ሕይወት አዲሱ ቦይፍሬንዷ ደረሰ ቤት ናት፡፡
ግንኙነታቸው የወራት ግን በፍጥነት እየጠበቀ ያለ ነው፡፡
ለወትሮው የአማካሪነት ስራውን በአመዛኙ ከቤቱ የሚሰራው ደረሰ ዛሬ ከጓደኞቹ ጋር ቁርስ ሊበላ በጠዋት ወጥቷል፡፡
ከጠዋቱ አምስት ሰዐት ቢሆንም እስካሁን በፒጃማ ስትንጎማለል የቆየችው ሕይወት የቤት ውስጥ ቢሮው ገብታ ልትሰልለው ወሰነች፡፡
ከደረሰ ጋር ፍቅር ከጀመረች አንስቶ እንዲህ ያለ ነገር አድርጋ አታውቅም፡፡
ከሳምንታት በፊት የላፕቶፕ ፓስወርዱን ‹‹ኢሜይል ቼክ ላድርግ›› ብላ ስትጠይቀው ያለማንገራገር ቢሰጣትም እንዲህ ያለው ነገር አልሞካከራትም፡፡
ታዲያ ዛሬ ለምን ልትሰልለው ወሰነች?
ብዙ ምክንያት አላት፡፡
ገራገርና ሰው አማኝ፣ ለሳቀላት ሁሉ ምስጢሯን ዘርጋፊ ብትሆንም ከደረሰ በፊት የነበሩ ፍቅረኞቿ በሙሉ በብዙ አቅጣጫ ጎድተዋታል፣ በብዙ ስለት ብዙ ቦታ ወግተዋታል፡፡ ሁሉም እምነታቸውን አጉድለው ማግጠውባታል፡፡ ልቧን በሃዘን እምሽክ አድርገውታል፡፡
በዚህ ሁሉ ስቃይ ውስጥ የተማረችው አንድ ነገር ቢኖር ከመከዳቱ በላይ የሚያመው ክህደቱ ሳይጠበቅ መከሰቱ ነው፡፡
ስለዚህ ዳግመኛ ሳትሰናዳ ላለመጎዳት፣ ጋሻ ሳይኖራት ጦር እንዳይሰበቅባት ለማይቀረው ክህደት መዘጋጀቷ ነው፣ ‹ሳይቀድመኝ ልቅደመው› አሰኝቶ ወደ ስለላ የከተታት፡፡
ገና ላፕቶፑን ከፍታ ፓስወርዱን ከማስገባቷ የትየሌሌ ያልተነበቡ መልእክቶች በየአቅጣጫው ጢን…ጢን…ጢን እያሉ ይገቡ ጀመር፡፡ ዋትስአፕ፣ ቴሌግራም፣ ፌስቡክ ሜሴንጀር ላይ፡፡
‹‹ይሄ ሰውዬ ተፈላጊ ነውና!›› አለች ለራሷ፡፡
ለመሆኑ ይሄ ሁሉ መልእክት ከማን ነው? ስለ ምንስ ነው?
ከአንድ ሰዐት በላይ ፈጅታ ሁሉንም መልእክቶች አነበበች፡፡
የሚረባም፣ የሚያጣራጥርም ነገር አላገኘችም፡፡
ሰላምታ፡፡
ስራ፡፡
ጭራ እና ቀንድ የሌለው ወሬ፡፡
በመሰላቸት ላፕቶፑን ዘግታ ልትነሳ ስትል ግን እስካሁን ያላስተዋለችው የቆየ አንድ የዋትስአፕ መልእክት ዐይኗ ውስጥ ገባ፡፡
ከፈተችው፡፡
መክሊት ናት፡፡ የደረሰ ታላቅ እህት፡፡
የመክሊት መልእክት፣
‹‹እሺ ደርዬ፣ እንዴት ነው ታዲያ፣ ከሒዊ ጋር ነገሮች እንዴት እየሄዱ ነው?›› ይላል፡፡
የደረሰ መልስ አስደነገጣት፡፡
‹‹እህቴ! እንደዚህ ዐይነት ፍቅር ይዞኝ አያውቅም፡፡ ፎንቃ ገብቶልኛል ስልሽ፡፡ ቸኮልክ ብላ እምቢ እንዳትለኝ ፍሪ እንጂ…. እሺ ትበለኝ እንጂ ሳላገባት አልቀርም፡፡ አንቺም ሚጡም አክስት ለመሆን ተዘጋጁ እንግዲህ›› ይላል መልሱ፡፡
ላፕቶፑን ሳትዘጋ ከቢሮው ተስፈንጥራ ወጣችና መኝታ ቤት ገብታ ያልተነጠፈው አልጋ ላይ ዘፍ አለች፡፡
ከዚያ ባላወቀችው ምክንያት ስቅስቅ ብላ ማልቀስ ጀመረች፡፡
ክህደትን የጠበቀው የተጎዳ ልቦናዋ የቃልኪዳን አዋጁ ስለምን አስደነገጠው…?
ስለምንስ ለእንባ ዳረገው?
እሷም አልገባትም፡፡
ያስለቀሳትን ምክንያት ፍለጋ ማልቀሷን ቀጠለች፡፡
እምባዋ የደረሰን እውነተኛና ልብ የሚያሞቅ የፍቅር እወጃ ከመስማት ወይም ከብዙ የመከራ ሙከራ በኋላ በወንዶች ተስፋ በቆረጠችበት ሰዐት የሚታመን ወንድ ከማግኘትዋ የደስታ ስፍራ ይመንጭ ፤ ለትዳር እፈልግሻለሁ ብሎ አዘናግቶ የጭቃ ጅራፉን መዥረጥ አድርጎ የሚያወጣ ከሌሎቹ የባሰ የሚጎዳኝ ወንድ ቢኖንስ ከሚል የፍርሃት ስፍራ ይምጣ መለየት አልቻለችም፡፡
የእምባዬ ምንጭ የቱ ነው የሚለውን ወስና ሳታበቃ የቤቱ ዋና በር ሲከፈት ሰማች፡፡
ደረሰ፡፡
ዱካውን እየሰማች…
ባመኑት መከዳት ክፉኛ ቢያሳምም፣ ገና ለገና እከዳለሁ፣ ገና ለገና እጎዳለሁ ብሎ ፍቅርን ከመግፋት አፍቅሮና ተፈቅሮ መገፋት ይሻላል ብላ አሰበች፡፡
ግን ደግሞ ወዲያው በተቃራኒው ስሜት ታመሰች፡፡
እምነት ያመጣበትን ጣጣ አስባ፣ ገና ያልጠገጉ ቁስሎቿን፣ ያልደበዘዙ ጠባሳዎቿን አስልታ ተረበሸች፡፡
ወዲያው ደግሞ
ይሄ… እንደ ሸማኔ መወርወሪያ አንዴ እዚህ- አንዴ- እዚያ የሚሄደው ስሜቷ
ደረሰ መቼም አላገኘውም ያልሽውን ፍቅር እነሆ በረከት ሊልሽ ደርሶልሽ እንደሆንስ?
ይሄኛው ባይከዳሽስ?
እንዲያውም የእስካሁኑን ቁስልሽን አካሚ፣ ከእግዜር የተቸረሽ ካሳሽ ቢሆንስ ?
ያንን ያረጀ ያፈጀ የፈረንጅ ተረት አታውቂውም?..ስለ እንቁራሪቶችና ልዑሉ የሚተርተው?
እስካሁን የሳምሻቸው ወንዶች እንቁራሪት፣ ደረሰ ግን በልክሽ የተሰራው ልዑልሽ ቢሆንስ? ብላ እንድታስብ ገፋፋት፡፡
ከዚያ…
ደረሰ መኝታ ክፍሉ ውስጥ ከመግባቱ በፊት…
አጠገቧ ደርሶ እንደሁልጊዜው ግንባሯን በስሱ ከመሳሙ በፊት…
ቁርስሽ ምን በላሽ ብሎ ከመጠየቁ በፊት…
የመካድ ፍርሃቷን አሽቀንጥራ ጥላ በደስታ ተቀበለችው፡፡