ከምሽቱ አስራ ሁለት ተኩል ገደማ ነው፡፡
ሐይለኛ ዝናብ የቆርቆሮ ጣራዎችን እየደበደበ ይወርዳል፤ መንገዶች ላይ ትናንሽ ጅረቶችን ሰርቶ ይፈሳል፡፡ ከተማይቱ ለዝናብና ለቆፈኑ በጊዜ እጅ ሰጥታ እንቅስቃሴዋ ለዝቧል፡፡
ሁለት ወጣት ፍቅረኛሞች በአንድ ክፍል ቤት ውስጥ ተቀምጠው ይጫወታሉ፡፡
🌧🌧🌧🌧🌧🌧🌧🌧
- ቴዲ…ጨላለመ እኮ…በል ተነስና ሸኘኝ እንጂ…መሄድ አለብኝ…ልሂድ…?
- የእኔ ቆንጆ… እየዘነበ እኮ ነው..
- እናቴ ይሄኔ በጭንቀት ልትሞት ነው…
- ዛሬ ደግሞ አይኖችሽ ከወትሮው ያበራሉ ልበል?
- ይሄን ጊዜ አባባ ሳሎኑ ውስጥ በንዴት እየተንቆራጠጠ ነው..
- ስሚ…ስሚማ… ዝናቡ ሙዚቃ እየተጫወተልን መሰለኝ…
- መሄድ አለብኝ ቴዲዬ!
- የሆነ የአለማየሁ ሂርጶ ዘፈን ነበር…ገና አንቺን ሳላገኘሽ በፊት የምወደው…በፈገግታሽ ወጥመድ ተያዝኩኝ ታሰርኩኝ የሚለው…ታውቂዋለሽ..?
- በዚያ ላይ እነዛ ወሬኛ ጎረቤቶቻችንም ይሄኔ በረንዳ ላይ ተደረድረው እስካሁን አለመግባቴን አጣርተዋል…በቃ ተበላሸች ብለው ነው የሚያስወሩት…
- ይገርመኝ ነበር እሱ ዘፈን…የትም ስላላየሁ ጥርስና ከናፍር ልቤን ጥዬ መጣሁ ወዳንቺ ሳላፍር የሚል ግጥም አለው…አሁን ሳስበው እንዳንቺ አይነቷ ውብ የገጠመችው ሰው ነው ይህንን ግጥም የፃፈው አይመስልሽም…?
- ደግሞ ያቺ ነገረኛ አክስቴ ከክፍለሃገር መጥታለች አላልኩህም? ..ይሄን አግኝታማ አትተኛም..ይሄኔ ቤቱን በወሬ አንዳዋለች…
- አንቺን ሳላገኝ በፊት ዝናብ አልወድም ነበር…ለካ ፍቅር ነው ዝናብና ብርድ የሚያስወድደው…አለ አይደል…ለመተቃቀፍ ይመቻል…አይደል?
- ቤቱ ባንድ እግሩ ቆሞ ነው የሚጠብቀኝ በቃ…
- የእኔ ቆንጆ..ይሄ ዝናብ ተነሱና ስሎው ዳንስ ደንሱብኝ እያለን እኮ ነው…በናትሽ ሪተሙን በደንብ አዳምጪው…?
- እርግጠኛ ነኝ ወንድሜ ታክሲ መውረጃው ጋር ቆሞ ይጠብቀኛል
- ጠጋ በይኝ እስቲ…ብርዱ ባሰ እኮ…ነይ…ተጠጊኝና ልቀፍሽ…?
- ምናለች በለኝ ከእንግዲህ ከትምህርት ቤት መልስ ቀጥታ ወደቤት ነው የሚለኝ አባባ….እንዴት ልንገናኝ ነው… ?
- አስቢው…ይህን የመሰለ ምሽት ለወደፊት ምን አይነት ትዝታ እንደሚሆን?
- አባባ ገደለኝ በቃ…
- ለልጅ ልጆቻችን የምንነግረው ትዝታ ነው የሚሆነው ታያለሽ…አንዱን ምሽት እኔ ቤት መጥታ ዝናቡ አልቆም ብሎ ምናምን ብለን ስንነግራቸው ደስ አይልም…?
- እሺ በቃ ትንሽ ልቆይ …ሻይ ከተረፈ ድገመኝ…
- ላሙቀውና እደግምሻለሁ የእኔ ቆንጆ
- ግን ብዙ አልቆይም ቴዲ
- የእኔ ቆንጆ…እየዘነበ እኮ ነው…እስኪያባራ ቆዩ
- ግን እኮ እናቴ….
🌸🌸🌸🌸🌸🌸🌸🌸🌸🌸🌸🌸🌸🌸🌸