ትላንት ማታ ክፉ ነገር ተፈጠረ።
መልከ መልካሙ እና ገራገሩ እጮኛዬ ላይ ማገጥኩበት።
ያች በልጣጣ ጓደኛዬ ትዕግስት ናት እዚህ ሁሉ ጣጣ ውስጥ የከተተችኝ። ሁሌም ለሰኔ ሚካኤል ቤቷ ድል ያለ ድግስ ታዘጋጃለች። የምታውቀውን ሰው ሁሉ ትጋብዛለች። ከልክ በላይ ታበላለች። ከመጠን በላይ ታጠጣለች። አንድ ውስኪ ለሶስት ሰው እየቀረበ፣ በረዶ አንሷል እየተባለ ውስኪ እንደተፈጠረ በጉሮሮ ሲንቆረቆር፣ ሰዉ ሁሉ ከማያውቀው ሰው እንደ አብሮ አደግ ይሳሳቃል፣ ያሽካካል። ምስጢር ይጋራል። ይሟዘዛል። የትእግስት ፓርቲ እንዲህ ነው። ነጠላ ሆኖ የመጣን፣ ጥንድ አድርጎ ይሸኛል። አይተው ከማያውቁት ሰው አደጋግፎ፣ አስተቃቅፎ አልጋ ድረስ ያጓትታል።
ውስኪዋ ውስጥ ትንሽ ቅንዝር ጠብ፣ ብዙ የፍትወት ፍላጎትና የመማገጥ አላማ ሙጅር ታደርግበት ይመስል፣ በየዓመቱ የሚወራ የወሲብ ገድል መነሻ ይሆናል።
ለስድስት ዓመታት ይሄንን የተቀበረ የመጠጥ ፈንጂ አልፌ ዘንድሮው ግን ረገጥኩት። እርግጥ አድርጌ ብ—–ው—-አደረግኩት። አጀማመሩ እንዲህ ነበር።
ጥሬ እና ጥብሱን ሥጋ ለሳምንት አትበሉም የተባልን ያህል ተስገብግበን ጎስረን ጎስረን፤ ‹‹እሰቲ አወራርዱት…እስቲ ጥረጉት›› እያለች የምታስተናብረውን ትዕግስት እየሰማን፣ ሁለት ጠርሙስ ውስኪያችንን በጉሮሯችን እያንቆረቆርን ስድስት ሆነን አንድ ጠረጴዛ ላይ ተሰይመናል።
ከለብታ አልፎ ሞቅታ፣ ከሞቅታ አልፎ ስካር ሲጀማምረኝ ትዕግስት ወደ ጠረጴዛችን መጥታ ‹‹አወራርዱት›› ባለች ቁጥር የሞት ሞቴን የብርጭቆዬን አፍ በእጆቼ ለመክደን ብሞክርም፣ ልክ ትንኝ እንደምታባርር ሁሌ እጄን ጧ እያደረገች ታስከፍተኝና በውስኪ ሞልታው ትሄዳለች።
ቺርስ ባሉ ቁጥር እጠጣለሁ።
አትጨምሪልኝ…በቃኝ እያልኩ በእጄ ብርጭቆውን ለመዝጋት እሞክራለሁ።
እጄን ጧ አድርጋ ብርጭቆዬን አስከፍታኝ ሞልታው ትሄዳለች።
ቺርስ ባሉ ቁጥር እጠጣለሁ።
አትጨምሪልኝ… በቃኝ እያልኩ በእጄ ብርጭቆውን ለመዝጋት እሞክራለሁ።
እጄን ጧ አድርጋ ብርጭቆዬን አስከፍታኝ ሞልታው ትሄዳለች።
ይሄ አዙሪት ለአስራ ምናምን ጊዜ እንደቆየ ሳሙኤል ከፊቴ ተከሰተ። ያንን ሰንደቅ የሚያሰቅል ቁመቱን፣ የቀይ ዳማ የደስ ደሳም ፊቱን፣ ቦርጭ አልባ ሰውነቱን ይዞ ሳሙኤል ከፊቴ ተከሰተ። ያውም አንዴ ሁለት፣ አንዴ አራት፣ አንዴ ስድስት ሆኖ… ሞቅታዬ አብዝቶት፣ ስካሬ አባዝቶት የቀድሞ ፍቅረኛዬ ሳሙኤል ከፊቴ ተከሰተ።
ሲቀመጥ ትዝ አይለኝም። እጆቼን ሲያሻሸኝ ግን ትዝ ይለኛል። መጀመሪያ ሲስመኝ ትዝ አይለኝም። አፌን አፉ ውስጥ ሳገኘው ትዝ ይለኛል። መኪናው ውስጥ መግባቴን አላስታውስም። አልጋው ውስጥ መግባቴ ግን ውል ይለኛል። ልብሳችንን ስናወልቅ ትዝ አይለኝም። ያ መልከመልካም ራቁት ሰውነቱ ግን በደንብ ትዝ ይለኛል።
ከንፈር እየተሻማን ስንቃበጥ፣ አንገቴን ሲልስም ሲስምም፤ ኋላም ሴትነቴን በወፍራም ወንድነቱ ሲከድን መሃሉ መሃሉ ጭለማ በገባበት ሁኔታ ትዝ ይለኛል።
ይሄው ነው።
ጠዋት ላይ፣ አልጋው ውስጥ ከሚፈልጥ ራስ ምታት ጋር ስነቃ፣ ትላልቅ ዐይኖቹ ተቀበሉኝ።
ራሴን በሁለት እጆቼ ካልደገፍኩ ቷ ብሎ የሚፈነዳ ስለመሰለኝ፣ በቀኝም በግራም እጆቼ ጭንቅላቴን ይዤ ከወገቤ በላይ ብድግ አልኩና፤
‹‹ምንድነው …! ምንድነው ያደረግነው?›› ብዬ ጩህኩ። ሳሙኤል ትላልቅ ዐይኖቹን ፊቱ ላይ እያንጎማለለ ሲያየኝ የራሴ ጩኸት ራስ ምታቴን እያባሰው ከወገቤ በታች አየሁ። እንደፈጠረኝ ነኝ።
‹‹ሳሙኤል..እዚሀ እንዴት መጣሁ…?ምንድነው ያደረግነው….?›› አልኩ በአንሶላው ተጠቅልዬ ከአልጋው የመሸሽ ያህል እየወጣሁ።
ከአልጋው ፈንጠር ብሎ ወጣ። ቁምጣ ከሚያህል ቡራቡሬ የውስጥ ሱሪ ሌላ ምንም አላደረገም።
‹‹ሆሆሆ ! ምንድነው ያደረግነው? ካርታ ስንጫወት ነዋ ያደርነው›› አለኝ ሣቅ በተቀላቀለው ድምፅ።
ዝም ብዬው ልብሶቼን ፍለጋ ጀመርኩ።
ሮዝ ጡት ማስያዣዬን አልጋው ግርጌ፣ ጥብቅ ያለው ቀይ የድግስ ቀሚሴን ከአልጋው በስተቀኝ መሬት ላይ አግኝቼ በሰማያዊው ለስላሳ አንሶላ እንደተጠመጠምኩ ወደ ማውቀው መታጠቢያ ቤት ገብቼ ፊቴን ሳልታጠብ መስታወቱ ፊት ቆምኩ።
ምንድነው የሠራሁት?
ምን ነካኝ?
እሺ ለብ ይበለኝ። እሺ ሞቅ ይበለኝ። እሺ ልስከር። እሺ እጄን እንዲይዝ ልፍቀድለት። እሺ ሲስመኝ ልሳመው። እሺ ትንሽ ልቃበጥ። ግን ምንስ ያህል ብጠጣ ከትእዕግስት ቤት ወጥቼ፣ መኪናው ውስጥ ገብቼ፣ ከብስራተ ገብርኤል ሰሚት ድረስ ንፋስ እየመታኝ መጥቼ፣እቤቱ ሄጄ፣ መኝታ ቤቱ ገብቼ፣ አልጋው ጋር ሄጄ፣ አልጋው ውስጥ ገብቼ፣ ልብሴን አውልቄ፣ ራቁቴን ሆኜ፣ እጮኛ (ያውም የሰው ጥግ) እያለኝ ከቀድሞ ፍቀረኛዬ ጋር ስዳራ ማደሬ ልክ ነው?
ለመልአክ ሩብ ጉዳይ በሆነ እጮኛዬ ላይ መልከስከሴ ግፍ አይደለም?
ቢሰማ አያብድም?
ቢያውቅ ራሱን አያጠፋም?
ፊቴን በቅጡ ሳልታጠብ ከመታጠቢያ ቤቱ ወጥቼ በጥድፊያ ጫማዬን አድርጌ፣ ቦርሳዬን አነገብኩና ምናምን የሚለኝን ሳሙኤል ሙሉ በሙሉ ዘግቼ እግሬ በፈቀደልኝ ፍጥነት ቤቱን ለቅቄ ወጣሁ።
የኮንዶሚኒየሙን ደረጃ እየወረድኩ ስልኬን አወጣሁ።
19 ያመለጡኝ ጥሪዎች። 7 የጽሑፍ መልዕክቶች።
ከፈትኩት።
16ቱ የእጮኛዬ ጥሪ ነው። ስማግጥ ያልመለስኳቸው 16 ጥሪዎች። እርምጃዬን አቁሜ እጄ እየተንቀጠቀጠ መልእክቶቹን ከፈትኳቸው። ሁሉም ከእሱ ናቸው። ‹‹ማሬ ስልክ አታነሺም…/በሰላም ነው…/አረ ተጨነቅኩ/…በደህናሽ ነው…እባክሽ ደውይልኝ…/ትዕግስትም አላነሳ አለችኝ…የት ነሽ….
በናትሽ ደውይልኝ….››
ኮንዶሚኒየሙ ጣራ ላይ ወጥቼ መፈጥፈጥ አማረኝ።
ልደውልለት ግን ጉልበት አጣሁ። እሱን ትቼ ትዕግስት ጋር ደወልኩ። በሁለተኛው ዙር ጥሪ አነሳች።
ሰላምም ሳልላት ‹‹አንቺ ማታ ምንድነው የተፈጠረው?›› ብዬ ጮህኩባት
– እንዴ እኔ ምናባሽ አውቅልሻለሁ…የት ሆነሽ ነው…? አለችኝ። ድምፅዋ ቤተክርስትያን ሲያስቀድስ አድሮ የመጣ ሰላማዊ ሰው እንጂ አሸሼ ገዳሜ ሲል ያደረ አይመስልም።
– ምን የት ነሽ ትይኛለሽ….ሳሚ ጋር ነበርኩ…እንዴት እንዲህ አይነት ነገር ሲደረግ …እዚህ ሲያመጣኝ ዝም ትያለሽ? አልኩ ቱግ ብዬ እርምጃዬን እያፈጠንኩ
– እንዴ…ኧረ ቀስ…!አንቺ አይደለሽ ስንት ሆነን ስንለምንሸ ከእሱ በስተቀር ማንም ጋር አልሄድም እያልሽ እንደ እባብ ስትጠመጠሚበት ያመሸሽው? አለችኝ ቆጣ ብላ
ወሬውን በስልክ መቀጠል ስላልፈለግኩ ቤት መሆኗን አረጋግጬ በኮንትራት ታክሲ ስበር ቤቷ ደረስኩ።
በስልክ የጀመረችልን አጠናክራ ለያዥ ለገናዥ ማስቸገሬን፣ ያየኝ ሰው ሁሉ ሲሥቅ እንደነበር፣ መጨረሻ ላይ እንደፈለጋት ትሁን ብለው እንደተዉኝ በሚያም ዝርዝር ነገረችኝ።
ያቀረበችልኝን ቁርስ ሳልነካ ሻዩን ብቻ እየማግኩ፤
‹‹ቲጂ…›› አልኳት
– ወይ… አለች አይን አይኔን እያየች
– ደሬ የሚሰማ ይመስልሻል…? ማለቴ ሰው ቢነግረውስ? አልኳት
– እህ …አይመስለኝም…ደግነቱ እንደዛ ስታብጂ የነበረው አብዛኛው ሰው ከሄደ በኋላ ነው…ማለቴ ሳሙኤል ካልተናገረ…አለችኝ።
ሳሙኤል ካልተናገረ!
በተቀመጥኩበት መርዶ እንደተረዳ ሰው ከወገቤ በላይ ወደፊትና ወደኋላ ሄድ መለስ እያልኩ፣ አፌን በእጆቼ እየያዝኩ፣ የተመሳቀለ ጸጉሬን እየፈተልኩ ፣አፍጥጬ እያየኋት ጠየቅኳት።
– ቲጂዬ…ሳሙኤል የሚነግረው ይመስልሻል…? ድምፄ እየተንቀጠቀጠ
– ነገሩን አልኩሽ እንጂ የት ተገናኝተው ይነግረዋል…?
ኡፎይታ ተሰማኝ።
– ግን….በሰው በሰው እንዳይሰማ መጠንቀቅ አለብሸ…
እፎይታዬ ተነነ።
የምሆነው ጠፋኝ። ተንስቼ አንዴ ወዲህ አንዴ ወዲያ በጭንቀት ስንጎራደድ ዝም ብላ ታየኛለች።
‹‹ኩኩዬ በቃ ረጋ በይ…ዋናው እኮ ይሄ ወሬ ከሳሙኤል ወደ ደሬ የሚደርስበትን መንገድ ካለ ማሰብ ነው…ማለቴ የወሬውን መንገድ ማጥፋት… አለ አይደል… ዱካ ማጥፋት…›› አለችኝ ትንሸ ቆየት ብላ።
በግርምት ዐየኋት። ልክ ናት። በጣም ልክ ናት።
‹‹ሳሙኤልንና ደሬን የሚያገናኛቸው ነገር ወይ ሰው አለ..?››አለችኝ ቶሎ ብላ።
ቲጂ ከመርዛማ ውስኪ ውጪ የፖሊስ ጭንቅላት ነው ያላት።
የውስልትና ዱካዬን ለማጥፋት አብሬው በወሰለትኩት ሳሙኤል እና በእጮኛዬ መካከል ያለውን የግንኙነት መስመር ማሰብ፣ የመማገጤን ወሬ ወደ እጮኛዬ ደሬ ሊያደርስ የሚችለውን መንገድ ማሰላሰል ጀመርኩ።
ኦኬ…ሳሙኤል…
ሳሙኤል ጋር መደወል አለብኝ።
ባለሁበት እየተንቆራጠጥኩ ደወልኩለት
– ሄሎ ሳሙኤል ..የት ነህ?
– ሄሎ…ቢሮ ነኝ…ምነው እንደዛ ቻው እንኳን ሳትይኝ በናትሽ…?
– በናትህ ሳሙኤል ጊዜ የለኝም…ስማ ይልቅ…
– እ…?
– ስለ ተፈጠረው ነገር ለማንም አላወራህም አይደል…?በናትህ ለማንም እንዳትናገር….
– እህም…ካሁን በኋላ አልናገርም እሺ…( ሳቀ።)
– ሳሙኤል በማርያም! አታሹፍ…እጮኛ እንዳለኝ ታውቃለህ…በናትህ ለሰው ነገርክ እንዴ…?
– ዌል…ለዳጊ ነግሬዋለሁ ኦልሬዲ…
ሃሞቴ ፈሰሰ። ውሃ ልኬ ተዛባ።
ትንፋሽ ሰብስቤ፣
– ማነው ዳጊ…ዳጊ ማነው?
– እንዴ…!ዳግምን ረሳሸው እንዴ…የዛሬ ወር አካባቢ ቃተኛ አግተሸኝ ያስተዋወቅኩሽ የቢሮ ጓደኛዬ ትዝ አይልሽም…?
– እህህ…እንዴ…አብሮህ የሚሰራው ቀዩ ልጅ ባልሆነ…አብሮህ የሚሰራው ያ ቀዩ ጸጉረ ሉጫው ልጅ ነው?
እንደ ጉድ ተርበተበትኩ። እንደ ጉድ ተንተባተብኩ።
መሆኑን ነገረኝ፡
ዳግም ሰማ አልሰማ ጉዳይ ኖሮኝ አይደለም መርበትበቴ። ብርክ የያዘኝ ዳግምን አንድ ሁለቴ ከእጮኛዬ ደሬ እህት ጽዮን ጋር ካፌ ቡና ሲያንቃርር ስላየሁት ነው።
ተበጠበጥኩ።
– ሳሙኤል…በናትህ የዳጊን ቁጥር ስጠኝ…ልደውልለት….. አልኩ በድንጋጤ በሰለለ ድምፄ።
– እ…ኦኬ…ቴክስት አደርግልሻለሁ አለኝ በፍጹም ግዴለሽነት።
ስልኩን ዘግቼ ወዲህ ወዲያ እየተራመድኩ፣ ባሏ እንደሞተባት ባልቴት ወገቤን ይዤ እያረገድኩ ቁጥሩን ስጠብቅ ማን ደወለ?
ጽዮን።
ኦህ- ማይ -ጋድ!
የማደርገው ጠፍቶኝ አንዴ ስልኩን፣ አንዴ ቲጂን እያየሁ ስርበተበት አንደኛው ጥሪ አበቃ። የሚካሄደው ነገር ያልገባት ቲጂ ‹‹ንገሪኝ እንጂ…ምንድነው እሱ…?!›› እያለችኝ ጽዮን እንደገና ደወለች።
አነሳሁት።
– ሄሎ…አልኩ አሁንም በሰላላ ድምፄ
– አንች ሸርሙጣ! ድሮም አውቄው ነበር፡….አይ ኔቨር ላይክድ ዩ! ለኔ ወንድም እንደማትመጥኚ አውቀው ነበር…ሸ-ር-ሙ-ጣ ነገር ነሽ!
አለቀልኝ።