ውሃ በተሞላ ብርጭቆ ውስጥ ማንም ውሃ መጨመር አይችልም ….ፍቅር የተሞላ ልብም ማንንም ማፍቀር አይችልም … ሁለት ሰዎች ከተፋቀሩ ብቸኛው ምክንያት ሁለቱም ልብ ውስጥ ያለው ክፍተት ነው ሊሆን የሚችለው ! ልእልት እኔ እንዳፈቀርኳት ካፈቀረችኝ ሲጀመር የፍቅር ፅዋዋ ጎደሎ ነበር ማለት ነው !
አይ ባለትዳር ስለሆንሽ የፍቅር ኮታሽን ጨርሰሻል የሚለው ማነው …..ማንም ሰው ፍቅር ከያዘው ማንም ጋር ይጋባ ማንም ጋር ይሁን …አብሮ ነበር እንጅ አንድ ላይ አልነበረም !! አብሮ በመሆን ውስጥ ስንት አይነት መለያየት አለ ….አንዳንዴ ያፈቀርነውን ሰው ጉድለት ልንሞላ ያለንን ሃይል ሁሉ አንጠፍጥፈን ተፈቃሪውም ሳይሞላ እኛም ባዶ ሁነን የምንቀርበት ስንት ሰቆቃ አብሮነት አለ ….እና ምንድነው የሚያስጨንቀኝ ….
ልእልት ጋር ማውራት አልደከመኝም አይደክመኝም … ስታወራኝ አፏ ጥግ ከናፍርቶቿ ግርጌ ተደቅኘ በጉጉት ነው የምሰማት ….ሁልጊዜ እንደአዲስ የሚጀመር ታሪኳ በትረካ እግሩ የትም ረግጦ ማረፊያው እኔ እሆን ይሆናል የሚል ተስፋ ታሪኳ ጋር ሲያናውዘኝ …ከከናፍርቷ የሚወጡት ቃላት በአንዳች ክር ከእኔ ፍርቱና ጋር ይቋጠሩ ይሆን ብየ ነው ስሰማት የኖርኩት ….. ያውም ለልብ ድካም የሚዳርግ ተስፋ ውስጤን እየናጠኝ ….አንዳንዴ እንደፊልም እንደሙዚቃ ‹‹በሪሞት ኮንትሮል›› የልእልትን ታሪክ ማሳለፍ ቢቻል ባንዴ አሳልፌው ዛሬ ምን ላይ ነሽ ነገስ የእኔና የአንች እጣ ፋንታ ምን ይሆን ማረፊያው የሚለውን ማየት እመኛለሁ ….
ጭንቀት አልፈልግም ….ሃሳብ አልፈልግም …ሞራል አልፈልግም… ህግ አልፈልግም …ሃይማኖት አልፈልግም …የምፈልገው ልእልትን ዝም ብየ ማፍቀር ነው !! ካለምንምና ካለማንም ገደብ!! አይኖቿን ማየት ምንም ታውራኝ ስታወራኝ ማየት !! ባለትዳር ነች አውቃለሁ ….ባለትዳርን ማግባት እንጅ ማፍቀር አይቻልም የሚል ህግ የት አገር ነው ያለው ….? ቢኖርም የራሱ ጉዳይ …ስሜቴን አፍኘ ባለትዳር ስለሆንሽ ካንች ጋር አልነከካም የሰው አፍ ቢስተኝ የግዜር ቁጣ በመብረቅ ያደባየኛል ‹‹ጎመን በጤና›› ብየ በየደይቃው የሚያስበረግገኝን ስጋት ነግሪያት የተጨበጨበለት ጨዋ መሆን እችላለሁ ! ‹‹ዋው እሱ የህሊና ሰው›› መባል እችላለሁ ! እሱ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው …መባል እችላለሁ …..ግን ፍቅር የነፍስ ሃቅ ነውና እድሜ ልኬን የሆነች ልጅ ስናፍቅ መኖር አልፈልግም … እንኳን ካሁን በኋላ ለናፍቆት ራሴን ላስማርክ ቀርቶ ሳላውቃት ስናፍቃት የኖርኳት ልጅ እሷ እየመሰለችኝ ሳስበው ያለፈው ትላንትም ይደክመኛል !!
ደግሞ ልቤ ላይ ያለው ፍቅር የሚነግረኝ ይሄንኑ ነው ….ልእልትን ‹‹ቻው›› ብየ እስከአለም ጥግ መሄድ እችላለሁ ….የሆነ ስርቻ ውስጥ መደበቅ እችላለሁ የሆነች ሴት እቅፍ ውስጥ ተሸጉጨ ‹‹ተውኩሽ›› ማለት እችላለሁ ….ግን ልእልትን ከልቤ ..ከህሊናየ ….ከአንደበቴና ከትዝታየ ስንዝር ማራቅ አልችልም ….አፍቅሪያታለሁ !! ….ልቤ ተወጣጥራ ከተወሰኑ ደይቃዎች በኋላ ልትፈነዳ የተዘጋጀች የሰአት ቦምብ ትመስለኝ ከጀመረች ቆየች !! እያንዳንዱ የልብ ምቴ ፍንዳታውን ለማብሰር ቁልቁል የሚምዘገዘግ ቁጥር መሰለኝ …10…9…8…7…. 6……እንደዜሮ ሩቅ ቁጥር የለም ወደዛ ፈንድቶ በበታተነኝና ባረፍኩት …እንደዚህ ሁኘ አላውቅም ….አፍቅሬ አውቃለሁ ግን እንደዚህ ሁኘ አላውቅም ! እንደውም ይሄም ፍቅር ያም ፍቅር ከሆነ ያለፈው ፍቅሬ እቃቃ ጨዋታ ነበር !!
ትንፋሽ ያጥረኛል …ሃሳብ ያጥረኛል …. በዚች አለም አጠረኝ ተብሎ የማይቆም ነገር ቢኖር ሃሳብ ነውና ልእልትን አስባታለሁ ….ሳላቋርጥ በቀን ሁሉንም ጊዜ አስባታለሁ ! በዚህ ሁሉ ስቃይ ውስጥ ፍርሃት ውስጥ አርጅቶ እንደቆመ ታንክ አፈሙዙን ዘቅዝቆ የኖረ የዛገ እኔነቴ ልእልትን ሳስብ ያንሰራራል ….አፈሙዙ ተቃንቶ ፊት ለፊቴ ወዳለው የብቸኝነት ተራራ ….የመገለል ግርዶሽ …. የልእልትን ፍቅር እንደጥይት ጎርሶ ሲተፋውና ሲያፈራርሰው ይታየኛል ….ለምን ቆንጆ ስለሆነች ነው ?…አይደለም!! ከምር አይደለም! ….ያፈቀርኳት ስላወራችኝ ነው … ልእልት ስታወራኝ የምታደምጠኝ ነው የሚመስለኝ ….ህይዎትን ስንዝር በስንዝር የምታይበት ጥልቀት አይኖቿ እኔ ላይ እንዲያርፉ ያስመኘኛል ….
ያሳለፈችውን ስቃይ የማትረሳ ሴት የሚመጣውን ፍቅርም ለመቀበል ብዙ ቦታ በልቧ እንዳለ ነፍሴ ሹክ ይለኛል !! ደግሞ ባለፈችበት የሰቆቃ ህይዎት ሁሉ እኔ አብሪያት ስላልነበርኩ እራሴን እወቅሳለሁ ….አይገርምም ? ከዚህ በፊት የማላውቃት ሳይሆን እያወኳት እኔን አምና አድነኝ እያለች ልብሴን ስትጎትት ጀርባየን የሰጠኋትና በእኔ ቸልተኝነት ይሄ ሁሉ ቆሻሻ ችግር የደረሰባት እየመሰለኝ እራሴን እወቅሳለሁ ….ከዚህ በኋላ በዚች አለም ከእኔ ውጭ ጠባቂ የሌላት ትመስለኛለች ….!! ቢሆንም ልእልት ስታወራኝ እሰማታለሁ ….ቃል በቃል ነጥብ በነጥብ ትንፋሽ በትንፋሽ ! እሰማታለሁ ሳይሆን አጠናታለሁ ! ጣቷ ላይ ካለው የቃል ኪዳን ቀለበት የጠነከረ አንዳች ሰንሰለት ነገር ልባችንን ያስታሳሰረው እየመሰለኝ በዚች ምድር ላይ ሁሉንም ነገር እንቃለሁ …ከእርሷ በስተቀር ….!
….በማፍቀሪያ እድሜዋ ይሄን ሁሉ የተንዘላዘለ መራር ታሪክ የሞላት ማነው ….እሰይ እንኳን አፈቀርኳት …ባለትዳር አፈቀረ ብለው እርኩስ ይበሉኝ ሰዎች …ከፈለጉ ሰልፍ ይውጡ !! ፎቶየን በየመንገዱ እያቃጠሉ ይቃወሙኝ ! አለም እኔን አስመስየ ከሚቀድሰኝ …እውነቱን ለራሷ ነግሪያት ሲያረክሰኝ ይኑር …. ሲጀመር ልእልት ያገባችው ባሏን ስለወደደችው እንጅ አብርሃም ከሚባል ልጅ ለመሸሽ ብላ ነበር እንዴ ?? ታዲያ ምንአባቱ ሁኖ ነው ህሊናየ የሚነተርከኝ ?? የልእልትን ትዳር ፈርቶ ? የህዝቡን አፍ ፈርቶ ? ነገ የሚሆነውን ፈርቶ ? ወይስ ፍርሃቱ በልእልት በኩል ይሆን ….በዛ ብሽቅ ባሏ የደረሰባት ግፍ ነገ ፍቅር ቀዝቅዞ በእኔም እንዳይደርስባት ልእልት ፈርታ ? ….ፈርቶ ፈርቶ … ኤጭ ይሄ ህዝብ የሚኖረው ፈርቶ የሚሄደው ፈርቶ !
ደግሞ የእኛ አገር ትዳር …እንደባህር አልጌ የተዝለገለገ እልፍ ጅራት እልፍ እግር የከበበው ….እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ማን ማንን ለምን እንዳገባው እርግጠኛ ሁኖ የሚናገር ማነው ? የዚች ልጅ ነገር ሊያሳብደኝ ነው … ባለትዳር አፈቀርኩ … እሷ ራሷ ባለትዳር ነኝና ካጠገቤ ጥፋ የማትለኝ ለምንድን ነው ….?? እኔስ ይሄን በውስጤ የሚደነፋውን የጓዳ ጀግንነቴን አውጥቸ የማላፈርጠው ለምንድን ነው … እሽ ሌላው ሁሉ ይቅር …መናገሩም ይቅር ልእልትን መራቁም ይቅር ግን እንዴት ማበድ ያቅተኛል ? ከምር አሁን ያማረኝ ማበድ ነው … !! እሱም ቁም ነገር ሁኖ ጠፋብኝ !! ማንኛውም እብድ ድንጋይ ወርውሮ መስተዋት ከመስበሩ በፊት እራሱን ከማንኛውም ሰዋዊ ክብር ወርውሮ ያለፈ ህይወቱን የሚያሳየውን መስተዋት ያንኮታኩተዋል !! ትላንትን ዛሬን ነገንም ልረሳ እብደት እንድመኝ ያደረገኝ ምንድነው? ….የልእልት ፍቅር ነዋ !! ደግሞ የታሪኳ መክፋት …. እንዲህ ስትል ቀጠለች ….
*** **** ***
ኢያሱ ጋር ነፍሳችን የተቀራረበ ይመስለኛል … ባለጌም ጨዋም ይመስለኛል …ደሃም ሃብታምም ይመስለኛል …ቆንጆም መልከ ጥፉም ይመስለኛል …..ኢያሱም ወንዴም ሲመስለኝ ነበር ለራሴ የደነገጥኩት ! አንድ ወንድ ጫማው ሳይሆን መነፅሩ ሳይሆን ከረቫትና ሱፉ ሳይሆን መኪናና ሃብቱ ሳይሆን ….ነፍሱ ባሌን ሲመስለኝ ነገር ተበላሸ !! ደመራ የሆንኩ መሰለኝ ….ግራ በመጋባት እሳት ተለኩሸ ህዝብ ከቦ ወደኢያሱ ከወደቀች ሲሳይ ነው ወደወንዴ ከወደቀች ዘመኑ ጦርነት ነው እያለ የሚተነብይብኝ …. ወዴትም ሳልወድቅ ወይ እንደጭስ ወደላይ ብን ብየ ብጠፋ ወይ እንደውሃ ወደመሬት ሰርጌ እልም ብል ደስታየ ነው !! እና እንዲህ ሳስብ እነኢያሱ ቤት ተቀምጨ የጠፋ ባሌ ወንዴ የሚባል ደወለ ….ስልኩ አላስደነገጠኝም …እንደውም ከአንድ ደይቃ በፊት ደውሎልኝ ስናወራ የቆየን እንጅ ያንን ሁሉ ቀን ባዶ ቤት ጣጥሎኝ የጠፋ ባሌ አልመስልሽ አለኝ ….ስልኩን አነሳሁት …
‹‹ልእልት ›› አለኝ
‹‹አቤት ››አልኩት
በቃ ልክ እንደዚህ ነበር የጠራኝ እንደዚህ ነበር አቤት ያልኩት …ደንግጦ ነው መሰል ትንሽ ዝም አለ ….አዎ ደንግጦ ነው …ሲደውል ትንፋሽ ነበራ የሚያጥረኝ …እንኳን ርቆኝ የሆነ ነገር ሊገዛ ወጣ ብሎ እንዲገዛ የነገርኩት ነገር ጠፍቶበት ሲደውል ተንሰፍስፌ ነበራ የማናግረው ሲጠራኝ አቤት ብየው አላውቅም እኔ ወንዴን ‹‹አቤት›› አልኩት ማለት ስድብ ነበር ….በምድር ላይ ለ ቁልምጫ ሁሉ የማይበቃኝ ነበርኩ ለወንዴ !! ለዛ ነው ዝም ያለው ….እና ትንፋሹን ሰብስቦ እንዲህ አለኝ
‹‹ማነው የቤት ኪራይ የከፈለልሽ ወንድ ?›› አብርሽ ታምነኛለህ … በዚች ቅፅበት ማስመሰል መደባበቅ ምናምን ከውስጤ ጥርግርግ ብለው ጠፍተው ነበር ….እና መለስኩለት
‹‹ኢያሱ ››
‹‹ኢያሱ ?!››
‹‹አዎ ኢያሱ ››(ድምፁ ጥያቄም ምንም አልነበረም …ኢያሱ የሚባለውን ስም የት ነው ሰማሁት የሚል ነበር የሚመስለው)
‹‹አሁን የት ነሽ ››
‹‹ ኢያሱ ቤት ቡና እየጠጣን ›› ስልኩን ጆሮየ ላይ ጠረቀመው …ምንም አልመሰለኝም …ገና ስልኬን ወደቦርሳየ ስመልስ …መልሶ ደወለ አነሳሁ …
‹‹ አሁኑኑ እቤት ላገኝሽ እፈልጋለሁ ››
‹‹እሽ›› ምንም አልተሰማኝም …
ተረጋግቸ ኢያሱ እንዲሸኘኝ ነገርኩት ….ገብቶታል አላንገራገረም …ኢያሱ ግቢ አድርሶኝ ‹‹ልእልት እራስሽን ጠብቂ›› ብሎኝ ተመለሰ …ለምን እንደሆነ እንጃ ሲሄድ ቅር አለኝ ….የፍቅር አይደለም ….ወንዴን የመጥላትና ወደኢያሱ የመቅረብ አይደለም ….ኢያሱ ልቤ ውስጥ ጭው ባለ ምድረበዳ ከሩቅ እንደሚታይ ብቻውን እንደቆመ ግራር አይነት ገዝፎብኝ ነው ! ከጥላው ስትርቅና ወደፀሃይ ስትገባ የሚሰማህን ቃጠሎ በመፍራት ጥላውን የመፈለግ አይነት ስሜት …..ደረጃውን ስወጣ ኬት እንደመጣ ያላወኩት የፍርሃት ስሜት ድንገት ወረረኝ …ወንዴ እቤት ውስጥ እንዳለ ሳስብ ጉልበቴ ተንቀጠቀጠብኝ …. በር ላይ ደርሸ ቁልፉን በሩ ላይ ልሰካ ስሞክር ሁለት ጊዜ የቁልፉን ቀዳዳ ሳትኩት ….በሶስተኛው ስሞክር በሩ ተከፈተና ወንዴ ፊቴ ተጋረጠ … አይኖቹ ፍም መስለው ቀልተዋል … ፀጉሩ ተቆርጦ ካለወትሮው ሽክ ብሎ ዘንጧል …. ከሰውነቱ ላይ የሚተነው ሽቶ ድፍን ሰፈሩን የሚያውድ ነው የሚመስለው (ወንዴን ሳውቀው ለሽቶ ያለው ፍቅር ብዙም አልነበረም ….)
ሳላስበው ጎትቶ ወደውስጥ አስገባኝ ….በሩን በፍጥነት ቆልፎ ተመለሰ ….እራሴን አቅፌ መሃል ሳሎን ላይ እንደእንግዳ ቁሚያለሁ ….ቦርሳየን መንጥቆ ወረወረው ….የለበስኩትን ሸሚዝ ከላይ ይዞ ግራና ቀኝ ሲመነጭቀው ቁልፎቹ ተነቃቅለው እየተፈናጠሩ ምንጣፉ ላይ ወደቁ … የጡት ማስያዣየን ከምኑ ላይ እንደበጣጠሰው እኔጃ …በሴኮንዶች ውስጥ እራቁቴን ፊቱ ተገተርኩ …..ለምርመራ ልብሴን አወላልቄ ሃኪም ፊት አልያም ለወንጀል ምርመራ ርቃኔን ገራፊ ፊት የቆምኩ መሰለኝ!! ወንዴ ጎትቶ ምንጣፉ ላይ አስተኛኝ (ጣለኝ ብል ይሻላል) ከዛ በሆነው ነገር ሁሉ ….እንደታዛቢ ከስሩ ተኝቸ እገረማለሁ ወንዴ ጭራቅ ሆነ …. አንዳችም ስሜት አልተሰማኝም …. እንደውም …ለምን እንደሆነ እስከዛሬም ባልገባኝ ምክንያት … በዚህ አጉል ሰአት ….ኢያሱን እያሰብኩ ነበር !!….
ኢያሱ ሶፋው ላይ ተቀምጦ በእጣኑ ጭስ ውስጥ …ፈገግ ሲል …ታየኝ …ኢያሱ ቡኒ ጫማ በነጭ ካልሲ አድርጎ ነበር … ኢያሱ የቀኝ እጁ አንጓ ላይ ከብር የተሰራ ቀጭን ብራዝሌት አድርጎ ነበር ….ኢያሱ የሸሚዙ ቁልፍ ተከፍቶ ቀይ ደረቱ ላይ ያለው ፀጉሩ ይታይ ነበር … ቡና ሲጠጣ ገና ቡናውን …ፉት ሲል ፊቱ ግራዋ እንደጠጣ ሰው ሲኮማተር አይቸዋለሁ ….እንዴ….. ኢያሱኮ ቡና አይወድም ነበር ….ታዲያ የዛን ጊዜ እቤት ሲመጣ … አሁንም እቤታቸው ስሄድ እንዴት ቡና ጠጣ ??….እኔ ጋር ስለሆነ እኔ እንድደሰት ….??
ወንዴ እንደመርግ እላየ ላይ ተከምሮ አንገቴ ስር ተሸጉጦ እያለቃቀሰ …‹‹አፈቅርሻለሁ ልእልትየ ›› ሲል ሰማሁት (ሰው እየፎከረ ሂዶ እያለቀሰ ሲመለስ እንዴት ያበሳጫል…ማንኛዋም ሴት ውስጥ እንዲህ አይነቱ ወንድ ልጅ ሽንፈት የሚፈጥረው ኩራት አለ እኔ ውስጥ ግን የመረረ ጥላቻ ነው የተፈጠረብኝ …የማፈቅረውን ልጅ አፈራርሶ አመጣው ይሄ የማይረባ ) ኤጭ ጠረኑ ደግሞ ምንምንድነው የሚለው ….ፍየል !!
ያ ሁሉ የተነከረበት ሽቶ እንኳን አላገደውም ! ፍቅር እውር ብቻ አይደለም አፍንጫንም ነው የሚደፍነው ….ባይሆን ኑሮ እዚህ ጠረን ጋር አንድ ቀን ማደሬም ተአምር ነው !! (ስለጠላሁት አይደለም …ያኔ የተከፈተ አፍንጫየ ከዛ ቤት እስከወጣሁበት ቀን ድረስ ያረጋገጠልኝ ነገር ይሄንኑ ነው ) ከምር አንገሸገሸኝ …አቅሙ ቢኖረኝ ወደላይ ወርውሬው ኮርኒሱ ጋር ባጋጨው ደስታየ… ወንዴ ከውስጤ ታጥቦ እንደወጣ የተሰማኝ ያኔ ነው …ሙሉ ሰውነቴ እሱን ተርቦ ሲያዛጋ እንዳላየ አርፎ ቆሻሻ ቅናቱ ገፍትሮት እንደጥንብ አንሳ በሃዘን የሞተ ስጋየ ላይ ሲከመር ዘገነነኝ …..ታዲያ እላየ ላይ ተከምሮ እንዳሻው እንዲሆን የምፈቅደው ለምንድን ነው …
አየህ አብርሽ በዚች ምድር ላይ አንደኛ አስደሳቹ ነገር ወሲብ ሲሆን ….አንደኛ ዘግናኙና አስቀያሚው ነገር ደግሞ ራሱ ወሲብ ነው !! እንደሰው የራሱን ሲኦል መፍጠር የሚችል ፍጥረት በዚች ምድር የለም … የትኛውንም ሰላም የትኛውንም ፍቅር ወደጦርነት መቀየርን ደግሞ እንደኛ ወንዶች የተካነ ፍጥረት የለም !! ጭር ሲል ያማችኋል …ፍቅር የቅናትና የእሰጣ ገባ ምርኩዝ ላይ ካልቆመ ጤነኛ አልመስል እያለው ጤናውን የሚያጣ ወንድ ጋር ስጋባ ቀለበቱን ያሰርነው ገነት ነበር ….የጫጉላ ሽርሽራችንን ሲኦል ያደረገው … በእሳት የተፈተነ ፍቅር ፈልጎ ሳይሆን አፍቃሪው ጀርባ ላይ እሳት አለንጋ እያሰረፈ የበታችነቱን የልቤ ጀርባ ላይ ለመፃፍ ነው ….ተሳሳተ!! እንደውም ልቤ ላይ ተፅፎ የኖረ በጎነቱን በሙሉ ሰረዘው !!
አሁን የእውነት የወንዴ አፍቃሪ ሳይሆን የወንዴ ሚስት ሆንኩ …መብትና ግዴታየን በልቤ ሳይሆን በሰማኒያ ብራናየ ላይ ፅፌ የምኖር ሚስት … ማታ ባሌን ሳይሆን ባሌ የሚመጣበትን ሰአት የምጠብቅ ሚስት …. !! ለወንዴ ሳይሆን ለትዳሬ የምታመን ሚስት ! እንግዲህ ሶስቱ ጉልቻ እኔ …ወንዴ እና ትዳር ሆንን ….ራቅ ራቅ ብለን አንድ ቤት ውስጥ የተቀመጥን ጉልቻዎች !! …የተጣደብንን የፍቅር ብረት ድስት ሳይበስል …ወዲያ ጥለን ….የሚነድብንን እሳት አጠፋፍተን …በተዳፈነ ምድጃ ዳር ህግ ለማክበር የቆምን ሶስት ጉልቾች ! ፓ ትዳር ….ይለናል የሚመለከተን !! ፓ ! አድንቀው ሙተዋል …!!
ያ ሁሉ ነገር እንደጤዛ ረግፎ ባዶ እንደመቆም…. እንደው የከንቱ ከንቱ ንፋስ እንደመከተል የሚባለው ነገር ነው የሆነብኝ ህይዎት ….ንፋስ መከተልም አንድ ነገር ነው ኧረ አብርሽ ….ንፋስ የለ ፀሃይ የለ ደመና የለ ጭር ያለ ጉድ ….የሰው ልጅ በየትኛውም ችግር ውስጥ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ይሁን ከማንም ከምንም ጋር ይሁን …ቢቻል ልብስ የሚያስጥል እብደትን የሚያስንቅ ካልቻለም የጥፍር ቁራጭ የምታክል ፍቅር ታስፈልገዋለች ! ኦህ አብርሽ ፍቅር እኮ እንዴት ደስ የሚል ነገር መሰለህ …..›› ብላ ልእልት ትክ ብላ አየችኝ ….
‹‹እኮ እና እኔስ ምናልኩ ልእልት !›› አልኳት በወሬዋ ተመስጨ ስለነበር ሳላስበው ….
‹‹እ ?›› አለችኝ
…ይቀጥላል….
15 Comments
kefele 23 yete lagegnew Alex
ክፍል 23 የት ነው የማገኘው
ክፍል 23 የት ነው የማገኘው
ክፍል 23 ኣይወጣም
ክፍል 23 የት ነው? በናታቹ…
Where is part 23 ???
መሳጭ እና ግሩም አገላለፅን የተላበሰ ነው ቀጣዩን ክፍል እስካነበው ቸኩያለሁ !!!
ክፍል23 የት ነዉ የሚገኘዉ?
ክፍል 23’ን በጉጉት እየጠበቅሁ ነው፡፡
እረበናትህ ክፍል 23 አፍጥነው ?
የሌለ ተመችቶኛል ግን ክፍል ፳፫ መቼ ነው የሚወጣው?
ድንቅ አተራረክ! ክፍል 23ትን አፍጥነው
ተጠባቂ የነበረውን እየረሳሁት ነወ23ን please please !!!!!!
እባካችሁ ክፍል 23 ይቀጥል !!