ትንሽ ልጅ ሳለሁ…
ይህች …ከልጅነት እስከ ጉልምስና የትም፣ መቼም ሳያት እምባ በአይኔ የምትሞላውን ሰንደቅ ዓላማ ትምህርት ቤት በተጠንቀቅ ቆሜ ሳሰቅል፣
ሳላሳልስ ‹‹ኢትዮጵያ…ኢትዮጵያ…ኢትዮጵያ ቅደሚ…አብቢ ለምልሚ›› እያልኩ በስሜት ሳዜም…
‹‹ይህች ሰንደቅ ዓላማ ተከፍሎባታል›› እያሉ ሲነግሩኝ፣
‹‹ባንዲራችን ብዙ ታሪክ አላት›› እያሉ ሲያስተምሩኝ….
‹‹ወድቆ በተነሳው ባንዲራ ተብሎ ተምሎባታል›› እያሉ ሲያወጉኝ….
የቀለማቱን ትርጉም ለማወቅ እጓጓ ነበር።
ጎጉቼ አልቀረሁም።
ገና ኢትዮጵያ ሰፈሬ ሳለች፣ ዓለሜ ሳትሰፋ፣ ከቤተሰቤ ውጪ ሰው ሳላውቅ በፊት የሰንደቅ ዓላማዬን ትርጉም መምህሬ እንዲህ ብሎ አሳወቀኝ።
››አረንጓዴው ለልምላሜዋ ተምሳሌት ነው
ቢጫው ለመጪው ጊዜ ተስፋዋ ምሳሌ ነው
ቀዩ …ቀዩ ደግሞ ለመስዋእትነት ምልክት ነው። ለሃገር ነጻነት የተከፈለውን ዋጋ ለማስታወስ››
ከዚያ ወዲህ እኔና ባልንጀሮቼ የቀለማቱን ምሳሌ ባንድ ጊዜ ሸመደድን።
ላገኘነው ሰው ሁሉ እንደምናውቅ ለማሳወቅ ቀደም ቀደም እያልን ‹‹ሰንደቅ አለማችን እኮ ትርጉሟ ይሄ ነው….አረንጓዴው ልምላሜ፣ ቢጫው ተስፋ፣ ቀዩ መስዋእትነት። ›› ስንል መለፈፍ ጀመርን።
በእኔ እድሜ ይሄን የማያውቅ ትምህርት ቤት የሚሄድ ልጅ አልነበረም።
ስለዚህ…እኔ እና.እንደኔ ያሉ ኢትዮጵያዊያን…
የሰንደቅ ዓላማችንን ትርጉም ባነሳን ቁጥር ፍቅሯ ከተፈጥሯችን እየተጋመደ፣
ስሟ በተጠራ ቁጥር መውደዷ ከደማችን እየተዋሃደ፣
ባየናት ቁጥር ትርጉሟ በልባችን እየሰረፀ…እንደዚያ ነው ያደግነው።
ለሰንደቃችን ያለን ፍቅር መጠን እና ስፋቱ፣ ቁመቱ እና ርዝመቱ አጠራጥሮኝ ባያውቀም…
ባንዲራችንን… የሚንቋት ቢንቁንም፣ የሚረግጧት ቢረግጡንም፣ የሚጠሏት ቢያስጠሉንም፣
መቼም ቢሆን ኢትዮጵያን ከእኛ በላይ የሚወዷት ኢትዮጵያውያን በየታሪክ ምእራፉ ብቅ እንደሚሉ ግን ጠፍቶኝ አያውቅም።
የማወራው ብዙዎቻችን በልጅነት የሸመደድነውን የሰንደቃችንን ቀለማት ትርጓሜ በእውን ስለኖሩት ኢትዮያውያን ነው።
የማወራው- እነዚያ፣ በየዘመኑ ኢትዮጵያን ዶግ አመድ ላድግሽ ብሎ የሚነሳባትን ሳይፈሩ መክተው፣ ከእነ ልምላሜዋ ዘመንን እንድታልፍ ስለቆሰሉት ኢትዮጵያውያን ነው።
የማወራው- ካልጠቀመሽኝ ላፍርስሽ የሚላትን ዋልጌ ባንድ ምላስ አሻፈረኝ ብለው ተስፋዋ እንዲያንሰራራ ስለደሙላት ኢትዮጵያውያን ነው።
የማወራው- የሰንደቅ ዓላማችን የቀዩ መደብ ህያው ትርጓሜዎች ስለሆኑት …
ሰንደቋ እንኳን ወድቆ ዘመም ሲል እንኳን ቀና ሊያደርጉት፣ ስለወደቁት፣ ስለሚወድቁት፣
ኑ ሳይባሉ ለሄዱላት ፣ እንኳንስ አጣጥራ፣ መሸበርዋን አይተው ሳይረፍድ ስለደረሱላት ኢትዮጵያውያን ነው።
…ኢትዮጵያን ከእኛ በላይ ስለሚወዷት ኢትዮጵያውያን ነው።
ድሮስ ከሞተላት በላይ የወደዳት ማነው?
