነው ሲያወራኝ አይኑ እዛና እዚህ እየተወናጨፈ አይኔን ማየት የሚፈራው ….ደግሞ እጁ ይንቀጠቀጣል …ከምር ሚስቴን የቀማኝ እንጅ በሚስቱ የጠረረገኝ አልመስልህ አለኝ !! እና ወንዴ አንበሳው ጋር ከዚች ቀን ጀምሮ ሰላም ወረደ ! ያች ነገረኛ ባልቴትም እኔና ወንዴ ሞቅ ያለ ሰላምታ ስንለዋወጥ በብስጭት ያሸሙራሉ ….
‹‹ወይ ስምንተኛው ሽ ሚስትን አስረክቦ መገልፈጥ … አይ አንተ መድሃኒያለም ይሄን ጉድ ከምታሳየኝ ምነው ብትወስደኝ ….እንደው አሁን ሞልቶ ለተትረፈረፈ ቸርነትህ በሰማይ ቤት ለኔ ኮስማና ነብስ ቦታ አጥተህ ነው ?… ወይስ እንደው እዚሁ የማንንም የወንድ አልጫ እያየች ድብን ትክን ትበል ብለህ ›› ይላሉ …
ወንዴ አንበሳው ጋር ከሰላምታም አልፎ ጥሩ ወዳጆች ሆንን እንደውም ባለማወቅ ሻንጣዋን ይዠ የሸኘኋት ሚስቱን መልሶ የማስታረቅ አደራው እኔ ላይ ወደቀና አረፈው … ወይ ጣጣ ያችን ውብ ልጅ ወደዚህ አንዴ አንበሳ አንዴ በግ ወደሚያደርገው ባሏ ለመመለስ ሳይሉኝ ሽማግሌ ሆኘ የልጅቱን ስልክ ተቀበልኩ !… ይሄን ነገር የሰሙት ነገረኛ ባልቴት ታዲያ
‹‹አሄሄ የልብን ሰርቶ በሽምግልና ስም ትራፈውን ለባል መመለስ ቱ እኔይቱ ልጅት የፊተኛውም የኋለኛውም ሶስተኛም ባሌ እንዲህ አይነት አልጫነት አያቃቸውም …እንኳን መንካት ቀጥ ብሎ በሙሉ ዓይኑ ያየኝን ወንድ በወይራ ብትር ግንባሩን እየሰነጠቁ ጉሽርጥ ነበር የሚያስመስሉት… ኤዲያ …ወንድ ድሮ ቀረ ››
ወቸ ጉድ! ሰው ካልተጣላ ብለው እንዲህ እንደእብድ ብቻቸውን የሚያስለፈልፋቸው ሴትዮ ምን ይባላሉ ….የሆነ ሁኖ ያችን አንዴ ብቻ ያየኋትን ቆንጆ ልጅ በሽምግልና ስም እንደገና የማየት እድሉ ሊገጥመኝ ሆነ….
One Comment
እባካችሁ ክፍል 23 ይቀጥል ?