እኔና ልእልት ባዶ ቤት ብቻችንን እንደተቀመጥን ….አንዳች ነገር ‹‹ንገረን›› እያሉ የሚለምኑኝ የሚመስሉ አይኖቿን እየተመለከትኩ ….‹‹ልእልት አፈቅርሻለሁ … ባለትዳር መሆንሽን አውቃለሁ ግን ከዚህ በኋላ ከአንች መለየት ለኔ ከባድ ነው ብሞት ይሻለኛል ›› ብየ እውነቱን ማፍረጥ ተራራ ሆነብኝ ….ልእልትን ፈራኋት … አንዲት ሴት ፊት ሳይሆን ትልቅ አዳራሽ ውስጥ የተሰበሰበ ህዝብ ፊት ቁሜ ንግግር እንዳደርግ የታዘዝኩ ያህል አፌ ተያያዘ ! ልእልት ታስፈራለች ረጋ ያለ ሰፊና ጥልቅ ውሃ ነው የምትመስለው ….
የማረባ ልጅኮ ነኝ !! ሰው ላይ የትም የማያውቃትን ቆንጆ መንገድ አስቁሞ ያዋራ የለ … ሰው ያውም በግልምጫ የምታቀምሰውን ሴት ግልምጫውን ቻል አድርጎ እየተከተለ ያሰበውን ይናገር የለ … እና እኔ አሁን ምን የሚሉኝ ሰው ነኝ …እንዲህ በአክብሮት የምትመለከተኝን ሴት እንደምወዳት እንደማፈቅራት መናገር ምኑ ነው ገደል የሆነብኝ ……በቃ እንዲህ አፌን እንደለጎምኩ ይመሻል ትሄዳለች ….እዛ ወረቀት ወረቀት የሚሸት ቢሮና ባዶ ቤቴ እየተንቆራጠጥኩ ስጨነቅ እከርማለሁ …በቃ ንገራት ይለኛል ውስጤ ! አይ ውስጤ ….
በመጨረሻ ምን አልኩ ? ‹‹እህቴ እግዜር ይይልሽ !!›› እንዲህ ምድጃ ላይ ጥላኝ ትሂድ
ልእልት ዝምታየ ጨንቋት ነው መሰል ስለስራ ጠየቀችኝ …መለስኩ … ‹‹ደባሪ ነው ትንሽ ይበዛል›› ብየ ! ስለእህቴ ደግነት ጥሩ ልጅነት ነገረችኝ …‹‹እ›› ብየ ዝም !!…ከምር የሆነ የሚያስጠላ ጋግርታም ባህሪኮ ነው ያለኝ …ኧረ በእግዚአብሔር አንድ ነገር ተናገር እለዋለሁ እራሴን ወይ ፍንክች …ድንጋይ !! ዝም ብየ ማየት (አይንህ ይጥፋ እቴ ሙትቻ) ቢጨንቀኝ …(በሰው ቤት )
‹‹ልእልት ፊልም ልክፈትልሽ ›› አልኳት
‹‹እሽ …ፊልም በጣ…..ም ነው የምወደው አንተን እንዳላስደብረህ እንጅ ብላ ከማትሰስተው ፈገግታዋ ልቤ መሸከም የሚያቅተውን ያህል ፈገግ አለችልኝ (ፍልቅልቅ ቢባል ይሻላል) ….. ተነስቸ ቲቪ ከፈትኩና የሆነ ፊልም አንድ ቻናል ላይ መርጨ ማየት ጀመርን ….. ልእልት ተመስጣ ፊልሙን ስትመለከት…. እኔ ስላለፈ ታሪኳ እያሰብኩ የነገረችኝን ወደኋላ ተመልሸ እያስታወስኩ የለሁም ….ፈሪ ምን መሸሻ አለው ያው ወደትዝታው ነው የሚፈረጥጠው !!
*** **** *****
አንድ ሰው ስንት ነው ? በተለይ አንዲት ሴት ስንት ነች ? ኧረ ሁላችንም እንኳን ለሌሎች ለራሳችን ስንት ነን ? የልእልት ታሪክ ቤቀኑ ሳስታውስ አንድ ሰው አልመስልህ እያለችኝ ግራ እጋባለሁ …. ሰው ማለት ከአካባቢው ባህልና ወግ ….ካደገበት ስነልቦና ….መደበኛም ይሁን መደበኛ ካልሆነው ትምህርት…. እንዲሁም ካለፈበት ውጣ ውረድና ከሚጠብቀው ተስፋ ተቀነጫጭቦ በአንድ ላይ በነፍሱ ልጥ የታሰረ ህያው ችቦ ነው ! እድሜ በሚሉት እሳት ተለኩሶ እየተቀጣጠለ ካለለት ለሌሎች እያበራ እና በህይዎት ጨለማ የተቀመጡ ደስታ ፍቅር ፀብ ወዘተ ሰዋዊ ስሜቶችን በራሱ ብርሃን እየተመለከተ …..ካላለትም በራሱ እሳት እራሱ እየተበላ ወደመቃብሩ የሚወርድ ፍጥረት …. ነው !! እንደዛ ሳይሆን አይቀርም …እንጅ እንዴት አንዲት ሴት ….አንዲት ወጣት ሴት …ይሄን ሁሉ ነገር ትሆናለች ….??
ወንዴ ማታ ሰክሮ በጎረቤቶቿ ፊት አሞልጮ አሞልጮ ከለቀቃት በኋላ የልእልት ህይዎት ሌላ ቅርፅ ሌላ ዓለም ሁኖ ‹ሀ› ብሎ ጀመረ ….እንዲህ ስትል ነበር የተረከችልኝ …..
‹‹ ወንዴ የዛን ቀን ሌሊት ባዶ ቤት ትቶኝ ከአባቱ ጋር ከሄደ በኋላ …. በቀጣዩም ቀን ሳይመጣ ቀረ…. እውነቱን ለመናገር አለመምጣቱ አስደስቶኛል … ‹‹እንኳንም ቀረ›› ነው ያልኩት !! እሱ ለተናገረው ፀያፍ ነገር ሁሉ እኔ አፍሬ ነበር….እንዴት አይን ለአይን እንደምንተያይ ጨንቆኝ ነበር ….. ወንዴ ይጥላኝ ግዴለም ….ከፈለገም አይንሽን እንዳላየው ሂጅልኝ ይበለኝ …ግን በሰው ፊት ልቡ የሚያውቀውን እምነቴን እንደምናምንቴ ቆሻሻ ጥሎ ረጋገጠው … ልክ እንደቁራጭ ስጋ የሃሜት ጥርሳቸውን አግጥጠው ለሚጠብቁ ጎረቤቶቸ ሻሞ ብሎ ወረወረኝ !! …..ከዚህ በኋላ ምን እንደምጠብቅ ለራሴም አልገባሽ አለኝ … በቃኝ !!
እናቴ ቤት ለመሄድ ወሰንኩ …. እንኳን እኔ እሱስ ዋጋ ቢስ አድርገው ያሳደጉት አባቱ ቤት ሂዶ የለ …. ደግሞ ያበሳጨኝ የአባቱ ሾካካነት …ማንም ሰው ልጁን ይወዳል አውቃለሁ …ማንም ሰው ለልጁ ያደላል አውቃለሁ …. ግን እንደትልቅ ሰው ….ቢያንስ እኔን አከበሩኝም ናቁኝም ትዳር ብለን ስንጋባ ጉልበታቸውን ስመን መርቀውን የሸኙን አባት ናቸው … የእኔም እናት እኮ አምና ልጇን ለልጃቸው ስትሰጥ ባለአደራ ናቸው …‹‹ምን ሆናችሁ ›› ማለት ማንን ገደለ ….ደግሞ ያውቁኛል ምንም ነገር ጠይቀውኝ እንደማልዋሽ ያውቃሉ (አብርሽ እኔ ለቀልድ እንኳን መዋሸት አላውቅበትም) …ልጃቸው የዋሻቸው ሲመስላቸው እንኳን ‹‹ልእልቴ አትዋሽም እሷ ትንገረኝ ›› የሚሉ ሰው ነበሩኮ !
‹‹ልጀን ሰው አደረግሽው ቤቴ ቤቴ እንዲል አደረግሽው የኔ ቆንጆ አንበሳ›› ይሉኝ ነበረኮ …..ደግሞ ወንዴ እኔጋር ከመተዋወቁ በፊት በወር ሁለት ሶስት ጊዜ የሚታሰር ….በየመሸታ ቤቶ ማንም ጋር የሚደባደብ ልጅ እንደነበር ያውቃሉ ….በየጣቢያው እና በየመጠጥ ቤቱ ሲጎተቱ ነበር ኑሯቸው ….ያን ሁሉ እፎይታ ያን ሁሉ ልጃቸው ላይ የተፈጠረ መረጋጋት አይክዱትም ….በእርግጥ እኔ ምንም አድርጌ አይደለም ….ወንዴን ተው ብየ መክሬውም አልነበረም ስለሚወደኝ ነበር እንጅ ….የዛን ጊዜ ግን…..አካሄዳቸውን ብታይኮ ልክ ልጃቸውን ከአውሬ የሚያሸሹ ነበር የሚመስሉት ! አለችና በምሬት ራሷን ነቀነቀች !!
ልእልት ስታወራኝ ዝም ብየ አያታለሁ …. በዚህ ሁሉ መከራ የተደቆሰች ሴት አትመስልም …. ከድምፅዋ ጀምሮ ፊቷ ላይ የሚታየው ስሜት ሁሉ አንዳች ግርማ ሞገስ አለው ….ውብ!!
አየህ አብርሽ ለእነዛ አስቀያሚ ጎረቤቶቹ ቁልፉን ወርውሬለት ….እናቴ ቤት ልብሴን ይዠ መሄድ ነበር ያሰብኩት …..ግን የሱን ድሪቶ ይዠ ብሄድ ለቀባጠረው ቆሻሻ ወሬ አጉል ማረጋገጫ መስጠት ይሆንብኛል ብየ የለበስኳትን ልብስ እንደለበስኩ እጀላይ የነበረችውን ሁለት ሽ ምናምን ብር አንስቸ በታክሲ ወደእናቴ ቤት ሄድኩ ! በመንገዴ ሁሉ አእምሮየ ይዝት ነበር ….እንደእብድ ከንፈሮቸ እየተንቀሳቀሱ ብቻየን አወራ ነበር ….
‹‹ምቾቱ ይቅር እንጅ ለማንም አሳልፋ የማትሰጥ እናት አለችኝ …እንኳን ንፅህናየን ክዳ ልታቆሽሸኝ ….ምንም ባደርግ ገመናየን ሸፋኝ እናት አለችኝ !ማሚየ እድሜዋ ይርዘምልኝ …. አዎ እናት አለችኝ … ሁሉም ነገር ቀርቶብኝ ….እየተናኩ የሚወረወርልኝ ሃብትና ምቾት ቀርቶብኝ ሩህሩህ አይኗን እያየሁ እግሯ ስር ዘላለም እኖራለሁ … !! ያደኩበት ቤት ….ያደኩበት ሰፈር እሄዳለሁ … ያሳደጉኝ ጎረቤቶች አሉኝ … ሰፈር አለኝ ቤት አለኝ …. ውስጣቸው ምንም ያስብ ምን እንደነዚህ ውሻዎች ስጋየን በጨካኝ ጥፍራም ብልግናቸው የማይቧጥጡ ….በፍቅራቸው ያሳደጉኝ ጎረቤቶች አሉኝ ! ከእነዚህ የሰው ጅቦች እሸሻለሁ …እኔ ልጃቸው ብሆን ነው ምን አደረኳቸው ? እሄዳለሁ እናቴ ጋር !!ማሚየ ጋ …
ድሮም የኔ የምንላቸውን ሰዎች ስንገፋ ነው ማንም እንደሆቴል በር ነፍስና ስጋችንን እየገፋ እንዳሻው ሲገባብንና ሲወጣብን የሚኖረው … ሰው ብርም እውቀትም ቢቀር እንኳን አጉል አፈቀርኩ ብሎ የእኔ የሚለውን ዘመድ …የእኔ የሚለውን ቤተሰብ…. የእኔ የሚለውን ታማኝ ጓደኛ መግፋት የለበትም ….ልክ ያስፈልጋል ….ፍቅር ሌላ …ሌላው ህይዎት ሌላ ነው …ሰው ራሱን ከወንዙ ነጥሎ ኩሬ ከሆነ ወይ መሻገት ወይ መትነን ነው እድሉ …. ማንም ሰው ደሴት ላይ መኖር አንድ ቀን ይሰለቸዋል …. አንድ ገፅ ብቻውን ህይቆት አይሆንም …..እናቴ ጋር እሄዳለሁ ….ቤተሰቦቸ ጋር እሄዳለሁ እዛው እኖራለሁ እግዚአብሔር እንደገና በይቅርታ እጆቹ እስኪያነሳኝ …ቤተሰቦቸ ላይ እወድቃለሁ!!
*** **** ******
እቤት ስደርስ እናቴና ሁለት ጎረቤቶቻችን ቡና እየጠጡ ደረስኩ ….እንደትልቅ ሰው ከወንበራቸው ተነስተው አገላብጠው ሳሙኝ ….‹‹ሳቢየ ከየት ብቅ አልሽ በጠራራው ›› አሉኝ እማማ አስረበብ የሚባሉ ጎረቤታችን (ንግስት ሳባ ነው የሚሉኝ ከህፃንነቴ ጀምሮ …ልእልት አይያዝላቸውም) እናቴ ልክ ትልቅ እንግዳ እንደመጣበት ሰው ጭንቅንቅ ብላ የሶፋውን ልብስ እያስተካከለች …‹‹ነይ ተቀመጭ ልእልቴ ምነው በጠራራው እናቴ›› እያለች እንደልጅ ፊቴን በሸካራ እጆቿ ስትደባብሰኝ ሰው ፊት አላለቅስም ብየ እንጅ እንባየ ተናነቀኝ …እናቴ እኔን አስቀምጣ ወደውጭ ብቅ እያለች ‹‹ወንዴስ ….ሳይገባ እንዳይሄድ የሱ ነገር ›› አለች …ሁልጊዜ አድርሶኝ ስለሚመለስ ዛሬም እሱ ያመጣኝ መስሏት ነበር ….
‹‹ እሱ….አልመጣም ማሚየ ….ስራ በዝቶበት ሌላ ሰው ነው ያመጣኝ ›› አልኩ …. (ይሄ ውሻ እናቴ እንዲህ ስታከብረው የአባቱ ንቄት የባሰ ውስጤን እንደስለት ሲያቆስለው ተሰማኝ ) ስለደህንነቴ ….ስለወንዴ እየተቀባበሉ ከጤቁኝ በኋላ …ከመምጣጤ በፊት የጀመሩትን ወግ ቀጠሉ ….እው እንግዲህ አብርሽ ህይዎት በየቦታው ምድጃዋን ጥዳ የምረገጠውን ሁሉ እሳት እያደረገች ስትጠብቀኝ …. አለችና በግርምት አፏን እንደመያዝ አድርጋ እንዲህ አለችኝ
‹ እነማሚየ ቤታቸው ከሶስት ወር በኋላ ለመንገድ ሊፈርስ ደብዳቤ ተሰጥቷቸው ሲጨናነቁ ነበር ለካ የደረስኩት ….
በጭንቀት ጎረቤቱ ሁሉ የሚያወሩትም ይሄንን ነበር …ጎረቤታችን እማማ አስረበብ ታዲያ በፍፁም የዋህነት ለማሚየ እንዲህ አሏት ‹‹ አንችስ በደጉ ቀን ልጅሽ ደህና ሰው ጋር ተጠግታለች …ህንጣውን ነው የምታቆመው የኔ ንግስተ ሳባ ›› እናቴ ዝም አለች ….እኔ ግን ጦር ነገር ልቤ ላይ የተሰካ ያህል ህመሙ እስካሁን ይሰማኛል ! እማማ አስረበብ ቀጠሉ ‹‹ሄሉም ብትሆን (ሄለን የልእልት ታናሽ እህት ነች ) ምን ቀራት እንግዲህ …አመቱ እንደሆነ ይሄዳል ….እግሯ ዩንበርስቲ ተረገጠ ጤናዋን ይስጣት እንጅ መመረቅ ነው ››
አብርሽ …ዝም ብየ ጎረቤቶቻችን የሚሉትን ሰማሁ …እናቴ ፊት ላይ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ተስፋ ነበር (በእኔ በልጇ መተማመን) …ይታይህ እናቴ እና ዩኒፈርስቲ የገባች እህቴ የሚተዳደሩት ከዚቹ ቤት በሚገኝ ኪራይ ነው …እሽ አሁን ፈረሰ ….ምንድን ነው ተስፋቸው? … ሁሉም እኔን ነው ተስፋ ያደረጉት …. በዛ ላይ እህቴ ታማ ከዩኒቨርስቲ መጥታ ነበር …. አሁን ተሸሏት ልትመለስ እየተዘጋጀች ነው …..
መቀሌ ዩኒቨርስቲ ኢኮኖሚክስ ነበር የምትማረው ….እህቴ ጎበዝ ተማሪ ናት… በህይዎቴ ብቸኛ ተስፋ የማደርጋት እሷን ነው …..እሷን ማስተማር የመጨረሻ ምኞቴ ነው ….ደግሞ እንዴት እንደምታሳዝንህ ብታያት አብርሽ….. ምግብ አትበላ …ከቤት አትወጣ ….ሰው ጋር ፈታ ብላ አታወራ በቃ አቀርቅራ ማንበብ ….የመጨረሻ ከቤት ወጣች ከተባለ ቤተክርስቲያን መሄድ ነው …. እንኳን እኔ እህቷ…. ወንዴ ሲወዳት ልክ አልነበረውም ….. (ዋሌቷን አውጥታ የእህቷን ፎቶ አሳየችኝ …ጠይም ቆንጆ ልጅ ነች … ከልእልት ቀጠን የምትል )
የእህቷን ፎቶ ስታሳየኝ እንባዋ ተዘረገፈ ….. ልእልት ስታለቅስ ልቤ እየተነሳች ስትፈርጥ ይሰማኛል …! ምን ማለት እንዳለብኝም አላውቅም ! ፎቶውን ከመለስኩላት በኋላ ትክ ብላ ስትመለከተው ቆየችና ….በረዝሙ ተነፈሰችና ….ሄሉ ብቸኛ መመኪያ ነበረች …አየህ ለወንዴ ጓደኞች እንኳን ስለሷ አውርቸ አልጠግብም ነበር ….እናተ ጋር ተቀምጨ ጫት ሳመነዝክ ብውልም ዩኒቨርስቲ የምትማር እህት አለችኝ …የምልላት ….እነሱ በቤታቸው ሃብት ሲኩራሩና ስለመኪናዎቻቸው ስለቤታቸው ሲያወሩ …..ብቸኛ በኩራት የምናገርበት ምክንያቴ ነበረች ሂሉ …. ማንንም ሰው ከጥፍር ቁራጩ የማይቆጥረው ኢያሱ እንኳን ሄሉን ሲጠራት በአክብሮት ነበር ! ምንጊዜም እኔን ሲገኘኝ የወሬ መክፈቻው ሄለን ነበረች ‹‹ሄሉ ቆንጆ ደህና ነች ›› ይለኛል እንዲህ ሲለኝ ደስ ነው የሚለኝ !!
እንግዲህ ‹‹ትዳር ምናባቱ ›› ብየ በኩራት ቀና ብየ ኮብልየ የመጣሁት ልጅ…. ይሄን ሁሉ የቤተሰብ አደራ ተሸክሜ እና ጎብጨ ሾከክ ብየ ሲመሻሽ ቆልፌው ወደመጣሁት ቤቴ ተመለስኩ ‹‹ምናይነት እድል ነው ›› እያልኩ ! ማሚየ ፊት ኡኡ ብየ አልቅሸ ላፈሰው ያዘጋጀሁት እንባ በውስጤ ነዳጅ ሁኖ የተለኮሰ ይመስል በእልህ ጡፌ እና ተቀጣጥየ ነበር ….በዚች ምድር ላይ ይሄን ቤተሰብ መታደግ የእኔ ሃላፊነት ነው በቃ …. ይህን ለማድረግ ደግሞ ራሴን መታደግ ያውም አሁኑ ግድ ነው አልኩ !
ተመልሸ ወደቤቴ ገባሁ ….. የሆነ ከገደል አፋፍ የተመለስኩ ይመስል እፎይታ ተሰማኝ ….ቤቴን እወዳታለሁ አብርሽ …. ለአንት ሴት ቤቷ ገዳሟ ነው ….እንዳይመስልህ ኬክ ቤት መዝናኛ ቦታዎች ሞልተን ስንገኝ ቤታችንን የምንጠላ …ለሴት ልጅ ቤቷ ሉአላዊ ግዛቷ ነው …ከቤቷ መገፋት ከአገሯ እንደመገፋት ነው … እራሴ ወንዴ ጋር በወታሁ ቁጥር እየመረጥኩ የምንገዛቸው ….ማንኪያ ሹካ ሰሃን ብርጭቆ ….ትራስ …አንሶላ ሁሉም አፍ አውጥተው እንደልጅ በመመለሴ በደስታ የተንጫጩ መሰለኝ …..ይሄ የኔ ቤት ነው አልኩ … ማንም እንደጥራጊ ገፍቶ የሚጥለኝ ልእልት አይደለሁም … ምቹ ሶፋየ ላይ ቁጭ ብየ የሖነውን ሁሉ ረስቸ ነገሮችን ከየት እንደአዲስ እንደምጀምራቸው ማሰብ ጀመርኩ ….
ከዛን ቀን በኋላ ወንዴ በማንኛውም ሰዓት ይመለሳል ብየ ብጠብቅም … በተከታታይ ሳይመጣ አንድ ሳምንት አለፈው ….አልደወለም እንኳን ! ግን አሞት ቢሆንስ ብየ አሰብኩ … እና አላስችል ብሎኝ ደወልኩ … ስልኩ ዝግ ነው …ለአባቱ ደወልኩ ስልኩን ዘጉብኝ …ደግሜ ደወልኩ ዘጉብኝ ….! እንግዲህ ስራ ላይ ሁነው ከሆነ ይደውላሉ ብየ ተውኩት ….በሰላሙ ጊዜ እንዲህ ደውየ ስልካቸው ድንገት ተይዞ ቢሆን እንኳን ዘግተው ነው ወዲያው የሚደውሉልኝ .. የነበረው ….እንዲቹ ስገረም ወንዴም እንደጠፋ እንደቀልድ አስር ቀን ሞላው … ለጓደኞቹ በየተራ ደወልኩ አያነሱም ….አንዱ እንደውም ዘጋብኝ …..
እኔ በህይወቴ የሚያቅለሸልሸኝ ነገር ቢኖር አብሮ በልቶ ጠጥቶ …ችግር ሲፈጠር እንደውሻ ጅራቱን ሸጉጦ የሚጠፋ ጓደኛ …የወንዴ ጓደኞች ጨርሰው ውሾች …እንኳን ደውየላቸው አይኔ ሲያርፍባቸው የሚሽቆጠቆጡ ጓደኞቹ … ገና ለገና ወንዴ ጋር ተጋጭተዋል ብለው ጀርባቸውን ሰጡኝ … እኔኮ የሚገርመኝ የሃብታም ልጆች ናቸው .. አንዳንዶቹ ‹‹ደረስ ብየ ልምጣ›› ብለው እዚህ ፒያሳ ደርሶ እንደመምጣት ኤሮፕ ደርሰው የሚመጡ ….ምንድነው እንዲህ ወኔያቸውን ሰልቦ ልክስክስ ጥገኛ ያደረጋቸው …. በእውነት የድሃ ልጅኮ ቆራጥ ነው አብርሽ !
እነዚህ አንበሳ ገዳይ መስለው መኪናና ልብስ እያሳመሩ ውስኪና ጫት ቤት የሚያጣብቡ የሃብታም ልጆች እንዴት አይነት የጨቀየ መንፈስ መሰለህ ያላቸው ….ስልባቦቶች መሰሉህ ….. ‹ኮንፊደንስ› የላቸው … በመሃበር ተደጋግፈው ካልቆሙ ራሳቸውን ችለው ስልክ እንኳን መደወል የማይችሉ ድንዙዞች …ስላበሳጩኝ ብቻ አይደለም አብርሽ ….ከሴት አቅም እንኳን በተፈጥሮ የተሰጣቸውን ማፍቀርና መፈቀር ጫት ላይ በመሃበር ካልተመከሩ ልባቸው አይከፈትም …. አውቃቸዋለሁ …..
ይታይህ ቤቴ መፈንጠዣቸው ነበር …በችግራቸው እህታቸው ነበርኩ …ሰክረው ሲያስታውኩብኝ ሳልፀየፍ ያስታመምኳቸው ልእልት ነበርኩ ….ሲጣሉ ተቆጥቸ የማስታርቃቸው ነበርኩ …… ዛሬ ትዳሬ ችግር ላይ ሲወድቅ ሁሉም ሰምተዋል (በኋላ አውቂያለሁ እንደሰሙ) ግን ቢያንስ ስላሳለፍነው ጓደኝነት ሲሉ ‹‹ምን ሆንሽ ምን ላይ ወደቅሽ ልእልት ›› ማለቱ ይቅርና ስልኬን እንኳን ማንሳት ፈርተው ቤጫት ጉድጓዳቸው ተደብቀው ገፉኝ !!
ወንዴ እቤት ሳይመጣ አስራ አምስት ቀን ….ሆነው …እጀ ላይ ያለው ብር እያለቀ ነው ….ፍሪጅ ውስጥ ምንም የለም ባዶ ሆኗል …ይሄም ሁሉ ብዙ አላስጨነቀኝም …አንድ ቀን በጧት በሬ ተንኳኳ …..ምን እንደሆንኩ እንጃ በድንጋጤ ራሴን ልስት ነበር …ወንዴ እንደሚሆን እርግጠኛ ነበርኩ …ልቤ ተፈትልኮ የሚወጣ እስኪመስለኝ እየመታብኝ በሩን ከፈትኩ ….
ፈፅሞ አይቸው የማላውቀው እድሜው አምሳ የሚሆን አንዳች ሚያክል ጥቁር ሰውየ ነው … ኮስተር ብሎ ‹‹ደህና አደርሽ ›› አለኝ ….በሩን ልክ እንደራሱ ቤት ገፋ አድርጎ ወደውስጥ ሲገባ ከመደንገጤ ብዛት አፍጥጨ ከማየት ውጭ ምንም ማለት አልቻልኩም ….ሊፈራ መሰለህ ….እልፍ ብሎ ሶፋው ላይ ተቀመጠና ቀና ብሎ ተመለከተኝ …ሰውየው ፊቱ ላይ በግራ በኩል ከጆሮው ጀምሮ እስከአገጩ የተጋደመው ጠባሳ ይዘገንናል ….. ደግሞ የተቆጣ ይመስላል …..በክፉ አይኑ ነው የሚመለከተኝ ….በዚህ ድረሱልኝ ብየ እንኳን ብጩህ ‹‹ይበልሽ›› የሚሉ ጎረቤቶች ባሉበት ፎቅ ….ምን ጉድ መጣብኝ ብየ አፍጥጨ አየሁት ……እሱም ቀና ብሎ አፈጠጠብኝ …ጠባሳው ራሱ ሶስተኛ አይን ይመስላል ……
One Comment