<<ማሞና ማሚቱ በሉ ዳቦ ቆሎ
ሮጡ ወደቁ ተነሱ በቶሎ>> /ቃላዊ ግጥም/
ማሞና ማሚቱ፣ ጠኔ እየጣላቸው፣
ነብስ የሚያነሳቸው
ሌሎች እኮ አይደሉም፣ እኔና አንተ ናቸው፡፡
ቶሎ እየወደቅን ቶሎ የምንነሳ
ቀለባችን ቆሎ ኑሯችን አበሳ
ማሞና ማሚቱ፣ እኛ ነን አትርሳ፡፡
ከህይወት ግብግብ፣ እየሮጡ ገብተው
መሮጥ መሃል ወድቀው፣ በቶሎ `ሚነሱ፣
ማሞና ማሚቱ፣ እኔና አንተ እንጂ፣ አይደሉም እነሱ!
ማሞና ማሚቱ፣
ቆሎ እየበሉ፣
በረሃብ የሚቆሉ
ቶሎ እየወደቁ፣ ቶሎ የሚነሱ
በ“ቋሚዎች“ መዝገብ፣ ፍፁም የተረሱ
መሮጥ ልማዳቸው፣ መውደቅ መድረሻቸው
ደጋግሞ ለመውደቅ፣ ደጋግሞ መነሳት፣
የሕይወት እጣቸው
መች ሌሎች ሆኑና፣ እኛና አንተን ናቸው፡፡
….ዳግም ይነሳሉ፣ ዳግም ዳቦ ቆሎ
ዳግም ይሮጣሉ፣ ሊወድቁ በቶሎ!
ማሞና ማሚቱ፤
ሳይወድቁ ለመቆም፣ ዳቦ ቆሎ በልተው
ሲሮጡ `ሚወድቁ፣ አቅም ጉልበት አጥተው
ዳግም የሚነሱ፣ መቆም ተስፋ አንግተው
የእኔና አንተው አምሳል እራሳችን ናቸው፡፡
ዳቦ ቆሎ በልተን፣ ልንቆም የምንታትር
ተሰብረን የማንቀር፣ በወደቅን ቁጥር
ለገፉን ያልወደቅን፣ ለጠሉን ያልጠፋን
በተሥፋ ሰማይ ስር፣ መከረኛ ቀኖች ዘውትር እየገፋን
መኖር የለመድን፣ ብንጮህ ያልተሰማን
…………………………እኔና አንተ እኮ ነን፡፡
`ባለቀኖች ` ገፍተው፣ ከቀን ያወጧቸው
`የጌቶቹ ጫማ` የሚዳምጣቸው
ቢጮሁ ተመልካች፣ ቢጮሁ አዳማጭ የተነፈጋቸው
ማሞና ማሚቱ፣ እኔና አንተ ናቸው!!
/መጋቢት 19, 2005/