አንድ ተረት ልነግራችሁ ነው በቅድሚያ ግን ጭብጤን ላስቀድም።
ላለፉት 13 ወራት እንደ ቀበሌ መታወቂያ በኪሴ ይዤ የማንከራትተው ፓስፖርቴ ከፍተኛ እንግልት ደርሶበታል። ከሀገር ሀገር ለመዟዟር ብቻ ያገለግል የነበረው ፓስፖርት፤ ኢትዮጵያም ውስጥ በተንጻራዊ ነጻነት ለመዘዋወር ብቸኛ አማራጬ ሆኖ ቆይቷል። ይህ ሁሉ የሆነው ቀበሌ ወይንም ወረዳ የሚሰጠው መታወቂያ ላይ፤ ብሔር መጥቀስ አሁንም ባለመቅረቱ ነው።
ሰሞኑን እንደሰማነው ከሆነ በኦሮሚያ ክልል ለመስጠት የተሰናዳው መታወቂያ ይህንን ብሔርን የመጥቀስ ችግር ከመቅረፍ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አካቶ መታተም መጀመሩ ከፍተኛ ለውጥ መሆኑን አምናለሁ። የክልሉ ፕሬዝዳት ኦቦ ለማ መገርሳም እያስቆጠሩ ካሉት መልካም ጅማሮዎች መሐል ይሔኛው በበጎ መልኩ የሚታይ ነው።
ዛሬ ሀሳብ ልሰጥበት የፈለግኩት ዋናው ርዕሴ ደግሞ፤ ይህ መታወቂያ በራሱ የኦሮሚያ [ክልል] አስተዳደር ብቻ የሚሰጠው በመሆኑ በሀገር ውስጥ በሁሉም አቅጣጫ ለመንቀሳቀስ በራሱ አሉታዊ ተጽዖኖ ይኖረው ይሆን ወይ? የሚለውን ጥያቄ መፈተሽ ነው።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አንድ ወጥ የሆነ ብሔራዊ መታወቂያ እንዲያገኝ የሚያስችል አዲስ ህግ በፌደራል መንግስት በቅርቡ መውጣቱን እናስታውሳለን። ይህ ህግ በተለያዩ ምክንያቶች እስከ አሁን ተግባራዊ አልሆነም። በዚህም ሳቢያ ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ብሔር ነጠል የሆኑ ጥቃቶችና ስደቶች እንዲከሰቱ ምክንያት የሆነው በየዜጋው እጅ ያለው መታወቂያ ላይ የተጻፈው የብሔር ማንነት እንደሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ አንጻር በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚኖሩ የየትኛውም ብሔረሰብ ተወላጆች ብሔር የማይጠቅስ መታወቂያ መያዛቸው በክልሉ ውስጥ በስጋት እንዳይኖሩ የሚያደርግ አወንታዊ ጎን አለው።
ከዚህ በተቃራኒ ግን ይህንን የክልሉን መታወቂያ የያዙ ነዋሪዎች በጥቅል ግምት ድምዳሜ ላይ ለሚመሰረት የሌላ ክልል ነዋሪ ተመሳሳይ ያለመገናዘብ ችግር ለመፍጠር የሚያስችል ቀዳዳ እንዳለው ይሰማኛል። ለዚህ ሁሉ ደግሞ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ተግባራዊነቱ የዘገየውን አንድ ወጥ አገር አቀፍ ብሔራዊ መታወቂያ የመስጠት ህግ በፍጥነት ተግናራዊ ማድረግ ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ብሔር ተኮር ፌደራሊዝም ስርዓት ለሚከተሉ ሀገሮች፤ እንኳን የብሔር ስም መጠቀስ ይቅርና የአንድ ክልልን ነዋሪነት ነጥሎ የሚያሳይ መታወቂያ መያዝ በራሱ የመንቀሳቀስ ስጋት የመጣል አቅሙ ጥያቄ ምልክት የሚፈጥር በመሆኑ ልክ እንደ ፓስፖርት ያለ ዜግነት ላይ ብቸኛ ትኩረቱን ያደረገ መታወቂያ በፌደራል መንግስት ብቻ ሊሰጥ እንደሚገባው ይሰማኛል።
በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ከሚያነሷቸው አንኳር ነጥቦች መሀል የብሔራቸው ማንነት እንዲጠቀስ ጽኑ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች መብት ከመጠበቅ አንጻር ምን አልባት ይህ ብሔራዊ መታወቂያ የፍላጎታቸውን ያህል ላይሆን ይችላል። ለዚህ ደግሞ በውዴታ ላይ ብቻ የተመሰረተ ተጨማሪ መታወቂያ በማንኛውም ክልል ውስጥ ሊሰጥ ይችል ይሆናል።
ይህ ደግሞ ለተለየ አድልዖ የሚከፍተውን አሉታዊ በር ግምት ውስጥ በመክተት ከነአካቴው ቢቀር ይሻላል ወደሚል ድምዳሜ እንደሚያመጣ ግምት ውስጥ ሊከተት ይገባል።
ከላይ የጠቀስኳቸው ሀሳቦች በሙሉ ከ13 ወራት በፊት ከምናወራበት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የማጎልበት ርዕስ በእጅጉ ራቅ ብለን፤ የብሔር ማንነት መጠቀስ በነጻነት የመንቀሳቀስ ስጋት እየሆነ በመምጣቱ፤ ይህ ብሔራዊ መታወቂያ የመስጠት ህግ ወደ ተግባር እንዲለወጥ ከፍተኛ ግፊት መፍጠር እንደሚገባን ይሰማኛል።
በአንድ ተረት ልሰናበት
ሰውየው ዘመድ ጥየቃ ቀየውን ለቆ በእግሩ መጓዝ ይጀምራል። ምሽትም ሲሆን አንድ የገጠር መንደር ይደርሳል። ቀን እርሻ ውሎ ወደ ቤቱ የሚያዘግም ገበሬ ያገኛል። ገበሬውም መንገደኛ መሆኑን ብቻ በማየት እኔ ቤት ካላደርክ ብሎ ይዞት ይሔዳል። ቤቱም እንደገባ እግሩን አጣጥቦ መኝታውን ለቆለት ያስተኛዋል። በማግስቱም ስንቁን ጨምሮ ቋጥሮ ይሸኘዋል።
መንገደኛውም ጉዞውን ቀጥሎ አመሻሽ ላይ ሌላ መንደር ይደርሳል። እንደ መጀመሪያውም ቀን ሌላ ገበሬ ያገኛል።
“ጌታዬ እንደምን አሉ የእግዜር መንገደኛ ነኝ። እባክዎ ያሳድሩኝ” ሲል ይጠይቃል። ገበሬውም
“ቤት የእግዚአብሔር ነው ለመሆኑ ወደየት እየሔዱ ነው?” ሲል ይጠይቀዋል። “ዘመድ ጥየቃ ሩቅ ሐገር እየሔድኩ ነው” ይለዋል። ገበሬውም ወደ ቤቱ ወስዶ አስተናግዶ ያሳድረዋል።
በሚቀጥለውም ቀን ጉዞውን ይቀጥላል። ምሽትም ሲሆን አንድ መንደር ይደርስና ይመሽበታል። ወደ አንድ ገበሬ ቤት ይሔድና አንኳኩቶ እንዲያሳድሩት ይጠይቃል። ገበሬውም ከበሩ እንዳቆመው ማንነቱን ይጠይቀዋል። ሰውየውም ማንነቱን ይነግረዋል።
“የአባትህ ስም ማነው?… ከየት ሀገር ነው የመጣኸው?… አሁን ወደ የት ነው የምትሔደው?… ማን የሚባል ሰው ለማግኘት ነው የምትሔደው?… ምን ልታደርግ ነው የምትሔደው?…” እያለ በጥያቄ ያጣድፈው ጀመር። መንገደኛውም ሁሉንም ጥያቄ እየመለሰ ወደ ቤቱ ለመግባት በጉጉት ይጠብቀው ጀመር። ገበሬውም ቆይ ሚስቴን ላማክራት ብሎ በሩን ዘግቶበው ወደ ውስጥ ይገባል። ጥቂት ከቆየ በኋላ በሩን ከፍቶ አስገብቶ ያሳድረዋል።
በማግስቱ ጉዞውን ቀጥሎ ሌላ ሀገር ይደርሳል። ከርቀት ወዳያት ቤት በመቅረብ ላይ ሳለ አንድ ታዳጊ ህጻን መንገደኛውን አይቶ ሩጦ ወደ ቤቱ ይገባል። አባቱና እናቱም ፈጥነው የቤታቸውን በር እና መስኮት እየተጠዳደፉ መዘጋጋት ይጀምራሉ። ወደ ቤታቸው የሚያስገባውንም የግቢ ፍርግርግ አጥር በችኮላ ይከረቻችሙታል። መንገደኛውም ይህንን ካየ በኋላ አጥራቸው ጋ ደርሶ ይመለሳል።
አሳዳሪ ፍለጋ ሲንከራተት ለአይን ያዝ ያደረገው ሰማይ ጨለማ ወረሰው። በዚህ ግዜ አንድ ዛፍ ፈልጎ ከስሩ አንጥፎ ተኛ። ሌሊት ላይ አስፈሪ የሆነ የጅብ ድምጽ ተሰማው። በፍርሀት ራደ። የጅቡ ድምጽ እየቀረበ መጣ። መንገደኛው ድምፁን ለመደው። በኋላም እንቅልፍ ወሰደው።
አንድ ክፉ ነገርም ከእንቅልፉ ቀሰቀሰው። ጅቡ የግራ እግሩን ታፋ ቦጭቆት ሮጠ። ይህን ግዜ ታዲያ መንገደኛው ህመሙን ችሎ እንዲህ አለው።
“በዚህ ጉዞ ከቀጠልኩ የሰው ጅብ ቀርጥፎ ስለሚበላኝ ታፋዬ ምን አላት?” አለ ይባላል።