በድንገት ከኋላዬ መጥተህ አትንካኝ ብዬህ ነበር፡፡
ያጠብኳቸውን ብርጭቆዎች አንድ በአንድ እያደረቅኩ ከጀርባዬ መጥተህ ስትጎነትለኝ ጩኸቴን ለቀቅኩት፡፡
በድንጋጤ የወረወርኩት ብርጭቆ ወለሉ ላይ አርፎ ሲበተን አንዱ ስባሪ እግሬ ላይ ተሰካ፡፡ ደሜ ወደ እግሬ ጣቶች ተንዠቀዠቀ፡፡
በድንጋጤ ደርቄ ቀረሁ፡፡
ሣቅክ፡፡
እኔ ግን አልሣቅኩም፡፡
እሱም እንዲህ ያደርገኝ ነበር ብዬ ነግሬህ ነበር፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ሲፈጠር እንኳን በእጄ የያዝኩት ዕቃ፣ ሽንቴ ያመልጠኛል፤ ሰውነቴን ማዘዝ ይሳነኛል ብዬህ ነበር፡፡
ሳትነግረኝ ዕቃዬን አትንካ ብዬ ነግሬህ ነበር፡፡
ቦርሣዬን ስትበረብር አገኘሁህ፡፡
‹‹የእኔ ኢርፎን ስለተበላሸ ያንቺን እየፈለግኩ ነበር›› አልከኝ ቀለል አድርገህ፡፡
ግን ዳዬሪዬን አግኝተህ አንዱን ገጽ ጮክ ብለህ እያነበብክ ነበር፡፡
መጀመሪያ ደነዘዝኩ፤ ከዚያ ቱግ አልኩ፡፡
‹‹አንቺ ደግሞ ለትንሽ ለትልቁ ማካበድ ትወጃለሽ›› ብለህ ተሳለቅክብኝ፡፡
የምለውን ነገር ማንም በማያምነኝ በዚያ ጊዜ፣ ብቸኛ ምስጢረኛዬ፣ ታማኝ ባልነጀራዬ ዳየሪዬ ነበር ብዬ ነግሬህ ነበር፡፡
እናቴ ከመሳቢያ አውጥታ አንብባብኝ ተገርፌያለሁ ብዬ ነገሬህ ነበር፡፡
ስለከሲታነቴ እንዳታነሣብኝ ነገሬህ ነበር፡፡ ዳሌና ጡት እንደሌለኝ፣ ወንድ እንደምመስል በቀልድም ቢሆን እንዳትነግረኝ ብዬህ ነበር፡፡
‹‹እኔ እኮ… ትበያለሽ ትበያለሽ… ግን ምንም አትጨምሪም… የት እየከተትሽው ነው?…›› አልከኝ፡፡
‹‹ስለዚህ ጉዳይ ማውራት አልፈልግም›› አልኩህ ደጋግሜ፡፡
ያን ጊዜ ሴት መስዬ ላለመታየት፣ ጎላ ብዬ ዐይን ላለመግባት የዘየድኩት መላ ነው ብዬ አውርቼህ ነበር፡፡
ትምህርት ቤት ቆዳ ቅብ ይሉኝ እንደነበር፣ ልብሴ እላዬ ላይ እየተንዠዋዠወ ስሄድ ደኅንነት ይሰማኝ እንደነበር ነግሬህ ነበር፡፡
እንቅልፍ ሳይወስደኝ መብራቱን አታጥፋ ብዬ ስንት ጊዜ ለምኜህ ነበር፡፡
‹‹ሕፃን ነሽ እንዴ?›› ብለህ ተሳለቅክብኝ፡፡
ያን ጊዜ እንቅልፌ ቢመጣ እንኳን አንድ ዐይኔን ከፍቼ እንደምተኛ፣ የእንጀራ አባቴን ኮቴ ቀድሜ ለመስማት ጆሮዎቼን ቀስሬ ትራሴን ደገፍ እንደምል፣ መብራት የጠፋ እንደሆነ በፍርሃት እንደምርድ ነግሬህ ነበር፡፡
ደንታ አልነበረህም፡፡
እኔ ደግሞ ካልጠፋ እንቅልፍ አይወስደኝም ብለህ ድርግም አደረግከውና በደቂቃዎች ውስጥ ማንኮራፋት ጀመርክ፡፡
መቼም ቢሆን ውሸታም እንዳትለኝ ብዬ ነግሬህ ነበር፡፡ ብንጣላ እንኳን፣ ባናድድህ እንኳን ያሻህን ስም ስጠኝ ውሸታም ግን አትበለኝ ብዬህ ነበር፡፡
አንዱን ቀን ሳናድድህ ውሸታም አልከኝ፡፡
ፊቴ ሲለዋወጥ
‹‹አንቺ በቀልድም ቢሆን ውሸታም አትበሉኝ ነው እንዴ የምትይው… ብዙ ችግር አለብሽ›› አልከኝ፡፡
‹‹አዎ ችግር አለብኝ›› ብዬ መለስኩልህ፡፡
‹‹የእንጀራ አባቴ ከዐሥራ አንድ ዓመቴ ጀምሮ ያደረሰብኝን በደል ስነግራት የገዛ እናቴ፣ ውሸታም ስላለችኝ ውሸታም መባልን ፈጽሞ ልቀበለው አልችልም›› አልኩህ፡፡
ዐይኖችህን በመሳለቸት ሰቅለህ ‹‹አቦ ልጅ ሆነሽ የነበረ ነገር… አሁን ትልቅ አይደለሽ እንዴ… እርሺው እንጂ›› አልከኝ፡፡
እርሺው፡፡
በምስጢር የነገርኩህን ታሪኬን፣ የልጅነት ጠባሳዎቼን፣ ያልዳኑ ቁስሎቼን በዐደባባይ አትናገር ብዬህ ነበር፡፡
አንዱን ቀን ጓደኞችህን ሰብስበህ ‹‹ሉላ እኮ እስካሁን ድረስ ረጅም የወንድ ጥላ ስታይ ትበረግጋለች… አይገርማችሁም!›› ብለህ ሥቀህ አሣቅክብኝ፡፡
አስገኘኸኝ!
የእንጀራ አባቴ ሌሊት ሌሊት የኮቴውን ዳና አለስልሶ ወደ መኝታ ክፍሌ ሲመጣ መጀመሪያ የማየው ረጅም ጥላውን ነው ብዬ ነግሬህ ነበር፡፡ ጥላው፣ ትንፋሹና እጆቹ የስቃዬ አስታዋሾች ነበሩ፡፡
እንዲህ ብዬህም ባልዳነ ቁስሌ እንጨት ሰደድክብኝ፡፡
ያንን ዕለት ሽንት ቤት ገብቼ ለሰዓታት አነባሁ፡፡
ቤታችን የሚያድር እንግዳ የሚመጣ ከሆነ ቀድመህ ንገረኝ ብዬህ ነበር፡፡
ሳትነግረኝና ሳታማክረኝ አጎትና የአጎትህን ልጅ ከባሕር ዳር መጥተው እኛ ጋር እንዲከርሙ ጋበዝካቸው፡፡
ሊመጡ ነው የለ፡፡ ቢመጡ ምን ይመስልሻል? የለ፡፡
የእንግዳ መኝታ ቤት እንዲያርፉ አደረግክ፡፡
አንዱን ሌሊት አጎትህ በውድቅት ለሽንት ተነሥቶ ወደ መታጠቢያ ክፍል ሲመጣ፣ እኔ ውሃ ልጠጣ ወደ ኪችን ስሄድ ኮሪደር ላይ ተገናኘን፡፡ እሪ ብዬ ጮኽኩ፡፡
ዘመዶችህን ስላስደነገጥኩብህ ‹ቀውስ ነሽ›› ብለህ ተቆጣኸኝ፡፡
ነገሩ ተረጋግቶ ወደ ዐልጋችን ስንመለስ ልታቅፈኝ ዳዳህ፡፡
ሸሸሁህ፡፡
ምነው አልከኝ፡፡
መልስ አልሰጠሁህም፡፡
በረዶ ሆንሽብኝ እኮ አልከኝ፡፡
ዝምታን መርጬ ጭለማው ላይ እንዳፈጠጥኩ ነጋ፡፡
ሲነጋ ሻንጣዬን በልብስና ጫማዎቼ ሞልቼ ሳላለቅስና ድምጽ ሳላሰማ ጥዬህ ሄድኩ፡፡
በዐሥራ አምስት ቀኑ ደወልክልኛና፣ ‹‹ከገዛ ቤትሽ እንደ ሌባ ሹክክ ብሎ ከመውጣት ምናለ ቅር የሚያሰኝሽን ነገር ቀድመሽ ብትነግሪኝ ኖሮ?›› አልከኝ፡፡
‹‹ነገርኩህ እኮ…! ስንት ጊዜ ነግሬህ ነበር›› ብዬ መለስኩልህ፡፡
የምታወራውን ሳትጨርስ ስልኩን ዘጋሁት፡፡