በጌትነት እንየው ፀሃፊነትና አዘጋጅነት የቀረበውን ‹‹የቴዎድሮስ ራዕይ›› ቲያትር ለመመልከት ትላንት ብሔራዊ ቲያትር ሄድኩ፡፡
ሞቶ በክብር የመኖር ተምሳሌት የሆኑት የአጤ ቴዎድሮስ ታሪክ የማይመስጠው ኢትዮጵያዊ ማን አለ! ቲያትር ቤቱ ቲያትሩ ከመጀመሩ አንድ ሰአት በፊት ሞልቷል፡፡
ቲያትሩ ዛሬ ዛሬ ከጌትነት እንየው ብቻ ልንጠብቀው በምንችለው፣ ጠብቀንም በምናገኘው ደረጃ ተሰርቷል፡፡
ግሩም ነው፡፡
ድንቅ ነው፡፡
የአጤ ቴዎድሮስን ታሪክ ከሽፍትና እስከ መቅደላ ሳያካልብ ግን ሳያሰለች የሚያቀርብ በቴክኒክ ብቃቱ እንከን የለሽ ቲያትር ነው፡፡
ግን ደግሞ እንደሁሉም የዘመናችን ነገር ልማታዊም ነው፡፡
አልፎ አልፎ አጤ ቴዎድሮስን ‹‹ህዳሴኛ››፣ ‹‹ኤፍ ኤም ዘጠና ሰባት ነጥብ አንድኛ››፣ ‹‹ኢቲቪኛ›› እያናገረና እያስፎከረ የሚያስደነግጥ ልማታዊ ቲያትር፡፡
የአጤ ቴዎድሮስን የመቅደላ ስንብት የብአዴን መደበኛ ስብሰባ ላይ የሚቀርብ በሚመስል መዝሙር የሚያጅብ ልማታዊ ቲያትር፡፡
እውነት እላችኋለሁ!
ከድግግሞሻቸው ብዛት የጆሮ ቃር የሆኑብንን ልማታዊ ቃላት ከአጤ ቴዎድሮስ አንደበት ለመስማት መገደድ ያማል፡፡
ለሁለት ሰአታት እንኳን በቲያትር ፈረስ ወደረሳነው ትላንታችን ሄደን ካሰለቸን ዛሬያችን መደበቅ አለመቻላችን ያቆስላል፡፡
ጌትነትን ያህል አርቲስት የአጤ ቴዎድሮስን ታሪክ ‹‹ልማታዊና ለዚህ ትውልድ ፋይዳ ያለው››ለማድረግ ሲውተረተርና ሲያለከልክ ማየት ያደማል፡፡
እኔ እንዲህ እንዲህ እያልኩ በቲያትሩ ላይ ያለኝን አስተያየት ለመወሰን በሃሳብ በምንገላታበት ሰአት፤ ከጀርባዬ ስድስት ሆነው
በእቴጌ ተዋበች ሞት የሚሳለቁ፣
በዘመነ መሳፍንት ታሪክ የሚዝናኑ፣
በመቅደላ ስንብት ትእይንት በሳቅ የሚንተከተኩ ልጆች ይበልጥ ግራ አጋቡኝ፡፡
የሮማንቲክ ኮሜዲ ፊልም ውጤቶች ናቸው፡፡
እጅ አልሰጥም ብሎ ራሱን ባጠፋ ንጉሱ ታሪክ የሚሳለቅ ‹‹እጅ ሰጥቶ የጠፋው›› ትውልድ አባላት ናቸው፡፡
የልጆቹን ሳቅና መሳለቅ በሰማሁ ቁጥር ጌትነት እንየው፤
በዚህ ነገር ሁሉ ‹‹ልማታዊ› ካልተባለ እንደ እፉዬ ገላ በሚቀልበት ዘመን፣
በዚህ የህዝባቸው ህልም የመሪዎች ቅዠት በሆነበት ዘመን፣
በዚህ ታሪክ እንደ ልቦለድ በሚደረስበት ዘመን፣
የሚደረገውን አድርጎ ታሪካዊ ቲያትር ከነ ሙሉ ለዛው ለመድረክ በማብቃቱ ሊመሰገን ብቻ እንደሚገባው ገባኝ፡፡
2 Comments
sehufochesh arife nachew brchlin hiwetachen
እጅግ በጣም አዝናኝ እና አስተማሪ ጵሁፎች ናቸው ቀጥሉበት