አጤ ምኒልክ የመጀመሪያውን ስልክ አገልግሎት ላይ ካዋሉ በኋላ የተወሰኑ መኳንንት እና አጤ ምኒልክ ስራቸውን በስልክ አማካኝነት ማከናወን ችለው ነበር። ሆኖም ግን የስልክ ግንኙነቱ የሚቀላጠፈው በስልከኞች አማካኝነት ነበር። ብዙውን ጊዜ ስልከኞቹ ከስልኩ ቤት እየጠፉ ችግር ስለፈጠሩ አጤ ምኒልክ የሚከተለውን የስልከኞችን የተራ እና የስራ ደንብ ኣወጡ።
————
ለቴሌግራም ፀሃፊዎች እና ለስልክ ቀጣዮች፣
ለባላገሮች እና ለጭቃ ሹሞች፣
ለአበጋዞችም የተሠጠው ትእዛዝ ይህ ነው።
መጀመርያ
ቴሌግራም ፀሃፊዎች ጧት በ፲፪(12) ሰአት ወደ ስልክ ቤት ገብተው እስከ ስድስት ሰአት ይቀመጣሉ። ከስድስት ሰአት በሇላ ግን በተፈለጉ በአምስት ደቂቃ እንዲገኙ ሆነው ተጠባባቂያቸውን እየተዉ ይሄዳሉ። በተፈለጉ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ያልተገኙ እንደሆነ በወር ቀለባቸው ይቀጣሉ። ፲፭(15) ደቂቃ የጠፉ እንደሆነ አንድ ወር ይታሰራሉ። ፳(20) ደቂቃ የጠፉ እንደሆነ አራት ወር ይታሰራሉ። ሌሎችም የሚፈለጉበት ጉዳይ የተገኘ እንደሆነ ከስልክ ቤት አይለዩም። በተራ ይጠባበቃሉ።
የስልክ ስራ ከሆነ ቴሌግራም ፀሃፊዎች የስልክ ቀጣዮችን ያዟቸዋል። ስልክ ቀጣዮችም ጠዋት በአንድ ሰአት እስልክ ቤት ይገባሉ። ማታ በሁለት ሰአት ይወጣሉ። ሌሊትም በተራ ይጠብቃሉ። ተረኛውም፣ ሌሊት ቢሆን፣ ቀንም ቢሆን ከስልክ ቤት አይወጣም። ነገር ግን የሌሊት እና የቀን ተረኛ ለብቻው ነው። ቀን የጠበቀው ሌሊት፣ ሌሊት የጠበቀው ቀን አይጠብቅም። ስልክ በተደወለ በአራት ደቂቃ ተረኛው ከዚያ መኖሩን ያላሳወቀ እንደሆነ በወር ቀለቡ ይቀጣል። ፲፭ ደቂቃ የጠፋ እንደሆነ አንድ ወር ይታሰራል። ከዚያ ወዲያ ያለው ቅጣት ብርቱ ነው።
ስልክ ቀጣዮች የመንግስት ቃል ከተፈፀመ በሇላ በዋጋ የሚነጋገረውን ሰው እየጠሩ በጭቃ ሹሙና በቴሌግራም ፀሃፌው ፊት ያነጋግራሉ። ዋጋውንም እየተቀበሉ በቴሌግራም ፀሃፊዎች መዝገብ እየተፃፈ በጭቃ ሹም እጅ ይቀመጣል። ያለ ዋጋ ያነጋገረ፣ ከዋጋ ከፍሎ ያስቀረ ሰው ዋጋውን ከፍሎ፣ ያስቀረው ገንዘብ ተሰልቶ፣ በአንድ አራት ይከፍላል። ደግሞ ጭቃ ሹምና ቴሌግራም ፀሃፌው ሳያዩ ስልክ ቀጣዮች ዋጋ የተቀበሉ እንደሆነ በአንድ አራት ይከፍላሉ።
ከቴሌግራም ፀሃፊዎች ወይም ከስልክ ቀጣዮች፣ ከነሱም ተጠባባቂዎች ቢሆን የመንግስት ሚስጥር አውጥቶ የተገኘ ሰው ቅጣቱ ካገር የተለየ አዲስ ቅጣት ነው። የሌላውም ሰው ጉዳይ ቢሆን መንግስት የሚያነሳ ነገር የሆነ እንደሆነ ለስልኩ ሹም ፈጥኖ ያስታውቃል። ከስልኩ ሹም በቀረ ለሌላ ሰው የነገረ እንደሆነ ብርቱ ቅጣት ይቀጣል። የቴሌግራም ዋጋ በ፳(20) ቃል አንድ ብር፣ በአስር ቃል አላድ፣ በአምስት ቃል ሩብ ነው። ደግሞ በቴሌፎን የሚነጋገር ሰው ዋጋ በአስር ደቂቃ አንድ ብር፣ በአምስት ደቂቃ አላድ፣ በሁለት ደቂቃ ሩብ ነው።
ከስልክ ቀጣዮች እና ከቴሌግራም ፀሃፊዎች ጋር ከስልክ ቤት እየዋለ፣ የስልክን ዋጋ እየተቀበለ የሚያስቀምጥ ጭቃ ሹም የሻለቆች ይሰጣሉ። ጭቃ ሹሙም ማታ በ፲፪ ሰአት ከስልክ ቤት ይወጣል። ስልክ የጠቆረጠ እንደሆነ ስልክ ቀጣዮች ሳያሥቀጥሉ አይውሉም። የስፍራው ርቀት የታወቀ ሩቅ ካልሆነ በቀር በመሬታቸውም ስልክ የተተከለባቸው ባላገሮች ስልኩን በስርአት ይጠብቃሉ። እሳት እንዳይበላው እና ከብት እንዳይጥለው ስልኩ የጠቆረጠ፣ እንጨት የወደቀ እንደሆነ፣ ያን ጊዜውኑ ለጭቃ ሹሙ ያስታውቃሉ። ያላስታወቁ የሆን እንደሆነ ግን በቀኑ ልክ አስር አስር ብር መቀጫ ይሰጣሉ። እስከ ሁለት ጊዜ። በሶስተኛው ርስታቸውን ይነቀላሉ። የዚህም የመቀጫ ብር በቴሌግራም ፀሃፊ መዝገብ እየተፃፈ በጭቃ ሹሙ እጅ ይቀመጣል።
ጭቃ ሹሞች፣ ባላገሮች ስልክ ተቆርጧል ወይም እንጨቱን ወድቇል ብለው ሲነግሯቸው ስፍራው ቅርብ እንደሆነ እስከ አንድ ሰአት ለስልክ ቀጣዮች ያስታውቃሉ። የራቀ እንደሆነ እስከ ፲፪ ሰአት ያስታውቃሉ። ያላስታወቁ እንደሆነ ግን እንደ ስፍራው ርቀት በቀኑ ቁጥር ፳ ብር መቀጫ ይሰጣሉ። በሁለተኛው ንብረታቸውን ይወረሳሉ።
ሰው በተንኮል ስልክ የቆረጠ እንደሆነ፣ ይህን ሰው ባላገሩ ባፍርሳታ አውጥቶ ለጭቃ ሹሞች ይስጥ። ጭቃ ሹሞቹም ለሻለቆች ይሰጧቸዋል። በመንግስት ፍቃድ ይሰቀላል። የሻለቆች እና ጭቃሹሞች፣ ባላገሮች ለስልክ የቸገረውን ነገር ስልከኞቹ ሲነግሯቸው ፈጥነው የሚመቸውን ነገር ያደርጋሉ። ለማድረግ የማይመቸውን ፈጥነው ለመንግስት ሹም ያስታውቃሉ። ይህን ሰምተው ዝም ብለው የመንግስት ስራ የቀረ እንደሆነ በመጀመሪያ ፭፻ ብር፣ በሁለተኛው ሺህ ብር መቀጫ ይሰጣሉ። በሶስተኛው ሹማምንቶቹ ሹመታቸውን ይሻራሉ። ባላገሮቹም ንብረታቸውን ያጣሉ።
ሥልክ ቀጣዮች ስልክ በሚቀጥሉበት አገር የስልክ እንጨትና መሰላል ባላገሮች ያቀርቡላቸዋል። ቀጥለውም እስኪሄዱ ራትና ምሳ ጭቃሹሞች ይሰጣሉ። ስልክ ቀጣዮች ውሃ የሞላባቸው እንደሆነ፣ ከብትም ከመንገድ የጠፋባቸው እንደሆነ ወይም የሞተባቸው እንደሆነ ጭቃሹሞች ከብት ያውሷቸዋል። በዋናም ያሻግሯቸዋል።
ስልክ ቀጣዮች እና ቴሌግራም ፀሃፊዎች በተራቸው ቀን አይከሰሱም። ቅጣትም የተገኘባቸው እንደሆነ የስልክ አለቃው ሰምቶ ይቀጣሉ። ቀለባቸውንም ቴሌፎን ከተተከለበት ስፍራ ይቀበላሉ። ጌታ ከሌለውና ጠባቂ ከሌለው መሬት የተተከለውን ስልክ የሚጠብቁ ጭቃ ሹሞች ናቸው። ውድማ የሆነ እንደሆነ ግን የሻለቃው ያስጠብቃል።
ለስልክ መቀጠያ አራት በቅሎ ከነመሳሪያው የሻለቃ ይሰጣል። ቴሌፎን ከተተከለበት አጠገብ እንዳይከሱ እያበላ ያስቀምታል። እነዚህንም በቅሎዎች እንዳይከሱባቸው ተተንቅቀው ያበላሉ። በቅሎዎቹ የከሱባቸው እንደሆነ ባንድ በቅሎ ፪ ብር ይከፈላል። በእነዚህ በቅሎዎች የመንግስት ትእዛዝ የሚፈፅሙ ስልክ ቀጣዮች ትእዛዛቸውን አድርሰው ሲመለሱ በቅሎዎቹን እዛው ከሚበሉበት ቦታ እየመለሱ ያስረክባሉ። ከቤታቸውም አያውሉም። አያሳድሩም። ከመንግስት ትእዛዝ በቀር። እነዚህ በቅሎዎች ስልክ ቀጣዮች ለጉዳያቸው የተመላለሱባቸው እንደሆነ፣ በመጀመሪያ አስር ብር፣ በሁለተኛው ሃያ ብር ይከፍላሉ። በሶስተኛው ብርቱ ቅጣት ይቀጣሉ። በቅጣት የሚሰበሰበው ገንዝብ ብርም ቢሆን፣ በቅሎም ቢሆን፣ በቴሌግራም ፀሃፊዎች መዝገብ እየተፃፈ በጭቃ ሹሙ እጅ ይቀመጣል።
ግንቦት ፲፫(13) ቀን ፲፰፻፺፰(1898) ዓ/ ም አዲስ አበባ ተፃፈ።
The Picture is rather recent taken by Walter Mittelholzer in 1934
—————
ምንጭ:
አጤ ምኒልክ
በጳውሎስ ኞኞ
One Comment
yehgerenetarekmanebebeewedlew merexe sewnhe