ስመጥሩ የእስልምና ታሪክ ተመራማሪና ፀሃፊ አህመዲን ጀበል ለ‹‹ከመጋቢት እስከ መጋቢት›› በተቀረፁት አጭር ቪዲዮ ላይ የተጠቀሟት ታሪክ ደስ አለችኝና አመጣሁላችሁ።
ታሪኳ እንዲህ ትላለች።
አንድ መሪ ህዝቡ ምን ያህል እንደሚወደው ለማውቅ ፈለገና አደባባይ ላይ ትልቅ በርሜል አስቀምጦ ህዝቡን እንዲህ ብሎ አዘዘ። ‹‹የሚወደኝ ሰው ሁሉ አንድ አንድ ኩባያ ወተት እያመጣ እዚህ በርሜል ውስጥ ይጨምር!››
ትእዛዙ መፈፀም እንደጀመረ፣ ከህዝቡ መሃከል አንድ ሰው መጣና ‹‹ሁሉም ሰው ወተት ይጨምራል። እኔ ውሃ ብጨምር ምን ለውጥ ያመጣል? ደግሞ የሚያይ ሰውም የለም›› አለና ኩባያ ሙሉ ውሃ ጨመረ።
በዚህ ሁኔታ ሁሉም የድርሻውን ሲጨምር ቆየና መጨረሻ ላይ በርሜሉ ሲከፈት በሙሉ ውሃ ሆኖ ተገኘ።
ለካስ ሁሉም ሰው ልክ እንደዚህኛው ሰው ‹‹ሁሉም ወተት ስለሚጨምር እኔ ውሃ ብጨምር ልዩነት የለውም›› እያለ፣ የራሱን ሃላፊነት ሳይወጣ ውሃ በመጨመሩ ሙሉ በርሜሉ በወተት በመሞላት ፈንታ በውሃ ተሞልቶ ኖሯል!
አሪፍ ታሪክ ናት። በተለይ ለዛሬዎቹ እኛ በልካችን የተሰራች አሪፍ ታሪክ ናት።
እኛ፤ ወተት ሙሉ በርሜል እንመኛለን ሆኖም ግን ኩባያችንን በውሃ ሞልተን ከበርሜሉ እንጠጋለን።
በወተት ፈንታ ውሃ መጨመራችንን ሌላ ሰው አያይም ብለን ኩባያ ሙሉ ውሃ በርሜሉ ውስጥ እንቸልሳለን።
ይሄ ብቻ አይደለም፤ ጭራሽ በርሜሉ ውሃ ብቻ ሆነ ሲባል ‹‹ይህ እንዴት ይሆናል!›› ብለን ቡራ ከረዩ እንላለን።
ኢትዮጵያ የምትለወጠው እኛ፣ እያንዳንዳችን የምንሰራው ስራ ለውጥ ያመጣል ብለን ስናምን፣ አምነንም የድርሻችንን ሳናጭበረብር ስናዋጣ መሆኑን እንረሳለን።
ሃገራችን የምትለወጠው እኛ በተለወጥነው ልክ ብቻ መሆኑን አውቀን እንዘነጋለን።
ለሁሉም፣ ‹‹ሃገሬ ሃገሬ ›› እያሉ ከመጮህ ውጪ ፣ ሃገራችንን እንደ ትልቅ የወተት በርሜል አይተን፣ ‹‹ለመሆኑ የእኔ ኩባያ ባለ ወተት ነው ባለ ውሃ?›› ብለን መጠየቅ የመጀመሪያው እርምጃ ነው።
One Comment
Lk bleshal ehte