(ክፍል አንድ)
‹‹እጅ ወደ ላይ!››
ሎጋ ቁመናው ተስተካክሎ፣
ፍቅሩ የሚስብ አይኑ አባብሎ፣
…ላፈጣጠሩ እንከን የለው፣
አረ እንዴት አርጎ ነው የሰራው
አረ እንዴት አርጎ ነው የሰራው››
ድምፃዊት ሂሩት በቀለ
ከአሰልቺ የጎበዝ ተማሪነት ቀናት በአንዱ….
ለስምንት ሰአት ሃያ ጉዳይ ገደማ ከዶርም ወጥቼ ክፍል ለመግባት አዘግማለሁ፡፡ ሁሌም ክፍል ከመጀመሩ አስር እና አስራ አምስት ደቂቃ በፊት ገብቼ ባለፈው የተማርነውን ነገር እየከለስኩ አስተማሪ የምጠብቅ ታታሪ ተማሪ ስለሆንኩ ለስምንት ሰአት ክፍል ሃያ ጉዳይ ላይ ግማሽ መንገድ ላይ እገኛለሁ፡፡
ቀኑ እንደሌላው ቀን ነበር፡፡ በግንቦት ወር መብረቅ እንደማየት ያህል የሚያስደነግጥና ሕይወቴን እስክሞት የሚቀይር ቀን አይመስልም ነበር፡፡ ትላንት እንደነበረው፣ ከትላንት በስቲያ እንደነበረው፣ ከትላንት በስቲያ በስቲያም እንደነበረው ዝ…ም ብሎ ቀን ነበር፡፡
‹‹ኢንስቲቲዩት ኦፍ ኢትዮፒያን ስተዲስ ላይብረሪ›› ጋር፣ እዛ ባንዲራው ጋር ስደርስ ግን ቁመቱን አየሁት፡፡ ከሰንደቅ መስቀያ የሚረዝም የመሰለ ሎጋ ቁመቱን ከነሙሉ ግርማ ሞገሱና ክብሩ አየሁት፡፡
ቁመቱን ጨርሼ ሳላየውና ሳላገግም ደግሞ ድምፁን ሰማሁት፡፡ ‹‹ኢትዮፒያን ስተዲስ ላይብረሪው ይሄ ነው?›› ነበር ያለኝ፡፡
ተራ የአቅጣጫ ጥያቄ ነው አይደል? እኔን ግን አቅጣጫዬን አሳተኝ፡፡ ድምፁ! ወይኔ ድምፁ! በዛ ቁመት ላይ ወይኔ ድምፁ!
‹‹አዎ››ም ‹‹አይ››ም ሳልለው ፊቱን አየሁት፡፡
ለጥቁር የሚቀርብ ጠይምነት፡፡ ሰልካካ ያልሆነ ግን ግርማሞገሳም አፍንጫ፡፡ መሳሳምን ብቻ የሚያሳስብ ከንፈር፡፡ ተበልቶበት የሚያውቅ የማይመስል፣ ሴትን በፈገግታ ትጥቅ ለማስፈታት ብቻ የሚውል የሚመስል ጥርስ፡፡ (‹‹ይሄ ልጅ የሚበላበት ተቀያሪ ጥርሶች አሉት እንዴ!›› የሚያስብል ንጣት…!)
ከአቀማመጣቸው የንጣታቸው፡፡ አቤት ንጣታቸው!
በአይኔ ወረድኩ፡፡
ከከንፈርና ጥርሶቹ በታች ውብ አንገት፡፡
ከውብ አንገቱ በታች የሚያኮራ ደረት፡፡
ከሚያኮራ ደረቱ በታች…
….ሌላው ሌላውማ ለማን ይነገራል!
ሁሉን ቻይ እግዜር ራሱ ሲደክምበት አድሮ ሲሰራው የዋለ ነው የሚመስለው፡፡
‹‹አዎ›› አልኩት ጉልበት እና ትንፋሼን አሰባስቤ፡፡ ማራቶን ለመሮጥ የምዘጋጅ መስዬ፡፡
በፍጥነት አመስግኖኝ ወደ ላይብረሪው ለመግባት ደረጃውን በረጃጅም እግሮቼ ሲወጣ እኔ ግን ከቆምኩበት መሬት ላይ የተመረግኩ ይመስል ቆሜ ቀረሁ፡፡
ምርኩዙ ወይ በትሩ እንደወደቀበት ሽማግሌ ተገትሬ ቀረሁ፡፡
ብዙ የአልኮል መጠጥ ስጠጣ እንደዋልኩ ደሜ ግሎ ሲዘዋወር ብቻ ይሰማኛል፡፡ ደሜ የወፈረም መሰለኝ፤ እንደ ቡላ አጥሚት ወፍሮ በጠባብ የደም ስሮቼ ለማለፍ የሚታገል፡፡
የሆንኩት አልገባኝም ግን በውስጤ በ‹‹ሬክተር ስኬል›› ሊለካ የሚችል ንቅናቄና ነውጥ ነበር፡፡
ተናወጥኩ፡፡
ኩላሊቴ የጉበቴ ቦታ፣ ጉበቴ የሳምባዬ ቦታ፣ ሳምባዬ ደግሞ አፌ ጋር የሄዱ ይመስለኛል፡፡
ፍፁም ተናወጥኩ፡፡
ምን ያህል እንደሆነ ያላወቅኩትን ጊዜ ያህል ቆይቼ አካባቢዬን ገልመጥ ብዬ አየሁ፡፡ የታዘበኝ ያለ እንደሆን ለማየት፡፡ አብሮኝ የቆመው ጥላዬ ብቻ ነው ያለው፡፡ የገዛ ጥላዬ ራሱ ጥሎኝ መሄድ ቢችል ታዝቦኝ ይሄድ ነበር፡፡
ሳልቆይ፤ ያለ አእምሮዬ ፈቃድ እግሬ የላይብሪውን ደረጃ መውጣት ጀመረ፡፡ ያለ መሳርያ ማርኮና ጥሎኝ የሄደውን ልጅ ተከትሎ ላይብረሪ ይዞኝ ገባ፡፡
የኔ ባልሆነ ፍጥነትና ብልጠት ላይብረሪውን ቃኘሁት፡፡ ጥግ ላይ ከነግርማ ሞገሱ ተቀምጧል፡፡ ጎንበስ ብሎ ያነባል፡፡ እግሬ ሂድ ሳይባል ወደርሱ ይዞኝ ሄደ፡፡
ደረስኩ፡፡
መሄድ ሳልወጥን ደረስኩ፡፡
ምን መሆኔ ነው…?ምን ላደርግ ነው…?
‹‹እህም…›› አልኩና ፊት ለፊቱ ተቀመጥኩ፡፡ መሃላችን ያለው ጠረጴዛ ብቻ ነው፡፡
ቀና አለ፡፡
ደንግጬ ጥርሶቼን ያላሳተፈ ፈገግታ አሳየሁት፡፡ ጥርሶቹን ካየሁ ወዲህ ጥርሶቼ አስጠልተውኛል፡፡
ቆንጆ አድርጎ ሳቀና ፤ ‹‹እዚህ ነበርሽ እንዴ…!አላወቅኩም ነበር እኮ…›› አለኝ በላይብረሪ ድምፅ፡፡ ድምፁ ሲቀነስ ይበልጥ ያምራል፡፡
‹‹አዎ…እ…እዚህ ነኝ…›› አልኩ የማነበው ነገር እንዳልያዝኩ ትዝ ሲለኝ አፍሬ፡፡ ደብተር ብቻ ነው የያዝኩት፡፡ ከምንም ይሻላል ብዬ ደብተሬን ጠረጴዛው ላይ ዘረጋሁት፡፡
‹‹ደብተር ለማጥናት ነው ላይብረሪ የመጣሽው…?›› መፅኃፉን ትቶ በትኩረት እያየኝ ጠየቀኝ፡፡
‹‹ዶርም አላስጠና አሉኝ…ፀጥታ ፈልጌ ነው›› አይኔን ከአይኑ እያሸሸሁ መለስኩ፡፡የውሸቴ ቅንብር ፍጥነት ራሴን አስደንቆኛል፡፡
‹‹ምንድነው ምትማሪው?››
‹‹ፖለቲካል ሳይንስ››
‹‹ ና…ይ…ስ!…ስንተኛ አመት?››
‹‹ሁለተኛ…›› (ለምንድነው እየተሸኮረምምኩ የማወራው? ስንተኛ አመት ነሽ መባል ‹‹አይንሽ ያምራል›› እንደመባል ያሽኮመምማል…?እንዴት እንዴት ነው የሚሰራኝ በናታችሁ!)
‹‹ዩ አር ጀስት አን ኢምብሪዮ ዜን….!›› አለ ጮህ ብሎ፡፡
የጨርቆስ ልጆች ቀልድ ስሰማ ብቻ እንደምስቀው ከጣሪያ በላይ ሳቅሁ፡፡ አስቆኝ አልነበረም፡፡ ቀልድ እንደሆነ ገብቶኝ ነው፡፡ ለስምምነት ነው መሳቄ፡፡
አጠገባችን የነበሩት ሁለት ተማሪዎች አፈጠጡብን፡፡
ይሄን ጊዜ ድምፁን ቀነሰና፤ ‹‹ግቢያችሁ ሻይ ቤት አለ አይደል…እዛ ሄደን እናውራ…ሳይገሉን›› አለኝ፡፡
ደስታ አቅበጠበጠኝ፡፡
ወዶኛል፡፡ ሻይ ካለ…ወዶኛል!
ተወርውሬ ተነሳሁና ከላይብረሪው ወጣን፡፡
ምን እንደነካኝ ግን አላውቅም…
ታምሜ እንኳን ከክፍል የማልቀረው ልጅ ክፍል እንዳለኝ ረሳሁ፡፡ (ለነገሩ ዛሬን በጠና አሞኛል)
ከትምህርት ሌላ ተስፋ የሌለኝ ልጅ ተማሪ እንደሆንኩ ረሳሁ፡፡
በሴትኛ መግደርደር እንዳለብኝ እያወቅኩ ሴት መሆኔን ረሳሁ፡፡
ይሉኝታ ሊይዘኝ ሲገባ ሀበሻ መሆኔን ጨርሼ ረሳሁ፡፡
ሰው ብቻ ሆንኩ፡፡ ከሱ ጋር መሆንን ከምንም በላይ የፈለገ ሰው፡፡
‹‹ሎው ላውንጅ›› ቁጭ ብለን፣ በረጅም ብርጭቆ የሚመጣውን ወተት በቡና በቦምቦሊኖ እና በወሬ እያማግን ለሶስት ሰአታት ስናወራ አዲስ ማንነት አበቀልኩ፡፡
እሱ እወደዋለሁ ያለውን ሁሉ የምወድ ሰው ሆኜ ቁጭ አልኩ፡፡
እሱን ለመምሰል ተንቀዠቀዥኩ፡፡
የሚልገውን ሆኜ ለመታየት ተንቀለቀልኩ፡፡
የሆንኩትን ሳይሆን ይወዳት የመሰለኝን ሴት በሰአታት ውስጥ ፈበረኩ፡፡
ስለኮሚውኒዝም ስናወራ በኮሚውኒዝም ስር ሰምቼ የማውቃቸውን ነገሮች በሙሉ እያገጣጠምኩ ብልህና ፈጣን ሆኜ ታየሁ፡፡ (ኮሚውኒዝም ሲል፤ …ድባብ መናፈሻ ጋር ካለው የማርክስ ፍርክስክስ ሃውልት እስከ ዶክተር ገብሩ መርሻ ውል አልባ የኮሚውኒዝም ሃሳቦች፣ ‹‹ከእያንዳንዱ እንደ አቅሙ፣ ለእያንዳንዱ እንደ ፍላጎቱ›› መርህ….ለፈለፍኩ)
ስለ ቻይና ምግብ መውደዱ ሲያወራ ስለቻይና የማውቀውን ነገር ሁሉ እያሰባጠርኩ አቅርቤ ብልህና ፈጣን ሆኜ ታየሁ፡፡ ( የቻይና ምግብ ሲል ስለ ሩዝ በሀገራችን አለመለመድና አለመወደድ…በ77 ድርቅ ጊዜ ..የኤፍሬም ታምሩ ዘፈን ዜማ ይዞ በህዘብ ስለተዘፈነው ‹‹ልመደው ልመደው ሆዴ፤ ተወዷል ጤፍና ስንዴ…ሩዙን ብላው በዘዴ›› ፣ ሁሌ በጊዮን ሆቴል ጋር ሳልፍ ስለማየው የቻይና አሮጌ ምግብ ቤት፣ ስለቻይኖች የባህር ምግብ መውደድ…ስለቻይኖች ሁሉን ነገር መብላት ለፈለፍኩ፡፡ ሰይፉ ፋንታሁን ሬዲዮ ላይ ሲያወራት ጨረፍታ ፈገግታ ያስፈገገችኝኝ የዛገች ቀልድ ሳይቀር የራሴ አድርጌ አቀረብኳት፡፡ ‹‹ቻይናዎች እኮ ከባህር ውስጥ የማይበሉት አሸዋውን ብቻ ነው››…ብዬ አሳቅኩት)
በማሊ ሙዚቃ ስለማበዱ ሲነግረኝ የሙዚቃ እውቀቴን የአላግባብ ለጥጬ ላስደንቀው ለፋሁ፡፡ ( የማሊ ሙዚቃ ከኢትዮጵያ ሙዚቃ ጋር ስላለው ቅርበት መላ ምትና ከኢንተርኔት የተገኘች ተባራሪ ወሬን ደባልቄ ላስገርመው ሞከርኩ)
እንዲህ እንዲህ አድርጌ ባልሆንኩት አፈዘዝኩት፡፡
ባስመሰልኩት አደነዘዝኩት፡፡
…..ከሁለት ሳምንታት በኋላ ቤቱ ተገኘሁ፡፡
ምሳ በልተን ምሳውንም ወሬውንም ጨርሰን ስንፋጠጥ እነዛ ከንፈሮቹን ሳይ ከከንፈር ብቻ የተሰራሁ መሰለኝ፡፡
በሳምኳቸው!
ባልስማቸው እንኳን እንደ ወይን ዘለላ ግንጥል አድርጌ ስልቅጥ ባደረግኳቸው!
ከንፈሮቹ እንደ እህል ራቡኝ፡፡
አቅበጠበጠኝ፡፡
አጠገቡ ሄድኩ፡፡
ተጠጋሁት፡፡
በጣም ተጠጋሁት፡፡
በጣም በጣም ተጠጋሁት፡፡
አላሳፈረኝም፤ በከንፈሩ ከንፈሬን ስሞ ህልሜን እውን አደረገልኝ፡፡
ተስገብግቤ ሳምኩት፡፡
በደስታ ናውዤ የተዳከመ ጭንቅላቴን ቅድም የነገርኳችሁ ውብ ደረት ስር ወሸቅኩ፡፡
በደስታ ሰክሬ የተዳከመ ጭንቅላቴን ቅድም የነገርኳችሁ የሚያኮራ ደረቱ ላይ አሳረፍኩ፡፡
ከዚያ…
ከዚያ….
‹‹ሌላው ሌላውማ ለማን ይነገራል›› ብዬ ያልኳችሁ ሰውነቱን የተልፈሰፈ ሰውነቴ ላይ ሲያሳርፍ..
ሴትነቴን በወንድነቱ ሲከድን..
….አያ ሆሆ ማታ ነው ድሌ!
5 Comments
ሌላም ታሪክ አቅርቡ
ምንምአይልም አሪፍነዉ
ያምራ!
ጥ…
በታም ደስ ይላል