Tidarfelagi.com

የ”ባቡር መጣ!?” ሁለት ጽንፎች !

‹‹…100 ዓመት የኋሊት…
እስኪ አንዴ እንንደርደር
በሸገር ጎዳና በለገሀር መንደር
ባቡር አዲስ ነበር ?
… አይደለም አይደለም
ባቡርማ ነበር በምኒልክ ቀዬ በጣይቱ ዓለም
አሁን ስለመጣ… ዘመናት ዘግይቶ
የምን ግርግር ነው የምን እንቶፈንቶ?
ይሄ ሁል ፍንጠዛ ይሄ ሁል ፍርጠጣ
‹ከባድ ባቡር ቀርቶ ቀላል ስለመጣ???›…››
………… ብላችኋል አሉ……….
ሁሉን ነገር መንቀፍ የምትወዱ ሁሉ
እና በዚያው ይቅር?
እስኪ አንዳንዴ እንፈር!

የመጣን መቃወም አሁን ምን ይባላል?
‹ዘግይቶም የመጣ ከቀረ ይሻላል›፡፡

ግን በሌላኛው ጽንፍ…
በማንኪያ ጨልፈን
እንዲያው ሀገራችን እንደተፈጠረች
ባቡር ባይኗ ሳታይ ዘመን ያስቆጠረች
…..እያስመሰላችሁ…..
…….ያለፈን ክዳችሁ…..
የታሪክ ጀማሪ ለመምሰል ‘ምትጥሩ
ባዶ አሉባልታ የምትቀባጥሩ..
እናንተም እፈሩ
ከታሪክ ተማሩ

መሠረትን ንዶ ጣሪያ ላይ ለመቆም
ምን ብዙ ቢለፋ ምን ብዙ ቢደከም
‹ከአየር ተወርውረው ምድር እስኪደርሱ›
ምን ጥቂት ቢቆዩም – እየተንሳፈፉ እስኪከሰከሱ
ውደቀት ከቶ አይቀርም ዳግም ላይነሱ፡፡
ይልቅ…
በቀጣዩ ትውልድ እንድትታወሱ
እናንተም ታሪክን ማስታወስ አትርሱ!

ታሪኩም ይወሳ አዲሱም ይደገፍ
በመነቃቀፍ ጦር ሲወጋጉ መውደቅ ከቀያችን ይለፍ!

መሠረቱ ይጽና ጣሪያውም ይገንባ
ወደ አንድ ጠንካራ ቤት ትውልድ ሁሉ ይግባ!

One Comment

  • ናታን commented on July 10, 2016 Reply

    መሌ አገኘሁህ ሃ ከፌስ ቡክ አጥቼህ ነበር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *