ሱሪ ልትገዛ አንድ ቡቲክ ጎራ አልክ እንበል።
“ስንት ነው? ” ጠየክ።
“አምስት መቶ ”
“መጨረሻው? ”
” አራት ከሰባ ውሰደው ”
“በልና ሽጥልኝ…”
እዚህ ውይይት ውስጥ፣ ነጋዴውም ገዢውም ውሸታሞች ናቸው። ነጋዴው፣ 470 ብር የሚሸጥ ከሆነ፣ ለምን 500 ብር ይላል? ገዢው የውሸቱ ተባባሪ ስለሆነ፣ “ቀንስ” እያለ ውሸቱን ያጅበዋል (የውሸት ባንዶች አጃቢያቸው ብዙ ነው)
ገዢው ነጋዴው ባለው ዋጋ እንደማይሸጥ ያውቃል። አጠያየቁ ግን ማወቁን የሚያውቅ አይመስልም። ሁለቱም አሿፊዎች ናቸው። ገዢው ከብዙ ተመሳሳይ ነጋዴ በዚህ መልኩ ገዝቷል። ነጋዴውም ሸጧል። ከዚህ በፊት ባይገናኙ እንኳን የተዘረጋውን የውሸት ስርዐት ያወቁታል።
የዚህ ቡቲክ ዋጋ፣ ቀድመህ ከጠየክባቸው ቡቲኮች የተሻለ ስለሆነ ገዛህ እንበል። ዋጋው ግን ከተገቢው በላይ እንደሆመ ታውቃለህ። የሚሸጥልህ ስለሌ፣ በማይሸጥበት ዋጋ ገዝተህ ገባህ። ምስኪን።
አንዳንድ ውሸቶች ሲለመዱ፣ አማራጭ የሌላቸው የአሰራር መንገዶች ይሆናሉ።
ደሞ፣ የመንግስት ቡቲክ ሄድክ እንበል።
“ባለሱቅ ”
“ምን ፈለክ?” ይላል፣ አንድ በማን አለብኝ የተኮፈሰ ድምፅ።
“ዲሞክራሲ ፈልጌ ነበር፣ ስንት ስንት ነው? ”
“ዲሞክራሲ፣ በደርግና በሀይለ ስላሴ ከሚከፈለው መስዋትነት አነስ ባለ ዋጋ ይሸጥልሃል። ዋጋው ስለተፃፈበት ከፍለህ ውሰድ ”
እዚህም ጋር ዋጋው ትክክል እንዳልሆነ ታውቃለህ። “ካለፈው ስርዐት” ይሻላል እያልክ የመንግስትን ጥቁር ገበያ ታስተዋውቃለህ። እዚህም ጋር ሁለት ዋሾዎች፣ በነፃ መሰጠት ያለበትን አስከፍሎ የሚሸጥ መንግስትና መብቱን የሚገዛ ሕዝብ።
እዚህ ሰፈር ያለው ሌላ ውሸት፣
መንግስት መንገድ ሰራ፣ መንግስት ፎቅ ሰራ፣ መንግስት ፍቅር ሰራ(ሃሃ… ) ምናምን…
አንተም፣ መንግስትም የመንግስት ስራ ይሄን መስራት እንደሆነ ታውቃላችሁ። እሱ ሰራው እያለ ይሸልላል፣ አንተ ተሰራ እያልክ ታጨበጭባለህ። ስታበዛው ደሞ፣ ካለፉት ስርዓቶች ጋር ታወዳድረዋለህ።
“በደርግ እንዲህ አልነበረም ” ትላለህ። በደርግ ሃጢያት፣ የኢህአዴግን ፅድቅ ልትሰራ ደፋ ቀና ትላለህ። መሰራት ያለበት ስራ ፃዲቅ አያሰኝም።
እውነቱ ምንድነው? እውነቱ አንድ መንግስት የተጠቀሱትን ስራዎች የመስራት ግዴታ ያለበት መሆኑ ነው። ውሸቱስ?
ውሸቱማ፣ ግዴታን እንደ ስጦታ… አለመስራትም ይችል ነበር የሚል ምክንያት አንተርሰህ ማቅረብ ነው።
ውሸት ሲለመድ፣ መሟላት ያለበት ግዴታ፣ እንደ ችሮታ ይቆጠራል!
ምስኪን አንተ፣ የመንግስትን ግዴታ እንደ ችሮታ ቆጥረህ በአንተው መጀን እያልክ፣ የእግሩ ጫማ የረገጠበትን መሬት ስትስም ትውላለህ!