Tidarfelagi.com

ውልደትህን ከማይሻ…

ብዙዎች በሚወዱት ቀን፣ ብዙዎች የማይወዱትን ግጥም ብንለጥፍ… የሚወደን አምላክ ምን ይለናል? እሱ ምንም አይልም፣ የሱ ነን የሚሉት እንጂ…

አዳም፣
በብዙ ምግብ መካከል
አንዲቱን ቢከለከል
እሷኑ አንክቶ በላ፣
ከእግዜር ጋር ፍቅራቸው ላላ።

እኔ፣
በብዙ ምግብ መካከል፣
አንዲት ጉርሻ ተነፍጌ፣
በማይላላ የጠኔ እጅ፣
እስክቃትት ተጠፍንጌ
ሞተልህ ሲሉኝ ለምን?
አዳነህ ሲሉኝ የማላምን
ገነት ቀረበች ሲሉኝ የማለምን…


ተ…

አዳም፣
ሴቶች በሌሉበት አንዲቱን ወደደ፣
እኔ፣
በሴት ጎርፍ መሃል፣ ላያት ተሰደደ
ለሚያረግድ ዳሌ፣ ሺ ጊዜ አረገደ።

አዳም፣
ዐይቶ ልቡ እንዳይሸፍት፣
ያለችው አንድ ነበረች
የኔ አንዲት ልብ ግን፣
ከእልፍ መሃል ተነከረች፣
አንድ ምረጪ ለሚል ቃሉ፣
ዐይን አዋጅ ሆነባት ሁሉ

እዛ ወዲያ ማዶ፣
የእግዜር ስፍር ቃል
“ያየ አመነዘረ” ፣ሲል ህጉን ያረቃል፣
እኔ እዚህ ማዶ፣
እልቤ መሃል ላይ ሺዋን አፀድቃለሁ
ከ”ሺ”ዋ ወድቃለሁ።
እዛጋ ሰባኪው፣
ተሰቅሎ አዳነህ ብለው ይነግሩኛል፣
ከመዳኔ በላይ ህመሜ ጣፍጦኛል።

እግዜር፣
አንዲት ጉርሻ ነስቶ
ሺ ሴት አሰልፎ
መዓት ህግ ፅፎ፣
“ጠብቀው” ይለኛል!
የመታመሜን ጫፍ የወደደው ልቤ፣
“ሊያድንህ ” ከሚል ቃል፣
ዘውትር ያጣላኛል።

እግዜር፣

የሚሰጥ ነስቶ
የሚከለከልን አብዝቶ ከሰጠኝ፣
መከልከል ስላቅ ነው፣ ምናለ ቢተወኝ?

አንድ ምግብ ነሳኝ
ሺ ሴት አሰለፈ
“ብላ” የሚልና፣
“አታመንዝር” የሚል
አስቂኝ ቃል ፃፈ።
የሚበላ ያለው፣
የሱ ስጋ ወ ደም
ለነብስ እንደሁ እንጂ
ለሆድ አልወረደም፣
አትይ፣ አታመንዝር ያለው ትዕዛዝ ቃሉ፣
“አትችለውን አድርግ” ይመስላል መሃሉ፣
ይህን ሁሉ አስቦ፣ ልቤ ይጠይቀኛል፣
ላልድን መሰቀሉ ምን ያደርግልኛል?

ህመሜን ከለመድኩ፣
መዳኔን ካልወደድኩ፣
ከውልደትህ ዕለት፣ ለኔ ምን አተረፍኩ
አንተስ ምን አተረፍክ?
ሲል ይሞግተኛል።

እና ባክህ ጌታ፣
አዳንኩህ ለሚል ቃል ወደኔ አትጠቁም፣
እኔና ውልደትህ፣ አይተዋወቁም።
*****

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *