Tidarfelagi.com

የሸገር ገበታን በጨበጣ ታደምኩኝ

በትላንቱ ስብሰባ ላይ ለመታደም ወደ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) ቅጥር ግቢ ልገባ ስል በር ላይ የቆመ ፖሊስ በዲያስፖራ ቅላፄ “ሞባይል ይዘሃል?” አለኝ። እኔም ጥያቄው ገርሞኝ “አዎ” አልኩት። “ሞባይል ይዞ መግባት አይቻልም!” አለኝ። ከአንዴም ሁለቴ በECA በተዘጋጁ ስብሰባዎች ላይ ተሳትፌያለሁ። ያኔ ግን ሞባይል ይዞ መግባት ክልክል ነው የሚል ነገር አላጋጠመኝም። “እንዴት ያለ ነገር ነው? ወይ ቀድማችሁ ሞባይል ይዞ መግባት እንደማይቻል አልነገራችሁን! አሁን ሞባይሌን የት ጥዬ ልገባነው?” ብዬ ስነጫነጭ ከጎኔ የነበረው የአዲስ አድማሱጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲኖር ነው እንዲህ የሚሉት” አለኝ። “ተው ባክህ! አብይ ይመጣል ተብሏል እንዴ?” አልኩት። ወዲያው የሪፖርተሩ ጋዜጠኛ #ታምሩ_ፅጌ ሞባይሉን በእጁ ይዞ መጣ። ከዚያ “ኑ ሞባይላችንን ኢሊሌ ሆቴል አስቀምጠን እንምጣ” አልኳቸው። ሞባይላችን ኢሊሌ አስቀምጠን ከመጣን በኋላ ወደ ECA ለመግባት በር ላይ ተሰልፈን ሳለ ሁሉ በተመስጦ እያሰብኩ ነበር። ወደ ቀልቤ የተመለስኩት #አስቴር በዳኔ ከፊቴ ቆማ “ሃይ” ስትለኝ ነው።

ዶ/ር አብይ ይመጣል ካሉኝ ቅፅበት ጀምሮ የማስበው እንዴት አድርጌ ከዶ/ር አብይ ጋር እንደምገናኝና በዛሬው የራት ግብዣ ላይ መታደም እንደምችል ነበር። በስብሰባው ላይ የተለያዩ ፅሁፎች ሲቀርቡ እኔ የማስበው ይሄኑ ነው። በመጨረሻ የሻይ ዕረፍት ላይ እንደምንም ብዬ ወደ ዶ/ር አብይን ለመቅረብና ሰው እየሰማ “አብይዬ! ጃንሆይ ግብር የሚያበሉት እኮ ባለፀጋዎችን ብቻ አይደለም! ደሃውም፣ ሃብታሙም፣ እንደ እኔ ያለውንም ግብር ያበላ ነበር። ታዲያ በዚህ አዳራሽ 5 ሚሊዮን በር የከፈሉ ባለፀጋዎች ብቻ መጋበዝ ያስተዛዝባል! ኧረ… እንደው ባይሆን አስተናባሪ ሆኜ እንኳን ልግባ?” ለማለት ወሰንኩ። ይህን ውጥን በውስጤ ይዤ እየተጠባበቅኩ ሳለ የመድረክ መሪዋ ገና “አሁን የሻይ…” ሲሉ ተስፈንጥሬ ተነሳሁ። ከጎኔ የተቀመጠው ታምሩ ፅጌ በአግራሞት አየኝ። እኔ እቴ… ጣጣ አለኝ እንዴ! በሰው መሃል እየተሽለኮለኩ ወደ ዶ/ር አብይ ገሰገስኩ። እኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቀመጡበት ቦታ ስደርስ ለካስ እሳቸው በሌላ በኩል ሄደው ኖሯል። ዞር ስል ቅድም እኔ የተቀመጥኩበት ቦታ ደርሰው አየኋቸው። እንደገና ወደኋላ በሰው ውስጥ መሽለኩለክ ጀመርኩ። ነገር ግን ፈፅሞ ልደርስባቸው አልቻልኩም። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሻይ መልስ በር ላይ በተጠንቀቅ ቆሜ ለመጠበቅ ወሰንኩኝ።

ሻይ-ቡና እንኳን ሳልል በሩ ላይ ተገትሬ ስጠብቅ የጠ/ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከሆነ ሰው ጋር እያወሩ ሲመጡ ተመልከትኳቸው። ከአቶ ንጉሱ ጋር ለረጅም ግዜ እንተዋወቃለን። የቁርጥ ቀን ወዳጄ መሆኑን ለማሳየት ያህል አምና ከመታሰሬ አንድ ቀን በፊት “መታሰሬ አይቀርምና በል ቻዎ” ብዬ የደወልኩት ለእሱ ነበር። ከማዕከላዊ እስር ቤት ስወጣ መጀመሪያ የደወለልኝ እሱ ነው። ልክ አጠገቤ ደርሶ “አጅሬው!” ሲለኝ “አብይ’ስ?” አልኩት። “አስቸኳይ ስራ ስላለበት ወደ ቢሮ ሄደ” ሲለኝ ብስጭት ብዬ እጄን አወናጨፍኩ። “ምነው?” ሲለኝ “እኔማ ድንኳንም ሰብሬ ቢሆን እገባለሁ እንጂ በጃንሆይ የግብር አዳራሽ’ማ ሚሊኒዬር አይፈንጭበትም!” አልኩት። ነገሩ ሁለታችንንም አሳቀን! “እንደውም ሃብታም እኮ ግብር አይበላም! ከበላ ደግሞ ሃብታምነቱን የሚያስታውሰው ቢያንስ አንድ ደሃ መኖር አለበት!” ስለው ጭራሽ ከት ብሎ መሳቅ ጀመረ። በሸገር ገበታ ላይ ለመታደም ምን ያህል ውስዋስ ላይ እንደሆንኩ አይቶ መሰለኝ ትንሽ በሳቅ ከተዝናናብኝ በኋላ “እንደ ወትሮ አትረብሽም?” አለኝ። “ኧረ በጭራሽ!” ብዬ በጉጉት አፈጠጥኩ። “በል ነገ ወደ አሜሪካ ስለምሄድ የእኔን ኩፖን እሰጥሃለሁ” ሲለኝ አንገቱ ጥምጥም ብዬ አቀፍኩት። ትላንት ከስብሰባ እንደወጣሁ “በጣም ደስ የሚል ስሜት እየተሰማኝ ነው” ብዬ የፃፍኩት ለዚህ ነው።

የበሸገር ገበታ ላይ የመታደም እድል ካገኘሁ በኋላ የደስታው ብዛት አፍኖ አሊያም በትንታ እንዳይገለኝ መጠንቀቅ ነበረብኝ። በራት ግብዣው ላይ የምለብሰውን ልብስ ላውንደሪ ወስጄ በጥንቃቄ ታጥቦ እንዲተኮስ አደረኩኝ። ከዚያ በእንዲህ ያለ ከባድ የራት ዲቪዞን ላይ ማድረግ ያለብኝን እና የሌለብኝ ነገር ለመጠየቅ ያልደወልኩለት ሰው የለም። ከዚያ ለማኝ አሩን ሳያሩ በጠዋት ተነስቼ የ5ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለውን ኩፖን አቶ ንጉሱ ካስቀመጠልኝ ቦታ ሄጄ ወሰድኩ። ስለ ሸገር ገባታ በፃፍኩት ፅሁፍ ላይ Alex Abreham ሃይለኛ ነቆራ ሰነዘረብኝ። እኔም እየሳቅኩ “ለእናንተ እልህ ስል ዛሬ ድንኳን ሰብሬ እገባለሁ!” ብዬ አቅራራሁ። ያልኩት አልቀረም ከአፄ ሚኒልክ የግብር አዳራሽ ለመግባት ከቱባ ቱባ ሚሊኒዬሮች እና የድርጅት ሥራ አስኪያጆች ጋር በሰልፍ እገባሁ ነው። አጠቃላይ ሁኔታው በትዝታ መቶ አመት ወደኋላ ይወስዳል።

ከዚያ ልብ የሚሰልብ ሽቶ ሸትቶኝና ዞር ስል የመዓዛው ምንጭ መሃደር አሰፋ ሆና አገኘኋት። በቀደም ስለፃፍኩት ሽሙጥ ነግረዋታል ማለት ነው። አንዴ በግልምጫ አንስታ ስታፈርጠኝ ዳግም እሷ ወዳለችበት አቅጣጫ ፊቴን ላለማዞር ወሰንኩ። ስለዚህ ማጅረት ገትር እንደያዘው ሰው ዞር ሳልል ወደፊት መራመድ ጀመርኩኝ። ከታች በምስሉ ላይ እንደሚታየው ዶ/ር አብይ በር ላይ ቆሞ ለእንግዶቹ አቀባበል እያደረገ ነው። ልክ እኔን ሲያየኝ ከትከት ብሎ መሳቅ ጀመረ!! ከዚያ “አንተ ድንኳን ሰባሪ!!” አለኝ። “ድንኳን ሰባሪ” ማለት ምን እንደሆነ ያልገባው ምድረ ቱጃር እሾኳን እንደ አንጨፈረረች ጃርት በዙሪያዬ ያለው ሰው ሁሉ ባንዴ ሸሸኝ!! “ኧረ… አብይዬ በአቶ ንጉስ ኩፖን ነው የገባሁት” ብዬ ቀና ስል በዶ/ር አብይ ቦታ ላይ አፄ ሚኒሊክ ቆመው አየኋቸው። “ልጅ ስዩም! ከእኛ ሌላ ንጉስ አለ እያልክ ነው?” ያሉኝ መሰለኝ። “ጃ…ን…ሆ…ይ!!!” ብዬ ተሰፈንጥሬ ተነሳሁ። ለካስ ቴሌቪዥኑን አላጠፋሁትም ኖሯል! BBC በኦስትሪያ ምርጫ ሊካሄድ እንደሆነ ያወራል። ከዛ የሞባይሌን ሰዓት ስመለከት ከምሽቱ 5:03 ሰዓት ይላል። “ኤጭ” ብዬ ተመልሼ ተኛሁ!!!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *