ከእለታት በአንዱ፣ በቅዱስ እርጉም ቀን
መንገድ ያገናኘን ድንገት የተያየን
አንቺ አልፈሽኝ ስትሄጅ፣ እዛው ያስቀረሽኝ!
…ላይሽን ሸፍኖት ጥቁር ጨለማ ጨርቅ
ዐይንሽን ብቻ እንጂ፣ ሌላሽን የማላውቅ
ማነሽ አንቺዬዋ? ማንነትሽ ማነው?
አቅል እያሳተ፣ መንገድ የሚያስቀረው?
ወንድን እንዳታስት ትጀቦን፣ ትሸፈን-ይሉትን የሰማሽ
አይታይ አካልሽ ውዴ ሆዴ ማነሽ?
ማነሽ እት ዓለሜ?
ስምሽን ያላገኘሁ፣ አስሼ ቃርሜ
አካልሽን ያላየሁ፣ ብማትር አልሜ
ማነሽ ቀልበ ልቤ? ማነሽ ቅዠት ህልሜ?
የለበሻት ቡርቃ* ፣
ለዓይን ቦታ ለቃ
ነፃይቱ ዓይንሽ፣ ልበ ነብሴን ነጥቃ
ከመንፈሴ ጋቢ፣ ተቋጭታ ተረቅቃ-
ከስጋዬ ጠልቃ
ካፈዘዝሽኝ ፍዘት፣ መች ነው የምነቃ?!
በርግጥ አትሸፈኝ፣ ተገለጭ አልልም
የሰው ውል አመሉ፣ ሊታወቅ አይችልም
የቡርቃሽን ግፈት፣ የአካልሽን መገለጥ አልወደው ይሆናል
ብቻ ዐይንሽ ይቆየኝ፣ በስህተት ኩላኩል ሳይቀይም፤ ሳይኳል
እቴ!…
ግን ማነሽ አንቺ
በዛች በትንስ ዓይንሽ አጥናፍ ዓለምን የምትረቺ
ዐይኖችሽ ከየት ነው የተለገሱ
እይታ ነብስን ሊቆርሱ
የአማኝን ልብ ሊጥሱ
የዝሙትን ህግ ሊያፈርሱ
ከየት ተነስተው፣ ለአንቺ ደረሱ!?
ማናት ቢሉ አላውቅሽ ዓይኖችሽን አስረው
ከዓይኖችሽ ውጭ ያለ ማንነትሽ ማነው?
ለቅኝ ገዥ ዓይኖችሽ ባሪያ መሆን ናፈኩ
ተቀበይኝ እንቺ፣ ይሄው ራሴን ለገስኩ
ተቀበይ ዓለሜ፣ ወዴት ነው ያለሽው
አይሰማሽም ወይ፣ ሲጮህ የማረክሽው?
ቆይ ግን ማነሽ አንቺ?!
ገድለሽኝ የማትፎክሪ
የግዳይሽን አትሰሚ ጥሪ
ማነሽ?
ያላሸነፈሽ ልመና ስግደት
ያላለዘበሽ ለቅሶና ጩኸት
ማነሽ?
ፀጉርሽ ምን ዓይነት፣ ዞማ ነው ከርዳዳ
የእግርሽ አወራረድ፣ ቀጤ ነው ወልጋዳ
የዳሌሽ መጠኑ፣ አናሳ ነው ትልቅ
አንገተ መቃ ነሽ፣ወይስ አጭር ድብቅ?
ማነሽ?!
ስጋዬን ወና አድርገሽ፤
ነብሴን በምድረ በዳ፣ ገትረሽ ዞር ያልሽው አንቺ
ይገልፁሽ የምታደክሚ፣ ለቃላት የማትመቺ
ከትንግርት ዓይኖችሽ በቀር፣ ለይቼሽ የማልናገር
የሞትኩኝ በእይታሽ አረር
ማነሽ?!!
ማነሽ ውድ ዓለሜ፣ ማነሽ ቀልበ ልቤ
ማነሽ እቴ ውዴ
ማነሽ ወለፈንዴ
ማነሽ?
አንቺ ማነሽ?
? ? ?
? ?
?
*ቡርቃ፡- ከዐይን ውጪ ያለውን ሙሉ የሰውነት ክፍልን የሚሸፍን ልብስ- ሙስሊም ሴቶች የሚለብሱት!
2003 ዓ.ም /ደብረ ዘይት/
2 Comments
አድናቂ ነኝ በዚህው ቀጥልበት
በዚሁ ቀጥልበት አድናቂቅ ነኝ