ክፍል አስራ አንድ፡ “የጨለማው መስከረም” (Black September)
የዮርዳኖሱ ንጉሥ ሑሴን የፍልስጥኤም ድርጅቶች እስከ መስከረም 20/1970 ከዮርዳኖስ ግዛት እንዲወጡ ያዘዙበት ውሳኔ ከዐረቡ ዓለም ውግዘት ሲያከትልባቸው ፈራ ተባ ማለት ጀመሩ። በዚህን ጊዜም የጸጥታ ኃይሎቻቸው ንጉሡን ሳያማክሩ አንድ ድራማ አቀናበሩ። በዚህም መሠረት የዮርዳኖስ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እና አንድ የጦር ሃይል ጄኔራል ባልታወቁ ሰዎች ተገደሉ። የግድያው ፈፃሚም “ፋታሕ የላከው ሰርጎ ገብ ነው” ተባለ። በዮርዳኖስ ሬድዮና በመንግሥት ፕሬሶች ላይ ስለግድያዎቹ ተደጋግሞ ተፃፈ። “የፍልስጥኤም ተዋጊ ድርጅቶች በእንግድነት በተቀበለቻቸው ዮርዳኖስ ላይ የፈጸሟቸው ደባዎች ዝርዝር” የሚል ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተካሄደ። “ጆርጅ ሐበሽ እና ያሲር አራፋት በመንግሥታችን ውስጥ የራሳቸውን መንግሥት መስርተው ሀገራችንን እየበጠበጡ ነው፣ ንጉሣችንን ሊገድሉ ሲያሴሩ ተገኝተዋል” ተብሎ ተጻፈ።
ነገሩን እውነት ለማስመሰልም ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የአማን ከተማ ከየት እንደተወረወሩ በማይታወቁ የበርካታ ቦምቦች ፍንዳታ ተናወጠች። ማንነታቸው ያልታወቀ እና ከመትረየስ እስከ ሽጉጥ የታጠቁ ፋኖዎች በባለስልጣናቱ ላይ የተኩስ እሩምታ ይከፍቱ ጀመር። ንጉሥ ሑሴን በመኪናቸው በመጓዝ ላይ ሳሉ ሁለት ጠባቂዎቻቸው እንደተገለዱም ተወራ። የእስራኤል ጋዜጦች ዜናውን እያጋነኑ አወሩት። ኒውዮርክ ታይምስን የመሳሰሉ የምዕራብ ሀገራት ፕሬሶችም ወሬውን አራገቡት። የዮርዳኖስ ፕሮፓጋንዲስቶች በጋዜጦች ዓምድ ላይ “ኡ ኡ! ንጉሣችን ምንድነው የሚጠብቁት? እነዚህን አሸባሪዎች ከሀገራችን ለምን አያባርሯቸውም” እያሉ ጻፉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በዮርዳኖስ መንግሥት ላይ የከረረ ጥላቻ የነበራቸው የኢራቅና የሶሪያ መንግሥታት በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም በንጉሥ ሁሴን ላይ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፈቱ። በተለይም ከደማስቆ፣ ከባግዳድ እና ከቤይሩት የሚተላለፉ ሬድዮ ጣቢያዎች “ንጉሥ ሁሴን አድኃሪ ነው፣ የጽዮናዊያን እና የምዕራባዊያን አሻንጉሊት ነው፤ ከእስራኤል በመጣበት ግፊት ፍልስጥኤማዊያንን ሊጨርስ ነው፣ እስራኤል ኢየሩሳሌምን እሰጥሃለሁ ስላለችው ነው እንዲህ የሚቅበጠበጠው፤ በቶሎ ካልተመታ ወደኛ መምጣቱ አይቀርም” እያሉ የፕሮፓጋንዳ መአት አዘነቡ።
በጉዳዩ ዙሪያ የተጨበጠ መረጃ ያልነበረው የዮርዳኖስ ህዝብ መንግሥቱ የሚያካሄደው ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆነ። በተለይም ከኢራቅና ከሶሪያ የሚሰራጨው ፕሮፓጋንዳ ህዝቡን ስላበሳጨው ከንጉሡ ጋር ለመቆም ተነሳ። በዚሁ መሠረት የዮርዳኖስ ህዝብ “የፍልስጥኤም ድርጅቶች እና ስደተኞች ከሀገራችን ይውጡልን” በማለት ታላላቅ ሰላማዊ ሰልፎችን አደረገ። መንግሥቱ ተዋጊዎቹን አስወጣበታለሁ ብሎ የተገበረው በአሻጥር የተቀናበረ ዘዴ ለሰፊው የፍልስጥኤም ስደተኛ ህዝብም ተረፈ።
የዮርዳኖስ የጦር ኃይል ይህንን አጋጣሚው በመጠቀም ያለምንም ማስጠንቀቂያ በፍልስጥኤም ተዋጊዎች ካምፕ ላይ ዘመተ። በሁለቱ መካከል ውጊያ ተቀሰቀሰ። ከመስከረም 18-30/1970 ከበድ ያለ ጦርነት ተካሄደ። የፋታሕ እና የPFLP ተዋጊዎች ከነርሱ በብዙ እጥፍ የሚበልጠውንና በደካማ ሁኔታ የተዋቀረውን የዮርዳኖስ ጦር በጀግነት ተዋጉት። የሀገሪቱ አየር ኃይል በሁለት ቀናት ብቻ ከመቶ የበለጡ ድብደባዎችን አካሄደ። ሆኖም የፍልስጥኤም ተዋጊዎችን ከይዞታቸው መነቅነቅ ተሳነው።
ሁለቱ ኃይሎች እንዲህ አምርረው በመዋጋት ላይ ሳሉ በመንግሥት የሐሰት ፕሮፓጋንዳ የተነሳሳው የዮርዳኖስ ህዝብ ሀገራቸውን ተነጥቀው ወደ ግዛቱ የመጡትን ፍልስጥኤማዊያን ለማባረር ወደ ስደተኛ ካምፖች ጎረፈ። የዮርዳኖስ ጦር ኃይል በዚህም መሀል ጣልቃ ገብቶ አደገኛ ድራማ ሰራ። ለነዋይ የተገዙ ዋልጌዎች ከስደተኛ ካምፖቹ ውስጥ ሆነው ወደ ውጭ እንዲተኩሱ በማድረግ ተከላካይ የሌላቸው ስደተኞች የሚገደሉበትን ሰበብ አዘጋጀ። ከዚህ በማስከተልም በትንሹ ከአስር ሺህ የማያንሱ ስደተኞችን ጨፈጨፈ። የንፁሐን ደም እንደ ጎርፍ ፈሰሰ።
የፋታሕ እና የPFLP መሪዎች የፍልስጥኤም ስደተኞች መጨፍጨፍ ወሬ ሲደርሳቸው ልባቸው በሐዘን ተሰበረ። ወንድማችን ነው ብለው የተጠጉት የዮርዳኖስ መንግሥት በህዝባቸው ላይ ያካሄደው ጭፍጨፋ ከባድ ምሬት ውስጥ ጣላቸው። ከዮርዳኖስ ጦር ኃይል ጋር የሚያደርጉትን ውጊያ አጠናክረው ከቀጠሉ በህዝባቸው ላይ የሚካሄደው ጭፍጨፋ የሚባባስ ሆኖም ታያቸው። በመሆኑም የግብጽ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጀማል ዐብዱናሲር በነገሩ ጣልቃ ገብተው እንዲገላግሏቸው ጠየቋቸው። ፕሬዚዳንት ጀማልም በአፋጣኝ ገብተውበት ጥቅምት 12/1970 ግጭቱን አስቆሙት። ለግጭቱ ማብረጃ እንዲሆንም የፍልስጥኤም ድርጅቶች የዮርዳኖስን ግዛት ለቀው እንዲወጡ ተነገራቸው። ድርጅቶቹም ውሳኔውን ተቀብለው ካምፓቸውን በመንቀል ከዮርዳኖስ ወደ ሊባኖስ ተሰደዱ። ከፍልስጥኤማዊያን ስደተኞች መካከልም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት ወደ ሊባኖስና ወደ ሌሎች ሀገራት ተሰደዱ።
ከላይ ያወጋነው ኩነት በፍልስጥኤማዊያን ዘንድ እንደ ታላቅ መቅሰፍት (catastrophe) ከሚቆጠሩት ክስተቶች አንዱ ነው። የፍልስጥኤም ህዝብ በየዓመቱ ክስተቱን በታላቅ ሐዘንና ተመስጦ ይዘክረዋል። ፍልስጥኤማዊያን የታሪክ ጸሐፊዎችም በመጽሐፎቻቸው ውስጥ ለክስተቱ ጉልህ ስፍራ ይሰጣሉ። ደራሲዎች፣ ባለቅኔዎች፣ ሰዓሊዎችና ከያኒዎችም በስራዎቻቸው ክስተቱን እየደጋገሙ ያወሱታል።
ፍልስጥኤማዊያን ይህ የንጹሐን ሰቀቀንና ሲቃ የታየበትን አሳዛኝ ክስተት “አይሉል አስወድ” በማለት ይጠሩታል። ወደ አማርኛ ሲመነዘር “ጭለማው መስከረም” እንደማለት ነው። ክስተቱ በበርካታ የታሪክና የፖለቲካ መጻሕፍት ውስጥ የሚታወቀው ግን Black September በተሰኘው የእንግሊዝኛ አጠራር ነው። ፍልስጥኤማዊያን በBlack September ያለቁት ወገኖቻቸው ብዛት ከ40,000 እስከ 50,000 እንደሆነ ነው የሚናገሩት። የዮርዳኖስ መንግሥት እና ምዕራባዊያን ጸሐፍት ግን የሞተው ሰው ብዛቱ ከ3000 ብቻ እንደሆነ ነው የሚጽፉት። በተጨማሪም ዮርዳኖስ በተባራሪ ጥይት ከሞቱት ጥቂት ሰላማዊ ሰዎች በስተቀር በውጊያው የሞቱት በሙሉ የፋታሕ እና የPFLP ተዋጊዎች እንደሆኑ ገልጻለች። ከሁለቱም ያልወገኑ ጸሐፊዎች ግን ብዙሃኑ ስደተኛ የሆነ አስር ሺህ ሰው መሞቱን ጽፈዋል።
እዚህ ላይ መታየት ያለበት ቁም ነገር የሟቾቹ መብዛትና ማነስ አይደለም። ልብ የሚነካው ዋነኛ ነገር በጉልበተኛ ወራሪ ሀገራቸውን ተቀምተው የተሰደዱ ንጹሐን ሰዎች “ወዳጃችሁ ነኝ” በምትለው ዮርዳኖስ መጨፍጨፋቸው ነው። የዮርዳኖስ ጦር ኃይል በፍልስጥኤማዊያን ላይ ያደረሰው ፍጅት ሀገርን እና ማንነትን በማጣት ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮች ፈርጀ ብዙ መሆናቸውን ነው የሚያስረዳው። በእስራኤል ጭካኔ እየተገደሉ ከሀገር መባረር በጣም አሳማሚ ነው። በስደት ላይ ሳሉ ለጥቃት መዳረግ ደግሞ እጅግ አሳማሚ ነው።
እርግጥ ዮርዳኖስ ከዓመታት በኋላ የጦር ኃይሏ በBlack September ወቅት በፍልስጥኤማዊያን ላይ ለፈጸመው ጥቃት ይቅርታ ጠይቃለች (“የኔ ጦር የገደለው የPLO ተዋጊዎችን ነው” የሚለውን አቋሟን ሳትቀይር ማለት ነው)። በሀገሯ ለሰፈሩት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ፍልስጥኤማዊያን ስደተኞችም ሙሉ ዜግነትን ሰጥታለች። በዚህ ረገድ ለየት ያለ እርምጃ የወሰደች ብቸኛዋ ሀገር ስለሆነች ክብርና ምስጋና ይገባታል። ቢሆንም በBlack September ወቅት በፍልስጥኤማዊያን ላይ የወረደው መቅሰፍት ሁልጊዜ በታሪክ ሲዘከር ይኖራል።
—–
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 14/2010
በሸገር ተጻፈ።
One Comment