ጎስቋሎቹ

የማለዳ ጀምበር ጣሪያዬን ማሞቅ ሳትጀምር በፊት የአንድ ክፍል ቤቴ በር በእርጋታ ተንኳኳ።

አባባ ናቸው፡፡

ክረምት በጋ ሳይሉ ዘወትር የሚለብሱትን አሮጌ ካፖርት ለብሰው ደጄ ቆመዋል፡፡

ካፓርቱ ከወትሮው የሰፋቸው ይመስላል፡፡ እንደዚህ ቀረብ ብዬ ባየኋቸው ቁጥር ከሲታ ሰውነትና ፊታቸው ይበልጥ ተጎሳቅሎ ይታየኛል፡፡

እንደሁልጊዜው በለሰለሰና ጨዋ አንደበታቸው፣

እንዴት ነህ

ስራ እንዴት ነው?

ደሴ ያለችው እናትህስ እንዴት ናት?

አባትህ ተሸለው ወይ?

እህትና ወንድሞችህ ደህና ናቸው?

የሚሉ ጥያቄዎችን አከታትለው ጠየቁኝ፡፡

እንዳስለመድኳቸው፣

እኔ ደህና ነኝ

እናቴም ይመስገን ደህና ናት

አባዬ አገግሟል

እህትና ወንድሜም ደህና ናቸው

ብዬ በትህትና መለስኩላቸው፡፡

ከዚያ አዘጋጅቼ ያስቀመጥኩትን የቤት ኪራይ ገንዘባቸውን ሰጠኋቸው፡፡

“ዳዊት ልጄ” አሉኝ ብሩን ተቀብለው ከሸሚዝ የደረት ኪሳቸው ከጨመሩ በኋላ አንገታቸውን ሰበር አድርገው፡፡

ሁኔታቸውን ስመለከት የሚመጣውን ገመትኩ፡፡

“እንግዲህ የቤት ኪራዩ ላይ ትንሽ መጨመር አለብህ” አሉኝ ጥፋቱን አውቆ ቅጣቱን እንደሚሸሽ ልጅ አይኖቼን ላለማየት እየታገሉ።

ምንም አላልኩም።

“መቼም ኑሮ ለሁላችንም ከብዷል፡፡ አንተም እንደሚቸግርህ አውቃለሁ ልጅ ግን ያው እንደምታውቀው…”

የጀመሩትን አረፍተ ነገር ሲቀጥሉ በሃሳቤ አብሬያቸው ጨረስኩት።

“የእኔ ጡረታ በዚህ ኑሮ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ይህንን ሰፊ ቤተሰብ የማስተዳደረው በዚህችው አንተ በምትሰጠኝ የኪራይ ገንዘብ ነው… ሁሉ ነገር በየእለቱ ያሻቅባል…በተለይ ደግሞ የእኔ መድሃኒቶች ዋጋ…”

ትኩር ብዬ አየኋቸው፡፡

የተገታተሩ የደም ስሮቻቸው ሰላላ እጆቻቸው ላይ ጎልተው ይታያሉ፡፡

የፊታቸው ቆዳ ከመገርጣት አልፎ ወደ ቢጫ ያደላ መሰለኝ፡፡ ምናልባት የሚወስዷቸው መድሃኒቶች ያመጡት ጣጣ ይሆናል፡፡

‹‹አልችልም አባባ›› ልላቸው ፈልጌ ነበር፡፡

የመንገድ ላይ እርጥብ የነጋ መሸ መብሌ ከሆነ እንደሰነበተ፣ የዚህን ወር የቤት ኪራይ አልሞላ ብሎኝ በእቁብ የገዛኋት ትንሽዋ ቲቪዬን በእርካሽ እንደሸጥኳት ልነግራቸው ከጅሎኝ ነበር፡፡

ግን አቃተኝ፡፡

በዚህ ፈንታ በረጅሙ ተነፈስኩና ፣ ‹‹እሺ አባባ›› ብዬ ራሴን በስምምነት ነቀነቅኩ፡፡

ያለ ማንገራገር የሰጠኋቸው እሺታዬ የበለጠ የጎዳቸው ይመስል ፊታቸው በሃዘን ከብዶ፣

‹‹በል ደህና ዋል ልጄ ›› አሉኝና ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡

ኑሮ ጨምቆ እያሰጣኝ ነው፡፡

እንድጨምር የጠየቁኝ ገንዘብ ግን ከእኔ በላይ ለእሳቸው ያስፈልጋቸዋል፡፡

እኔ ገና አፍላ ወጣት ነኝ፡፡ ሰውነቴን በቀን አንዴ በልቶ መኖርን አስለምደው ይሆናል፡፡

ዛሬ ቀን ቢጥላቸውም ብዙ የድሎትና የጥጋብ ዘመናትን ላሳለፉት ለእሳቸው ግን በማምሻ እድሜያቸው ይሄን ማድረግ ያዳግታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *