Tidarfelagi.com

ዶ/ር ኣበራ ሞላ

ዶ/ር ኣበራ ሞላ መጋቢት ፳፬ ቀን ፲፱፻፵ ዓ.ም. ሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ መናገሻ ኣውራጃ፣ በረህ ወረዳ፣ ሰንዳፋ ከተማ የተወለዱ ሲሆን በኮምፕዩተር ግዕዝ ፊደልን መጠቀም እንዲቻል ያደረጉ ምሁር ናቸው። ይሀንንም ያደረጉት የዓማርኛውን የጽሕፈት መሣሪያ (ታይፕራይተር) ለሚያውቁት ቀላል እንዲሆን በ“a”፣ “b”፣ “c”፣ “d” ምትክ “ሀ”፣ “ጠ”፣ “ሸ”፣ “ዘ” እና እንግሊዝኛ ለሚያውቁ በ“A”፣ “B”፣ “C”፣ “D” ምትክ “አ”፣ “በ”፣ “ቸ”፣ “ደ” ቀለሞችን በመመደብ ዓይነት ሠላሳ ሰባቱን የግዕዝ ቤት ሆሄያት ለ፴፯ የኮምፕዩተር መርገጫዎች ስሞችም በማድረግ ነበር። ስምንቱን የፊደል ቤቶች ወይም እንዚራን ስምንት ፎንቶች ላይ በተኑዋቸው። በእዚህ ዘዴ በእጅ ጽሑፍና ማተሚያ ቤቶች ብቻ ይታተሙ የነበሩት የግዕዝ (Ethiopic) ፊደላት ለመጀመሪያ ጊዜ በኮምፕዩተር ተከተቡ። ሞዴት በመባል የታወቀውን የቃላት ማተሚያ የማይክሮሶፍትን ዶስ በመጠቀም በ፲፱፻፹ ዓ.ም. ኣሜሪካ ውስጥ ለገበያ ኣቀረቡ። ጊዜውም ኮምፕዩተሮችና ማተሚያዎች በቂ ኃይል ማግኘት የጀመሩበት ነበር። ግዕዝ በኮምፕዩተር እንዲከተብ የፈጠሩበትን ዘዴ በዩናይትድ እስቴትስ ፓተንት መጠበቅ ቢችሉም በእዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ የፓተንት ሕግ ስላልነበራት የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ሕጉ ሲወጣ ጉዳዩ ይታያል በማለት ስለወሰነ ፓተንት ኣልወጣለትም።

የዓማርኛ የጽሕፈት መኪና ቅጥልጥል ፊደል

በዚህ ጉዳይም እንዲህ ብለው ፅፈዋል፤

የብዙ ሺህ ዕድሜ ያለው የግዕዝ ወይም ኢትዮፒክ ፊደል እንደ ላቲኑ እያንዳንዱ ፊደል እራሱን የቻለ እንጂ ከሚበጣጠሱ ቁርጥራጮች የሚሠራ ኣይደለም።

ከእዚህ በላይ ያለው ደብዳቤ በ፲፱፻፹፪ ዓ.ም. የተጻፈልኝ በዓማርኛ የጽሕፈት መሣሪያ ወይም ታይፕራይተር ነበር። የደብዳቤውን ሥዕል ካቀርብኩበትም ምክንያቶች ኣንዱ ግዕዝን ኮምፕዩተራይዝ ከማድረጌ በፊት የኢትዮጵያ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ይጠቀሙባቸው የነበሩት የኣማርኛ የመኪና መጻፊያ ፊደላት ምን እንደሚመስሉ ለማሳየት ነው።

ፊደላቱ ወረቀት ላይ የሚሠሩት ከሚቀጣጠሉ ቆብ፣ ጫማ፣ ቀለበትና ጭረት መቀጣጠያዎች ነበር። ይህ የተደርገው የታይፕራይተር የመርገጫዎቹ ቁጥር ለሁሉም ፊደላት ስለማይበቃ በመሆኑ የታይፕ መጻፊያ የተጠቀመው በዓማርኛ ፊደላት ኣይደለም። እነዚህንና የተመሳሰሉትን ቁርጥራጮች ከኣንድ የፊደል ገበታ መደብ ከኮምፕዩተር እየቀጣጠሉ ግዕዝ ነው የሚሉና ከዚህም ኣልፎ ለእነ ዩኒኮድ ያቀረቡና ሲያስቸግሩኝም የከረሙ ኣሁንም (፳፻፩) ኣላረፉም።

እኔ ግዕዝን ኮምፕዩተራይዝ ያደረግኩት እዚህ በምታነቡት ፊደልና ለእያንዳንዱ ፊደል የተለየ የእራሱን ቦታ በመስጠት ፊደላቱን ስምንት ፎንቶች ላይ በመበተን ሲሆን ይኸው ትክክለኛው የግዕዝ ፊደላችን ኣሁን የዩኒኮድ ፊደል ሆኗል።

የዓማርኛ የጽሕፈት መኪና ፊደልም ለብዙ ሺህ ዓመታት በእጅና በብራና በኋላም በማተሚያ ቤት ሲጻፉ ከነበሩት ፊደሎቻችን በብዛትና ኣጠቃቀም ኣንድ ካለመሆኑም ሌላ ተሻሽሎም የማያዋጣ ስለሚሆን ወደ ኮምፕዩተር እንዳይገባ ተቃውሜ ከጻፍኳቸው መካከል የ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. (1991 ኤ.ዲ.) ኢትዮጵያን ሪቪው መጽሔት እንግሊዝኛ ጽሑፌን እዚህ ማንበብ ይቻላል።

ዶ/ር ኣበራ ሞላ

 ከ ጋዜጠኛ ደምሴ አጎናፍር ጋር “ዘገባ” በተሰኘ ህትመት ላይ ካደረጉት ቃለ ምልልስ የተወሰደውን እነሆ፡-

ጥያቄ፣ ተቀዳሚ ሙያህ በሕክምና ዙሪያ ላይ ያተኮረ ሲሆን ነገር ግን የዛሬ 25 ዓመት ገደማ ዓማርኛና ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለኮምፕዩተር ቅንብር ብቃት ኖሯቸው እንዲዋሃዱ ለማድረግ የሚያስችል የቃላት ማቀነባበርያ ለመፍጠር የገፋፋህ ዓላማ ምንድነው?

ዶ/ር ኣበራ፦ ፊደላችንን ከልጅነቴ ጀምሮ እወደዋለሁ። ኣምስተኛ ክፍል እያለሁ በችሎታዬ ይደነቁ ከነበሩት የጅማ ሰንበቴ ትምህርት ቤት ኣስተማሪዎቼ ወይዘሮ ኣዳነች ይግዛው ለሚባሉት ጥላ ያለው የዓማርኛ የጥልፍ ፊደል ስሠራ እንደነበረ ኣስታውሳለሁ። በኋላም የዓማርኛ የመኪና (ታይፕ) መጻፊያንም ሳይ ፊደሉ በመበጣጠሱና በመበላሸቱ ቅሬታ ነበረብኝ። እንግሊዝኛው በኮምፕዩተር መጻፍ ሲጀመር የሚሠራው በኣንድ የፊደል ገበታ ብቻ በመሆኑ ለግዕዝ እንዲጠቅም ኃይሉ እስኪሻሻል ጠብቄ በ1987 ኤ.ዲ. (፲፱፻፹ ዓ.ም.) ለመጀመሪያ ጊዜ የግዕዝ መጻፊያ ሥራዬን ኣቅርቤያለሁ ። ግዕዝን በኮምፕዩተር መጻፍ የቻልኩትም ፊደሎቹን ከስምንት የፊደል ገበታዎች በላይ ላይ በመበተን ነበር። ቴክኖሎጂው ሲጀምር ታግዬ የማተሚያ ቤቱን ዓይነት በኮምፕዩተር እንዲሠራበት ማድረግ ባልጀምር ኖሮ የግዕዝ ፊደል ተብሎ ወደ ኮምፕዩተርና የዓለም ፊደላት መደብ ውስጥ የሚገባው የዓማርኛ የጽሕፈት መኪናው ዓይነት ዓማርኛ ያልሆነው የቅጥልጥል ፊደል ነበር። ኣንዳንድ ኣዳዲስ ነገሮችን ኣንብበን የመፍጠር ችሎታ ያለን ሰዎች ቴክኖሎጅው ሲጀምር ሌሎች ሊሠሩልን የማይችሉትን ታግለን ኣብረን ካልጀመርን ብዙ ከተገሰገሰ በኋላ እንኳን ሊደረስበት የኣሠራሩ ደብዛ ስለሚጠፋ ታግያልሁ።

ጥያቄ፣ ኣንተ የፈጠርከው የቃላት ማቀነባበርያ በወቅቱ በሰፊው ሥራ ላይ ይውል ከነበረው የመኪና ጽሕፈት መሣሪያ ተመስሎ የተሠራውን ኋላ ቀር የቅጥልጥል ፊደል ጽሕፈት ሙሉ በሙሉ እንዲጣል ማድረጉ በሰፊው ይነገራል። እስኪ ስለዚህ ጉዳይና በዚህ ሳቢያ ከሌሎች ሙያተኞችና ጠበብቶች ጋር የተነሳውን ያካሄድ ግጭቶች እንዲሁም ሌሎች ችግሮች ብታብራራልን?

ዶ/ር ኣበራ፦ እኔ ግዕዝ በኮምፕዩተር እንዲሠራ ስሞክር ቀደም ብዬ ማውጣት የምችለውን የዓማርኛ የመኪና መጻፊያውን ዓይነት በተለይ እ.ኤ.ኣ. ከ1985 ወዲህ ያወጡ ነበሩ። የእኔው ለገበያ ሲቀርብ እያንዳንዱ ፊደል ላይ ጭረትና ቀለበት የመሳሰሉትን በመጨመር የሚከተበው የቅጥልቅሉ የዓማርኛ የመኪና መጻፊያ ሳይሆን እያንዳንዱ ፊደል እራሱን የቻለና ትክክለኛውና በእጅ የምንጽፈው ወይም ማተሚያ ቤቶች የሚጠቀሙብት የግዕዝ ፊደል በመሆኑ ሌሎቹን ዋጋ ኣሳጣቸው።እንዲህም ሆኖ ትክክለኛው ተፈጥሯልን እንደግፍ እንደማለት የቅጥልጥሉን ኣሠራር በነፃ በመስጠትና በ1990 ለተቋቋመ ዩኒኮድ ለሚባል የዓለም ፊደላት ድርጅት በሓሰት የግዕዝ ፊደል ብለው ኣቅርበው ብዙ ችግሮች ኣድርሰውብኛል። ለምሳሌ ያህል የዓማርኛ የታይፕ መጻፊያ ያለው የመርገጫዎች ብዛት ከመቶ ያነሱ ስለሆኑ ዓማርኛን ለመጻፍ ከመቶ ያነሱ ስፍራዎች በቂ ናቸው ብለው ለዩኒኮድ ኣቅርበዋል። ይኸንንም ተቃውሜና ጽፌ ከእነሱ ተገላከልኩ ስል ደግሞ ሌሎች ትክክለኛዎቹን የዓማርኛ፣ ትግርኛና ኦሮምኛ ፊደላት ኣቅርበው የቀሩትን እንቀጣጥላለን ብለው ለሁለተኛ ጊዜ ያልተሟላ ፊደል እ.ኤ.ኣ. በ1993 ለዩኒኮድ ኣቀረቡ። ዩኒኮድንም ያልተሟሉ የግዕዝ ፊደላትን እንደገና ትቶ የተሟሉና ትክክለኛዎቹ የግዕዝ ፊደላት የዓለም የፊደል መደብ ውስጥ በቅርቡ (2002) ገብተዋል። ግን ይህ የሆነው ሌሎቹ በቅጥልጥል እንዲገቡ የፈለጉት ከተሳካላቸውና ለግዕዝ ወደ 368 ግድም ቦታ ከተመደበለትና ቦታው ከተዘጋበት በኋላ በመሆኑ የተተዉት የግዕዝ ፊደላት ከሌሎች ኣዳዲስ የዩኒኮድ ስፍራዎች በቅርቡ ዩኒኮድ ውስጥ ገብተዋል። የግዕዝ ፊደል፣ ኣኃዝና ምልክቶች ብዛታቸው ወደ 480 ስለሆኑ ያንን ያህል ቦታ ይመደብ ብዬ ብቻዬን ብታገልም ስላልተሳካልኝ ሌሎች በጀመሩት ጠንቅ ነው ዛሬ የግዕዝ ፊደላት ዩኒኮድ ውስጥ ተበጣጥሰው ሦስት ቦታ እንዲመደቡ የሆነው። እነዚህም ከኣንድ ቦታ ሊቀርቡ ይችሉ የነበሩት ዛሬ ግዕዝ፣ ተጨማሪ ግዕዝና ተራዛሚ ግዕዝ (Ethiopic, Supplemental Ethiopic, Extended Ethiopic) በሚል የፈጠራ ስም ተሰጥቷቸው ተበታትነው የቀረቡት። ይህም ለግዕዝ ውርደት ነው። እንዲህም ሆኖ ነገሩ ገብቷቸው ከእኔ ጋር ለእውነት የደከሙ ቢኖሩም ያልገባቸውና ዛሬም በቅጥልጥል የዓማርኛ የመኪና መጻፊያ ዓይነት ፊደላትም የሚጠቀሙ ኣሉ። ሥራዬንም ለማዳከም እኔ የሠራሁትን የግዕዝ ኣጠቃቀም ቀድተው ለመሸጥ ያልተሳካላቸውና በነፃም ሲበትኑ የነበሩ ኣሉ። የቅጥልጥሉን የዓማርኛ ፊደላት ለኮምፕዩተር ካቀረቡት ኣንዱ እውሸቱን ኣሻሽሎ ግዕዙን ኣቀረብኩ ማለት ጀምሯል። ይህም ዝምታና ግዴለሽነት ግዕዝ ላይ ያመጣው ሌላ ውርደት ነው። ከእዚህም ሌላ የእነዚህን ማወናበድ በመከተል የተለያዩ ፊደላት ኣቀማመጥ ያላቸው ወደ ሠላሳ የሚጠጉ የማይናበቡ መጻፊያዎች ቀርበው ሕዝቡን ሲያበሳጩት ከርመዋል። ያበላሹትም ፊደላቱን ብቻ ሳይሆን የኣከታተብ ፈጠራዬንም ነበር። ምክንያቱም የዓማርኛ የመኪና ኣጻጻፍ ለዓማርኛ በቂ ስላሆነና ኣሠራሩም ኋላ ቀርና ብዙ መርገጫዎችን መነካካትን የሚያስፈልግ በመሆኑ ወደ 480 ለሚጠጉት የግዕዝ ፊደላት፣ ኣኃዛትና ምልክቶች እያንዳንዱን ከሁለት መርገጫዎች ባላበለጡ የሚጻፍበትን ፈጠራዬንም ጭምር ነበር ያበላሹት።

ጥያቄ፣ የኣዲስ ኣበባ ዩኒቨርሲቲ የዓማርኛ ፊደላት ይቀነሱ በማለት ኣንዳንድ ተደጋጋሚ ሆህያት እንዲቀሩ መወሰኑን ሰምተናል። ኮምፕዩተር ይህን ውሳኔ ይረዳል ወይስ ይጎዳል?

ዶ/ር ኣበራ፦ ትክክለኛ ሆህያትን ለማወቅ የሚያስችል መዝገበ ሆህያት እና መዝገበ ቃላት ስላሉ ኮምፕዩተር ተራድቷል። የኮምፕዩተር ኣንዱ ጥቅምም ቃላትን ከጽሑፍ ወይም ኢንተርኔት ለመፈለግ ነው። ጸሓፊዎች ቃሎቻቸውን በትክክለኛዎቹ፣ በተቀነሱ ወይም በተገኘው ፊደል መጻፍ ጀምረዋል። እነዚህን ቃላት ለማግኘት በሚጻፉባቸው ዓይነቶች ሁሉ መፈላለግ ስለሚያስፈልግ ፊደላቱን መቀነስ ሥራ ሳያስጨምር ኣልቀረም። ይህ ሰውን ሊያሰለችና ቋንቋውን ሊያዳክም ይችላል። ለምሳሌ ያህል “ሰረቀ” እና “ሠረቀ” የሚባሉት ቃላት ከግዕዝ የመጡ ስለሆነ ትክክለኛዎቹን ሆህያት ካልተጠቀምን ስሕተት ነው የሚሉ ኣሉ። ኣንዱን “ሰ” ብቻ ተጠቅመን ትክክለኛውን ትርጕም ከዓረፍተ ነገር ማግኘት መሻሻል ኣይደለም። የቃላት ኣመጣጥ ጥናት ኤቲሞሎጂ (Etymology) ይባላል። ይኸን ማወቅ ኣዳዲስ ቃላትን ለመፍጠር ይረዳል። ፈረንጆች ቃላት እንዳይበላሹ በእስፔሊንግ ጣጣ ሲቸገሩ እያየን ትክክለኛዎቹን ሆህያት እንደማስተማር የዓማርኛ እስፔሊንግ ጣጣ መጀመር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ይመስለኛል። ይቅሩ የተባሉትን ፊደላት እያስተማርን ኣትጠቀሙባቸው ማለትም ዓዋቂዎችን ማደናቆር ይመስላል። የግዕዝ ኣኃዞች እንዳይዳከሙ የግዕዝን ኣልቦ (ዜሮ) በመሥራት ከ፩ እስከ ፱ ካሉት ጋር እንድንጠቀምባቸው ለሃያ ዓመታት ሳቀርብ የኣዲስ ኣበባ ዩኒቨርስቲ ሲደግፍ ኣልሰማሁም። በኣሁኑ ጊዜ የግዕዝ ኣኃዞች ዩኒኮድ ውስጥ ያሉት በፊደልነት እንጂ በኣኃዝነት ኣይደለም። ማንም ዕውቀትን ማጥፋት ይችላል። መጨመር ግን ከምሁራን ከሚጠበቁት ኣንዱ ነው። ሰለዚህ ፊደል መቀነሱ ላይ ስናተኵር ቋንቋውን እንዳናዳክም ባይ ነኝ። የኣዲስ ኣበባ ዩኒቨርስቲ (Addis Ababa University) ማድረግ ካለበት ኣንዱ የእራሱን ስም ትክክለኛ ስም በዓማርኛ (ኣዲስ ኣበባ ዩኒቨርስቲ) በማለት እንዲሁም በእንግሊዝኛ (Addis Abeba University) ብሎ ማረምና ማሳወቅ ይመስለኛል።

ጥያቄ፣ ኣንዳንድ የመንግሥት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶችና የኪነት ሰዎች እንዲሁም ግለሰቦች ኣዙረው ሳያስቡ ያለማመንታት የባእድ ቃላትን በተለይም እንግሊዝኛ ቃላትን ቋንቋችን ውስጥ እየዘነቁ ሲያጎድፉ ይስተዋላል። ለመሆኑ የፈጠርከው የኢትዮጵያ ቃላት ማቀነባበርያ ይህንን ነውርና ኣሳፋሪ የቃላት ድቀላና ብረዛ ኣሠራር ባሕል ለመቀየርና ብሎም ለማስወገድ በምን መልክ ይረዳል?

ዶ/ር ኣበራ፦ በርግጥ ጥሩ ጥያቄ ነው። ይሄ ጉዳይ እስካሁን ድረስ ቁርጠኛ መፍትሄ ያልተገኘለት ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ችግር ነው። ሳይታሰብበት እንግሊዝኛ እየከለሱ ዓማርኛን መናገርና መጻፍ እንዲሁም ሕዝባዊና መንግሥታዊ ተቋማት በቸልተኝነት በላቲን ቋንቋ በታጀቡ የመለያ ስሞች ማስተዋወቅንና መንግሥታዊ ገለጻዎችን ማድረግ በሰፊው የሚታይ ብሔራዊ ገጽታ ነው። በጣም የሚገርመው ለምሳሌ ኣንዳንድ ሰዎች የሚያወሩት ውስጥ በርከት ያሉ የእንግሊዝኛ ቃላት ስለሚጨምሩ እንግሊዝኛ የማያውቁ ስለ ጉዳዩ ስለማይገባቸው የሰው ጊዜ ያጠፋሉ። ከእነዚሁ ኣስመሳዮች በእንግሊዝኛ ኣውሩ ቢባሉ ደግሞ የባሰ ችግር ውስጥ የሚገቡ ኣይጠፉም። ለማንኛውም የዕውቀቱ መጀመሪያ ዋቤውን መጻፍና መናገር መሆኑ መታወቅ ስላለበት ኢንተርኔት መብት ስለሰጠን መጻፍና ማንበብን ማስፋፋት ይቻላል። በተጨማሪም መዝገበ ቃላትንና ትክክለኛ ሆህያትን በቀላሉ ማቅረብ ስለሚቻል ዕድሉ ኣለ። በቴክኖሎጂ መመንጠቅ የተነሳ ኣዳዲስ የእንግሊዝኛ ቃላትን በመተርጎም ማቅረብ ሳይጠቅም ኣይቀርም። እንዲህም ሆኖ እንግሊዝኛ ኣንስማ ማለት ሳይሆን እነ ቸርችና እስኩል የመሳሰሉትን ቃላት ዓማርኛ ውስጥ መቀላቀል አስፈላጊ ስላልሆነ ያልተማሩትን ማስተማር እንጂ የተማሩት መጥፎ ኣርኣያ መሆን ኣይጠቅምም። በኣንጻሩም የኢትዮጵያ ከፍተኛ የቋንቋ ጥናት ተቋሞች በዚህ ጉዳይ ላይ ከመጠን በላይ ርብርብ በማድርግ ብሔራዊ ግዴታቸውን መወጣት ኣለባቸው። የመንግሥት ኣካላትም ይህንን ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እንዲሁም እራሳቸውን በቀዳሚነት በማሰለፍ የችግሩ ዋና ተፋላሚዎች በመሆን ቋንቋችንን መስመር ለማስያዝ የላቀ ሚና መጫወት ይችላሉ የሚል ከፍተኛ ግምት ኣለኝ።

ጥያቄ፣ በኣሁኑ ሰዓት የተሻሻለው የኢትዮጵያ ቃላት ማቀነባበርያ በምን ደገጃ ላይ ይገኛል? ሥራህስ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ውጤት ኣስገኝቷል?

ዶ/ር ኣበራ፦ ከዚህ በፊት የሠራኋቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ጥሩ ተቀባይነት ኣግኝተው ወደ ፼ (10ሺ) ኮፒ ሸጫለሁ። የጀመርኩትን እየቀናነሱና እየቆራረጡ ሲሸጡ የነበረው ዓይነቱ በዝቶ ገበያው ሲጠፋ በነፃ ማደል ስለጀመሩ ፈረንጆች ገብተውበት በእንግሊዝኛ ኣጻጻፍ ዓይነት ኣንዳንዱን የዓማርኛ ፊደል ከሁለት መርገጫዎች በላይ የሚጻፍበት ኣቅርበው ሕዝቡን እያጃጃሉት ነው። ኣንዳንድ ኣዳዲስ ነገሮችን የሚሠሩ ሰዎች መብት የሚጠበቀው በፓተንት ሲሆን ኢትዮጵያ ዛሬም የሶፍትዌር ባለቤትነት መብት የማስከበር ሥርዓቱ የለም። የባለጥንት ፊደል ኣገር ወደኋላ መቅረት በተለይ ለፊደሉ የደከምነውን ኣሳፍሮናል። ለግዕዝ የሚጠቅሙ ነገሮችን እየሠራን ያለነው መብቶቻችንን በሌሎች ኣገሮች ፓተንቶች ማስጠበቅ ይኖርብናል።

ጥያቄ፣ በኣገራችን የቀን መቍጠሪያ ላይም በግልህ ከፍተኛ ጥናት ኣድርገሃል። ለመሆኑ ግዕዝን በተመለከተ ላለፉት ሦስት ሺህ ዓመታት ያለማቋረጥ ሥራ ላይ የዋለ ብቸኛው የዓለም ቋንቋ ነው ቢባል ማጋነን ይሆናል?

ዶ/ር ኣበራ፦ የኢትዮጵያ የቀን መቍጠሪያ የጁልያን ነው እየተባልኩ ትክክል ያልሆነ ነገር መማሬን ኣውቃለሁ። የእየሱስን መወለድ ኢትዮጵያውያን የሰሙት ከሰባት ዓመታት በኋላ ስለሆነ ነው ዓመታቱ ወደኋላ የቀሩትም የሚባለውንም ኣስታውሳለሁ። በምርምሬ እንደደረስኩበት ከሆነ ግን ሮማውያን የኢትዮጵን ቀለንጦስ ዓይነት የቀን መቍጠሪያ በ525 ዓ.ም. ሲቀዱና ለኣዲሱ ቀን መቍጠሪያቸው ጁልያን የሚል ስም ሲሰጡት ነው ሰባት ዓመታት ግድም የጨመሩበት። የግዕዝ ፊደላችን ዕድሜ ሦስት ሺህ ዓመታት ነው የሚሉ ኣሉ። ከክርስቶስ ልደት በፊት 3350 ዓመት ሄኖክ መጽሓፉን በግዕዝ ፊደል ጽፎበታል በማለት የሚያምኑም ኣሉ። ይህ ግዕዝን የመጀሪያው ፊደል ያደርገዋል። ረዥም ዕድሜም የማይሰጡት ቢኖሩም ምርምሬን እንደጨረስኩ ኣንድ ጽሑፍ ለማቅረብ ኣስቤኣለሁ።

ጥያቄ፣ በሌላ በኩል ወደ 200 የሚደርሱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የኣትክልት ዘሮችን ባሕላዊ ስማቸውን ኣዲስ ከተሰጣቸው የሳይንስ ስም ጋር በማዛመድ ኢንተርኔት (የዓለም መረጃ መረብ) ላይ ኣቅርበሃል። ይኸንን ለማድረግ ምን ኣነሳሳህ?

ዶ/ር ኣበራ፦ መሬት በመንግሥት ይዞታ ስር ነው እየተባለ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን ሰምቻለሁ። በየዓመቱ ያሉት ዛፎችና የተለያዩ ኣትክልት ይመነጠራሉ እንጂ ስለመተካታቸው ብዙም ኣይሰማም። ከሕንድ ውቅያኖስ የሚነፍሰው ውሃ-ኣዘል ነፋስ የኢትዮጵያ ተራራዎች ላይ ሲደርስ ዝናብ እየሆነ ስለሚወርድ ነው ሰሃራ በረሃ የሆነው። ኢትዮጵያውያን ዛፉን እየመነጠሩና ኣትክልቱን እያጋዩ ይህ ዝናብ ኣፈሩን እየወሰደ ስለሆነ የሚቀረው ድንጋይ ኢትዮጵያንም በረሃ ሊያደርጋት ይችላል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለሕይወት ኣስፈላጊ ላልሆኑ እንደ ቡና ዓይነቱ ላይ መመርኮዝ የለበትም። ስለዚህ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ ኣይብቀል መቆም ኣለበት። ኣትክልት እኛ ወደውጭ የምንተነፍሰውን መጥፎ ኣየር ወስደው ወደ ውስጥ የምንተነፍሰውን ጥሩ ኣየር ይሰጡናል። ኣፈሩን ዝናብን ጎርፍ እንዳይወስደው ይከላከላሉ። ብዙ ዓይነት መድኃኒቶች ይሰጡናል። ምግብ ናቸው። ስለእያንዳቸው ብዙ የተጠኑና ያልተጠኑ ነገሮች ስላሉ የሳይንስና ያካባቢ ስሞቻቸውንና ጥቅሞቻቸውን ማወቅ ኣለብን። ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ያሉ ዛፎች ኣሉ። ዕውቀቱ እዲስፋፋ ነው ይኸን ስመ ኢጸዋት ገጽ የጀመርኩት። ኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ዛፎች መትከል መጀመሩን ስለሰማሁ ተደስቻለሁ። ዕድሉ ያለን በምንችለው መርዳት የእግዚኣብሔር ፀጋ የሚቀርብበትን ማዘጋጀት ነው።

ምንጭ፡-

http://freetyping.geezedit.com/Q_and_A_with_Dr._Aberra_Molla_in_Amharic.htm
http://archive.is/No43M
wikipedia.org

 

 

2 Comments

  • Kebede commented on February 8, 2016 Reply

    Thank u doctor

  • Anonymous commented on February 11, 2016 Reply

    like

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *