Tidarfelagi.com

የብሄር ፖለቲካ

አማራ የለም የሚለው ክርክር የሚያሳቅ ነገር አለው። ሌላውን ማንነት ተፈጥሯዊ የማድረግ የዋህ ተግባር ነው።
የትኛውም ሕብረት ሰው ሰራሽ ነው። እንኳን አንድ ብሔር ሀገር እራሱ ከተለያዩ ምናልባቶች ውስጥ በአንዱ ምናልባት የተገነባ አንድ አጋጣሚያዊ ማንነት ነው።

አዎ አማራ የሚባል ማንነት የለም። በዛው ልክ ኦሮሞ የሚባል ማንነትም የለም። ትግሬ በል ሲዳሞ፣ በተለያዩ ተላውጦዎች የተፀነሱ፣ አንዳንዱ ከስሞ የጠፋ አንዳንዱ ቅርፁን ቀይሮ የፋፋ አጋጣሚያዊ ክስተት ነው።

የለም ማለት ግን ነን የሚሉ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም። ለምሳሌ፣ በባይሎጂ ሰፈር ከእናትና አባት ሃምሳ ሃምሳ በመቶ የሚወሰድ ዘረ መል እንጂ ብሔር የሚባል ሥነ ሕይወታዊ ክስተት የለም። ከዚህ ሳይንሳዊ ሀቅ ውጪ ግን ሰዎች እንደማንኛውም ማህበር በፈጠሩት ተረት የጋራ ማንነት ሊገነቡ፣ ሊተባበሩ ይችላሉ። ሀገር እና ብሔርም ከዛ የሚመደቡ እንጂ ሥነ ተፈጥሯዊ ጣት ያረፈባቸው ሀቆች አይደሉም።

ችግሩ የሚመነጨው የለም ከመባሉ አይደለም። ለዓላማቸው ሲባል ሕዝቡን ሁሉ በአንድ አቁማዳ ጨምረው እንትን ብሔር ነህ የሚሉ ሰዎች፣ የሃሳብ ልዩነቱን እንደ ሰዋዊ ባህሪ ከመቀበል ይልቅ «የለም» ብለው አቋማቸውን የገለፁትን ዝም ለማሰኘት የሚሄዱበት ርቀት ነው። በጉዳዩ ላይ አንድም ድምፅ እንዳይሰማ የማድረግ ቶታሊቴሪያን አመለካከት!

ሁለት ችግር ይታየኛል።
አንደኛው የለም ባይ ሰዎች የምር ምንድነው ሃሳባቸው? ብሔር የሰዎች ፈጠራ እና ከደም ጋር ግንኙነት የሌለው እንደመሆኑ በየትኛውም ጊዜ ሊፈጠር እንደሚችል እንዴት ጠፋቸው?

ሁለት፣ አለ ባዩቹ አለ የሚሉት ትልቅ ብሔር በሁለት ሶስት ሰዎች የለም ባይነት የሚከስም ተራ እና ልል ሕብረት አድርገው የለም በተባለ ቁጥር በድንጋጤ ክው የሚሉት ነገር ምንድነው? አለሁ ካልክ በቃል ትፈርሳለህ?

ብሔር ለልዩነቶች በሩ ጠባብ ነው። የአንድ የብሔር ልጆች አንድ ጭንቅላት ያላቸው ብቻ አድርጎ ያስባል። ሀቁ ሌላ ነው። ያ የሰው ተፈጥሯዊ ባህሪ አይደለም። ለፈጠራ ማንነት ተብሎ ተፈጥሯዊ ማንነትን መናድም ደግ አይደለም።

ለልዩነት እድሜ ይስጠው!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *