በጀርባዬ ተኝቼ አላውቅም። በደረቴ ካልተኛሁ እንቅልፍ አይወስደኝም። … ዛሬ እንቅልፍ ስለመተኛት አይደለም ግዴ…… አይኔን ብከድን ስነቃ አጠገቤ የማጣት ነው የመሰለኝ
ፒጃማ ለብሼ ተኝቼ አላውቅም። ይጨንቀኛል። ዛሬ እሷ ምቾት እንድታጣ አልፈለግኩም። ……
እቤቴ ማንም ሴት መጥታ አታውቅም። ዛሬ ስምሪትን አቅፊያት ለወትሮዬ ሰያፍ የምሰመርበት አልጋዬ ላይ አብሪያት ተኝቻለሁ። ……
ይሄንን ሁሉ ብታውቅ? እየጠበቅኳት እንደሆነ ነቅታ ብታይ? …… አሰብኩት። ወዲያው እንዲህ አሰብኩ… … የሚሰማኝን ስሜት ነው የማደርገው ወይስ እሷን ለማማለል?
አብዛኛዎቻችን ጥሩ ስናደርግ እኮ ግብዝ ነው። ደግ ለመሆን ከምናደርግ ይልቅ በሌሎች ዘንድ ደግ ለመባል ነው ደግነት የምናሳየው…… ለቅድስና ደግ ከመሆን ይልቅ ለእውቅና ደግ እንሆናለን። …… 50 ብር ስንቸር ያደረግንለት ሰው እውቅና እንዲቸረን እንፈልጋለን። 500 ሺህ ብር ስንሰጥ በሬዲዮ እና በቴሌቭዥን እንዲነገርልን እናደርጋለን። እስኪ ማናችን ነን ማንነታችን ሳይታወቅ ሰውን ከመቀመቅ ያወጣን? ኸረ ስንቶቻችንስ ነን ለማናውቀው ሰው ቸርነት ያሳየን?
አነሰም በዛም ደግነታችን አይንና ልብ እንዲስብ እንፈልጋለን። …… ያደረግኩት ይሄንን መሰለኝ። ቢያንስ የሚሰማኝን ስሜት እንድታውቅልኝ መመኘት……
ተወራጨች። እየቃዠች እንደሆነ ገብቶኛል። አጥብቄ አቀፍኳት።
“እሽሽ… … ” አልኳት እንደ ህፃን ልጅ። እያማተበች ተነሳች።
“እኔጋ ነሽ!! አለሁ!” አልኳት አልመለሰችልኝም። ሙቀት እንደሚፈልግ ህፃን ተጣበቀችብኝ። በእግሮቿ ጭኖቼን ፈልፍላ እግሮቿን እግሮቼ መሃል አስገባቻቸው፣ ጭንቅላቷን አንገቴ ስር ሸጉጣ ከአልጋው ይልቅ ከግማሽ በላይ ሰውነቷ እኔ ላይ ተኛች። በሁለቱም እጆቼና በሁለቱም እግሮቼ ወደ ራሴ አስጠግቼ አቀፍኳት። ደስ አለኝ። ለወትሮው እንዲህ መንሰፍሰፍ የወንድ ልጅ ስሜት አይመስለኝም ነበር።
ለዛሬ እንዳመነችኝ አይደለም የተሰማኝ…… ለሁሌውም ‘ጠብቀኝ‘ ያለችኝ ነው የመሰለኝ…… እንዴትና ከምን እንደምጠብቃት አላውቅም። …… በፍፁም እንድትጎዳ እንደማላደርጋት ግን ለራሴ ቃል ገባሁ። ብዙም ሳትቆይ እንደገና እንቅልፍ ወሰዳት። …… ከሚደበድባት ሰውጋ ለምንድነው የምትሆነው? በምንም መልኩ ለማስቆም አቅሙ አላት…… ለምን?
“አንዳንድ ሰወች አብሮነታቸው ከሚጠቅምህ ይልህ ይጎዳሃል። እየጎዱህም ግን ልታጣቸው አትፈልግም።” ትል ነበር እናቴ ብዙ ጊዜ ……እሷ ማውራት የፈለገችው ስለ ባሏ መሆኑን አውቃለሁ።
ስምሪት ስለእናቴ ያለችውን አሰብኩ። የት ልትሆን ትችላለች? ምናልባት ገዳም ገብታ? ምናልባት ሌላ ባል አግብታ ሌሎች ልጆች ወልዳ? ማን ያውቃል ምናልባትም አሁንም ሀብታሞች የሚዝናኑበት ሆቴል እየሸረሞጠች? …… የነበራትን ገንዘብ ሰጥታኝ… … ቤቷን ጥላልኝ… … የት ልትሄድ ትችላለች? ምናልባት ራሷን አጥፍታ ቢሆንስ? …… አንዴ ስለእናቴ መልሼ ደግሞ ስለ ስምሪት ስፈትል ስቋጭ ሽልብ እንዳደረገኝ ነጋ። …… ያንን ሁሉ ሰዓት አለማጨስ የኑሮ ያህል ትግል ነበረው።
መንቃቷን አውቃለሁ። መንቃቴን አውቃለች። …… ጀርባዬጋ ዞሮ ባቀፈኝ እጇ ጣቶች በቀስታ ትነካኛለች። ……
“በልጅነቴ ነው ያገባሁት። …… ” አለችኝ ሳትንቀሳቀስ ወዲያው ግን ከአንገቴ ዝቅ ብሎ እንባዋ ረጠበኝ።
“የማታለቅሺ ከሆነ ብቻ ነው መስማት የምፈልገው። ካለዚያ አልፈልግም። እንባሽን ማየት አልችልም።” አልኳት ቀና ብዬ እያየኋት… … የፊቷ እብጠት ጠፍቶ ብልዘቱ ብቻ ቀርቷል። … በጭንቅላቷ እንደማታለቅስ ነግራኝ ተመልሳ ደረቴ ላይ ተጋደመች እና ማውራት ጀመረች። ማውራት ከመጀመሯ በፊት የሆነ አስማት ነገር ሰርታለች። ደረቴን ሳመችኝ። …
ስታወራልኝ ቅደም ተከተሉን አልጠበቀችም። አልረበሽኳትም። ብስጭት፣ ፀፀት፣ አልፎ አልፎ እንባ…… እየተፈራረቁባት በስሜት ነው የምታወራኝ። ፀጉሯን በጣቶቼ እያበጠርኩ ስሰማት የገባኝ ይሄ ነው።
ያገባችው ሰው ቤተሰብና የሷ ቤተሰቦች በገንዘብ የተጣሉ ፀበኞች ናቸው። …… የቤተሰቦቿ ብቸኛ ልጅና ተስፋቸው ነበረች።… ቤተሰቦቿ ከጠላታቸው ልጅ ጋር ፍቅር መጀመሯን ሲያውቁ ከፍቅሯና ከቤተሰቧ እንድትመርጥ ምርጫ ሰጧት። …… ቆይቶ ስታውቀው የእርሱ ቤተሰቦች ፀበኛቸው ገንዘባቸውን ከማጣታቸው ይልቅ ልጃቸውን ማጣታቸው እንደሚጎዳቸው ያውቁ ስለነበር ልጃቸውን ይደግፉት ነበር። …… ፍቅሯን መርጣ ከቤቷ ስትወጣ ደግሰው ተቀበሏት። አባቷ ምን ያህል ቆራጥ መሆናቸውን ብታውቅም እስከመጨረሻው ይከፉብኛል ብላ አላሰበችም። በሰዓቱ ሁሉም ሰላም እና ውብ ነበር።
እየቆየ የባሏ ባህሪ መቀየር ጀመረ። … እሷ መርማሪ ፖሊስ መሆኗን ተከትሎ ቤቷ ብጥብጥ ወረሰው። ዘግይቶ ሲገባት በብዙ ህገወጥ ንግዶች ላይ እጁ እንዳለበት ገባት። …… ቢሆንም በቂ መረጃ የላትም…… ቢሆንም ታፈቅረዋለች። ከለሱ አንካሳ ናት። …… በዚህ ትርምስ ውስጥ አርሴማ መጣች…… በመጀመሪያ የአርሴማ መወለድ ነገሮችን ያበረደ መሰለ። …… ውጪ ማደሩን ተወ። … መደብደቡን አቆመ።…… ድጋሚ ጥሩ ትዳር ኖራት… … አርሴማ እያደገች ጤነኛ አለመሆኗን ሲያውቅ ከበፊቱ በባሰ ከፋ። …
“እሺ እኔ ምን ማድረግ ነበረብኝ? እኔ እግዚአብሄር ነኝ? ልጄ ጤነኛ ብትሆን እኔስ ደስተኛ አልነበርኩም? ምን ማድረግ እችል ነበር?” አለችኝ ቀና ብላ
አርሴማ ከፍ ስትል ጭራሽ ከቤቱም ወጣ። በሁለት ሳምንት አንዴ (ትናንት እንዳደረገው) አርብ ከሰዓት መጥቶ አርሴማን ቤተሰቦቹጋ ይዟት ይሄዳል።… … ለልጁ የሚያስፈልገውን እሱም ሆነ ቤተሰቡ ከማድረግ ቦዝነው አያውቁም። … እሷን ከወንድ ጋር ታየሽ፣ ለልጄ መልካም አርአያ እየሆንሽ አይደለም…… እያለ መቆጣጠሩን አለፍ ሲልም ትላንት እንዳደረገው መደብደቡን ቀጠለ። …… ምንም ማድረግ እንዳትችል አርሴማ አሰረቻት። …… አርሴማ አባቷን ስታይ ፈንጠዝያዋ የሚቀሙት አይደለም። … … እሱ ሄዶ ከትምህርት ቤት ያመጣት ቀን ስትጫወት ታመሻለች።
“ልጄ ጤነኛ ብትሆን እና እንደ ጤነኛ ልጅ በሌላ ነገር የምትደሰት ብትሆን እሺ… … እንዴት አንድ የሳቋን ምክኒያት ልንጠቃት? ታውቃለህ? ሲደበድበኝ እያየች እንኳን አትጠላውም። አትፈራውም…… እስሩ ገብታ ነው የምትሄደው።” አለች ጥልቅ መከፋት ባለው ድምፅ
ለአመታት እንዲመለስላት የምትችለውን ስታደርግ ኖራለች። አሁንም ድረስ። …… ከእርሱ ጋር የነበራትን ህይወት ከመመለስ ውጪ ሌላ አማራጭ አታስብም።
“ዛሬ ወደ ቤት የምትመለሺበት ምክኒያት የለሽም። አብረን እንዋል!! ማታ እራት ልጋብዝሽ!” አልኳት ካለችበት ድብርት እንድትወጣ። አልመለሰችልኝም። ቀና ብላ እያየችኝ…
“የእናትህን ጉዳይ ዛሬ እንድናጣራ አስቤ ነበር።” አለችኝ ድምፅዋ ውስጥ ደስ የማይል ጥርጣሬ አደመጥኩ። አመነታሁ። ለማወቅ ጉጉት አድሮብኛል። ለዛሬ ግን ከዚህ በላይ ትራጄዲ ለመስማት ዝግጁ አልነበርኩም።
“ነገ እናድርገው። ነገ ጠዋት። አሁን ምንም መስማት አልፈልግም። አሁን ስትስቂ ማየት ብቻ ነው የምፈልገው።” አልኳት በምንቸገረኝ ትከሻዋን ሰበቀች።
የገጠማትን እረስታ ከኔጋር መሆኗን ብቻ እንድታጣጥም ስጣጣር ዋልኩኝ። … ቁርስ ሰርቼ አበላኋት። …… ተመልሰን ተኛን። ማታ ስላልተኛሁ እንቅልፍ ወሰደኝ። ስነቃ አጠገቤ ሳጣት ጮሄ ተጣራሁ። ምሳ እየሰራች ነበር። …… ገብቷታል። ሆዷን ይዛ ሳቀችብኝ። መቃም እንደምፈልግ ስነግራት ቡና እንደምታፈላልኝ ነገረችኝ። … በየመሃሉ ጭልጥ ትልብኛለች። …… ሊመሻሽ ገደማ ወጥተን ቀሚስ እና ጫማ ገዛሁላት። …… እራት ልንወጣ ቀሚሷን ለብሳ ተኳኩላ ብቅ አለች። ዝም አልኳት።
“አላማረብኝም? እ?” አለችኝ
“ምንም ተጨማሪ ነገር ሳትጠቀሚ እኮ ውብ ነሽ!” መለስኩላት
“እሱ ግን ሳልኳኳል አስጠላዋለሁ።” አለችኝ ከንፈሯን ወደ አንድ ጎን አጣማ (ቁሌታም ሴት ይወዳል ብላኝ ነበር ጠዋት ስታወራኝ)
“አሁን ለእኔ ብለሽ ነው የተቀባሽው? ለእኔ ብለሽ ከሆነ አጥፊው ምክኒያቱም እንደዛ ቆንጅዬ ነሽ! ለራስሽ ብለሽ ካደረግሽው ተይው።” ስላት አመነታች… ከዛም አጠፋችው።…
……
……
…
እራት እየበላን እሷ ወይን እኔ ቢራ እየጠጣን እንዲህ ከወጣች አመታት መቆጠራቸውን ከእንባዋ እየታገለች ነገረችኝ። … ሁለት ብርጭቆ እንደጠጣች ሞቅ አላት
“ታውቃለህ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም። ትክክል መሆኑንም እንጃ!” አለችኝ እቤት እንደገባን
“ምኑ?”
“የሚሰማኝ ስሜት”
One Comment
በጣም ደስ ይላል