አክስቴ አክሊል በመላው ቤተሰብና ዘመድ አዝማድ ዘንድ የምትታወቅበትና የምትፈራበት አንድ ባህርይ አላት፤ ሽሙጧ!
የአክስቴ አክሊል ማሽሟጠጥ ግን ዝም ብሎ ማሽሟጠጥ ብቻ አይደለም፡፡ ከባድ ጥበብ አለው፡፡
ቂቤ የምትቀባ መስላ በኩርኩም ታነድሻለቸች፤ ያሞገሰች መስላ ትሞልጭሃለች፡፡
በአንድ ሰበብ ዘመድ በተሰበሰበ ቁጥር ከእነ ረጅም ቁመቷ የድግስ ቦርሳዋን ብብቷ ሥር ወሽቃና ልክ እንደ ሰላም አምባሳደር ቀና ብላ ስትገባ ሰው ሁሉ ይሸበራል፤ እሷ ያለችበት ሰላም የሚባል ነገር የለማ!
ዛሬም ያው የአሽሙር ባህሪዋን እንደ ቦርሳ አነግባ መጥታለች፡፡
የተሰበሰብነው የሌላዋ አክስቴን (እና የአክሊልን የታናሽ ታናሽ እህት) አዲስ ቤት ለመመረቅ በተዘጋጀ ግብዣ ነው፡፡
ገና ከመግባቷ እንደተለመደው የለበጣ ፈገግታዋን ፊቷ ላይ ስላ የተሰበሰብነውን ሁሉ አንድ በአንድ ሰላም ስትልና ስታወራ ሰቀቀኑ ተጀመረ፡፡
ዛሬ ደግሞ በዚያ የአግቦ ንግግሯ ምን ትለኝ ይሆን?
ምኔን አሽሟጣ ምኔን ታቆስለው ይሆን ? በሚል፡፡
ገባች፡፡
የመጀመሪያዋ ዒላማዋ ጥሩዬ ነበረች፡፡ ጥሩዬ ጅሏ፡፡
ሌላው ሰው የሚደርስበትን ጥቃት ባያስቀርም ለማዘግየት በየቦታው ሲወሸቅ እሷ ግን ዋናው በር ላይ ቆማ ጠበቀቻት፡፡
‹‹ጥሩዬ!›› ብላ ጮኻ ካቀፈቻት በኋላ፤
‹‹ጭራሽ አባበጥሽ እኮ ልጄ!..በስመአብ! ብቻ ካንቺ ደስ የሚለኝ ግን ኮንፊደንስሽ! ይሄኔ ሌላ ሰው ቢሆን ይሄን ውፍረት ይዞ በመሳቀቅ ከቤቱ አይወጣም፡፡ አንቺ ግን ሁሉን ሰው የታባቱ ብለሽ በዚህ ጠባብ ቀሚስ ጠቅጥቀሽው መጣሽ…ጎበዝ …! እኔ በበኩሌ ሴት ልጅ እንዲህ በራሷ ስትተማመን ደስ ይለኛል!›› አለቻት፡፡
ጥሩዬ አይኗ በፍጥነት በእምባ እየተሞላ ጎላ ብሎ የወጣ ቦርጭዋን በእጆቿ መከለል ስትጀምር አክስቴ አክሊል ወደሚቀጥለው ተጠቂ ደርሳ ነበር፡፡
የእኔው እህት መክሊት፡፡
መክሊት ሜክ አፕ ደመኛዋ ነው፡፡ አይኗን እንኳን አትኳልም፡፡
‹‹መክሊትዬ! ዛሬም እግዜር እንደፈጠረሽ መጣሽልኝ የኔ ደፋር…የዛሬ ሴቶች የሰፈር ሱቅ እንኳን ሲሄዱ ካለ ፋውንዴሽን ንቅንቅ አይሉም…. አንቺ ግን ባዶሽን ዓለምን ትዞሪያለሽ….አንበሳ…! አንዳንድ ሰው ድግስና ሰርግ ላይ እንዲህ ሆኖ መምጣት ጋባዥን መናቅ ነው ሊልሽ ይችላል ግን አትስሚያቸው….ፊትሽን ካልወደዱት መጀመሪያውኑ ለምን ይጠሩሻል..?! ለማንኛውም ቻፒስቲክ ከፈለግሽ ቦርሳዬ ውስጥ አለ…ከንፈርሽ ውሃ የጠማው መሬት መስሎ የለ እንዴ…››
ከዚያ ወደ ናኒ ዞረች፡፡ ናኒ የወንድሜ ሚስት ናት፡፡
ሁለተኛ ልጃቸውን ከወለደች በኋላ ጂም በመመላለስና ምግቧን በመመጠን አስራ ሶስት ኪሎ ቀነሳ ሽንቅጥቅጥ ብላለች፡፡
‹‹ናኒዬ! በስመአብ…! .በጣም ቀንሰሻል…መልክሽ ሁሉ ጠፋብኝ እኮ አንቺ….ጎበዝ ነሽ መቼም ….እኔ ግን እውነቱን ተናገሪ ካልሽኝ ሞላ ስትዩ ይሻለኝ ነበር…አሁን በጣም ከሳሽና ገመምተኛ መሰልሽ…አንዳንድ ሰው ክሳት አያምርበትም ማለት ነው? ልክ እንዳንቺ ባንዴ ሲከሳ ያረጃል …ይገርማል..ቢሆንም በስንት ጥረት እንዲህ መቀነስሽ ለሌሎች ሴቶች ብርታት ይሆናል…ጎበዝ››
ከአክስቴ አክሊል እሾሃማ ምላስ የሚያመልጥ አንድ ሰው የለም፡፡
ደጋሽ እንኳን ቢሆን፡፡
ለዚህ ነው የዛሬዎቹን ደጋሾች ታናሽ እህቷ አስራት እና ባለቤቷ ፍቅሬንም ያላስተረፈቻቸው፡፡
ሰዉን ለማስተናገድ አብረው ወዲህ ወዲያ እያሉ አስቁማቸው፣
‹‹አስራትዬና ፍቅሬ፤ በጣም ቆንጆ ቤት ነው የሰራችሁት…በዚህ ኑሮ ቤት መስራት መቼስ ጉብዝናችሁ..በእርግጥ ትንሽ ጠበበብ ያለ ነው…ካረጋችሁ አይቀር ለቀቅ ቢል ጥሩ ነበር ግን የምታባርሩት ልጅ የለ! ለእናንተ እንኳን ይበቃል…ይሁን! እንኳን ደስ ያላችሁ›› አለቻቸው፡፡
እኔ ሁሉን እያየሁ አንዱ ጥግ ደበቅ ብዬ ነበር፡፡
ፊት ለፊት ስታጣኝ ብትምረኝ ብዬ፡፡
ትንሽዬ ደብተሬ ላይ ምናምን እየጻፍኩ፡፡
‹‹የኔ ደራሲ! አሁንም ይሄን መሞነጫጨርሽን አልተውሽም? ….ጥሩ ነው…በወደዱት ነገር ላይ መበርታት…እንጀራ ባያበላም ለነፍስ ደስታ…ብቻ እንደው ይሄ ጨዋታና ፌዙን ትተሽ እንደ እነ በዓሉ ግርማ…እንደ ሐዲስ ዓለማየሁ ኮስተር ያለ ነገር ብትፅፊ ጥሩ ነበር…ስራዬ ብለሽ ከያዝሽው አይቀር…ያው የአሮጊት አክስት ምክር ነው….ከሁለት ያጣ ጎመን እንዳትሆኚ…ለነገሩ ስራሽም ቢሆን በዛሬ ኑሮ አያኩራራም። ከኪራይ ቤት የማያወጣ ደሞዝ። ተይው እንደ ልብሽ ብትኖሪ ይሻላል››
ድግሱ አብቅቶ ሰዉ ወደየቤቱ ለመሄድ ማኮብኮብ ሲጀምር የአክስቴ አክሊል ተጠቂዎች ፊት ደመና ለብሶ ነበር፡፡
ከዚያ በአንድ ጊዜ ብድግ አለችና ባለቤቶቹን ከበን የተቀመጥነው ሁሉ እንድንሰማ አድርጋ፣
‹‹በሉ እንግዲህ…ደግሞ እንደዛሬው በጤና አክርሞ በቸር ያገናኘን…›› ብላ ወጣች፡፡
ሰዉን ሁሉ በጅምላ ጤናውን አውካ ስታበቃ፡፡