(የዚህ ፅሁፍ ባለቤት፣ እራሱን ከትውልዱ መገለጫዎች አልነጠለም፣ አይነጥልም። ፅሁፉም ፍፁም ጅምላ ምደባ አይደለም)
ይሄ የኔ ትውልድ የተካደ ትውልድ ነው። ከገዛ ዘመኑ ተገፍቶ ላለመውደቅ ፈፋ ዳር የሚውተረተር ምስኪን። ሀገር የሚያስረክቡት መስሎት ደጅ በመጥናት ሲንከራተት ቆይቶ ገሚሱ ወደ ሃይማኖት ቤት፣ ገሚሱ ወደ መጠጥ ቤት፣ ገሚሱ ወደ ቴክኖሎጂ ዋሻዎች፣ ሌላው ወደ ጫት የተሰደደ፣ ቀሪው በእግር ኳስ ያበደ። ከኋላው «ከንቱ ትውልድ» የሚል የሂያጁ ትውልድ ስድብ የሚከተለው።
ለሁሉ ነገር አቋራጭ ያሰላል። ዲቪ ይማጠናል። ነገሩ ሁሉ ለብ ለብ ነው።ፍቅሩ ለብ ለብ። እውቀቱ ለብ ለብ። ጥልቀት ይጨንቀዋል። አለመደውም። አላስለመዱትም።ለዚህ ለኔ ትውልድ «ሀገር ማለት፣ ወደ ተሻለ ሀገር እስኪሄዱ የሚጠለሉበት መጠባበቂያ ቤት ነው»
ወዲህ የአያቶቹ ባህል ይስበዋል። ወዲያ የወዲያ ዓለም ባህል በጥቅሻ ይጠራዋል። በሁለቱ መሃል ተሰትሮ ይወዛገባል። ቅዳሜ ሲጨፍር አድሮ፣ እሁድ ጠዋት ቸርች ይስማል።
ከአባቶቹ የወረሰውን ለብሔር መጮህ ወርሶ ጉሮረው የሰለለ፣ ርዕዮተ ዓለሙ የቀለለ፣ «ሳር የሚበሉትን ስንጠላ፣ ግንድ የሚበሉ መጡብን ብሎ» በሙሰኞች የደነገጠ።የተደናገረ ነው። ብሔርተኛው በብሔርተኛነቱ የኮራ፣ ከተሜው ከተማነቱ እንደ ሰማያዊ ፀጋ ያየ…ቀሪውን የናቀ ነው።የሰጡትን ሳይፈትሽ፣ ያለፈ ዘመን በረከት ሁሉ ውብ ነው ብሎ የተቀበለ የሚመስል ነው። መናናቅን በብላሽ የሚገበያይ የአባት እናቶቹ ልጅ ነው።
ይሄ የኔ ትውልድ፣ ከሀገሩ ለመውጣት የሞት መንገድ የሚደፍር፣ አምላኩን ሌት ተቀን ንቀለኝ ብሎ የሚማፀን፣ ዘመኑን ቀምተው «ስራ ፍጠር» እያሉ የሚቀልዱበት ምስኪን ነው።
ዘመኑን ሲነጥቆት፣ለማስለቀቅ የማይደፍር «ከደላቸው ይኑሩበት» ብሎ ሀገሩን የሚለቅላቸው፣ በየቤተ እምነቱ ገብቶ፣ ስልጣን አጋንንት መሆኑ በልቡሰ ጥላው ገብቶት «ልቀቅ» የሚል ጨዋ ትውልድ ነው።
«ሀገር እንወዳለን» የሚለው ቃል፣ እፊቱ ዓመድ ሲለብስ ያየ፣ «ያየ አይታለልም» ብሎ ሀገሩን ከልቡ፣ ልቡን ከመሬቱ የነቀለ ስደተኛ ትውልድ ነው።
«አይ ዘመን» ለሚል የታካች አንደበት ማማሿ የሆነ፣ የተገፋ… መገፋቱን መልሶ ያልተጋፋ ነው።
ታሪክ መማሪያ ነው ሲሉት፣ «መጣያ መሆኑንም» ያሳየ «ምሳሌ» ትውልድ ነው።
እግሩን ይዘው ሂድ የሚሉት፣ የእግሩ መያዝ ያልገባው፣ እዛው እዛው የሚጣደፍ። ቀሪው ዓለም በእግሩ መሃል የሚያመልጠው።
«የምን መጨነቅ» የሚል ዘፈን የሚያሰምጠው ነው።
በልጅነቱ ቤተሰብ፣ በነብስ ማወቁ ዘመን የመንግስት ዱላ ደጋግሞ የሚጎበኘው «የዱላ ቅብብል» ማካሄጃ መም ነው።