Tidarfelagi.com

“አልወለድም!” (ክፍል አንድ)

‹‹አልወለድም!›› የደራሲ አቤ ጉበኛ እጅግ ታዋቂ ስራ ነው፡፡
የሚከተለው ድርሰት በአመዛኙ በአቤ ጉበኛ አልወለድም መፅሃፍ ጭብጥ፣ ገፀባህርያትና ምልልልሶች ላይ በደንብ ተመስርቼ የፃፍኩት የአልወለድም ዘመነኛ እና አዲስ ገፅ ነው፡፡ የትረካው አቅጣጫ፣ የገፀባህሪዎቹ ገለፃ እና ምልልሶች ግን በአመዛኙ ተለውጠዋል፡፡


‹…ግን ከተመረጡ ሃብታሞች ለጥቅም፣
ድሆች ለመከራ ለችግር ለድካም፣
ምንጊዜም ባንድ ሀገር ጭቅጭቅ አይጠፋም፡፡››

የእለት ምግባቸውን በህልምና በማሽተት ካልሆነ በቀር ማግኘት ከማይችሉ ፍፁም ድሆች አንዷ ናት፡፡ ጥቂት ሃብት አንቆ ያዦች በነገሱባት፣ ለአንዱ በኪሎሜትር ለሌላው በስንዝር ከምትከፋፈል ሀገር ውስጥ የተፈጠረች ፍፁም ደሃ፡፡ የምታጋጫቸው ሁለት ሳንቲሞች የሌሏት፣ እነሱ በቁንጣን ሲታመሙ በርሃብ የምታዛጋ፣ እነሱ በመጠጥ ሲሰክሩ የምትጠማ ፣ እነሱ ቅጥ ባጣ ድሎት ሲታመሙ በችግር የምትገረፍ ፍፁም ደሃ ናት፡፡ የሃብታሞች አኗኗሪ፣ በሕይወት ተሳታፊ ናት፡፡ ሳትሞት ገሃነም የገባች ትበላው ትልሰው ያጣች ፣ ጠማማ ጎጆ ትቀልስበት ቁራሽ መሬት የተከለከለች ደሃ- ግን ደግሞ ፈጣሪ ድህነቷን ተንብዮ ያለሆድ ያልፈጠራት እድለ ቢስ ደሃ፡፡

ሌጣውን የማይማርከው መልኳ ኩልና ሊፒስቲክ የሚቀባው ቢያገኝ፣ ትንሽ ፖውደር ቢነሰነስበት፣ ቶነር ጣል ቢደረግበት ከአስቀያሚነት ለትንሽ ያመልጥ ነበር፡፡ ቂጥና ጡቶችዋን አፍጥጦ የሚያወጣ ልብስ በትለብስ፣ ሴትነቷን በመረጃ የሚያረጋግጥ የአጭሬ አጭር ቀሚስ ብታደርግ ሴት አዳሪ ሆና መብላት ትችል ነበር፡፡

ከወራት በፊት የሰው ቤት ተቀጠራ ትሰራ ነበር፡፡ እንደው በልማድ የሰው ቤት አልነው እንጂ ቤቱስ የአውሬ ነበር፡፡ ያልተለመደ ነገር አልደረሰባትም ግን በደሏ የሚለመድ አልነበረም፡፡ በማያበራ ረሃብ ውስጥ ሆና ቀን ከሌት ትሰራ ነበር፡፡ ታዲያ ነገሩ ‹‹በወላቃ ላይ ገጣጣ›› ሆነ እና ከአሰልቺ ኑሮዋ ለመሸሽ የመሸገችበት የግቢያቸው ዘበኛ ለፍቅር ብታቅፈው፣ ኑሮን ለመርሳት ብትስመው ጉድ አደረጋት፡፡ ሳምኩሽ ብሎ ነከሳት፡፡ አዘልኩሽ ብሎ ፈጠፈጣት፡፡
አስረገዛት፡፡
ከዚያ ወዲህ ለማኝ ሆነች፡፡ ሆዱን ያባባችው ቤተክርስትያን ደራሽ ሳንቲምም ብርም እየጣለላት ትኖራለች፡፡ ወይም በሕይወት ትሳተፋለች፡፡ ከታከታት፣ ግን ደግሞ ዛሬም መኖርን ካላስጠላት ኑሮዋ ትታገላለች፡፡

የገፋ ሆዷን እያሸች ዘወትር ፍርፋሪም ሳንቲምም ትለምናለች፡፡ በሳንቲሙ ፍርፋሪ እየገዛች፣ በፍርፋሪው ከረሃብ ፋታን እያገኘች ትኖራለች፡፡
እንደዚህ ባሉት ተመሳሳይ የመከራ ቀናት በአንዱ ግን እጅግ ያልተለመደ ነገር ሆነ፡፡

ረሃብ እየሞገታት ከቤተክርስትያኑ አጥር ስር ኩምትር ብላ ሆድዋን እያሸች በተቀመጠችበት ‹‹አልወለድም!›› የሚል ድምጽ ሰማች፡፡
በመደናበር አማተበችና የድምፁን አቅጣጫ ለመገመት ሞከረች፡፡
‹‹አልወለድም!›› ተደገመ፡፡
ድምጹ የመጣው ከሆድዋ መሆኑን ለማወቅ ደቂቃዎች ፈጁባት፡፡ ስታውቅ ግን በከፍተኛ ፍርሃትና ድንጋጤ ፍንጥር ብላ ተነሳችና ‹‹በስላሴዎች!…ምን የቀትር ሰይጣን ነው የተጠናወተኝ ዛሬ ደግሞ!›› ብላ ዳግም አማተበች፡፡
‹‹ሰይጣን አይደለሁም እማ! ልጅሽ ነኝ…አልወለድም ነው የምልሽ…!ይልቅ መደናበሩን ተይና አዳምጪኝ!›› አለ በሆደዋ የያዘችው ፅንስ፡፡
ድንጋጤዋ ሳይለቃት ተመልሳ በቂጥዋ ዘጭ አለች፡፡
‹‹ምንድነው የምትለኝ…!ምንድነው ይሄ ጉድ…?ምንድነው….?›› አለች በደመነፍስ፡:
‹‹ተረጋጊ፡፡ ያልኩሽ አልወለድም ነው›› ፈጣን መልስ ሰጣት::
‹‹ምንድነው አልወለድም ማለት?…ምን ማለት ነው…እንዴትስ ነው ምታወራኝ…?››
‹<እንዴት እንደማወራሽ አላውቅም…..ቁምነገሩ ማውራቴ ነው እንጂ እሱ አይደለም…አሁን ጊዜ ስለሌለ ዝም ብለሽ ስሚኝ…አልወለድም ኣማ!››
ረጅም ትንፋሽ ሰበሰበችና ሆድዋን ተመለከተች፡፡ ቅድም እንደነበረው ነው፡፡ ሰው አበደች የሚላት፣ ብሎም ሳንቲም ሳይሆን ድንጋይ የሚወረውርባት መስሏት ሽምቅቅ አለችና፤
‹‹አንት ሰይጣን…አትጩህ…!እንጀራዬን አትዝጋ››
‹‹የቱን እንጀራሽን!? ይሄ ፍርፋሪሽን ከሚታይበት የማይታይበት ጊዜ ሚበልጠውን ፍርፋሪሽን ነው እንጀራ የምትይው?!…ይልቅ ዝም ብለሽ…በፅሞና ካልሰማሽኝ እጮሃለሁ…››
‹‹እሺ እሽ…እሰማለሁ…ለምንድነው የማትወለደው?…››ድምጽዋን ዝቅ አድርጋ ጠየቀች፡፡
‹‹የድሃ ልጅ ነኛ! …የድሃን ልጅ የሚጠብቀው የወላጆቹ መከራና ችግር ብቻ ነው…››
‹‹አይ ልጄ…!ያንተን እድል ማን ያውቃል ብለህ ነው…››
‹‹በዚህ ዘመን የልጅሽን ኑሮ ለእድልና ለእጣ ፈንታ ስትሰጪ አታፍሪም?…አሁን ይህ ዘመን ልጅ በእድሉ የሚያድግበት ጊዜ ነው?!›› ብሎ አምባረቀባት
‹‹ተው ልጄ..አትጩህ…ማን ያውቃል…››
‹‹እኔ አውቃለሁ…ስለዚህ አልወለድም!…ስለማውቅ ነው ለሌሎች የድሃ ፅንሾችም<< የተወለዱት ድሆች በወግ እስኪያዙ አትወለዱ>> የምለው…ስለማውq ነው <<የእያንዳንዱ ሰው ተገቢ ድርሻ እና የመኖር እድል እስኪታመን አትውለዱን>> የምለው…ስለማውቅ ነው <<ለባርነት አልወለድም>> የምለው…አልወለድም!››
‹‹ወይ እድሌ…! እሺ አሁን ተረገዝክ…ምን አርጊ ትለኛለህ…?››
‹‹አትውለጂኛ! ወይ መርዝ ጠጥተሸ አብረን እንሙት ወይ ደግሞ አስወርጂኝ እና የመከራሽን ኑሮ ብቻሽን ግፊ…››
‹‹ውይ…ተው እንጂ ልጄ! ሞት እኮ ያስፈራል›› አለችው ሰውነቷ እየተዘንዘፈዘፈ፡፡
ከባድ ሳቅ ሳቀና፤ ‹‹ተይ እንጂ! ሞት ያስፈራል! ሀብታም ሲል ሰምተሸ <<ሞት ያስፈራል>> ትይኛለሽ…! እነሱ ከተቀማጠሉበትና ከሚወዱት አለም ላለመለየት ሞት ያስፈራል ቢሉ የነሱ የገደል ማሚቶ ትሆኛለሽ….?አየሽ…የደሃ እጣው ይሄ ነው…የሃብታም የገደል ማሚቶ መሆን…ይልቅስ ሞት የድሆች ወዳጅ ነው…ከሃብታም የግፍ ቀንበር የሚያውጣሽ ብቸኛው ወዳጅሽ ሞት ነው…››
‹‹ተው ልጄ…ሞት …ሞት አትበልብኝ…!›› መንዘፍዘፍዋ ሳይቆም ተናገረች::
‹‹እልሻለሁ…እንደውም መርዙን ገዝተሸ ሁለታችንም እስንገላገል ድረስ ይሄን ዘፈን እዘፍናለሁ …መርዙን እስክተገዢ አላቆምም…›› አለና በመልካሙ ተበጀ <<ብእር ብእር ብእር>> ዜማ የሚከተለውን ዜማ ይዘፍን ሳይሆን ይጮህ ጀመር::
‹‹የድሆች ነፃ አውጪ- የእውነት አርነት
የእንቅልፍ ታላቅ ወንድም- የዘልአለም እረፍት
ፍጡራን በሃሰት ስለሚደለሉ
ደሃም እንደሃብታም አንተን ጠላህ አሉ!››
ይሄን ዘፈን በጩኸት ያለ አፍታ ሲደጋግምባትና መድረሻ ሲያሳጣት …‹‹የለም፤ ከሰይጣን ነው ያረገዝኩት…!የለም ፤ከሰይጣን ነው ያረገዝኩት….!›› ብላ እየጮኸች፣ ከሰው ሁሉ እየተላተመች አእምሮውን በሳተ ሰው ዘዬ ወደ ሰፈሯ እየሮጠች ሄደች…

“አልወለድም” (ክፍል ሁለት)

One Comment

  • በቀለ እሸቴ commented on February 15, 2016 Reply

    ግሩም ስንኞች የተቋጠሩበት
    ዘመን ተሻጋሪ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *