Tidarfelagi.com

የአባዬ መደረቢያ

ያኔ …ከዛ ከኛ ቤት ከባሰ አመዳም ደሃ ጎረቤታችን ቦቸራ ሳረግዝ…… ለአባዬ ውርደቱ ሆንኩ። በየሴሚስተሩ አንደኛ እየወጣች ስሙን የምታስጠራው ልጁ በአንድ ቀን ስህተት አፈር ከድሜ ገባች።

… ወራት ነጎዱ… ትምህርቴን ከ11 ተውኩት። ልጄን ገጠር አክስቴጋ ሄጄ ወለድኩ።…… የአባዬ ውርደት የነበረው ሌባው ወንድሜ የቤቱ ኩራት ተባለ።…… ሰርቆ እቃ ቢያመጣ እንጂ ልጅ ይዞ አልመጣማ……!!!
ከሩቅ ያኔ ቀጥሎ……

እኔ ነኝ ያለ በቅሌቱ መንደር ያወቀው ሀብታም እጄን ለትዳር ጠየቀ። ከነ ልጇ አንቀባርሬ አገባታለሁ አለ። ደስተኛ እሆን እንደሆነ አይደለም የተጠየቅኩት። ሽማግሌዎቹ ከቤት እንደወጡ ምን ያህል እንዳኮራሁት ነበር አባቴ የነገረኝ።

…… ጊዜው ግድ አለው?… ወራት ነጎዱ… ድል ባለ ሰርግ ተዳርኩ።… ልጄን እና የበደነ ልቤን ይዤ ብዙ ቅምጥ ያለው ባሌ ቤት ገባሁ።
እሙሙዬ እኔ ጭኖች መሃል ተለጠፈች እንጂ በእድሜ ቁጥሬ እንደገባኝ የአባዬ መደረቢያ ናት።

በሱ ሚዛን የማይሆን ሰው “አክሱም” ሲጎበኛት
“ያለእናት አሳድጌሽ አዋረድሽኝ። የሰፈር መሳለቂያ አደረግሽኝ። ማቅ አለበሽኝ።” እያለ ነጠላ ወጉን የሚለቅባት ፤ በሱ ልኬት ክብሩን የሚመጥን ሰው አክሱም ሲጎበኛት “አኮራሽኝ ልጄ… ወግ ማዕረግ ክብር አሳየሽኝ።” እያለ ድርብ ወጉን የሚጠርቅባት……
ክብርም ሆነ ማቅ የትኛው የሰውነት አካል ላይ እንደሚንሳፈፍ ባይገባኝም። የእኔ እሙሙ ግን የአባዬ አንገት ላይ ጣል እንደሚደረግ መደረቢያ ትመስለኛለች። አንዴ ማቅ ሆና የምታንቀጠቅጠው … ሌላ ጊዜ ክብር ሆና የምታሞቀው……
ቅርብ ያኔ ለታ…

ሀብታሙ ባሌ በወንጀል ታስሮ የምኖርበትን ቤት ጨምሮ ንብረቱ በሙሉ ተወርሶ ወደ ቤት ስመለስ። አሁንም አባቴን የሰፈር መጠቋቆሚያ አደረግኩት።
ትንሽ ከአሁን ቀድሞ……
ልጄን ጥዬ አረብ አገር ሄጄ ብር መላክ ስጀምር። ድሮምኮ ልጄ መኩሪያዬ ናት አለኝ አባቴ……
…… ጊዜው አብሮ ምን እንደሚያንገዋልል መች ቅም ይለዋል?… አመት ነጎደ…… የምሰራበት ቤት ሴትዮ በቃሽኝ ባሌ ዓይኑ አርፎብሻል ብላ አባረረችኝ።…… ስራ ማግኘት አልቀለለኝም። ውበቴን ያየ ደላላ በሙሉ አረብ ባጫውት ብዙ ብር እንደምሸቅል መከረኝ።
አባቴን የምጠላው ጊዜ ይበልጣል።…… ግን መገላገል በማልችለው ዓይነት ልክፍት የሱ ኩራት መሆን እፈልጋለሁ። አኮራሽኝ እንዲለኝ እንጂ አዋረድሽኝ እንዲለኝ አልሻም። አሁን ደግሞ ከእርሱ በተጨማሪ የልጄ ኩራት ለመሆን ነፍሴን እሰጣለሁ።
አሁን እለት……

አንደኛ ደረጃ ሸርሙጣ ሆንኩ።…… ለአባዬና ለልጄ ክብሬን መሰረት ድንጋይ ጥዬ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ገነባሁ።…… አባቴ ክብር ደረበ።…… ከአንገቱ ቀና ብሎ በኩራት ሰፈር ውስጥ ተንቀዋለለ።…

“ልጄ ካሰችኝ! ፐ ከወለዱ አይቀር አንድ የእኔን ልጅ ዓይነት ነው እንጂ… ” እያለ የወግ አልበሙን ለቀቀ።……
ክብሬን ደጋግሜ መሬት አንጥፌ ለልጄ በቋሚነት ወጪ የሚሸፍንለት ሚኒባስ ገዛሁ።………

ከዛ ግን በቃኝ አልኩ። ለአባቴ ክብር ልደርብ እኔ ደጋግሜ ተዋረድኩ። የእርሱ ኩራት ለመሆን ደጋግሜ ተናቅኩ።…… በቃኝ አልኩ። ያለኝን ይዤ ሀገሬ እገባለሁ። በቀረኝ ዘመን ራሴን ላክብር…… ደሞ ራሴ ልኑር አልኩኝ …. እና ውሳኔዬን ልነገረው ደወልኩ።
“አባዬ ልመጣ ነው። ጠቅልዬ ልመጣ ነው።… ለልጄ እናት ልሁነው።… ባለኝ ገንዘብ የሆነውን ሰርቼ እንኖራለን።”
“እንድች ብለሽ እግርሽን ወዲህ እንዳታነሺ…… ተዋርደሽ አዋረድሽኝ!! እዛ ምን እንደምትሰሪ ጉድሽን የአይናለም ልጅ መጥታ ነገረችኝ።… ቤት አለኝ ብለሽ እንድች እንዳትሞክሪያት ነው የምልሽ…… ”
…… ጨርሰናል!!………

One Comment

  • Melaku commented on September 13, 2022 Reply

    You are correct!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *