ጨዋታው ፈረሰ
ዳቦው ተቆረሰ
የሚል ተረት ይዘን
በባዶ ሆዳችን
ጨዋታ ማፍረስ ነው-ትልቁ ትልማችን
የዳቦ መቆረስ
በጨዋታ መፍረስ
ታጅቦ ከመጣ
ደህና ሁን ጨዋታ-ከሀገራችን ውጣ!
ሆዷን በመብሰክሰክ ለሞላች እቺ ሀገር
ከጨዋታው ሳይሆን ዳቦው ነው ቁምነገር
ይህንን በማመን…
ስንት ዓይነት ጨዋታ ግብ እንደናፈቀ
ዳቦ ያመጣ በሚል በጅምር አለቀ
ስንት ዓይነት ጨዋታ ለግብ የታለመ,
በዳቦ ግርማ ፊት ጠውልጎ ከሰመ
“ማፍረስ ማለት ዳቦ” በሚል መንሸዋረር
ስንት ዓይነት ጨዋታ ቅዋጨን ሳይጀምር
ለአንዲት ቁራሽ ዳቦ ጨዋታ እየናድን
‘ከጨዋታ ውጪ’ መሆን ተላመድን!
ሺ ጨዋታ መጣ; ሺውን አፈረስን
ያማረንን ዳቦ አንዴም አልቀመስን!!