Tidarfelagi.com

የመጨረሻው እራት፣ ዳ ቬንቺ፣ ክርስቶስ እና ይሁዳ

ሊዮናርዶ ዳ ቬንቺ እንዲሁም ሥራ በማዘግየት የሚችለው የለም፤ በተለይ “የመጨረሻው እራት” የሥዕል ሥራውን አዘገየው አይገልፀውም – አደረበት እንጂ። ሥዕሉን ለመጨረስ ዓመታት ፈጅተውበታል።

እርግጥ በዚህ ማንም ዳ ቬንቺን የሚወቅስ የለም። እንደእሱ መሳል ካልቻልክ አዘገየህ ብልህ ልትወቅሰው እንዴት ይቻልሃል ! በዳ ቬንቺ ታሪክ ላይ የፃፉ ሁሉ ይሄን የዳ ቬንቺን ሥራን ለነገ የማሳደር ባህሪ ቢጠቅሱም ማንም ሊተቸው አይደፍርም። ያውም እኮ በዚህ ባህሪው ሳቢያ ሳይጨርሳቸው የቀሩ የሚያስቆጩ የጥበብ ሥራዎች አሉ…
ግን ማን አፍ አውጥቶ ዳ ቬንቺን ሀይ ይላል…
ሃይ… ዝም ነው እንጂ…
በነገራችን ላይ … ተቀናቃኙ እና ሌላው ዘመነኛው (contemporary) ሰዓሊና ቀራፂ ማይክል አንጄሎም ይህቺ አመል ሳትኖርበት አትቀርም። ለነገሩ የሚያስቡት በጣም ትልቅ ስለሆነ ቀን ከሌት እያሰቡ እየተጨነቁበትም ለመጨረስ ረጅም ጊዜ ይወስድባቸዋል። እንደዛም ሆኖ በሰሩት መርካታቸውን እግዜር ነው የሚያውቀው – ዓለም በሥራቸው ጉድ ይበል እንጂ እነሱ በእርግጠኝነት በሥራቸው ረክተውበታል ብለን መደምደም አንችልም።

አሁን ወደ ዳ ቬንቺ ድንቅ ሥዕል “የመጨረሻው እራት” የአሳሳል ታሪክ…
በዚህ ሥዕል የአሳሳል ታሪክ ዙሪያ የሚነሳ ትውፊት አለ። ዳ ቬንቺ ከክርስቶስና ከይሁዳ በስተቀር የሌሎቹን ምስል ለመሳል ጊዜ አልፈጀበትም ነበር። የክርስቶስና የይሁዳን ግን ከየት ያምጣው። በየመንገዱ፣ በየገበያው፣ በየመንደሩ እየሄደ የሰው ፊት ያጠና ጀመር – የክርስቶስን እና የይሁዳን ሊመስል ይችላል የሚለው መልክ ግን አጣ…
ከብዙ ጊዜያት በኋላ አንድ ቀን ግን ባልገመተው መልኩ በአንድ ዛፍ አጠገብ ሲያልፍ ከገበያ የሚመለሱ ገጠሬዎች መሃል መልኩ ክርስቶስን ይመስላል ያለውን አንድ ትንሽ ልጅ አገኘ።
በደስታ ዘለለ።
ልጁ መልኩ ክርስቶስን እንደሚመስል ሲነግራቸው ልጁም ዘመዶቹም ደስ አላቸው። እዛው በዛው የልጁን ወዘና በ‘ስኬች’ ሳል ሳል አደረገው።
በ“የመጨረሻው እራት” የመሃለኛው ቦታ ያለውን የክርስቶስን ምስል ሥሎ ጨረሰ።

የይሁዳ ቀረ…
ይሁዳን የሚመስል ሰው ከየት ይምጣ። ወንጀለኞች ይበዙበታል የሚላቸው ቦታ ሁሉ ‘ስኬች’ መስሪያ መሳሪያዎቹን ይዞ ተንከራተተ። ከዚያ በፊት ወንጀለኞች በስቅላት የሚቀጡበት ቦታ ድርሽ ብሎ ባያወቅም – አሁን ግን ይሁዳን የሚመስል እዚያ ቢገኝ በሚል በሞት የሚቀጣ ወንጀለኛ አለ በተባለበት ሁሉ ሄደ።
የለም ይሁዳ….
ነገሩን ሊተወው በቋፍ ላይ እያለ የታሰር ጓደኛውን ሊጠይቅ እስር ቤት ሲሄድ ይሁዳን የሚመስል ወጣት እስር ቤት ውስጥ አያይም !!
ዓይኑን ማመን አልቻለም።
የእስር ቤቱን ኃላፊ አስፈቅዶ እስረኛውን አስጠርቶ እሱን የሚመስል ሰው ሲፈልግ ዓመታት እንደተቆጠሩ ሲነግረው እስረኛው ፈገግ አለ…
መልኩ ይሁዳን እንደሚመስል ነግሮት ሊስለው እንደሚፈልግ ሲገልፅለት ግን እስረኛው በንዴት አበደ…
ዳ ቬንቺ ይሁዳን ትመስላለህ ስላለው ተፀፀተ። እርግጥ ነው ማንም ቢሆን ክስርቶስን የሸጠውን ከሃዲውን ይሁዳን ትመስላለህ ሲሉት ቢናደድ አይገርምም – ምን አይነቱ ደደብ ነኝ አለ ዳ ቬንቺ።
ቢሆንም ግን የእስረኛው ንዴት ከልኩ ያለፈ ሆነበት – ምንድነው ይሄን ያህል – ደግሞም እኮ … መቼም … አለ አይደለ … እስር ቤት ውስጥ አይደለ እንዴ ያገኘው።
ምንድነው ይሄን ያህል…
እስረኛው በንዴት እጆቹን እያወናጨፈ ዳ ቬንቺን፣ “የፈለግከውን ብትሰድበኝ ምንም አልልህም ነበር” አለው፣ “አዎን እኔ የሰው ነፍስ አጥፍቼ የተፈረደብኝ የተረገምኩ ነፍስ ነኝ … ይገባኛል … ግን ቢሆንስ … የዛሬ ስንት ዓመት ልጅ ሳለሁ ክርስቶስን ትመስላለህ ብለህ የሳልከኝን ልጅ ዛሬ ላይ ምንስ ቢሆን … ይሁዳን ትመስላለህ ትለኝ … ይሁዳን … ምን በደልኩ … ምን አጠፋሁ … እርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነኝ … ቢሆንስ ግን … ክርስቶስን ትመስላለህ ብለህ እንደገና ደግሞ ቁርጥ ይሁዳን ትመስላለህ ትበለኝ … ምን አለበት ብትገድለኝ … ይሄን ያህል ለዚህ የሚያበቃ ምን ሰራሁ … አዎን የሰው ነፍስ አጥፍቻለሁ … ቢሆንስ ግን”
ዳ ቬንቺ ዓይኖቹ ፈጥጠው ቀረ…
ይሄ ለማመን የሚከብድ ነገር ነው። ይሄ ምን ማለት ነው – አረ የዚህ ሚስጥሩ ምን ይሆን…
ደግሞ በንዴት ሲንቦገቦግ ቁርጥ ይሁዳን !!
ዳ ቬንቺ በድንጋጤ ክው እንዳለ ከክፍሉ ወጥቶ መቼም ከዓይኑ የማይጠፋውን የ‘ይሁዳ’ን ምስል በስኬች አንስቶ ሄደ…
የጎደለው ሞላ – ይሁዳን ሳለው – “የመጨረሻው እራት”ም ሆነ…
ይሄው እስካሁን ድረስ…
ዳ ቬንቺን ግን ድንጋጤው ቢለቀውም – ሚስጥሩ ግን አይለቀውም።

2 Comments

  • EyobkelbessaE commented on April 30, 2021 Reply

    ሚስጥሩ፡ገባኝ፡መከራዬ፡በዛ

  • Eyobke commented on April 30, 2021 Reply

    ገኝ፡እሺ፡ቃሌን፡እጠብቃ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *