(Peace be up on him)
“An economist should have cool mind and warm heart”!
Professor Eshetu Chole
በዘመኑ የምሁራን ልሂቃን ስብዕና፣ የንቃት ደረጃና ለሕዝባቸው ባላቸው ቁርጠኝነት (መስዋዕትነት እስከመክፈል ድረስ) ደካማነት የተበሳጨ ኢትጵያዊ ወጣት ፅሁፍ፡፡
ከላይ ለመግቢያነት የተጠቀምኩበትን የፕ/ር እሸቱ ጮሌን አገላለጽ ትንሽ ማስተካከያ አደርግበት ዘንድ እወዳለሁ፡፡ “A social Scientist should have cool mind and warm Heart”! የማሕበራዊ ሳይንስ ምሁራን ሊላበሱት ከሚገባው ፀባይ አንዱና ዋነኛው የተረጋጋ አእምሮ ባለቤት መሆንና ለሕዝባቸው የሚገዳቸው ልባም መሆናቸው ነው፡፡ ይህንን የፕ/ር እሸቱ አባባል የተወሰነ ማስተካከያ ባደርግበት ፕሮፌሰር እንደማይከፋብኝ አውቃለሁ፡፡ ምክንያቱም እሱም ደፋር ምሁር ነበረና ደፋር ምሁርነትን ያበረታታል ብዬ ስለማስብ፡፡ (Peace be up on him)
በርግጥ ዛሬ ስለ ፕ/ር እሸቱ ለማውሳት ብዕሬን አላነሳሁም፡፡ ይልቁንም ከሱ በፊት የነበረውን ታላቅ ኢትዮጵያዊ አሳቢና ልባም ልሂቅ ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝን በፕ/ር አባባል መዝኜ ላወድሰው በመፈለጌ እንጂ፡፡
ገ/ሕይወት ለምን?
እንደኔ አመለካከት የማሕበረሰብ ሳይንስ (Social Science) ተማሪዎች እንዲሁም ምሁራን ብሎም ልሂቃን የመጀመሪያ ተግባር በተማሩት ሳይንስ ዕገዛ የሚኖርበትን ማሕበረሰብ ማንነት መገምገምና መረዳት ከዛም ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ለይተው በማውጣት ደካማውን ባህል ትቶ ጠንካራውን አጎልብቶ ማሕበረሰቡን ወደተሻለ የስብዕና ደረጃ ማድረስ ነው፡፡ እርግጥ ነው ይህን ከባድ ሀላፊነት ለመወጣት ራስንና ማሕበረሰብን መረዳት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ የሌሎችን ሕዝቦች ባሕል፣ ልምድና ተሞክሮ በማጥናት ከራስ ጋር በማነፃፀር የተሻለውን መለየትን ጭምር ይጠይቃል፡፡ አለፍ ሲልም በየጊዜው ከሚነሱ ከሚታሰቡ ዓለም አቀፋዊም ሆነ አገራዊ አመለካከቶችን ማጤንና መመርመርንም ግድ ይላል፡፡
እነዚህን ሁሉ መንገዶች በማወቅ በመረዳትና በመመርመር የሚዘለቁ ብቻ አይደሉም፡፡ ከየአቅጣጫው ለሚመጡ ተፅዕኖዎች (በተለይም ገዢው መደብ የሚፈልጋቸውን አመለካከቶችና አስተሳሰቦች) በድፍረት መቆምን ያካትታል፡፡ ታዲያ እነዚህን ሁሉ መስፈርቶችን ያሟላ ኢትዮጵያዊ ልሂቅ ሳስብ በአእምሮዬ የሀሳብ ሸራ ላይ ከሚከሰቱልኝ አሳማኝ ምሁራን አንዱና ዋነኛው ገ/ህይወት ባይከዳኝ ነው፡፡
የገ/ሕይወት ልቀት
ገ/ሕይወት ከተርታው ምሁራን ጎን የማይሰለፍበትና ከጥቂቶቹ ልሂቃን ጎራ የሚያስልፈው ሁለት መሰረታዊ መንገድ ነው፡፡ የመጀመሪያው የተረጋጋና ንቁ የሆነ አእምሮ ባለቤት በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ለትልቅ አሳቢነቱና ነገሮችን በተሻለ መልኩ ለመመርመር ረድቶታል፡፡
የሚቀጥለው ለሰው ልጅ በጠቅላላው እንዲሁም ለሀገሩ ዜጎች የነበረው የተሻለ የመኖር ምኞትና ራዕይ የነበረው ልበ መልካም ሰው መሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱን ማጣመር ለአንድ ልሂቅ ግዴታ መሆኑን ሲያጠነክር ነው ፕ/ር እሸቱ አእምሮና ልበ መልካምነትን ከምሁርነት ጋር ያገናኛቸው፡፡
የገ/ሕይወት ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አመለካከት
ሕዝቡ እንዳይጎዳበት የሚፈልግ መንግስት ዋነኛና ትኩረት ሰጥቶ ሊንቀሳቀስበት የሚገባው ነገር ቢኖር ትምሕርት እንዲስፋፋ እንዲበዛ ማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም ይላል ገ/ሕይወት መንግስትና የሕዝብ አስተዳደር በሚለው መጽሀፉ “እንዲህ ያለው ሕዝብ የሚመጡበትን ውስጣዊም ይሁን ውጫዊ ችግሮች የመመከት አቅም ይኖረዋልና”፡፡ የእውቀትን መሰረታዊነትና አስፈላጊነት በደንብ ማሳሰብ የወደደው ገ/ሕይወት “ሰው ሲፈጠር ጌታና ድሀ ሆኖ አልተፈጠረም ድሕነትና ጌትነት የተለየው በሰው እውቀት ነው፡፡” (ገፅ55) ይለናል፡፡ ስለ ንግድ ስርዓት ሲመክርም “… ባንድ አገር ውስጥ ነጋዴ ሲበዛ ሹምም ወታደርም ቀማኛም ይበዛል የፊት የፊቱም ሥራ በከንቱ እያለቀ በእንደዚህ ያለ አገር ውስጥ ሀብት አይከማችም፡፡ ድህነትና ችጋር በሽታም ሞትም እጅ ለእጅ ተያይዘው ይገቡበታል፡፡” (ገፅ 66) (እዚህ ላይ ደላላና ነጋዴ በዛበትና በሥራ ሳይሆን በአፈ- ቀላጤነት የሚመራው የዛሬውን የኢትዮጵያ ገበያ ስርዓት ልብ ይሏል)፡፡
ትዕንቢተ ገ/ሕይወት
ገብረ ሕይወት መገናኛ ብዙሀንና የመሰረተ ልማት አውታሮች ባልተጀመሩበት (ባልተስፋፉበት) እና ከዓለም ተነጥላ በምትኖረው ኢትዮጵያ የወደፊቱን መተንበይ የቻለ ምሁር ነው፡፡ (እንደኔ አመለካከት ከቅርብ ጊዜ ምሁራኖቻችን የኖሩበትን ዘመን ሁኔታ ከተረዱት በላይ እሱ ድሮ የተገነዘበው ተሽሎ ተገኝቷል ባይ ነኝ)፡፡
“እነሆ መሬት በጥቂት ሰዎች እጅ ሲገባ ላገሩ ክፉ ምልክት ነው፡፡ ሕዝቡ እንደደኸየና የመንግስቱ ሀይል እያነሱ እንደሄደ ይመሰክራል፡፡ መሬቱ ተከፋፍሎ በብዙ ሰዎች እጅ የሆነ እንደሆነ ግን የሕዝቡን ሀብትና የመንግስቱን ኃይል ያመለክታል፡፡ ይህ ስለተባለ ግን መሬት አይሸጥም አይለወጥም ተብሎ ቢታወጅ ለሕዝቡ የበለጠ ጉዳት ይሆንበታል” (ገፅ88) አሁንም ድረስ የምንነታረክበትን መሬት ፖሊሲ ምን መሆን እንዳለበት ጠቁሞን ሲያበቃ መሬት በጥቂቶች እጅ ከሆነ አገሪቷ መድከሟንና መደህየቷን እንደሚያሳብቅ ነግሮናል፡፡
በሥራ ያልሰለጠኑና ያልተማሩ ሕዝቦች እጣ ፈንታ ስደትና በሀገር ጉዳይ ምንተዳዬ መሆኑን አስገንዝቦ ያ ከመሆኑ በፊት ግን ትምሕርትና ስልጣኔ ወደ ሀገራችን ገብቶ ከድህነትና ከአስከፊው መዘዝ እንድንጠነቀቅ በተረጋጋው አእምሮውና ሞቅ ባለ ልቡ መክሮናል፡፡ (ገፅ 119)፡፡ መስማት ያለብንን እውነት ዘለነዋልና ከብልፅግናና ከስልጣኔ መዝገብ ተዘለናል፡፡
ዝክረ ገ/ህይወት
እንደ ገ/ሕወት ያለን ዘመን ተሸጋጋሪ ምሁርና ልሂቅ በዚች ጥቂት ፁሁፍ መዳሰስ ድፍረት መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ይሁንና በተገኘው አቅምና ዕድል እንዲሕ ዓይነቱን ልሂቅ መዘከር በቅንነት እስከሆነ ድረስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
Cool Mind + Warm Heart = Courage to do everything
እንደ ገብረ ሕይወት ያሉ ምሁራን በዘርፉ የሉምና ወይም በፍርሀት ተደብቀዋልና አልታደልንም ይሁንና ገ/ሕይወትን አፍርታለችና ሀገሪቷ ወደ ፊትም ታፈራለች፡፡ አሁን ያሉንን ምሁራን ግን አንድ ነገር ማለት ብቻ ወደድሁ፡፡ከናንተ ያጣሁትን የተረጋጋ አዕምሮና የሚገደዉ ልብ ፍለጋ ገ/ሕይወትን ፈለግሁ እናም የገብረ ሕይወት ያለህ! አስባለኝ፡፡