አገራችን ላይ ትልቁ ችግር የሚመስለኝ ….ታላላቆች በሁሉም ነገር ትልቅ እንደሆኑ አድርጎ ማሰብና ‹ታናናሾች › በሁሉም ነገር ትንሽ እንደሆኑ አድርጎ ማናናቅ ነው …ለምሳሌ ሰፈራችን ውስጥ ያለን ታዋቂ አርቲስት …ህግም ፣ፍልስፍናም፣ መሃንዲስነትም ፣ የተበላሸ ቧንቧ ጥገናም ፣ ፖለቲካም ፣ስፖርትም ከሱ በላይ አዋቂ እንደሌለ አድርጎ መሃበረሰቡ ያስበዋል …ችግሩ ማህበረሰቡ ይሄን ማሰቡ አይደለም አርቲስቱም አሚን ብሎ መቀበሉ እንጅ !
በበርካታ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ላይ ለምሳሌ … የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጆች …ከሙያቸው ውጭ የስነልቦና ባለሙያዎች ሁነው ቁጭ ይላሉ …. እንደኔ እንደኔ በተለይ ውስብስቡን የሰው ልጅ ባህሪ ለባለሙያዎቹ መተው ተገቢ ይመስለኛል …ይሄ ብቻም ሳይሆን ሙያን ለባለሙያው መተው ጤናማ ነው …በፊልሞቻችን ብትሄዱ …በፖለቲካው ብትመለከቱ ሰዎች በሆነ ነገር ታዋቂ ከሆኑ የህዝብ አይን ካወቃቸው ስለሁሉም ነገር ያውቃሉ ተብሎ ይታመናል(በብዙሃኑ) በተቃራኒው የተማረ የመተቸትም ይሁን ይህን ነገር የማስተካከል አቅም አለው የምትሉት ማህበረሰብ ሰዎቹ የማያውቁትን እናውቃለን ሲሉ ብቻ ሳይሆን የሚያውቁትም በትክክል ሲናገሩ በደፈናው ማጥላላትና ማናናቅ ልምድ ስላደረገ ሌላው ማህበረሰብ ትክክለኛውንም ተቃውሞ ‹‹ምቀኝነት›› አድርጎ ይመለከተዋል!!
አሁንማ አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ ባሰብንኮ …ልክፍት ነው ከምር ልክፍት ነው …. አንዳንዱ ኮስተር ብሎ ህመማችሁን ስታወሩ መድሃኒት ሁሉ ያዝላችኋል … ምናልባትም ሙያው የታክሲ ሹፍርና ይሆናል !አንድ ቢሮ ስትገቡ ከጥበቃው ጀምሮ እስከጸሃፊዋ የማይመለከታቸውን ጉዳይ የሚመለከተውን ባለሙያ ወክለን ካላስረዳን ሲሉ ታገኟቸዋላችሁ …ወደሚመለከተው ማለት ማንን ገደለ! ድሮ በሰገሌ ፍቅረኛዋ የካዳት ሴት ስለዓለም ወንዶች ሁሉ ባህሪ ‹ከእኔ በላይ አዋቂ› በሚል …ሰፊ ልብ የሚያንሸራትት ትንታኔ ትሰጣችኋለች ወንዱም ይብሳል ‹‹ውይ ሴቶች›› ብሎ ከጀመረ ማቆሚያ የለውም … ተሞክሮን ማካፈል ጥሩ ነገር ቢሆንም እኛን የገጠመን ጥሩም ይሁን መጥፎ ነገር ግን ‹‹ያለቀለት እውቀት ነው›› ማለት አይደለም… በዛ በዚህ ብሎ ያለፈለት አንድ ሰው ሚዲያ ላይ ሲወጣ ‹‹ትውልዱ ስራ አይወድም እንጅ እኔ …ሊስትሮ ጠርጌ ነው እዚህ የደረስኩት ›› የሚል የጭቃ ጅራፉን ያጮኸዋል ….ቢያንስ ትውልዱ ጫማ ማስጠረጉን ረስቶት!
ሌላው በባለፈው ግምገማ እድገት ስላገኘ ‹‹የገዥውን ፓርቲ መለዓክነት ››ካልሰበኳችሁ ከኔ በላይ የፖለቲካ ተንታኝ ሲል ….በተቃራኒው የደበቀው ግብር ስለተደረሰበት መንግስት ‹‹ቀንድ ያለው ሰይጣን ነው›› የሚል ትንታኔውን የነጠረ የፖለቲካ ሃሳብ መሆኑን ለማሳመን የሚፍገመገም ‹ብሶት ወለደው የፖለቲካ ተንታኝ›› ይሆናል …መንግስትን ከግል ጥቅማችንም ጉዳታችንም ሳንነሳ በሃቂቃው ጉድለቱንም ስኬቱንም ማየት ሙያና የሰከነ አእምሮ ይጠይቃል!!የማናውቀውን ከሚያውቁት እንጠይቅ …እሱም ታላቅ ጥበብ ነው …እዚህ ላይ ሁለት የምወዳቸውን ታሪኮች ልንገራችሁና ላምልጥ (ስራ አለኝ ሂሂ)
**** **** *****
እና….ታዋቂው አለም አቀፍ ወንጌል ሰባኪ ቢሊግርሃም ወደአንዲት አገር ኮንፈረንስ ተዘጋጅቶ ለማስተማር ይሄዳሉ …..እንግዲህ እሳቸው ያሉበት መድረክ በመቶ ሽዎች የሚታደሙመበት መሆኑ ግልፅ ነው …ከተማው በሙሉ ይህ ታላቅ የወንጌል ሰው ወደዚያች ከተማ መግባታቸውን ነበር የሚያወራው …ታዲያ ዝግጅቱ ከመጀመሩ አንድ ቀን በፊት ቢሊግርሃም ከተማውን በእግራቸው ዞር ዞር ብለው ማየት ይፈልጋሉ እግረ ምንገዳቸውንም በፖስታ ቤት በኩል መልእክት ለመላክ ያስባሉ ….እናም መንገድ እንደጀመሩ የፖስታ ቤቱ አድራሻ ስለጠፋባቸው …መንገድ ላይ ሲጫዎት ያገኙትን ህፃን ልጅ ….
‹‹ማሙሽየ ፖስታ ቤቱ የቱ ጋ ነው›› ብለው ጠየቁት
‹‹በዛ ጋ ታጥፈው ያገኙታል ›› ብሎ ወደጨዋታው ተመለሰ ….ታዲያ ይህን ቅን ልጅ ነገ የሚሰብኩበት ኮንፈረንስ ላይ የክብር እንግዳ ሊያደርጉት ስለፈለጉ ‹‹ማሙሽ ነገ ትልቅ ኮንፈረንስ አለ እዛ የምሰብከው እኔ ነኝ …የዘላለም ህይዎት የምታገኝበትን መንገድን አሳይሃለሁ እና እንድትመጣ ጋብዠሃለሁ›› ይሉታል ! ህፃኑ በመገረም ቢሊግርሃምን እየተመለከታቸው እንዲህ አለ
‹‹ እርስዎ የሰፈራችንን ፖስታ ቤት መንገድ እንኳን የማያውቁ ሰውየ የዘላለም ህይዎትን መንገድ እንዴት ሊያሳዩኝ ይችላሉ››፡)
*** **** *****
ይችኛዋ በኢስላም አስተምሮት የምትታወቅ ምሳሌ ነች … አንድ ቀን አሊና ዱቄት ሻጭ ጓደኛው ሲጨዋወቱ አሊ ለጓደኛው ‹‹በዚች አለም ቁርዓን ላይ ያልተፃፈ ምንም ነገር የለም ›› ይለዋል …ጓደኛው አላመነውም እናም ማረጋገጥ ፈለገ …
‹‹ጥሩ… ቁርዓን ላይ ሁሉም ነገር ተፅፏል ካልክ እሽ አንድ ኩንታል ዱቄት ስንት ባለብር ዳቦ ይወጠዋል›› ብሎ አሊን ጠየቀ ….
አሊ ታዲያ ‹‹ይሄማ ቀላል ነው ›› አለና ተነስቶ ወደሰፈሩ ታዋቂ ዳቦ ጋጋሪ ዘንድ ሄደ ..እናም አንድ ኩንታል ዱቄት ስንት ዳቦ ሊወጣው እንደሚችል ጠይቆ መጣና ትክክለኛውን መልስ ለዱቄት ሻጭ ጓደኛው ነገረው ….ጓደኛው ግን ሳቀ ….‹‹ይሄማ ተገቢ አይደለም የጠየኩህን ጥያቄ ከቁርዓን ላይ ነበር ልታሳየኝ የሚገባው ቢለው …..አሊ ፈጠን ብሎ ‹‹ነውና ያየሁት›› አለው
‹‹እንዴት ማለት …ከመንደሩ ዳቦ ጋጋሪ አይደለም ጠይቀህ የመጠሃው ?››
‹‹ልክ ነህ …ወዳጀ ! መልሱን ከባለሙያው ነው የጠየኩት …ምክንያቱም ቁርዓን እንዲህ ይላል …‹‹የማታውቁትን ከሙያው ባለቤቶች ጠይቁ!! ››
እና ምን ልል ፈልጌ ነው …አላውቅም ነውር የሆነበት አገር ገንብተን በማያውቁት የሚዘባርቁ ይዞሟቾችን እንዳናፈራ …መመዘኛ መስፈርታችንም እንደህፃኑ ልጅ በህፃን እሳቤ ልክ አይሁን ! የቄሳርን ለቄሳር !!
3 Comments
This was a very interesting article. Thanks once more I will visit again.
Clean website. Do you ever accept guest posts? I am maintaining a site on my latest hobby water filters and wanting to trade some content with good sites. I looked around your blog and you’ve got some good content and I was thinking our readers would both find value. Thanks!
I just updated my site with a new list. I hope you all are having a great week.
[Link deleted]