‹‹ተመስገን…. ዋናው መትረፉ ነው ! ወደልቡ ከፍ ቢል ኖሮ ወይ ቆሽቱን ቢያገኘው የማን ያለህ ይባላል ›› የሚል ድምፅ ስሰማ ልክ እንደብርቱ ክንድ ትከሻና ትከሻየን ይዞ እያርገፈገፈ ከከባድ እንቅልፍ የቀሰቀሰኝ መሰለኝ ! አ?? አላመንኩም …. መትረፌ ብቻ አይደለም የገረመኝ …. የመትረፌን የምስራች በመትረፌ የተቆጨ በሚመስል ድምፅ ቀድሞ በመንገር ያነቃኝ የዛች የነገረኛ ‹‹እማማ ቁንጥሬ ›› ድምፅ መሆኑ እንጅ ! ከዛም ሁሉም ነገር ዝምምም አለ…ወዲያው ግን ጉንጨ ላይ ግራና ቀኝ ሁለት ሸካራ መዳፎች ሲያርፉ ተሰማኝ …እንኳን ሰመመን ውስጥ ሁኘ ሙቸም ቢነኩኝ እነዚህ እጆች የማን እንደሆኑ የምለያቸው ይመስለኛል …የእናቴ እጆች ናቸው!! …
‹‹አቡቹ›› ስትል ሰማኋት ስጋት በተሞላና ቀስ ባለ ድምፅ …..ይሄው ድምፅዋ ተከተለ ራሷ ናት !! ጥፋቴ ባይሆንም በአጉል ጀብደኝነት በሩን በመክፈቴ አዘንኩ ‹‹ፈሪ ለናቱ ›› ይሉት ሃቅ የገባኝ በዚች ቅፅበት ነው ! ….አቤት አለሁ …ተርፊያለሁ …በዚች አለም ለመኖር ሌላ እድል ተሰጥቶኛል ብየ ለመጮህ አስቤ ነበር …አንችም አይኖች ላይ ሊዘንብ እንደተዘጋጀ ደመና የተንቸረፈፈ እንባሽ ይትነንና ከንፈርሽ በሳቅ ይሞላ …..ልላት ነበር እናቴን ….ግን ለምን እንደሆነ እንጃ ወደዚህ አለም ሙሉ ለሙሉ ከመመለሴ በፊት በሞትና ህይዎት መሃል ባለችው ሰመመን ትንሽ ጊዜ መቆየት ፈለኩ …‹‹አቡቹ አለህልኝ …አለሁ በለኝ ›› ቀጠለ የእናቴ ጥሪ …ሰው በጥሪ ከሞት ይመለስ ይመስል ! ምን እዚህ አገር መሰመሚያ(በሰመመን መቆያ) የለ …መተኛ የለ …መሞቻ ራሱ የለም !
አይኔን ቦግ አድርጌ ገለጥኩት ….ብዥ ካለ የብዙ ሰዎች ምስል ጋር የእናቴ እልልታ ከግድግዳ ግድግዳ ….ከዛም ግቢውን ከዛም ሰፈሩን …ድፍን አዲስ አበባን እንደእፊያ ሲከድነው ተሰማኝ …እማማ ቁንጥሬም እልል ሲሉ ሰማሁ …አሄሄ ይች የእማማ ቁንጥሬ እልልታ ጥሪ መሆን አለባት ‹‹ ወንዴ አንበሳው ይሄ ነጃሳ አጉል ነካክተህ ተርፎልሃል ና ጨርሰው ›› የምትል ጥሪ ! እንጅ ማን ይሙት አሁን በእኔ መትረፍ እማማ ቁንጥሬ ደስ ብሏቸው እልል ሊሉ ??!!
‹‹ይቅርታ ማዘር እንዲህ አይጮህም ሌሎች በሽተኞች ይረበሻሉ …›› የሚል የተቆጣች ሴት ድምፅ ተከተለ …ሌሎች በሽተኞች ? እንዴ ያ መናጢ ‹‹ወንዴ አንበሳው ›› ማታ ጉድ የሰራው ድፍን የብሎኩን ሰው ነው እንዴ …እና ሌሎች በሽተኞች ከየት መጡ ?…ተገለጠልኝ !! …ያለሁት ሆስፒታል ነበር …..ክንዴ ላይ የተመሰገው የግልኮስ መርፌ ሲጠዘጥዘኝ የመድሃኒት ሽታ ሲሰነፍጠኝ የተኛሁበት አልጋም ካለዎትሮው
ከወደትካሻየ ቀና ሲልብኝ ሆስፒታል መሆኔን ወዲያው አወኩ ! ጆሮየ አፍንጫየ እና አይኔ በየተራ ስራቸውን ሲጀምሩ ሁሉም ነገር ተገከለጠልኝ ….የቀኝ ጎኔ ላይ አንዳች ሃይለኛ ህመም እና መጠዝጠዝ ሲሰማኝ ደግሞ ማታ የሆነው ሁሉ ግልጥ ብሎ ታወሰኝ ….ይሄ ብሽቅ ሰካራም ቆይ ልነሳ ብቻ !!
ማታ በሬን ሲያንኳኳ ….ያው መቸም አንዳንዴ አጉል ጀግና መሆን ይዞ ሟች ነገር ነው …በሬን ከፈትኩ ….ልክ ስከፍት ‹‹ወንዴ አንበሳው›› እንደጅብራ በሬ ላይ ተገትሯል …. ‹‹ሰላም አመሸህ ወንዴ›› አልኩት እኔማ ሰው ነው ብየ ነበር ….
እሱ ግን ለድፍን መንደሩ በሚሰማ ጋጋኖ ድምፁ ‹‹አንተ ሰውየ ግን ከሚስቴ ራስ ላይ አትወርድም እንዴ ኧረ ስለግዚሃር ተወኝ ….ተወኝ ብያለሁ ተወኝ …እኔ አልደረስኩብህም ተወኝ ….በህግ አምላክ ተወኝ ….. ›› ብሎ ሲጮህ በሃፍረት ሽምቅቅ አልኩ ….ትንፋሹ ጋኒቱን ራሷን ! በዛ ላይ እጁ ኪሱ ውስጥ ነው ….የሆነ ነገር እንደያዘ አለመጠርጠሬ አሁን ሳስበው ይገርመኛል ….ለነገሩ ብዙ ጊዜ ሰካራሞች እጃቸውን ኪሳቸው ውስጥ አስገብተው መጀነን ባህሪያቸው ነው ብየ ችላ ብየውም ይሆናል !
‹‹ምን ሁነሃል?›› አልኩት እንዲህ የተበደለ መስሎ ኡኡ ሲል ግራ ተጋብቸ !
‹‹ምን ሁነሃል ?›› ብሎ ከበፊቱ በጎላ ድምፅ መልሶ ጥያቄን ደገመውና ‹‹ምን ሁነሃል ትለኛለህ እንዴ ….ከዚህ በላይ ምን ልሁንልህ ….በቁሜ ሚስቴን ቀማሃኝ …የሞቀ ትዳሬ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ በባልዲ ገለበጥክበት …..አይኔ እያየ ያውም በአልጋየ ትክክል ….አብረሃት አድረህ …ሂጅ ወንዴን ሜዳ ላይ ጥለሽው ጥፊ ብለህ ሚስቴን የግራ ጎኔን አካሌን ….በኩንትራት ታክሲ ሸኘሃት ….ትዳሬን በተንክ ፈጣሪ ይፍረደኝ ብየ እንባየን ወደላይ ረጭቸ ጉልበቴን አቅፌ ብቻየን ኩርምት ብየ በተኛሁበት ….ጭራሽ ለእኔው ለራሴ ደውለህ ….››
‹‹አንተ አፍህን አትክፈት …ማን ጋር እንደምታወራ እወቅ መጀመሪያ!! ›› አልኩ ከምር ተበሳጭቸ…ደግሞ እንዴት እንዴት ነው ወሬውን የሚያሳምረው በእግዚአብሔር …..
‹‹ …ማን ጋር እንደምታወራ እወቅ ?????? ይችን ይወዳል ወንዴ አንበሳ…….ው ….›› ብሎ ፎከረና ‹‹ አንተም ማን ጋር እንደምታወራ አሳውቀሃለሁ ›› ብሎ እንድ እርምጃ ወደኔ ተራመደ…በዛው ቅፅበት ከኪሱ ተፈትልኮ የወጣ እጁ ወደ ሆዴ ሲወነጨፍ የሆነ የሚያብረቀርቅ ነገር በለጭ ሲል አየሁ … ቢላ ነበር …እንዳጋጣሚ ዞር ማለቴ ጠቀመኝ እንጅ እንዳሰነዛዘሩ ቢሆን አልተርፍም ነበር ….ይሄ ሁሉ የሆነበት ፍጥነት ከጥቂት ሴኮንዶች አይበልጥም ….ለካስ ይች ጤዛ ህይዎት እንዲህ በሰከንድ ነው እርግፍ ብላ የምታርፈው !
ከዛ በኋላ መንደርተኛው ሲንጫጫ …… እሪታው ሲቀልጥ ነው በደብዛዛው የተሰማኝ (የሪታው ጀማሪ እማማ ቁንጥሬ ነበሩ እንግዲህ እስኪወጋኝ ተደብቀው በጉጉት እየጠበቁ ይሆናል ) …በሬ ላይ በአንድ ሰካራም እንዲህ መሆኔ …መደፈሬ ቢቆጨኝም መትረፌ ተአምር ነበር …. የግቢው ዘበኞች ‹‹ወንዴ አንበሳውን›› እንደአህያ እየወገሩ ለፖሊስ ሲያስረክቡ እኔንም አፋፍሰው እዚህ ያለሁበት ሆስፒታል አመጡኝ …..መንገድ ላይ የፈሰሰኝ ደም ይሁን ወይም ቁስሉ እንጃ ብቻ ሁሉም ነገር ጨላለመብኝ ይሄው እዚህ ነቃሁ !!
የተኛሁባት ክፍል በሰው ተሞልታለች … እናቴ ከትራስጌየ ተቀምጣ አይን አይኔን ታያለች …ሁለት እህቶቸ አልጋውን ከበው ቁመዋል ……ደግሞ ጥግ ላይ የቆሙት ጎረምሶች እነማን ናቸው ? አሃ ….…..የሁለቱ እህቶቸ ፍቅርኞች ….አይይ እነሱም መጡ? (ይችን ይችንማ እናውቃታለን ….የኔን አደጋ ሰበብ አድርገው በእናቴ ፊት ‹የብረት በር የሆንን አማቾች አለን› የምትል ግንባር ማስመታት ናት ሂሂ ….በሰው ችግር መሞዳሞድማ ተገቢ አይደለም !) በኋላ ስሰማ አንዱ የእህቴ ጓደኛ ‹‹ወንዴ አንበሳውን ›› በሽጉጥ ግንባሩን እንደሸንኮራ ካልሰነጣጠኩት ብሎ በስንት ገላጋይ ነው አሉ የተመለሰው …እህቴን ጠርቸ
‹‹እኔ የምልሽ ….በሽጉጥ ነው የተባለው?›› አልኳት
‹‹ አዋ ›› አለች…የሆነች ኩራት ቢጤ ፊቷ ላይ በስሱ እየተንሳፈፈችባት! (ሌላው ቢቀር ላንተ ለወንድሜ ደምህን የማይመልስ ፍቅረኛማ አላጣም አይነት፡)
‹‹አሃ ….ጓደኛሽ ቀድሞ ታጋይ ነበር እንዴ›› አልኳት …
‹‹ከግንድ ያታግልህ !….እስቲ ታመሃል አሁን እንኳን ዝም ብለህ ተኛ ›› ብላኝ እየተቆናጠረች ወጣች … ምን መተኛ አለ ….ዛሬ ‹‹ወንዴ አንበሳው ላይ›› ሽጉጥ የመዘዘ የእህቴ ፍቅረኛ ነገ እህቴን ለትዳር ብንከለክለው ይች አፈሙዝ ወደኛው መዞሯ አይደል ? ኧረ እኔ እዳ አያጣኝም ! የአርባ ቀን አድሌ አነፍንፎ ችግር ይጠራል !
ይሄን እያሰብኩ ስማረር ….ድንገት ያለንበት ክፍል በቀስታ ተንኳኳ….በር አካባቢ ያሉት ለመክፈት ሲራኮቱ በውስጤ እንዲህ እላለሁ (((ተው የተንኳ በር ዘላችሁ አትክፈቱ…በኔ ይብቃ ትውልድ ይዳን ))) ….እህቴ ከፈተችው ….. አንዲት ቆንጆ ሴት በነጭ ፌስታል ሙሉ… የሆነ ነገር የያዘች በቀስታ (እየፈራች) ገባች …
ከላይ ትንሽ እንደበረዶ የነጣች ነጠላ ፀጉሯና ትከሻዋ ላይ ጣል አድርጋለች …..ብዛቱ የጤፍ ክምር የመሰለ ጥቁር ፀጉሯ ነጠላውን የተወጠረ ድንኳን አስመስሎታል ! እርፍ !! የ‹‹ወንዴ አንበሳው›› ሚስት መጣችላችሁ!!!! (ድሮ እቃ ጠፍቶ በፍለጋ ስንማስን ‹‹ተውት ሰይጣኑ ሲበርድ አፍንጫችሁ ስር ታገኙታላችሁ›› ይል ነበር አያቴ ….) ይች ውብ ልጅ ግን ሰይጣኑ ሲሞቅ ያለሁበት ድረስ ከች አለችና አረፈችው ! እግዚዮ ደግሞ እንዴት አምሮባታል …. ምንም እንኳን ካለስራየ ቢሆንም ለዚህ የበቃሁት …ለዚች ቆንጆ የከፈልኩት መስዋእትነት ግን አንሶ ታየኝ … ምን አላት ያ ናዚላ ባሏ በሽንኩርት ቢለዋኮ ነው ጫር ያደረገኝ ….ለነገሩ ጥቃቱ ከ‹‹ጫርም›› ያለፈ ነበር ከኩላሊቴ ከፍ ከጎድን አጥንቴ ዝቅ ብሎ በቀኝ በኩል ነው ያገኘኝ በግራ ቢሆን ልብህን ያገነው ነበር ይሉኛል …ልብ ቢኖረኝ መቸ በሬን ስከፍት ! ግን ይችን መልዓክ የመሰለች ልጅ ሳያት በስለት መወጋቴ ‹‹ጫር›› ሁና ታየችኝ !!ታየኛ በቃ !
ልጅቱ ቀስ ብላ ወደኔ መጣችና ‹‹እንኳን እግዚአብሔር አተረፈህ›› ብላ እንባዋ እንደሃር በለሰለሱ ጉንጮቿ ላይ ድንገት ተዘረገፈ …. ማታ ከፈሰሰው የእኔ ደም ይልቅ የዚች ልጅ እንባ አሳዘነኝ ! ፊቷ ክረምት የጠባበት ውብ ምድር ይመስላል …አይኖቿ በሃምሌ ሰማይ ላይ የሚያብለጨልጩ ኮከቦች ….በተፈጠረው ነገር ክፉኛ ደንግጣለች …እራሷን እንደጥፋተኛ ስለቆጠረች በፊታችን ተሳቃ ነበር …ልክ እሷ ስታለቅስ እስካሁን ጥጋቸውን ይዘው እናቴ ጋር ሲያወሩ የነበሩት እማማ ቁንጥሬ በረዥሙ ተንፍሰው (የነገር ናት ትንፋሻቸው) ‹‹በ………ሉ ደህና ዋሉ ›› ብለው በሩን ከፈቱ ….ልክ የበሯን እጀታ እንደያዙ ይችን ቆንጆ ከእግር እስከራሷ ገርምመዋት ወጡ !አስተያየታቸው የሆነ መኪና በጨለማ ውስጥ ረዥም መብራቱን ያበራው አይነት ነበር የሚመስለው …እንኳን ሄዱ !አንድ አዛ ቀለለ …አሁን እንዲህ የተጣደፉት …ሰፈር ሂደው ከምድር እስከአራተኛ ፎቅ የቡና ሙቀጫ ነጋሪታቸውን ጎስመው …. ‹‹ጭራሽ የመንደሩ አልበቃ ብሏት ሆስፒታል ድረስ ሄደች ወይ ዘጠነኛው ሽ›› ብለው ለማውራት ነው ….ይሄ ጮማ የሆነ ወሬማ ‹በስምንተኛው ሽ› ብቻ አይደምቅም !! እስቲ ምን ታድርጋቸው ለራሷ ሆድ ብሷታል !
ከእህቶቸ ፍቅረኛ አንዱ እማማ ቁንጥሬ የለቀቁትን ወንበር ለዚች ቆንጆ ጠጋ አደረገላት ‹‹ ጎበዝ ! ይሄ የተባረከ ልጅ ነው …እህቴን ለትዳር ቢጠይቅ አሁኑ ነበር ከነትምህርት ማስረጃዋ አፋፍሸ የምሰጠው፡) ኧረ ይውሰድ …ሽጉጥ ከመምዘዝ ወንበር መስጠት ታላቅነት ነው ! ይችኛይቱ እህቴ ምርጫዋ ልክ ነው …ድሮም አስተዋይ ነበረች !የዛችኛይቱ እህቴ ጓደኛ ግን ሰፌድ የሚያክል ስልኩን እየጎረጎረ ጥግ ላይ ግድግዳ ተደግፎ ቁሟል …ይሄን ጊዜ የፌስ ቡክ ግድግዳው ላይ ‹‹ሃኒየ ወንድምሽ ላይ በተፈጠረው ነገር ከልቤ አዝኛለሁ እግዚአብሔር ምህረቱን ይላክለት ግፈኞችን የገቡበት ገብተን ለፍርድ እናቀርባቸዋልን ›› የሚል ፅሁፍ እየለጠፈ ይሆናል ! አንዱ ችኩል ጓደኛው ታዲያ ‹‹RIP›› ብሎ አስተያየት ሰጥቶም ይሆናል ! ገፊ ሁሉ !
ልጅቱ አልጋየ ጎን ተቀመጠችና አሁንም እንባ በሞሉ ትልልቅ አይኖቿ እያየችኝ …‹‹ይቅርታ አብርሽ ይሄ ሁሉ የኔ ጦስ ነው !›› ብላ እንባዋን በሶፍት ጠረገች ….አብር((ሽ )) ? እስቲ ዶክተሩን ጥሩልኝ …ጆሮየ ላይ አደጋው ያሳደረው ተፅእኖ አለ ወይስ ይች ((ሽ)) በትክክል ከልጅቱ አፍ ወጥታለች ??((ሽሽሽሽሽ)) እንደሬዲዮ እሽታው ጆሮየ ላይ ጮኸብኝ ….ማጥራት ሳይኖርብኝ አይቀርም …
‹‹ኧረ ምንም አይደል ያው ትንሽ ተበሳጭቶ ነው ›› አልኩ ….አለ አይደል ‹‹ቢበድሉንም ይቅር ባይ ነን›› አይነት ጨዋነት በቆንጆዋ ልብ ውስጥ በሊዝ ለማስቀመጥ ! አሁንኮ ‹‹ባሌ ልክ ነው›› ብትል ዘራፍ ነበር የምለው …የጨዋነት ካባ የለበሰች ስንት ትእቢት አለች!
‹‹ ምን ይበሳጫል ድሮም ውሻ ነው … እኔን ያሰቃየው ቁም ስቅሌን ያበላኝ አነሰውና ምንም የማያውቅ ትሁት ሰው ቀና ብሎ የማያይ ልጅ ጋር እንዲህ ያለ ጉድ …. ›› አለች…. ይህኛውን ስትናገር ለእኔ ይሁን ለእናቴ አልያም ለራሷ እግዜር ይወቅ ….እንደገና አለቀሰች …. ኤዲያ እንዲህ አልቅሳ የምትቀብር ቆንጆ ባለችበት አገር እንኳን ቆስሎ መትረፍ ቢሞትስ …ብየ ሳስብ እናቴ የልጅቱን ለቅሶ ተቀብላ የራሷን ስትመርቅበትና በነጠላዋ ጫፍ እንባዋን ስትጠርግ ‹‹ ኧረ ለናቴ ልኑር›› ብየ ሃሳቤን ቀየርኩ ….ለካስ ለቅሶ እና ለቅሶ ይለያያል !! ቆንጆዋ ብዙ ሰዓት ስታወራን ቆየች የበዛውን ሰዓት ከእናቴ ጋር ነበር ያወሩት ….አልፎ አልፎ አይኗን ጣል ታደርግብኛለች …ይሻለኛል፡) አይኗ እንደተሳለ የፋሲካ ቢለዋ ልቤን ሸርክት ያደረገው ይመስለኛል … ባልና ሚስት ባለቢለዋ ( ባል የጀመረውን የስለት ጥቃት ሚስት ዳር ለማድረስ በውብ አይኖች ስለት እንደማስቀጠል ተልእኮ ዓይነት …እንኳንም ተላከች)
ባል ባለቢላዋ ሚስት ባለጎራዴ
እዚች ሆስፒታል ውስጥ መክረምህ ነው ጓዴ ( እያልኩ እገጥማለሁ…የግጥም ተሰጥኦ እንዳለኝ የጠረጠርኩት አሁን ነው )
ድንገት እጀን ላንቀሳቅስ ስሞክር ብርድ ልብስ ያረፈበት የ ‹ግልኮስ ቲዩብ› ያዝ ስላደረገኝ እናቴ ‹‹ቆይ ላስለቅቅልህ››ብላ ከወንበሯ እንደመነሳት ስትል ….ልጅቱ ቅርብ ስለነበረች ከእናቴ ቀድማ ተነሳችና በእኔ ላይ ተንጠራርታ ብርድ ልብሱን አስለቀቀችው ….ተኝቸ ስላየኋት ነው መሰል አቤት መለሎነት ….በዚች ቅፅበት ሶስት ነገሮች ተከሰቱ ..አንደኛ…ጡቶቿ ከበላየ ሁነው እንደደመና ተንሳፈፉ ….ደግሞም በትንሹ የግራ ትከሻየን እና ደረቴን ነካ አደረጉኝ … ሲነኩኝ ጫፋቸው ሁሉ ሲወጋኝ ተሰምቶኛል !!
ሁለት…. ጠረኗ አውሎ ንፋስ እንዳስነሳው አቧራ አፍንጫየ ላይ ተሞጀረብኝ …ሃኪም ካዘዘልኝና ሲያገሳኝ አስቀያሚ ጠረኑ በአፍንጫ ከሚመጣው መድሃኒት ይልቅ ይሄ ጠረን አገግም ዘንድ በቀን አንድ ቢታዘዝልኝ ባንድ ጀምበር ሳልድን አልቀርም ብየ አጋነንኩት !!
ሶስት በሉማ…. ብርድ ልብሱን አንስታ እጀን በለስላሳ መዳፎቿ ያዘችና ወደግራ በኩል አስተካከለችው (ይችን እንኳን እንደምርቃት የጨመረቻት መሆን አለባት) ይሄን ያህል በጎራዴ አንገቴ አልተቆረጠ ….የምን በሽተኛን ማቅበጥ ነው እንኳን ፊት ሰጥታኝ …) እነዚህ ሶስት ነገሮች ከልጅቱ ቁንጅናና ካለሁበት ሁኔታ ጋር ተዳምረው ….አለ አይደል ‹‹በዚች ልጅ የታማሁት እውነት ይሆን እንዴ›› ብየ እራሴን እንድጠረጥር አደረገኝ !!
በመሃል ….ስንትና ስንት ብርቱካን እየተላጠ ተበልቶ …ለእኔም ቅቤው እንደጀልባ የሚንሳፈፍበት ሾርባ (ልጅቱ ያመጣችው) አንኮላ በሚያክል ቀንዳም ኩባያ ተሰጥቶኝ …‹‹አቤት ሙያ ›› እያልኩ ግማሽ አድርሸው….ደግሞም ‹‹መልኩን ይስጠኝ እንጅ ሙያ ከጎረቤት ›› የሚባለው ተረት ትዝ ብሎኝ ‹‹አሁንይችን ልጅ መልኩን ብቻ ሰጥቶ ቢተዋት ኑሮ ከየትኛው ጎረቤት ሙያ ትማር ነበር ….መቸስ ከእማማ ቁንጥሬ አይሞከርም ›› እያልኩ ….ሳስብ …..እናቴ ድንገት ልጅቱን …ምን ልትጠይቃት ፈልጋ እንደሆነ እንጃ እንዲህ አለቻት
‹‹ማን አልሽኝ ስምሽን እናትየ ›› ….ፓ! የኔ እናትኮ…. በአለም ላይ ያሉ ጋዜጠኞችን ሁሉ የምታስከነዳ ምርጧ ጠያቂ ናት … ይሄን ጥያቄ ማሰብ ከጀመርኩ ስንት ቀኔ? …ለዚህ አደጋ የዳረገኝስ ምን ሆነና ..ይሄው ማዙካ አፈረጠችዋ …የህዝብ አይንና ጆሮ ሆነቻ ! …. ልጅቱ በትህትና እንዲህ ስትል መለሰች ‹‹ልእልት›› !! ይሄው …ተረቱ ልክ ሲመጣ …ስምን ማን ያወጣዋል ??????? መለዓክ !! ይሄን ስም አሁን ማን ይሙት ገንፎ የበላ አራስ ጠያቂ ጎረቤት ሊያወጣ ይቻለዋል ????በፍፁም !! ….በቃ መለዓኩ ራሱ ነው በክንፉ ለክቶ በሌላኛው ክንፉ ቆርጦና አስተካክሎ በልኳ አምጥቶ እዚህ ውብ ስጋና ደም ላይ ልክክ ያደረገው …ልእልት …….
‹‹ልእልት ሆይ ! ለሽ አመት ብርቱካን ለሌላ ሽ አመት ሾርባ ይዘው ይጠይቁኝ !!››ሃሃሃ ! ል እ ል ት…. አፍ ላይ እንዴት ደስ የሚል ስም ነው ….የሆነ እንደፈንድሻ አፍ ሙልት አድርጎ ኮርሸም ሲያደርጉት ጥፍት የሚል አይነት ስም ….የማይጠገብ ስም ! ልእልት ….ታዲያ ይችን ልእልት በሽንኩርት ቢለዋ የሚፋለም ሙትቻ ንጉስ ላይ ማነው የጣላት …? ደሃና ገበያ ሳይገናኝ ይሞታል ማለትኮ ይሄ ነው !
ልእልት ተመልሳ እንደምትጠይቀኝ ….ነግራኝና እንደገና ለባሏ የብልግና ድርጊት ይቅርታ ጠይቃኝ …ወጣች…. ስትወጣ አይኔ ተከተላት … አንዳንዱን ሲፈጥረው ከኋላም ከፊትም ከግራም ከቀኝም ውብ ያደርገዋል እንደልእልት ! ፈዘዝኩ …የዘጋችው በር ላይ አይኔን ተክየ ቆይቸ መለስ ሳደርገው ማን ጋር ተገጣጠምኩ ? እናቴ ጋር !
‹‹አቡቹ እንዴት ነው አሁን ቀለል አለህ?›› አለችኝ !! አስተያየቷም ሆነ አነጋገሯ ‹‹ እውነትም ልጅቱ ጋር እንደሚባለው ተነካክተሃል እንዴ አንተ ልጅ›› የሚል ትዝብት ቢጤ ነበረበት !
ማ……እኔ ያንች ልጅ እዚች ልጅ ጋር ? ያውም እዚች ባለትዳር ልጅ ጋር ልነካካ ??????? በምን እድሌ !!
One Comment