Tidarfelagi.com

በአልጋው ትክክል (ክፍል 15)

ዝም ያለ ነበር ህይዎቴ ….ዝምታ ሰላም እንዳልሆነ ያወኩት አሁን ነው …አንዳንዴ ዝም ያለና ፀብም ፍቅርም የለሌበት ህይዎት ስጋትም ተስፋም የሌለበት ኑሮ እንደኩሬ ውሃ መሆኑም የተገለጠልኝ ሰሞኑን በልእልት ምክንያት በተፈጠረው ትርምስ ነው ! ላለፉት አምስት አመታት ተመልሸ የኖርኩትን ህይዎቴን ሳስበው ማንም ጋር ተጣልቸ አላውቅም … በምንም ነገር ሰግቸም አላውቅም ….እሰራለሁ ደመዎዝ እቀበላለሁ እኖራለሁ ! ሰዎች ሁሉ ‹‹ጥሩ ልጅ›› ይሉኛል ….አበቃ ! ልእልት ግን መጣችና ልክ ወደውሃ እንደተወረወረ ጠጠር ዝም ባለ በረጋ አኗኗሬ ላይ ሞገድ አስነሳችበት (ጌታ ይባርካት) …. አንዳንዴ ፍቅር ራሱ ‹‹ካልደፈረሰ አይጠራም›› በሚባለው የአበሻ ብሂል ሳያምን አይቀርም መሰል …እንደፍቅር ደስ የሚል ረብሻ አለ እንዴ ? ምንም ህግ የማያውቅ ለምንም አይነት ህግ የማይገዛ ጋጠወጥ ስሜት እኮ ነው …ደግሞ ማንቀዥቀዡ ….ተንቀዠቀዥኳ ….!

ቢሮየ ውስጥ ወንበሬ ላይ ደገፍ ብየ እያንዳንዷን የልእልትን ቃል እከልሳታለሁ ….ደግሞ የእህቴ ‹‹ከዚች ልጅ ተጠንቀቅ › ምክር ያብሰለስለኛል ….ግን ….ለምን እንደሆነ እንጃ አልፈራም …ልእልትን ከወደድኳት ጀምሮ ፍርሃት የሚባል ነገር ከስሜቴ መዝገበቃላት ተሰርዟል … የልእልት ታሪክ ያሳለፈችው ውጣ ውረድ ነው እንደጅረት አይምሮየን ሞልቶ የሚፈሰው ….. ከነአተራረኳ ከነውብ ፈገግታና ሃዘኗ ……ልእልት ልእልት ….. የወንዴ አንበሳው ሚስት ልእልት ….የእኔ ልእልት …..የእኔና የወንዴ አንበሳው ልእልት …እንዲህ አለችኝ …እንደኩሬ ውሃ ጥርት ባሉ አይኖቿ ግድግዳውን እየተመለከተች …..
**** **** *****
‹‹ በቃ ወንዴ ካኮረፈኝ ጀምሮ ፊልም አስጠላኝ …መውጣት ከበፊቱም አልወድም … ቁጭ ብየ እቆይና እተኛለሁ … እነሳለሁ …..አንዳንዴ የተዘጋጀውን ቤት እንደገና እመነቃቅረውና ማዘጋጀት እጀምራለሁ …(ምንድነው የሚባለው …ስራ ያጣ መነኩሴ ምኑን ቀዳዶ ይሰፋል እንደሚባለው) የቁም ሳጥኑን ልብስ ተጣጥፎ ከተቀመጠበት እየጎለጎልኩ አወጣና እንደገና እያጣጠፍኩ መደርደር መሰቃቀል እጀምራለሁ …እያንዳንዱ ልብሴ ላይ ትዝታ አለኝ ….እያንዳንዱን ቀሚስ ባነሳሁ ቁጥር ለብሸ የሄድኩበት ሬስቶራንት ….የሄድኩበት ኮንሰርት ተግተልትሎ ወደአእምሮየ ይመጣል …. ….ቁም ሳጥኑ ልብስ ሳይሆን ትዝታ የታጨቀበት ይመስለኛል …አየህ አብርሽ ልብስ ሰውነታችንን መሸፈኛ ግርዶሽ ብቻ አይደለም እያንዳንዱ ውሏችን የሚፃፍበት የሚለበስ ብራና ነው !! ››
ልእልት በለበሰችው እጅጌ ረዥም ሹራብ ወደመዳፏ እጅጌውን ሳብ አድርጋ እንባዋን እንደህፃን ልጅ በልብሷ ጠራረገች …

‹‹….በፊት በፊት ገደል መስሎ የሚታየኝ የቤት ስራ አሁን ሳልጀምረው ያልቅብኛል ቀኑ አይሄድም … (ቀኑ እንዴት እንደሚንቀረፈፍ አብርሽ ) በረንዳ ላይ ወጥቸ እቆማለሁ…ዝም ብየ ከላየ ወደታች አላፊ አግዳሚውን አያለሁ ….በደህናው ጊዜ ስራ ሲሄዱና ሲመጡ ወደትምህርት ቤት ዩኒፎርማቸውን ለብሰው የሚሄዱ ተማሪዎች ያሳዝኑኝ ነበር …..እንዲህ የሚደክሙት እንደኔ ለማረፍ ነበር የሚመስለኝ ….አሁን ግን ቀናሁባቸው ….ቢያንስ የሚሄዱበት ቦታ አላቸው ! …ብዙም በረንዳ ላይ አልቆይም … የጎረቤቱ አይን ሊበላኝ ይደርሳል ….ኑሮየ መበጥበጡን የሰሙና የሚስቁብኝ ይመስለኛል … ለምን እንደሆነ እንጃ ሁሉም ጎረቤቶቻችን አይወዱኝም ….. በኋላ ነው የተረዳሁት ይሄንን …
….አብርሽ ….‹‹ጫት መሃበራዊ ኑሮን ያበረታታል …. ሰው ጋር ያቀራርባል ምናምን ሲባል ሰምተህ ይሆናል ውሸት ነው !! ውሸት !! ….ጫት የመጨረሻ ግዴለሽ ነው ሚያደርግህ ….ጫት እየቃምክ የምትቅምበት ቤት ተቃጠለ ቢሉህ እንኳን መነሳት ሸክም ነው የሚሆንብህ … ከቃሚ ጓደኞችህ ውጭ ….ለዘመድ ግድ የለህ …ጎረቤቶችህ ሰው ይሁኑ አውሬ ቀና ብለህ አታያቸው ….ቢታመሙ ቢቸገሩ አታስታውሳቸው …..መሃበራዊ ኑሮህን ግድል ነው የሚያደርገው ግድል!… በቃ እያለህ የለህም !! አይገርምህም ….እንኳን ሌላ ቦታ መሄድ ኮካ ምናምን ምንጣፍ ላይ ሲደፋ እንኳን ከፍራሽህ ተነስተህ መወልወያ ማምጣት እዳ ነው ሚሆንብህ … ስንት የሚቆጨኝ አጋጣሚ አለ መሰለህ ….እየቃምኩ እናቴ ደውላ እንደምትፈልገኝ እየፈራች ስትነግረኝ እቤት ላለመሄድ ሰበብ ደርድሬ የቀረሁበት ጊዜ አለ …..››
ልእልት ሳግ እየተናነቃት አለቀሰች …..ውስጧን በቁጭት ያቃጠላት ነገር አለ …..በተለይ ‹‹እናቴ›› ስትል ጉሮሮዋ ላይ አንዳች ነገር የተሰነቀረባት ነበር የምትመስለው …. ዝም ብ አያታለሁ …. ከቃላት በላይ ፊቷ ላይ ያለው ሃዘን ብዙ ነገር ይናገር ነበር !
‹‹አንድ ቀን ያች እማማ ቁንጥሬ የሚባሉት ሴትዮ ቤት ቡና ተፈልቶ ጎረቤቶቹ ሁሉ ሲሳሳቁና ሲጫዎቱ በረንዳ ላይ ቁሜ አያቸዋለሁ ….እንዴት እንደቀናሁ አብርሽ …. ቢጠሩኝ ‹እሽ› ብየ ነበር የምገባው … እንደውም አትታዘበኝና የሆነ እንዲያዩኝና …ነይ ምናምን እንዲሉኝ በረንዳው ላይ ወደደረጃው በኩል ጠጋ ብየ ቆምኩ ….ቡና ፈልጌ አይደለምኮ …ሰው ናፈቀኝ በቃ ….እኩያቶቸ አይደሉም ግን ምንም ይሁኑ ….ራሴ ከመፈንዳቱ በፊትና ልብሴን ጥየ ከማብድ የሆነ ሰዎች መሃል መሆን ፈለኩ… ልክ እንደሱስ ….ለካ የሰውም ሱስ ይዞኝ ነበር …ከህፃንነቴ ጀምሮ ወንዴ ጋር እስክንጣላ በሰው አጀብ መሃል ነበርኩ …ዛሬ ራቁቴን አስቀሯት ነብሴን … ሳቃቸው ጨዋታቸው ናፈቀኝ …. እስቲ አሁን ሌላው ሁሉ ቢቀር ያ እባብ ኢያሱ ይናፍቃል ?…አብርሽ ሙት የወንዴ ጓደኛ ኢያሱ ናፈቀኝ …
ቆይ እኔ የዚህ አገር ልጅ አይደለሁም እንዴ ….ብየ አሰብኩ …የሆነ አረብ አገር ምናምን ብቻቸውን ጓዳ ውስጥ ይዘጋባቸዋል እንደሚባሉት ሴቶች አረብ አገር ያለሁ መሰለኝ ….አዲስ አበባ ያለሁ አልመስል አለኝ …. ዝም ብየ የእማማ ቁንጥሬን በር በራቸውን እያየሁ ቁሚያለሁ ….እማማ ቁንጥሬ ድንገት ወጥተው በር ላይ የከሰል ፍም ትርክክ ብሎ የተያያዘበትን ምድጃ አንስተው ሊገቡ ቀና ሲሉ አይን ለአይን ተገጣጠምን … ሰላም ልላቸው ፈለኩ …..
ያኔ ስማቸውን አላውቀው … ምን ብየ ሰላም እንደምላቸውም ግራ ገባኝ …መቸም ትልቅ ሰው ናቸው ሰላም ይሉኛል ብየ አይን አይናቸውን ሳይ …. ‹‹የምን እንደ ቱሪስት ሰው ላይ ማፍጠጥ ነው… ተኮርቶ ተሙቷል ›› ብለው ወደቤታቸው ገቡና በራቸውን ፊቴ ላይ ደረገሙት ….አዘጋጋቸውን ብታይ ተናካሽ ውሻ የሚያሯሩጣቸው ነበር የሚመስሉት ! ምንምኮ አላደረኳቸው ….አለም ሁሉ ፊቱን ያዞረብኝ ነው የመሰለኝ ….ሾክክ ብየ እቤት ገባሁና አርፌ ቁጭ አልኩ እስከማታ ከተቀመጥኩበት አልተንቀሳቀስኩም !
‹‹ በቃ ባዶ ቤት ….እንዲቹ ስንቆራጠጥ ይመሻል …. ወንዴ ይመጣል … ደግሞ ማታ ሲመጣ አያመሽም …. በጣም ቆየ ከተባለ እስከአንድ ሰአት ነው ….አይገርምህም አብርሽ ባያናግረኝም መምጣቱ ውስጤን ያስፈነድቀዋል ወንዴ ብርቅ ይሆንብኛል …ቤት ውስጥ የማይናገር የማይጋገር መንፈስ የገባ እንጅ ሰው የገባ አይመስለኝም አናወራም … ባናወራም ካሁን አሁን የሆነ ቃል ከአፉ ወጥቶ ይፈውሰኛል እያልሁ እንደፈጣሪ ቃል የወንዴን ድምፅ በጉጉት እጠብቃለሁ ! ይገዝፍብኛል …ወንድ ቤት እግርና እጇን ብቻ ይዛ የገባች ሴት ታላቅነቷ ፍቅር እስካለ ብቻ ነው …ፍቅር ያከተመለት ቀን … በስፒል እንደወጉት ፊኛ መንፈሷም ታላቅነቷም እየሞሸሸ ከባሏ እግር ስር ነው ኩርምት የምትለው ..!!
ወንዴ ገብቶ ይተኛል ሰላምታ የለ ምን የለ ወደኔ ሁሉ አያይም መአም ማን ይመጣል ብሎ እንጅ ሶፋ ላይ በእኔ ምትክ የሆነ ሰውየ ተቀምጦ ቢጠብቀው እንኳን የሚለየን አይመስለኝም ….ወደምኝታ ቤት ሲገባ የእርምጃው ፍጥነት ላይ የሆነ መልክት አለ ‹‹እዚሁ ሳሎን ተኝ እንዳትመጭብኝ የሚል›› የሆነ መግፋት አለ ! ፀብም እኮ አይነት አይነት አለው ….እንዲህ ጋግርታም ፀብ እንዴት ይቀፋል መሰለህ …በባልና በሚስት መሃል ሳይሆን በሟችና በገዳይ መካከል ግድያው ከመፈፀሙ አንድ ሰዓት በፊት የሚኖር አይነት የመረረ ኩርፊያ ነበር !
ሰው እንዴት እንዲህ ባንዴ ይቀየራል እያልኩ አስባለሁ ….ቀን እንዲሁ ሰውነቴ ስለማይደክም ነው መሰል ሌሊት እንቅልፍ ያስቸግረኛል …. እንቅልፍ የወሰደው ሰው አጠገብ እንቅልፍ እንደማጣት የሚያሳቅቅ ነገር የለም …..መገላበጥ ራሱ ያስፈራሃል …የምረብሸው እየመሰለኝ እጨነቃለሁ ….ወንዴ ድብን ያለ እንቅልፍ ይወስደዋል …. ሌሊቱ ከቀኑ የበለጠ ረዥም ነው …. አንድ ነገር ታዲያ ይከነክነኝ ጀመረ …. ሌላው ሁ……ሉ ነገር ይቅር እሽ ……ግን ወንዴ የወሲብ ፍላጎቱ የት ሄደ ?›› ልእልት ይችን ቃል ስትናገር እንደማፈር አለች …እፍረቷ በምሬት የተቀየጠ ነበር !

‹‹ ……ቢያንስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተጋጨን በኋላ (ከተጋጨን ልበል እንጅ ) ከሃያ ቀን በላይ እንዲች ብሎ አልነካኝም….ያ እንኳን አንድ አልጋ ላይ አጠገቡ ተኝቸ በጓደኞቹ መሃል እንኳን አይኑ ሲያርፍብኝ አይኑ በእኔ ፍላጎት የሚንቀለቀል ልጅ እጀ ሲነካው በደስታ የሚቃትት ልጅ …ያ በሰው መሃል ሳይቀር አጉል ቦታ እየነካ የሚያሳቅቀኝ የሚያቅበጠብጠው ልጅ እንደሃረግ እኔ ላይ ካልተጠመጠመ የማይቆም ልጅ … እንዲህ ነገር አለሙን ትቶት ለሽ የሚልበት መረጋጋት ከየት አመጣ … እንዲሁ ይከነክነኝ ጀመረ … እንዴ …እንዲሁ መቅበጥ አምሮኝ እንኳን ጀርባየን የሰጠሁት ቀን(አለ አይደል ነገ የተም አትሂድ ብየው የሆነች ጉዳይ አለችኝ ደረስ ብየ ልመለስ ምናምን ብሎኝ ነገር ) ጆሮ ግንዴ ስር ከንፈሩን ደቅኖ የሚያንቆረቁርልኝ የማለማመጥና የቁልምጫ መዓት ፊቴን ወደሱ ካላዞርኩ በስተቀር አይቆምም ነበር ….እኔም አልጨክንበትም ነበር ያው መቆላመጡን መለመኑን ፈልጌ እንጅ …እና ዛሬ ምን ተፈጠረ …ከምር ምን ተፈጠረ ….
አለችና አምስቱንም የግራ ጣቶቿን ውጥር አድርጋ ዘርግታ ቀለበት ያለበትን ጣቷን በትኩረት ስትመለከት ቆየች (ቆንጆ ጣቶቿን የምታደንቅ ነበር የምትመስለው ) ግን ልንገረው አልንገረው የሚል ማንገራገር ፊቷ ላይ ያየሁ መሰለኝ …ደግነቱ ራሷ ቀጠለች
‹‹አንድ ቀን ሌሊት ወንዴ እንቅልፍ ሳይወስደው ልክ እንቅልፍ እንደወሰደው ሰው ሲተነፍስ ታወቀኝ (ይችንማ ስንት ቀኔ እኔ ሳደርጋት… ትጥፋኝ እንዴ…እስቲ አሁን ምን ድራማ ያስፈልጋል …) እናም ማረጋገጥ ፈለኩ …አየህ በዛች ቅፅበት ወሲብ ፈልጌ አልነበረም በጭራሽ …. ግን ቁርጤን ልወቀው ብየ ነው … ለወንድ ልጅ የወስቢ ፍላገቱን የሚያስገፋ ስሜት በልቡ ካደረ ነገሩ ቁርጥ ነው …. ፍቅር ሙቶ መተሳሰብ አፈር በልቶ እንኳን ወንድን ልጅ እንደቀጭን ክር ከሴት ጋር አያይዞ የሚያቆየው ወሲብ ስሜቱ ነው ….እሱን ከገፋ …
እናም ወንዴን ጠጋ ብየ ከኋላው አቀፍኩት ….እንዳልሰማ ሰው ዝም አለ … (ትንፋሹን ዋጥ ሲያደርጋት ግን ገብቶኛል እንዳልተኛ) ጡቶቸ ጀርባው ላይ እስኪጨፈለቁ ተለጠፍኩበት … በረዝሙ ተንፍሶ ወደኋላ በትከሻው ገፋ አደረገኝና ተነስቶ መብራቱን አበራ …. የአልጋ ልብሱን ጓፎ ከአልጋው ላይ አነሳና እየጎተተ ወደሳሎን ሄደ … በቃ ሳሎን ሂዶ ተኛ !!›› ብላኝ ‹አትገረምም እንዴ ›› በሚመስል አስተያየት ትክ ብላ አየችኝ
‹‹ …..ከምሽቶችም በጣም የጨለመች ምሽት አለች …ከጥላቻም አጥንትህን ሳይቀር ሰነጣጥሮ የሚጥል ጥላቻ አለ … ከንቄትም እንበረዶ የሚያገግርህ ንቄት አለ …ፍቅርህ ሲናቅ ስጋህም ይናቃል … ወንድን ልጅ ሁልጊዜ እንደውሻ ስጋ እየጣልክ ወዳንተ አታመጣውም … አንዳንዴ ከውሻም የባሰ አውሬ ሁኖ ጫካውስጥ ያጠመደውን ስጋ እንክት አድርጎ መጥቶ ይሆናል ! የወንዴ ነገር እስካሁን ‹‹ነጋችንን እናስተካክል ›› በሚል ተራ የነገ ህልም ነበር ሲያመናቅረኝ የነበረው ….አሁን ግን ነገ አብረን ስለመሆናችንም ተጠራጠርኩ ….ስለዚህ ወንዴ ገደል ይግባ ለሱ ብየ እስረኛ ሁኛለሁ ትምህርቴን ትቻለሁና ካሳ ይገባኛል የሚል ሃሳብ ልቤ ውስጥ ጠጫረ ….አብሮ ለመሻገር ሳይሆን ድርሻየን ይዠ ለማምለጥ ብቻ ማሰብ ጀመርኩ …‹‹ እኔ ›› ብቻ ሆነ አጀንዳየ ! ደግሞ አፈርኩ ወንዴ አሳፈረኝ … አያናግረኝ …ግን እንደቆሻሻ ሲፀየፈኝ አሳፈረኝ ….በዛች ቅፅበት ብችል እኔም ወንዴ ከሸሸው ሰውነቴ ወጥቸ ወደሆነ ጥግ ብደበቅ ደስታየ …ቆዳየን እንደልብስ አውልቄ እዛው አልጋው ላይ ጥየው ወደልጅነቴ ማንም ወዳልነካው ወንዴም ወደሚንሰፈሰፍለት ልጅነቴ ብሸሽ ደስታየ …
እንዲቹ ስንገበገብና ስገላበጥ ሊነጋ አካባቢ እንቅልፍ ወሰደኝ ! ስነቃ ረፍዶ ነበር …እንደውም የምሳ ሰዓት እየተቃረበ ነበር …. ወንዴ የለም …. ተነስቸ በፒጃማ ሳሎኑ መሃል ቆምኩ … ወንዴ ለብሶት ያደረው ብርድ ልብስ ግማሹ መሬት ግማሹ ሶፋው ላይ ተዝረክርኮ ተቀምጧል የሌሊት ልብሱ የሶፋው ጠረጴዛ ላይ በግዴለሽነት ተጥሏል ..ታውቃለህ ወንዴ ተጣላን ብየ አይዋሽም መዝረክረክ የማይወድ ልጅ ነበር ….ቢሞት የተኛንበትን አልጋ እንኳን ሳያነጥፍ አይወጣም ….ልብሱንማ ሲያጥፍ ትኩረቱ ራሱ የሆነ ተአምር የሚሰራ ነው የሚመስለው ….እንግዲህ ይሄ መዝረክረክ ‹‹ይህን እንኳን ሰርተሸ ብይ ›› የሚል ንቄት መሆኑ ነው ….ዝም ብየ ቤቴን አፀዳዳሁ …..ፍሪጅ ውስጥ ያገኘሁትን ወተት ጠጥቸ መልሸ ወደምኝታ ቤት ገብቸ ተኛሁ … በሽተኛ የሆንኩ ነው የመሰለኝ … ሻወር እንኳን ለመውሰድ አቅም አነሰኝ …ከውስጤ የሆነ ነገር ተንጠፍጥፎ ሲያልቅ ይሰማኛል !
ብርሃን ማየት አስጠላኝ ሽፍንፍን ብየ ተኛሁ ….መደበቅ በለው …ከማን እንደምደበቅ እንጃ …. እናቴ ጋር መሄድ ፈልጌ ነበር ግን እንደዚህ በተሰበረ ልብ መሄድና የእሷን አይኖች ፍተሸ በማስመሰል አልፌ ልሸውዳት አልችልም ….የእኔ ፊት ለእናቴ መፅሃፍ ነው ታነበዋለች ‹‹ምን ሆንሽ ብትለኝ ምን እላለሁ ›› ይሄን እያሰብኩ እንደተኛሁ በሬ ሲንኳኳ የሰማሁ መሰለኝ …ምን እንዳስበረገገኝ እንጃ ዘልየ ተነሳሁ (ሰው መናፈቅኮ ነው አብርሽ ) ….እንደገና ተንኳኳ ….ማንም ይሁን ሌባ ነብሰ ገዳይ …ምንም ይሁን ብቻ ሰው ቤቴን አንኳኳ እንኳን እኔ በሩም መንኳኳት የሰው እጅ የናፈቀ ይመስለኛል …..ድምፁ ሙዚቃ ነው የሆነብኝ …..
ማነው እንኳን አላልኩም በሩን ከፈትኩ ….ኢያሱ !! ማመን አልቻልኩም …በጉያው በጋዜጣ የተጠቀለለ ጫት ይዟል … ፈገግ አለ ….ታምናለህ አብርሽ ያ መጥፎ ልጅ አልመስልሽ አለኝ ዘልየ ብጠመጠምበትና ብስመው ደስታየ …. ዝም ብየ አየሁት …
‹‹ምነው መግባት ተከለከለ እንዴ ›› አለኝ ..ተሳሳቅን …እቤት ገብቶ ጫማውን ሲያወልቅ ጫቱን ሶፋው ላይ ወርወር አድርጎ ፍራሹ ላይ ሲቀመጥ ..ዝም ብየ እንደእንግዳ ፍጥረት አየዋለሁ ….በሩን እንኳን አልዘጋሁትም …. እንደውም እንባየ መጣ …..
‹‹ዛሬ ልእልትን ሳላያት አልውልም ብየ ሳልነግራቸው ሹልክ ብየ መጣሁ …አላስችል አለኝ …ጀመዓውማ ከቤቷ አባረረችን ብሎ አድሟል ሃሃሀሃ ›› አለ ሊያየኝ ስለመጣ ደስ አለኝ …አሁን ገና ነው በአጭር የሌሊት ልብስ መሆኔ ትዝ ያለኝ ከውስጥ እንኳን ምንም ነገር አለበስኩም ….በሩን ዘግቸ ወደመኝታ ቤት ገብቸ ያገኘሁትን ፒጃማ አጥልቄ ፀጉሬንም እንደነገሩ አስተካክየ ወጣሁ ….የሆነ አመትባል ነው የመሰለኝ … የኢያሱ ማንነት ያ የምፈራው ነገሩ ሁሉ ከአእምሮየ ድራሹ ጠፍቶ እንዲሁ ውስጤ ሲቀርበው ተሰማኝ ……ምሳ ልሰራ ቡናም ላፈላለት ጉድ ጉድ ማለት ጀመርኩ …. እንደውም እንደገና እርም ብየ የተውኩት ጫት አምሮኝ እርፍ !! ምናለበት አንድ ሁለት ቅጠል ብነክስ ?…. ካላበድኩ በስተቀር እንዲህ አስታውሶኝ የመጣ ልጅ እንደገና አላስቀይም መቸስ . . .
‹‹ተጫወት ››አልኩት
‹‹ ምኑን ተጫዎትኩት ትተሸኝ ጠፋሽኮ ›› አለኝ በፈገግታ ….
‹‹መጣሁ እኔም አልበላሁም ምሳ እየሰራሁ ነው …..››
‹‹አምሮብሻል ደግሞ …›› አለኝ ከእግር እስከራሴ እያየኝ
‹ምን ያምርብኛል …. ድብር ብሎኝ ነበር ባክህ …›› አልኩትና ወደኪችኔ ተመለስኩ ….….ግን ከበረዶ ግግር ውስጥ ወጥቶ ፀሃይ እንደነካው አይነት አድናቆቱ ሰውነቴን ፈታ ሲያደርገው ተሰማኝ . . .

በአልጋው ትክክል (ክፍል 16)

3 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *