Tidarfelagi.com

አማርኛ እንዳበጁሽ አትበጂም

“ ያስለቅሳል እንጂ ይህስ አያሳቅም
ግንድ ተደግፎ ዝንጀሮ ጫት ሲቅም”
(አማርኛ እንዳበጁሽ አትበጂም)

እህህ…..ኡህህ…..ውይይ….. አማርኛ ተኝታ ታቃስታለች። የሀገር ውስጥ እና የዓለም ትልልቅ ቋንቋዎች በዙሪያዋ ተሰብስበዋል። ጥቂት የቋንቋ ምሁራንም አሉ።
“ኡውይይ…. ኸረ አልቻልኩም፣ ቆረጣጥሞ ሊገለኝ ነው!”
“ አይዞሽ…. አይዞሽ… እኛም እኮ አንድ ሰሞን አፈር ልሰን ነው ተነሳነው” አለ እብራይስጥኛ… ( ሞት ደረጃ ደርሶ ያንሰራራ ቋንቋ ነው)

“አይይ…ተወኝ እስቲ እብራይስጥ… I don’t think there is a remedy for this one. እኔው ነኝ ጥፋተኛ። ’ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ…..” አማርኛ ንግግሯን አንጠልጥላ ቀረች። ደነገጠች ትመስላለች። “እንዴ….” አለች። ከግዙፍ መደንገጥ የተገፋ እንዴ! አሰብ አድርጋ እንደገና ለማለት ሞከረች። “ጥንት ነበር እንጂ መጥኖ……….ኸረ ጉድ ተረቱም ጠፋብኝ!” ዙሪያዋ ተሰበሰቡትን በድንጋጤ አየች። ባለማመን ያይዋታል። ዓይኗ ኦሮምኛ ላይ አረፈ።

“ኦሮምኛ ካወከው አግዘኝ እስቲ በፈጠረህ….ምን ነበር ተረቱ?” ኦሮምኛ አሰብ አድርጎ በትክክል ነገራት። አማርኛ ሽምቅቅ! እንዴት የገዛ ተረቷን መናገር አቅቷት…… ደንገት ስቅስቅ ብላ ማልቀስ ጀመረች። በዙሪያዋ ሉት ቋንቋዎች ተደናገጡ። ቢሏት ቢሰሯት ልታቆም ነው!….

“ኸረ ምን ሆነሻል?!…” ጭንቀት የማይወደው ጣሊያንኛ ጠየቀ።
“ አታየኝም እንዴ… የገዛ ተረቴ እኮ ጠፋኝ! ሃሳቤን በምሳሌ ማስረዳት አቃታኝ። እንግዲህ እኔ ከምሳሌዎቼ ውጪ ምንድን ነኝ!” መንሰቅሰቋን ቀጠለች። እንደምንም አባብለው ዝም አሰኟት። እንባዋን እየጠረገች በአፍረት ዙሪያዋ የተሰበሰቡትን ቋንቋዎች ቃኘቻቸው። አንድ ቋንቋ እንደጎደለ አስተዋለች። አዎ! እንግሊዘኛ የለም። የት ሄደ? ከቋንቋዎች ሁሉ ተለይቶ እንዴት ይቀራል። ጥሩ ቅርርብ እንዳላቸው ታውቃለች። ታዲያ እንዴት ይቀራል?!!

ስለእንግሊዘኛ ቋንቋ መቅረት እየተብከነከነች ሳለ ሃይለኛ ውጋት ውስጧን ሲጠቀጥቃት ተሰማት። ጎኗን ይዛ “ኣኣ….”ስትል አቃሰተች።
*****************

ጥግ ላይ ግዕዝ ቆዝሞ ተቀምጧል። ስለአማርኛ ህመም ቅኔ እየቀመረ ይሆን? የለበሰው ልብስ ብዙ ቦታ ተቀዳዷል። አስተውሎ ላየው የቀደመ ጊዜ ሞገሱን ለማስተዋል አያዳግትም። ዝምታው አንዳች ነገር የተገለጥ ያስመስለዋል- ከሌሎች ተለይቶ የገባው።

…የሚግባቡ ቋንቋዎች እርስ በእርስ ያወራሉ። የማይግባቡት ቋንቋውን በሚችሉ ምሁራን ተርጓሚነት ያወጋሉ። አንዳንዶቹ ሰላምታ ሲለዋወጡ፣ ሌሎቹ ዘለግ ያለ ወግ ይዘዋል። ድሮስ ቋንቋዎች ከማውራት ውጪ ምን ያውቃሉ? ሃይለኛው የአማርኛ ማቃሰት ግን ንግግራቸውን ገታው። ትኩረታቸውን ወደ እሷ አደረጉ። ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛ እና ሌሎችም አዝነው ተቀምጠዋል። እነሱም ቢሆን ሙሉ ጤነኛ አይደሉም። የሆነ ነገር እንደጎደላቸው መገመት አይከብድም….

….ዶክተር ሥነልሳን በሩን ከፍቶ ገባ። ለረጅም ሰዓታት አማርኛን ሲመረምራት ነበር የቆየው። አማርኛ እሱን ስታይ ከማቃሰቷ ጋር እየታገለች ጠየቀች፤

“ዶክተር የምርመራው ውጤት ምን ሆነ?”
ዶክተር ሥነልሳን እጁ ላይ ለውን ወረቀት በጥሞና ሲያይ ቆይቶ በረጅሙ ተንፍሶ መናገር ቀጠለ…
“ እንደሚታወቀው ቋንቋዎች ከቋንቋዎች ይዋዋሳሉ። እዚህ ካላችሁት ውስጥ ይህ የማይነካው የለም። አየሽ አማርኛ፣ ለዚህ ሁሉ ጤና ማጣትሽ እና ሃሳብሽን በትክክል ለመግለፅ እንቅፋት የሆነው አንድ ነገር ነው። ደምሽ ተመርዟል። ይሄ ደምሽን የመረዘው ነገር….” አማርኛ ምንነቱን ለማወቅ ካላት ጉጉት ሳታስበው አቋረጠችው።

“ ምንድን ነው ዶክተር?!!”
“ እንግሊዘኛ ነው! እንግሊዘኛ ደምሽን መርዞታል። መዋዋስ ያለ ቢሆንም ባንቺ ደም ውስጥ ግን ከተገቢው በላይ የሆነ እንግሊዘኛ ተገኝቷል።”
አማርኛ በድንጋጤ ጨው መሰለች። ዓይኖቿ ፈጠጡ። ዶክተሩ ቀጥሏል።

“ ከዚህ በላይ ይበልጥ የሚያሰጋው ደግሞ፣ አሁን ወደ ጭንቅላትሽ እየሄደ መሆኑ ነው። በዚህ ከቀጠለ ምንም እንኳ ጊዜው ቢረዝምም ለገድልሽ ይችላል!” የዶክተሩ የመጨረሻ ንግግር በክፍሏ ውስጥ ከባድ ሰጥታ ጣለ። ለወሬ የማይሰንፉት ቋንቋዎች ሁሉ ፀጥ አሉ! በነገሩ ቦታ ራሳቸውን ተክተው የሚያስቡ ይመስላሉ። ፀጥ!! ግዕዝ ብቻ ፈገግ አለ። ፈገግታ ውስጥ ትምክህት ያለ ይመስላል። “መች አጣሁትና ድሮስ!” የሚል ዓይነት ፈገግታ! ፈገግ…. ከረዥም አመታት በፊት እሱም እንዲሁ ታሞ ነበር። አማርኛ ነበር ያመመው። ዛሬ ደግሞ አማርኛ በተራዋ እንግሊዘኛ ታማለች! በሽታ እንደለውዝ የሚዞርባት ሀገር አለ ለራሱ!

አማርኛ እንግሊዘኛን ከቋንቋዎች ሁሉ ለምን እንዳጣችው ገባት። እንግሊዘኛ አልቀረም። አዎ! እንግሊዘኛ ቀርቶ አይደለም፣ ውስጧ ገብቶ ነው!! ቅድም በእንግሊዘኛ ቀላቅላ ማውራቷም ትዝ አላት። ውስጧ ነው…. ይህን እያሰበች ከውስጧ የፈለቀ ሃይለኛ ውጋት በሃይል አስቃሰታት…. ኣኣኣኣ…Oh My God …ኡውይይይ…… እንግሊዘኛ!

One Comment

  • ሀያት commented on June 10, 2017 Reply

    ምርጥ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *