Tidarfelagi.com

የነገን አልወልድም

“መላኩ ተፈራ፣ የእግዜር ታናሽ ወንድም
የዛሬን ማርልኝ፣ የነገን አልወልድም”

በቀይ ሽብር አመታት ልጆቻቸውን ለሞት መገበር ያንገፈገፋቸው እናቶች መላኩ ተፈራ ጎንደርን ያስተዳድር በነበረበት ዘመን ይሉት የነበረ ግጥም ነው።

የአማርኛ ፊልሞችን አያለሁ።
አረረም መረረ አይታክተኝም…በትጋት አያለሁ።
የውድቀታችን ባንዲራ ለመሆን በተርታ ከተሰለፉ ፊልሞቻችን መካከል ግን ‹‹ ይሄ ታሪኩ ያልተለመደ ነው››፣ ‹‹ይሄ ቀረፃው የመጠቀ ነው››፣ ‹‹ይሄኛው ደግሞ ትወናው አስደማሚ ነው›› እያልኩ ፣ ከነ ቅሬታዬ፣ ሁለት ልብ ሆኜም ቢሆን የወደድኳቸው ትንሽ የማይባሉ ፊልሞች አሉ።
‹‹ለእንከን የለሽነት የቀረቡ ናቸው›› የምላቸውን ለመቁጠር ግን ከአንድ እጄ ጣቶች በላይ ፈጅቶብኝ አያውቅም።
ቆጠራዬ ‹‹እንትን አንድ፣ እንትን ሁለት…እንትን ሶስት…እና…እ..አዎ…እንትን ደግሞ አራት›› ከሚል አያልፍም።
ትላንት የተመረቀው ‹‹የነገን አልወልድም›› የተባለው የአብርሃም ገዛኸኝ ፊልም ከነዚህ ውስጥ የሚቆጠር ነው።
በልሽቀት መሃከል ልህቀት፣
በውድቀት መሃከል አስደማሚ ብቃት፣
በኮከብ የለሽ ሰማይ ላይ አብሪ ኮከብ የሆነ፤
ለእንከን የለሽነት የቀረበ እፁብ ድንቅ ፊልም።

https://youtu.be/S8kz8ZSp1-g

በገነነ ሊብሮ ‹‹ኢህአፓ እና ስፖርት›› ላይ ተመርኩዞ የተሰራው ‹‹የነገን አልወልድም›› ፊልምን ልምድ ባለው ተመልካች አቅም ስገመግመው፤ ቅር የሚያሰኝ ነገር ለመፈለግ ሌሊቱን ሙሉ የሚያለፋ ግሩም ፊልም ነው።

ለዋዛ ፈዛዛ ተጨብጭቦ ለቁም ነገር ማዛጋት በነገሰበት በዚህ ፈታኝ ዘመን…
ሀገራችን በአንደኛ ደረጃ ፊልም ሊነገር የሚችል አንደኛ ደረጃ ታሪክ እንዳላት፣
ሊነገር የሚችል አንደኛ ደረጃ ታሪክ እንዳላት የሚያውቁ እዚሁ የተፈጠሩ አንደኛ ደረጃ የፊልም ባለሙያዎች እንዳሏት ፤
ኖረዋትም ይህን ታሪክ ሊነገር በሚገባው አግባብ መንገር የሚያስችል ንቃት እና ብቃት እንዳላቸው ያየሁበት ፊልም ነው።
ማስታወቂያ አልወድም…ግን ይህንን ፊልም አይቼ ለናንተ አለመንገር ንፍገት መስሎኛል እና… የሚጥምም ጥም የሚቆርጥም የሀገራችሁ ፊልም ያማራችሁ ወዳጆቼ ሳይረፍድባችሁ ሄዳችሁ እዩት!

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *