እኔማ ችግር አለብኝ …ከምር ችግር አለብኝ !! አሁን ሰው ሲሉኝ አሁን አፈር …አሁን ደህና ነገር እያወራሁ በቃ ሰው አፉን ከፍቶ እየሰማኝ በመሃል ዘብረቅ አድርጌ ሰው ማስቀየም ! ኤጭ …..ይሄ ልክፍት ነው እንጅ ሌላ ምን ይባላል … ለኔማ እንኳን ቢላ ጎራዴም ሲያንስ ነው የማረባ …!! እግዜርም በኔ ነገር ተቸገረ …አንድ ነገር ስፈልግ በልመና መቆሚያ መቀመጫ አሳጣውና ‹‹እስቲ ያውልህ›› ብሎ ሲሰጠኝ ብልሽትሽት ! ለነገሩ ይሄን እንኳን እድል ያመቻቸልኝ እግዚአብሔር አይመስለኝም …. ሰይጣን ራሱ ነው …. ነዋ ….እና እግዚአብሔር የሰው ሚስት ‹‹ንፁህ›› ካለው አልጋዋ ‹፣ቅዱስ›› ካለው ትዳሯ አንስቶ እንዳረካት አድርጋት ያቻትልህ አይልም ….እሱ እንዲህ ያለው የተዝረከረከ ጉዳይ ውስጥ እንዲች ብሎ እጁን አይልክም ! ….
ነቅቸበታለሁ ልእልትና እኔን እንዲህ ብቻችንን ያውም በመስኮት በኩል ፅዱ በነፋስ በሚንሻሻ …አየሩ በተከፈተው መስኮት ለስለስ ብሎ የሚገባ ክፍል ውስጥ እንደሂሳብ ውጤት ቀንሶ ደምሮ ቁጭ ያደረገን ሰይጣን ነው …..እንኳን እግሯን አይኗን እንኳ ከታመምኩ ጀምሮ ከእኔ ላይ ያልነቀለች እናቴን ዛሬ እቤቷ የላካት ሰይጣን ነው …. ንግስት ወንበሯን እንዲህ አፍንጫየ ስር አቅርባ በጠረኗ ተከብቤ እንድትቀመጥ ያደረገው ሰይጣን ነው …. ግን ሰይጣን ይሄን ሁሉ ውለታ የሚሰራልኝ ምናባቱ ሊያስከፍለኝ ይሆን ? እሱ እንደሆነ ሂሳቡ ጥልቅ ናት … ሲጀምር ግብዣውን በነፃ ያውም ‹‹አፈር ስሆን›› እያለ ያቀርብና ….መጨረሻ ላይ ቢሉን ሲያቀርበው ዋጋው ካለነፍስ አይመነዘርም ! ቢሆንም ዛሬ ሰይጣን የሰራት ስራ ከመሰይጠኑ በፊት ከነበችው የዋህ ልብ የቀረች እንጥፍጣፊ ቸርነቱን ተጠቅሞ መሆን አለበት …..ምን ዋጋ አለው … እኔ ሁሉንም ነገር አበላሸሁት !
ልእልት አጠገቤ ከተቀመጠች በኋላ ትኩሳቴን ለመለካት ይሁን ወይም ሌላ እንጃ ግራ እጇን አንስታ ግንባሬ ላይ አሳረፈችና ‹‹ዛሬ ትኩሳቱም ቀንሶልሃል›› ብላ ፈገግ አለች …እጇን ግን ቶሎ አላነሳችውም ….((ትኩሳቴን ነው ወይስ የማስበውን የምትለካው ))የእጇ ልስላሴ ከደመና የተሰራ ጓንት ያጠለቀች ነው የሚመስለው ….እጇ ላይ ሰመመን የሚመስል ልስላሴ አለ ያውም ለብ ያለ ሙቀት ጋር ….
ድንገት ግን በዚህ ልስላሴ መሃል እንደብርጭቆ ወረቀት የሻከረ ….በዚህ ለብታ መሃል እንደበረዶ ግግር ግንባር የሚፈነክት ….በዚህ ሰመመን መሃል እንደመድፍ ጩኸት አናት የሚያናጋ ….በዚህ ስስ አነካኳ ውስጥ እንደ ብርቱ ኩርኩም ራስ የሚቆፍር ነገር ተከስቶ አስበረገገኝ …..ቀለበቷ ! የጋብቻ ቀለበቷ ….ሲነካኝ እንደሌላ የሚለዋ ጥቃት ነው ሰቀጠጠኝ …. እውነቱን ለመናገር የሰውን ሚስት ክፉኛ ለተመኘ ሰው የመሻት አጋንቱን የሚያባርር ፀበል በባለትዳሮች ግራ እጅ ጣት ላይ ይፈልቃል ….ቢባል ግነት አይሆንም ! ትዳር አንዳች ሃይል አለው ….ባለቤቱ ድንበሩን ካልከፈተው በስተቀር ….ቀለበት የትዳር ቅጥር ትልቅ ሰረገላ ቁልፍ ነው ….!! ድፍን የከተማው ወንድና ሴት ጣቱ ላይ ሰክቶት ወዲያ ወዲህ ሲል ቀላል ነገር ይመስላል እንጅ ቀለበት ከወርቅ የተሰራ መንፈስ ነው ….መሻቴ ለቅፅበትም ቢሆን እብድ የበላው በሶ ሲሆን ተሰማኝ ….ብትን !!
‹‹ምነው ….››አለችኝ ልእልት በድንጋጤ እጇን ሰብስባ ….(ስትደነግጥ ስታሳስን) ሳላስበው በርግጌ ይሆናል ያስደነገጥኳት ….አንግዲህ በዚች ቅፅበት ምናለበት ‹‹ትንሽ ቁስሉ አሞኝ ነው›› ብየ ባረጋጋት …ወይም ‹‹ኧረ ምንም አልሆንኩ ›› ብል ….እኔ ግን የማይገናኝ ጥያቄ ልእልት ፊት አፈረጥኩና ፊቷን እንደበርበሬ አቀላሁት …
‹‹ወንዴን እስር ቤት ሂደሽ ጠየቅሽው ? ›› ግርምት ይሁን ትዝብት ባልገባኝ አስተያየት አየት አደረገችኝና ….አንገቷን ደፍታ ዝም አለች ከንፈሯ የተንቀጠቀጠ መሰለኝ ….ዝምምምምም…. ድንገት በዝምታ ጋን የጠነሰሰችው የሚመስል እንባ ጉንጯ ላይ ተዘረገፈ …..ኧረ ጉዴ …. ይች ልጅ መፍሰሻ ያጣ ብዙ እንባ ውስጧ አለ ልበል ….ዛሬ ጋር ስታለቅስ ሳያት ሶስተኛዋ ! ባልሽን እስር ቤት ሂደሽ ጠየቅሽው እንዴ ማለት ምኑ ያስከፋል ….አዎ ወይም አልጠየኩትም አበቃ ….
‹‹ይቅርታ ለማለት የፈለኩት ›› አልኩ …በነጠላዋ ጫፍ አይኗንና አፍንጫዋን ጠራረገችና …ከወንበሯ ተነስታ ‹‹ልሂድ›› አለች …. ‹‹ልእልት …ይቅርታ እኔ ላስቀይምሽ ፈልጌ አልነበረም …›› ተንተባተብኩ ….እኔ ስንተባተብ ልእልት ልትሄድ አንድ እግሯን ስታነሳ በሩ ተከፈተ ….እህቴ ! ‹‹ወይ ልእልትየ መጥተሸል እንዴ? ›› አለች ወደሷ በፈገግታ እየቀረበች …ወቸ ጉድ እስቲ አሁን ከምኔው አውቃት ሰው ሚስት ስም ላይ ‹‹የ›› ጨመረችበት … ?? ጉንጭ ለጉንጭ ተሳሳሙ እሟ እሟ እሟ ….አቤት አሳሳም …. እህቴ ከዘመቻ የመጣች ልእልትም የናፈቀቻት (ላለፉት ሰባት አመታት ያልተያዩ) እናትና ልጅ ነውኮ የሚመስሉት ! ደግሞ የልእልት ፊት ከምኔው ያንን ሁሉ በቦንድ እንኳን የሚገደብ የማይመስል እንባ ዋጥ አድርጎት እንዲህ ፈገግታ በፈገግታ ሆነ …..ውይ ሴቶች ! በዚህ አይነት እህቴስ ፍቅረኛዋ ጋር ሙሾ ስታወርድ እንባ ስትራጭ ቆይታ ላለመምጣቷ ምን ማረጋገጫ አለ ?? እህቴ ፈገግታዋ ፊቷ ላይ ሳከስም ጠየቀች
‹‹ምነው ቆምሽ ልትሄጅ ነው እንዴ ›› ኧረ የኔም ጥያቄ ነው …
ልእልት ‹‹አዎ ከመጣሁ ቆየሁኮ ልሄድ ነው›› ትላለች ብየ ስጠብቅ …
‹‹ አይ ሾርባ ልቀዳለት ስነሳ ነው የመጣሽው ›› ብላ እርፍ! ….አአአአአአአአአአአአአአ….. ሴቶች ምንም በማያስዋሽ ቦታ ወሪያቸው ዘነፍ ካለች ችግር አለ ማለት ነው (አንድ ጥናት አይደለም ያመለከተው እራሴ ከልምድ አውቃታለሁ) …..አለ አይደል ‹‹የእኔና አንተን ኩርፊያም ይሁን ቅይይም የግላችን ነው ….ሌላ ሶስተኛ ሰው በመሃላችን አያገባውም ›› አይነት መልእክት….ኧረ ቆይይይይ….ደግሞ ልእልት ካለወትሮዋ ዛሬ እንዴት ሾርባውን ረስታው ቆየች ‹‹ሳይቀዘቅዝ ቶሎ ልቅዳልህ›› አልነበር የምትለው …….
ያዝ እንግዲህ ….የልእልታችን ነፍስ በትንሹ ሞቅ እንዳለው ሰው(በልክ እንደሰከረ) ገድገድ ያለች መሰለኝ …. ተመልሳ ቬርሙዝ ወደተቀመጠበት የብረት መደርደሪያ ሂዳ ሾርባ ስትቀዳ ….ውብ አቋሟን ከኋላዋ እየቃኘሁ (በአንድ አይኔ እህቴን በሌላኛው ልእልትን አየ እንዳልባል አድርጌ እያየሁሂሂ) ልእልት ስለተመለሰች ደስ ብሎኝ …..‹‹ማነሽ ልእልት‹የ› ….. ከበር መልስ በኔ ሂሳብ ሾርባ ቅጅላቸው ›› ማለት ዳድቶኝ ነበር ሂሂ …..
እህቴ እየተፍለቀለቀች ….‹‹ልእልቴ ትንሽ ከቆየሽ ጓደኞቸን ሸኝቻቸው ልምጣ አቡቹ ጋር ተጫወቱ ›› አለቻት
‹‹ኧረ ችግር የለም ….የምቸኩልበት ጉዳይ የለም ደርሰሽ ነይ ›› አለቻ ልእልት ….እውነቷን ነው ምን ያስቸኩላል ….ባሏም ታስሯል ! ‹‹አንበሳው ፍርግርግ ውስጥ ነው ›› እህቴ ሹልክ ብላ ወጣች ….ልእልት በዝምታ የሾርባውን ኩባያ አቀበለችኝ….እና ወንበሯን ትንሽ ወደኋላ ሳብ አድርጋ እግሯን አነባብራ ተቀመጠች …አቀርቅራ አንድ እግሯ ላይ ተንጠልጥሎ የሚወዛወዝ እግሯን እየተመለከተች ….ዝም ብየ ሾርባየን መምጠጥ ጀመርኩ …. ድንገት ቀና ብላ ‹‹ቅቤ አነሰው እንዴ ›› አለችኝ …ሃሳብ ውስጥ ሰምጨ ዝም ብየ እጠታለሁ እንጅ ይጣፍጥም ይምረርም አላጣጣምኩትም ነበር
‹‹ኧረ አሪፍ ነው ›› አልኳት …..
እንደገና ረዥም ዝምታ በመካከላችን ሰፍኖ ቆየና ልእልት ያለምንም መንደርደሪያ እንዲህ አለች (ስታወራ ለእኔ አይመስልም)
‹‹ወንዴ ባለጌ ነው ›› …ደነገጥኩ ! ምን ልበል ….እሷም አምልጧት ውስጧ ስታስበው ቆይታ የነገር እርሾ ያቦካው ብሶቷ ገንፍሎ ይመስለኛል ቃል ሁኖ ያመለጣት ….እና ምን ልበል ‹‹ልክ ነው ባልሽ ባለጌ ነው ›› ልበል … ወይስ ምናባቴ ልበል ….ነገ ዙረው ቢታረቁ (አይበለውና) ለምን ‹‹አለ›› መባል ይትረፈኝ ብየ ላፅናናት አሰብኩ
‹‹አይ ….ማንም ሰው በብስጭት ያልሆነ ነገር ሊሰራ ይችላል በዛ ላይ ሞቅ ብሎት ነበር …ስለዚህ እኔን በቢለዋ መውጋቱ ባለጌ አያስብልምኮ ልእልት ….››
‹‹አንተ ላይ ስላደረገው ነገር አይደለም ያወራሁት አብርሽ ›› አለችና ኩም አደረገችኝ …..ኩም ብየ ሳላባራ …..በቁጣ የሚንተገተጉ አይኖቿን ወደኔ አዙራ ‹‹ታውቃለህ እኔ ተጣላሁ ብየ እንኳን ባሌን ማንንም የማማ ሴት አይደለሁም ….ላለፉት ሰባት አመታት አንዲት ቃል ለአንድም ሰው ስለወንዴ ተንፍሸ አላውቅም …ለእናቴም ቢሆን …..›› አለችና ስለወንዴ ….ትዘረግፈው ጀመረ …
እግዚዮ ይሄ ኮንዶሚኒየም ስንቱን ጉድ ነው እንዳነባበሮ ደራርቦ የያዘው … ልእልት በእልህ የሚንተገተጉ አይኖቿን ተክላብኝ በጓዳ ታፍኖ የኖረ ገመናዋን ትዘከዝከው ጀመረ …ከምር ተሳቀኩ ….አሁን ወንዴ አንበሳውን ይሄ ብሽቅ ብለው አንባቢ ‹‹ሚስቱን ስለከጀልካት ወደሷ ማድላትህ ነው ›› ይለኛል …ግን አይደለም … ማንኛዋም ሴት ብትሆን ይሄን ያህል ግፍ ከምትሸከም እንደኔ ቢለዋዋን ቀምሳ እርፍ ብትለው በስንት ጠዓሙ ….!! እኔ የምለው ግን እሽ ነገሩስ መቸም አንዴ ሆነ …ሲሆን ኖረ ልእልት እንዴት ለእኔ ነገረችኝ ….ከቢለዋ የባሰ ግፍ ተሸክሜ ኑሪያለሁ ብላ ባሏ ላደረሰብኝ ጥቃት በሷ በኩል የሚደርሰኝን ይቅርታ እና ማፅናናት እየሰጠችኝ ይሆን ?
ልእልት ያንን አስገራሚ ህይቷን እያወራችኝ ….ቆይታ እህቴ ስትመጣ ተሰናብታን ሄደች …..ልቤ አብሯት ሄደ …..ልክ ልእልትን ሸኝታ በሩን እንደዘጋች ….እህቴ አንድ አይኗን ጨፍና ወገቧን ልክ እንደነገረኛ ባልቴት ይዛና ፊቴ ልክ እንደሞዴሊስት አንድ ሁለቴ ሰበር ሰካ ብላ
‹‹አጅሬው የሚባለው እውነት ነው እንዴ ….??›› አለችኝ
‹‹ምኑ? ››
‹‹ባክህ ገብቶሃል! ….ልጅቱ ጋር ጉዳይ ሳይኖራችሁማ አይቀርም!! …››
‹‹ዝም ብለሽ የመጣልሽን አታውሪ ባክሽ… ይልቅ የምጠጣው ውሃ ስጭኝ ››አልኩ ቆጣ ለማለት እየሞከርኩ
‹‹ባክህ አልጠማህም ›› ብላ የልእልት ወንበር ላይ ተቀመጠች …ከምር እውነቷን ነው አልጠማኝም ነበር (ቡዳ የሆነች ልጅ)አንገቷን ሰገግ አድርጋ ….
‹‹ስማ ቅድም ስመጣ በሆነ ነገር እንደተቋቆራችሁ ባንኘባችኋለሁ …. አረጋጉት ብየ ነው የወጣሁት እሽ? ማንንም አልሸኘሁም ››
‹‹አንች ስራ ፈት ነሽ አቦ ››
‹‹ተው እንጅ ….እና በየት አገር ነው በሽተኛ ጠያቂው ጋር ተጣልቶ እንደዛ ተወርውራ ልትሄድ ያለች ሴት እኔን ስታይ የተረጋጋችው ?….ደግሞ አልቅሳ ነበር ››
‹‹እንዴዴዴዴደዴ አንች ልጅ ዛሬ ምን ሁነሻል ›› አልኩ ከምር ተበሳጭቸ …..ሰው የልቡን ሲነግሩት የኮረኮሩት የህል መሳቅ ብቻ ሳይሆን የጠረቀሙት ያህልም ይቆጣል ….ተቆጣሁ ….
‹‹አብርሽ ….እኔ ሚስጥርህን ላስፈለፍልህ አይደለም ….ግን ይሄ ነገር ሸክኮኛል ….ከባለትዳር ሴት ጋር መሳፈጥ ከቢላም የባሳ መዘዝ ነው የሚመዘው … እንደውም ይሄን ያህል መመላለስም አያስፈልጋትምኮ ….ባሏ በቢላ የወጋህ ሳይሆን ራሷ በመኪና ገጭታህ ምታስታምምህኮነው ምትመስለው ….እግዜር ይስጥልኝ ብለህ በጊዜ ሸኛት… ልጅቱም እንዳንት ጅል ቢጤ ነች ተያይዛችሁ እንዳታልቁ ….በኋላ የለሁበትም ….አሁንም ምን ከመሳሳለ ፕሮግራም ቀርቸ ነው እዚህ አንተን የማስታምመው …. ›› ተንቀለቀለችብኝ እህቴ …
ይች ልጅ ግን እኔ የት ሂጀ ነው እንዲህ ጣጥላኝ ያደገችው ….ከምር ታላቄ መሰለችኝ ! ያለችው ሁሉ ልክ ነው ይገባኛልኮ ግን ምን ላድርግ ልእልትን ክፉኛ ነው የምናፍቃት …
‹‹ለማንኛውም ሁለተኛ በዚህ ጉዳይ እንዲህ ስትይ እንዳልሰማሽ ….ምንም አይነት ግንኙነት የለንም …እግዚአብሔርን ‹እስካሁን› ምንም ርሌሽን የለንም ….›› አልኩ …አመነችኝ እህቴ ካላመረርኩ እንደማልምል ታውቃለች !
‹‹ይሄን በመስማቴ ደስ ብሎኛል …ውዱ ወንድሜ …..ግን ‹‹እስካሁን ›› የሚለው ቃል ‹‹ካሁን ኋላስ›› የሚል ጥያቄ አነሳ ዘንድ ያስገድደኛል ብላ ….ከት ከት ብላ ሳቀች …እኔም ሳኩኝ አሁንስ …ምናባቴ ልበል ታዲያ …..
‹‹እሽ ውሃ ስጭኝ …. ››
‹‹አሁን የእውነት ጠምቶሻል ታስታውቂያለሽ ….ውሃ ውሃ አሰኘችህ …አይደል ….ግንኮ ልጅቱ እንዴት አባቷ እንደምታምር …›› ብላ ውሃውን አቀበለችኝ …..ስጠጣ ትክ ብላ እያየችኝ ነበር ጥናት የሚመስል አስተያየት …. በቀልዷ ውስጥ ስጋቷ ቁልጭ ብሎ ይታየኝ ነበር …. ቢሆንም ወዲያው ልእልት የነገረችኝ ጉዳይ አእምሮየን ሞላውና እህቴን በቆመችበት ረሳኋት !!
One Comment