Tidarfelagi.com

የመጀመሪያው የአማርኛ ልቦለድ

በ1908 ዓ.ም. በሮም ባሳተሟት ልቦለድ ታሪክ የፈጠራ ሥራቸው-በኢትዮዽያ የአማርኛ ዘመናዊ ሥነጽሑፍ መሥራች ካሰኛቸው ማእረግ ባሻገር በአፍሪካ ቋንቋዎችም ታሪክ- በሀገርኛ ቋንቋ በመጻፍ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ የሚል ምስክርነት አግኝተዋል። ደራሲው ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ ሲሆኑ የልብወለድ ድረሰታቸው ‘ጦቢያ’ ትባላለች። አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ በ1860 ዓ.ም ዘጌ በተሰኘችው ስፍራ ተወለዱ፡፡ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የሥጋ ዝምድና እንዳላቸው የሚነገርላቸው አፈወርቅ በልጅነት ዕድሜያቸው አዲስ አበባ መጥተው አደጉ። ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ ያውሮፓን ሥልጣኔ ቀስመው እንዲመጡ ወደውጭ ሀገር ከላኳቸው ብልህ ወጣቶች መካከል አንዱ አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ ናቸው። አፈወርቅ የ20 ዓመት ብላቴና ሳሉ በአጤ ምኒልክ በጎ ፈቃድ ከሁለት ወጣቶች ልጅ ጉግሳ ዳርጌ እና ልጅ ቅጣው ዛማኑኤል ጋር በ1880 ዓ.ም ወደ ስዊዘርላንድ ተላኩ። ከዚያ ከደረሱ በኋላ በገዛ ፈቃዳቸውና ባልታወቀ ምክንያት ወደ ጣሊያን ቱሪን ሄደው በኮሌጅ ኢንተርናሲዮናል ደ.ቤሊ አርቲ ከፍተኛ የሥነ ጽሑፍ ትምህርት ተከታተሉ። ከአድዋ ጦርነት በ1986 በፊት ወደ ኢትዮዽያ ተመልሰው በ1882 በቤተመንግስት ባለሟልነትና በሠዓሊነት ሙያ ያገለገሉት አፈወርቅ፥ በተለይ ከእቴጌ ጣይቱ ጋር በመቀያየማቸው በ1888 ዓ.ም. በስደት መንፈስ ወደ ኢጣሊያ ተመለሱ።

በናፖሊ የምስራቅ ጥናት ኢንስቲቲዩት የአማርኛ ቋንቋ በማስተማር የፕሮፌሰርነት ማእረግ አግኝተዋል። አፈወርቅ በ1908 ዓ.ም. በሮም ባሳተሟት ጦቢያ-ልቦለድ ታሪክ የፈጠራ ሥራቸው-በኢትዮዽያ የአማርኛ ዘመናዊ ሥነጽሑፍ መሥራች ካሰኛቸው ማእረግ ባሻገር በአፍሪካ ቋንቋዎችም ታሪክ- በሀገርኛ ቋንቋ በመጻፍ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ የሚል ምስክርነት አግኝተዋል። ጦቢያ ወይም ልብወለድ ታሪክ ጦቢያ በአፈወርቅ ገብረ እየሱስ የታተመ ሲሆን 90 ገጾች አሉት። በኢትዮጵያ የሥነ ፅሑፍ ታሪክ የመጀመሪያ ልብወለድ መፅሐፍ ለመሆኑ የሚነገርለት ይህ መጽሐፍ በወቅቱ ተነስቶ የነበረውን የአረማውያንንና የክርስቲያኖችን ጦርነት ይተርካል። ደራሲው በመፅሐፉ ውስጥ ስለተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ማለትም ስለደግነትና ክፋት፣ ስለሀይማኖትና ፍቅር በሰፊው ያትታሉ። መፅሐፉ በተለይ የፍቅርን ሀያልነት ለማሳየትና የሀይማኖት ልዩነት ስላልበገረው ታላቅ ፍቅር በሰፊው ይተርካል። በተጨማሪም ደራሲው በጽሑፉ ውስጥ ሊያስተላልፉ የሞከሩት መልዕክት የሰው ልጅ በባዕድ አምልኮ ተሸብቦ ከመኖር ይልቅ ፈተናና ችግር ቢገጥሙት እንኳን ለእነዚህ ሳይበገር በአንድ አምላክ አምኖ ከጸና ድል ሊያደርግ እንደሚችል ነው። ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ፣ “ጦቢያ” ባሏት “ልብ ወለድ” ሥራቸው የመጀመሪያው አንቀጽ፣ (ኧረ በመጀመሪያውም ዓረፍተ ነገር) ስለይቅርታ ጠያቂ እና ይቅርታ አድራጊ አስገራሚ አባባል ተጠቅመዋል፡፡ “ይቅርታ ጠያቂ ያከበረ፣ ይቅርታ አድራጊውም የተከበረ ነው!” ለዘመናዊት ኢትዮዽያ ሥልጣኔ መስራች የሆኑት አፈወርቅ በኢጣሊያ ሳሉ ለኢትዮዽያ ዘመናዊ ሥነ ጽሁፍ ዕድገት የበኩር ልጅ ሊያሰኙዋቸው የቻሉትን የአማርኛ መጻሕፍት የጻፉ ሲሆን እንደገና ወደሀገራቸው በ1922 ዓ.ም. እስከተመለሱ ድረስ፥ በግእዝ፥ በአማርኛ፥ በኢጣሊያንኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች የመማሪያ መጻሕፍት፥ የታሪክ እና የፈጠራ ልቦለድ መጻሕፍትን አሳትመዋል።

ቀደም ሲል ለሀገራቸው በአስተርጓሚነት፥ በጉምሩክ ሥራ ኃላፊነት ነጋድራስነት እና በአምባሳደርነት ሮም ያገለገሉት አፈወርቅ በኢትዮዽያና ኢጣሊያን ጦርነት ወቅት 1924 – 1933 ኢጣሊያን ወገን ሆነው በ የቄሣር መንግስት መልእክተኛነት በሀገራቸው ልዩ በደል ፈጽመዋል በሚል ከነፃነት በኋላ በ1933 የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶባቸው በጅማ ጅሬን እሥር ቤት ለ6 ዓመታት በግዞት ቆይተው፥ በእርጅና እና በጤና ማጣት መስከረም 15 ቀን 1939 ዓ.ም በ79 ዓመታቸው አረፉ።

ምንጭ:ብርሀነመስቀል ደጀኔ 2000ዓ.ም ብራና.ማ.ቤ ካሌንደር።

2 Comments

  • ALEMENESH commented on December 22, 2016 Reply

    WAW

  • Negusie commented on December 19, 2019 Reply

    የአደዋ ጦርነት 1986 ላይ ነበረ እንዴ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *