(እውነተኛ ታሪክ)
ያ የኦነግ ወታደራዊ አዛዥ ከእግር እስከ ራሴ ከገረመመኝ በኋላ ወደ “አይካ” እና ዘኮ በመዞር “ይህ ልጅ ከናንተ ጋር ነው የመጣው?” በማለት በኦሮምኛ ጠየቃቸው። እነርሱም “አዎን!” አሉት። ከዚያም ወደኔ ዞሮ “የድርጅታችን አባል ነህ?” አለኝ። እንዳልሆንኩ ነገርኩት።
“ታዲያ ለምን ወደዚህ መጣህ?”
“ትንሽ ችግር ስለገጠመኝ ከርሱ ለመሸሽ ብዬ ነው”
“ምን ዓይነት ችግር?”
“አንድ የኦህዴድ ካድሬ እገድልሃለሁ ስላለኝ ነው”
“የምትናገረው ነገር እውነት መሆኑን እንዴት እናውቃለን?”
“ወላሂ እውነቴን ነው”
ሰውዬው እንደገና ከእግር እስከ ራሴ ካየኝ በኋላ ከኛ ፈንጠር ብሎ ከሁለት ጓዶቹ ጋር መማከር ጀመረ። ሁለቱ ጓዶች ወደኔ ገልመጥ እያሉ ከርሱ ጋር ይነጋገራሉ። ከነርሱም አንደኛው በእጁ ወደኔ ሲጠቁም አየሁት። በዚህን ጊዜ ፊቴን ወደ “አይካ” እና ዘኮ መለስኩና በመማጸን አኳኋን ተመለከትኳቸው። ዐይኖቼም እምባ ማቀር ጀመሩ። “አይካ”ም ጭንቀቴን ስለተረዳልኝ የራሱን እርምጃ ለመውሰድ ተነሳ። እኔን ጎትቶኝ አስነሳኝና ወደ አዛዡ ዘንድ ወሰደኝ። አዛዡንም “Jaallewwan! Yeroo takka isin dubbisuun barbaada” (ጓዶች! አንድ ጊዜ ላናግራችሁ እፈልጋለሁ) አለው። ሰውዬውም እንዲናገር ፈቀደለት። አይካም እንዲህ በማለት ተናገረ።
“ስለዚህ ልጅ ጉዳይ እየተነጋገራችሁ ከሆነ ተሳስታችኋል፤ ልጁ የኛ ነው፤ የታዋቂው አርበኛ የአሕመድ ተቂ ወንድም ልጅ ነው፤ ወደ አባቶቹ ሰፈር በመሄድ ላይ እያለ ነው እኛን አይቶ ወደዚህ የመጣው እንጂ ሌላ ዓላማ ኖሮት አይደለም፤ ስለዚህ በመጥፎ ዓይን ልትመለከቱት አይገባም”።
አዛዡ የአሕመድ ተቂን ስም ሲሰማ በጣም ደነገጠ። ዐይኖቹ ብልጥጥ ብለው ወጡ። ከዚያም ወደራሱ አስጠግቶኝ ጸጉሬን እያሻሸ ይቅርታ ጠየቀኝ። እኔም ሳይታወቀኝ እምባዬን አፈሰስኩ። ሰውዬውም እንዳላለቅስ ከለማመነኝ በኋላ “ይህንን በረባሶ ለምንድነው የለበስከው?” በማለት ጠየቀኝ። ጫማው በከተማ እንደ ፋሽን የሚለበስ መሆኑን፣ እንዲሁም በእግር ጉዞ ከቆዳ ጫማ ይበልጥ ተመራጭ እንደሆነ ነገርኩት። ሰውዬው “አይዞህ” ካለኝ በኋላ እኔን የጠረጠረበትን ምክንያት እንዲህ በማለት አስረዳኝ።
“አየህ! እኛ ለጠላቶቻችን የስለላ መረብ በሰፊው ተጋልጠናል፤ ጠላት የኛኑ ሰዎች በውስጣችን እያሰማራ መረጃ ይሰበስባል። በዚህ አካባቢ ለስለላ ከተሰማሩት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ታዳጊዎችና ሴቶች ናቸው። ከነርሱ መካከልም አንዱ በረባሶና ኮንጎ ጫማ የሚለብስ ትንሽዬ ልጅ መሆኑ ተነግሮናል። ያ ልጅ ቀይ መልክና ቀጫጫ ሰውነት እንዳለውም ሰምተናል። እነዚህ ታዳጊዎች ካምፕ በነበርንበት ጊዜ የዘመድ መልዕክት የሚያደርሱ በመምሰል የስለላ ስራ ሲያካሂዱ ነበር። ከነርሱ ራሳችንን መጠበቅ ስላለብን ነው አንተን የጠረጠርኩት”
ሰውዬው እንደዚያ ሲለኝ በውስጤ የሰፈነው ሽብርና ፍርሃት በአንድ ጊዜ ጠፋልኝ። በምትኩ ትኩስ ጥያቄዎች ተቀሰቀሱብኝ። “እነዚህ የስለላ ስራ የሚያካሄዱ ሴቶችና ህጻናት እነ ማን ናቸው? ያ በረባሶ የሚለብሰው ትንሽዬ ልጅስ ማን ነው?” እያልኩ ነገሩን በውስጤ መላለስኩት። ይሁን እንጂ እርሱ የሚላቸው ዐይነት ሴቶችና ታዳጊዎች በፍጹም ሊከሰቱልኝ አልቻሉም። በተለይም በረባሶ ለባሹ ልጅ ለኔ እንግዳ ነው የሆነብኝ። ቢሆንም ሰውዬውን አመንኩት እንጂ አልጠረጠርኩትም (በነገራችን ላይ በረባሶ ለባሹን ልጅ ከጊዜ በኋላ አውቄዋለሁ፤ በከተማው “ከሁለቱም ሀይሎች ገንዘብ እየተቀበሉ ይሰልላሉ” እየተባሉ ስማቸው በሰፊው ይነሳ ከነበሩት ሰዎች አንዱ ነው፤ ነገር ግን ያ ታሪክ ከአሁኑ ታሪክ ጋር ስለማይሄድ ለጊዜው እናልፈዋለን)።
*****
ቀኑ እየገፋ ነው። የኦነግ ወታደሮች ከነበሩበት ቦታ ንቅንቅ አላሉም። ከአንዱ ጎልማሳ ወታደር ጋር ወሬ ቢጤ ገጥመን ስናወራ “አሁን የምንጓዘው ገለምሶና በዴሳን ለመያዝ ነው፣ ዛሬ ማታ እንንቀሳቀሳለን” አለኝ። በዚህም የተነሳ ሌላ ፍርሃት በውስጤ ተቀሰቀሰ። እኔ ወታደር አይደለሁም። እድሜዬም ለውትድርና አልደረሰም። ከከተማ የወጣሁት ያ የኦህዴድ ካድሬ “እገድልሃለው” ብሎ ስለዛተብኝ ነው። ከዚያ ካድሬ ስሸሽ ገድሎ ለመሞት ከታጠቀ ሌላ ሃይል ጋር በድንገት ተቀላቀልኩኝ። እነዚህን ሰዎች ትቼአቸው ከሄድኩ ደግሞ “ሰላይ ነው” የሚለው ጥርጣሬ እንደገና ሊቀሰቀስባቸው ይችላሉ። ምን ይዋጠኝ እንግዲህ..?
ቁጭ ብዬ ስተክዝ አንድ ሃሳብ ተከሰተልኝ። በልበሌቲ የሚባለው የአያቴ መንደር እኔ ከነበርኩበት ቦታ በቅርብ ርቀት ላይ ነው የነበረው። መንገዱ ዳገትና ተራራ ቢበዛበትም በልጅ አካሄድ በሁለት ሰዓት ልደርስ እችላለሁ። በመሆኑም ቀኑ ሳይጨልምብኝ ከዚያ ቦታ መልቀቅ እንዳለብኝ ራሴን አሳመንኩት። ሰዎቹ እንደፈለግኩት ቢጠርጥሩኝም ከአካባቢው መሸሽ ግዴታ ነው የሚል እምነት በውስጤ አሰፈንኩ። በዚህም ያላሰብኩት ድፍረት መጣልኝ። ወደ አዛዡ ተጠግቼም “አክስቴ እየጠበቀችኝ ስለሆነ እንድሄድ ፍቀድልኝ” በማለት ጠየቅኩት። እርሱም አልጨነከብኝም። “መሄድ ትችላለህ፤ ነገር ግን መንገዱን ለቀህ ከሌላ ጦር ጋር እንዳትቀላቀል፤ አደጋ ሊደርስብህ ይችላል” በማለት በአደራ ሸኘኝ። እኔም እሺታዬን ገለጽኩለት።
በአስር ሰዓት ገደማ ጉዞዬን ጀመርኩ። ከገለምሶ ወደ ደረኩ የሚወስደውን የመኪና መንገድ ይዤ ወደ በልበሌቲ አቀናሁ። “ካራ ጭፍራ” ከሚባለው ዳገታማ ስፍራ ስደርስ ወደ ግራዬ ታጥፌ ቁልቁለቱን ጀመርኩ። ጥቂት እንደተጓዝኩ ከመንገዱ በስተቀኝ በኩል ከሰፈረውና “ጋራ ጉራቻ” (ጥቁሩ ተራራ) ከሚባለው ተራራ ላይ እየተምዘገዘገ የሚመጣ የተኩስ ድምጽ ተሰማኝ። ለኔ የተተኮሰ ስለመሰለኝ በ“ሃጂ ዑመር” መንደር የተውኩት ፍርሃት እንደገና ተቀሰቀሰብኝ። ሆኖም ወደየትኛውም አቅጣጫ ሳላይ ጉዞዬን መቀጠሉ እንደሚያዋጣኝ ራሴን አሳመንኩ። ጥቂት እንደሄድኩ ግን በድጋሚ የእሩምታ ተኩስ ሰማሁ። በዚህም ፍርሃቱ ሊበጣጥሰኝ ደረሰ። ከአፍታ ቆይታ በኋላ ደግሞ ከበድ ያለ የመሳሪያ ድምጽ ሰማሁ (የካሊበር መትረየስ ድምጽ ይመስለኛል)። በዚህም ተኩሱ ለኔ እንዳልሆነ አረጋገጥኩ። በመሆኑም ዝም ብዬ መጓዙን ቀጠልኩ። ከጥቂት ጉዞ በኋላ “የመጣው ይምጣ” የሚል ድፍረት ተሰምቶኝ ወደ ተራራው ዞሬ ስመለከት ሁለት የኦነግ ባንዲራዎች በዛፍ ላይ ተሰቅለው አየሁኝ። በዚህም በጋራው ላይ ወታደሮች እንደሰፈሩ ለማወቅ ቻልኩኝ።
*****
ሰኞ ሰኔ 15/1984፡ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት
በጉዞዬ ረሃብ ድክም ቢያደርገኝም እንደ ምንም ብዬ ወደ አያቴ መንደር ደረስኩኝ። ዘወትር የማርፈው “ሐኒፋ ሼኽ ሙሐመድ ረሺድ” ከምትባለው አክስቴ ዘንድ ስለሆነ በዚያን ቀንም ወደዚያው ሄድኩኝ። ገና ከቤቱ ከመግባቴ አክስቴ አለባበሴን አይታ ደነገጠች። “የኢህአዴግ ወታደሮች የሚለብሱትን ጫማ ለምን ለበስክ?” በማለትም ተቆጣችኝ። ለኦነጉ ሰውዬ የሰጠሁትን መልስ ለርሷም ደገምኩላትና በጫማዬ ምክንያት የደረሰብኝንም አጫወትኳት። እርሷም ካጽናናችኝ በኋላ ምግብና ወተት ሰጠችኝ። ምግቡን በልቼ ሳበቃ በከተማው ስላለው ሁኔታ ጠየቀችኝ። እኔም ሁሉንም አጫወትኳት። እርሷም በሰፈሩ ስላለው ሁኔታ አንድ በአንድ አጫወተችኝ።
*****
አክስቴ ከነገረችኝና በመንገድ ላይ ካየኋቸው ሁኔታዎች እንደተረዳሁት ኦነግ ሰራዊቱን ከካምፕ ካስወጣ አምስት ቀናት ሆኖታል። ወደዚያ መንደር የመጡት የኦነግ ወታደሮች በሰፈሩ አናት ላይ በነበሩት ተራሮች ላይ በሁለት አቅጣጫ ነው የሰፈሩት። አንደኛው ሀይል “ጋራ አባ ያያ” በሚባለው ተራራ ጥግ ስር ካለ የዋርካ ዛፍ ስር ነው ያለው። ሁለተኛው ቡድን ቀደም ብዬ በጠቀስኩት “ጋራ ጉራቻ” ተራራ ላይ የሰፈረው ነው። የሁለቱ ቡድኖች ረዳት የሆነ ሶስተኛ ሀይል “ኩሉባስ” ከሚባለውና በእርሻ ማሳዎች በተሞላው ረባዳ መሬት ላይ ሰፍሯል።
የኦነግ ወታደሮች በወቅቱ ለስንቅ የሚጠቀሙት ወደ ካምፕ በገቡበት ጊዜ ከአሜሪካ መንግሥት የቀረበላቸውን ራሽን ነው። ያ ራሽን በአብዛኛው ጠንከር ባለ የመሸፈኛ ፕላስቲክ የታሸጉ አልሚ ምግቦችን ያካተተ ነው። ጣፋጭ ብስኩቶች፣ ለውዝ፣ ስኳር፣ ስጋ፣ አትክልት፣ ሾርባ በልዩ ልዩ መጠን ታሽገው ለወታደሮቹ ቀርበው ነበር። ሲጋራ፣ ክብሪት፣ የጺም መላጫ፣ የመሳሰሉትም በእሽጎቹ ውስጥ ነበሩ። የኢትዮጵያ መንግሥት (ኢህአዴግ) በበኩሉ በቃሊቲ ምግብ ፋብሪካ የሚሰራውን ደረቅ ኮቾሮና የጣሳ ሽሮ ለኦነግ ወታደሮች በብዛት አቅርቦ ነበር።
ማክሰኞ ሰኔ 16/1984
በዕለቱ በአካባቢው የተሰማ አዲስ ነገር የለም። ከሰፈሩ ነዋሪዎች መካከል ጥቂት የማይባሉት በተራሮቹ ላይ ከሰፈሩት የኦነግ ወታደሮች ዘንድ እየሄዱ ይጨዋታሉ። አንዳንድ እናቶች ደግሞ ሆጃ በኪትሊ (ማንቆርቆሪያ) እየያዙ ለወታደሮቹ ይወስዳሉ። እኔ ግን በጫማዬ ሳቢያ በገባሁበት ጣጣ ምክንያት ወደ ጋራው ልሄድ አልቻልኩም። ቀኑን ዘመዶቼን በመዘየር ካሳለፍኩ በኋላ ፀሐይ ስታዘቀዝቅ ወደ አክስቴ ቤት ሄድኩኝ። አክስቴ በድንጋጤ ቁና ቁና እየተነፈሰች ወደ ቤቱ ገባች። “ምን ተፈጠረ፣ የሰማሽው ነገር አለ” በማለት ጠየቅኳት። ለማክሰኞ ገበያ ውሎ ገለምሶ ሄደው የተመሰሉ ሴቶች ያመጡትን ወሬ እንዲህ በማለት ነገረችኝ።
“ኢህአዴግ ያለ የሌለ ሀይሉን አስገብቷል፤ በዛሬው እለት ወታደሮቹ በማክሰኞ ገበያ በኩል ወደ ገለምሶ ስታዲየም ሲተሙ ነው የዋሉት አሉ፤ በሰልፍ ሆነው ስታዲየም ከደረሱ እዚያው ሰፍረዋል፤ አዛዣቸው በአጉሊ መነጽር በሁሉም አቅጣጫ እየዞረረ ተራሮቹን ሲመለከት ነበር”
አክስቴ እንዳለችው ከሆነ የኢህአዴግ ጦር ከቦርዴዴ ተነስቶ በሀርዲም አቅጣጫ እየተመመ ነው ወደ ገለምሶ የገባው። ይህም በፊት ከገባው ሀይል በተጨማሪ መሆኑ ነው።
ምሽት ላይ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮን የሚያሰራጨውን ወሬ ለመስማት “ኢስከንደር ሼኽ ሙሐመድ” ከሚባለው አጎቴ ቤት ሄድን። የኦነግ ሬድዮ ጣቢያ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ የሚያስተላልፈውን ፕሮግራም ከሰማን በኋላ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ሲሆን የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ተከፈተ። ጣቢያው በዕለቱ ካስተላለፋቸው ዜናዎች አንዱ “የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት መውጣቱን አስታወቀ” የሚል ነው። የኦነግ መውጣት ቀደም ብሎ ያወቅነው ጉዳይ በመሆኑ ብዙም አልገረመንም። ከዚያ ይልቅ በኦነጉ አቶ ሌንጮ ለታ እና በኢህአዴጉ አቶ ዳዊት ዮሐንስ መካከል የተደረገው ክርክር ነው ስሜታችንን የማረከው። በተለይ አቶ ሌንጮ በክርክሩ ወቅት አቶ ዳዊትን “እንደዚያ አላልኩም፤ ዋሽተዋል” ማለታቸውና አቶ ዳዊትም በእፍረት አኳኋን መለሳለሳቸው በቤቱ ውስጥ የነበሩ ብዙ ሰዎች “ዋጋውን ሰጠው! ጎሽ!! ሌንጮ የኛ አንበሳ!” እንዲሉ አደርጎአቸው ነበር።
ሬድዮ ጣቢያው ስርጭቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ አክስቴ ቤት ተመለስኩ። ከአክስቴ ልጆች ጋር የባጥ የቆጡን ካወጋን በኋላ ፈጣሪ መልካሙን እንዲያሳየን በመመኘት ተኛን። ሌሊቱ ተገባዶ ሊነጋጋ ሲል (ከማለዳው 11፡ 40 ሰዓት ገደማ) ሀይለኛ ረብሻና የሰዎች ግርግር ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ። ጆሮዬን አቁሜ ሳዳምጥ ራቅ ካለ ስፍራ የሚመጣ የከፍተኛ ፍንዳታና የአውቶማቲክ እሩምታ ተኩስ ሰማሁ!!
“ጦርነቱ እዚሁ ተጀመረ እንዴ” አልኩኝ!!
—
(ይቀጥላል)
—-
አፈንዲ ሙተቂ
መስከረም 13/2007
—–
ኦነግና ኢህአዴግ በአንድ ቀን ጦርነት (ክፍል አራት)